Sunday, 08 December 2019 00:00

ለክፉም ለደጉም - የደስቲኒ ኢትዮጵያ አወንታዊ ገፅታ!

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(4 votes)

 • የዛሬ ሃሳብና ተግባር፣ ለክፉም ለደጉም (ለንጋትም ለፅልመትም ‹‹ሴናሪዮ››) የ10 የ20 ዓመት ውጤትና መዘዝ አለው፡፡
                • የደስትኒ ኢትዮጵያ ሙከራ፣ ይህንን እውነት የተገነዘበ መሆኑ፣ አወንታዊ ገፅታው ነው፡፡
                   

            በየጊዜው ተደጋግሞ፣ የሚጠቀስ የምኞት ወይም የፀሎት አባባል አለ (ሦስት አይነት የመልካም ሥነ ምግባር ባህርያትን ለመቀዳጀት)::
‹‹…the serenity to accept the things I can not change, the courage to change the things I can, and the wisdom to know the differenece.››
‹‹ሊለወጡ የማይችሉ ነገሮች›› ሲባል፣ ሁሉም አንድ አይነት ናቸው ማለት አይደለም:: አንደኛ፣ በጭራሽ የማይለወጡ ነገሮች አሉ፡፡ ውሃን የመሰለ ፈሳሽ ነገር፣ ከከፍታ ወደ ዝቅታ መፍሰሱ፣ ሲቀዘቅዝ መጠጠሩ፣ በሙቀት ብዛት መትነኑ… ዘላለማዊ እውነት ነው - የእውኑ ዓለም አይነኬ ተፈጥሮ፡፡ ይህንን በአዎንታ መገንዘብ፣ ማወቅ ነው - የአእምሮ ፋንታ።
ይህንን እውነታ ያልተገነዘበ ሰው፣ የመስኖና የኤሌክትሪክ ግድብ፣ የክትባትና የምግብ ማቀዝቀዣ፣ የመኪናም ሆነ የአውሮፕላን ሞተር የመስራት ይቅርና የማሰብ ቅንጣት አቅም አይኖረውም፡፡ ‹‹ውሃ ከከፍታ ወደ ዝቅታ መፍሰስ የለበትም፤ መጠራቀም አለበት›› ብሎ በምኞት ብቻ የውሃን ተፈጥሮ መቀየር የሚችል ከመሰለው፤ እንዴት ግድብ ለመስራት ያስባል?
በምኞት ዘላለማዊ ተፈጥሮን መቀየር አይቻልም፡፡ በሌላ ዘዴም አይቻልም፡፡ ጤናማና ብልህ ሰው፤ ውሃን ማጠራቀም ከፈለገ፣ የውሃን የፍሰት ተፈጥሮ በአወንታ መገንዘብ ይገባዋል:: ‹‹Nature to be commanded must be obeyed›› እንዲል ፍራንሲስ ቤከን፡፡  
ከዚህ ጋር በማዛመድና ከሰው ህልውና ጋር በማስተሳሰር፣ ዘላለማዊ እውነታዎችን መመልከት ይቻላል፡፡ ሰው፣ ምንን እንዴት ማምረት እንደሚችል ካላወቀ፣ የሙያ ብቃት እየገነባም ተግቶ ካልሰራ  ህይወቱን የማሻሻል ይቅርና የመሰንበት አቅም አይኖረውም፡፡ ይሄም ዘላለማዊ እውነታ ነው፡፡ ያለ እውቀት፣ ያለ ሙያ፣ ያለ ትጋት… የሰው ህይወት አይለመልምም፡፡ (ከሌላ አምራች በምፅዋት ለመቀበል፣ በሸፍጥ አታልሎ ለመውሰድ ወይም በሽፍትነት ለመዝረፍ ካልሆነ በቀር)፡፡
አይነቱን አጣርተው፣ መጠኑን ለክተው በንጽህና መመገብና ስፖርት መስራት ለጤንነት ጠቃሚ የመሆኑን ያህል፤ የንጽህና ጉድለትና የምግብ እጦት፣ ስራ መፍታትና ከስፖርት መራቅ ደግሞ ጤናን ያሳጣል - ይሄም ከሰው ሕይወት ጋር የተያያዘ ዘላለማዊ እውነት ነው - የእውኑ ዓለም፣ በተለይም የእውኑ ሰው ተፈጥሮ፣ እንዲህ ነው፡፡ ዝንተ ዓለም አይለወጥም፡፡
በወቅቱ መመገብ ለጤንነት የሚበጅ፣ ሳምንቱን አለመመገብ ጤንነትን የሚቀጭ መሆኑ፣ የማይሻር የማይከለስ እውነት ነው - ተቀያሪ የለውም፡፡ እውነት የመሆንና ያለመሆን ጉዳይ ነው፡፡ ተገቢ ነው ወይስ አይደለም ተብሎ አይዳኝም፡፡
በወቅቱ በሳህን የቀረበውን ምግብ መብላትና አለመብላት፣ ግን የሰው ምርጫ ነው፡፡ መብላት አለመብላት ተገቢ ነው ወይስ አይደለም? ተብሎ ይዳኛል፣ ፋይዳው ይመዘናል፡፡
ሌላ ሦስተኛ አይነት እውነትን እንጥቀስ፡፡
አንደኛ፣ መቼም፣ የትም፣ እንዴትም ለምርጫ የማይቀርቡ፣ ተቀያሪ የሌላቸው ዘላለማዊ እውነታዎችን ጠቅሰናል - ከሰው ህልውና ጋር በማዛመድም አይተናል፡፡ ለዳኝነት የማይቀርቡ በአወንታ ልንገነዘባቸው የሚገቡ እውነታዎች ናቸው፡፡
ሁለተኛ፣ አሁን ‹‹ልብላ፣ አልብላ››፣ ዛሬ ‹‹ልስራ፣ አልስራ››፣ ዘንድሮ ‹‹ትምህርቴን ልቀጥል፣ ላቋርጥ››፣… ተብለው የሚከናወኑ ነገሮች ግን፤ ተገቢ መሆን አለመሆናቸውን እየዳኘን፣ የፋይዳና የጉዳት መጠናቸውን እየመዘንን ልንገነዘባቸው የሚገቡ፣ የሰው ምርጫና ተግባርን የተከተሉ እውነታዎች ናቸው፡፡
በእነዚህ በሁለቱ መካከል ያለ ነው፤ ሦስተኛው አይነት፡፡
የሰው ባህርይና ልማድ፣ ብቃትና የሰብዕና ጥንካሬ፣ የአገር ባህልና ልማድ፣ ብቃትና የስልጣኔ ደረጃም በአንድ በኩል ሲታይ፤… የሰዎች ምርጫና ተግባርን የተከተሉ፣ ሰው የሚገነባቸው ወይም የሚያፈርሳቸው ነገሮች ናቸው፡፡ ነገር ግን ደግሞ በተፈጥሯቸው፣ በአንድ ቅጽበት፣ በአንድ ጀንበር፣ በአንድ አመት ተቆርሰው ለጉርሻ፣ ተጥደው ለእራት፣ ተዘርተው ለአዝመራ የሚደርሱ አይደሉም፡፡ በቅጽበት ተቃጥለው፣ አዳራቸውን ወድቀው፣ ለከርሞ ፈራርሰው የሚጠፉም አይደሉም፡፡
የአገር ባህልና የሥልጣኔ ደረጃ ከዕለት ዕለት ሊለወጥ፣ ክረምት አልፎ መስከረም ሲመጣ ሊያብብና ሊያፈራ አልያም ጠውልጎ ሊከስም አይችልም፡፡ በዚህ በዚህ ወደ ዘላለማዊ እውነታ ይጠጋሉ፡፡
የሰው ምርጫና ተግባርን ተከትለው የሚመጡ፣ ለክፉም ለደጉም በሰው ሊቀየሩ የሚችሉ በመሆናቸው ደግሞ፣ ከዘላለማዊ እውነታ ይለያሉ፡፡
ለምሳሌ ‹‹የኢትዮጵያ ድህነት››ን፣ በሁለት ወይም በሦስት ዓመት ‹‹በኢትዮጵያ ብልፅግና›› መቀየር አይቻልም። ከአምስት ዓመት በኋላም ኢትዮጵያ፣ ደሃ አገር መሆኗ አይቀርም፡፡ ሃብታም አገር ልትሆን አትችልም። በ5 ዓመት ውስጥ የማትችል ከሆነ፣ ‹‹ለምን ሃብታም አልሆነችም?›› ብሎ ማማረር፣ ማውገዝና መወንጀል ከንቱ አላዋቂነት፣ አልያም ፀብ ፍለጋ ክፋት ይሆናል፡፡
ከ10 እና  ከ15 ዓመት በኋላስ? ያኔም ድሃ አገር ልትሆን ትችላለች፡። ወይም የባሰባት:: ግን ደግሞ የተሻለች፣ በፍጥነት ያደገች፣ ወደ ብልጽግና የተቃረበች፣ በብልፅግና ከሚጠቀሱ አምስት የአፍሪካ አገራት መካከል አንዷ መሆንም ትችላለች፡፡
ለክፉም ለደጉም፣ ለድህነቱም ለብልጽግናውም፣ ለስልጣኔም ለኋላ ቀርነትም፣ ከአመት ዓመት እየተሻሻለ ወይም እየተባባሰ፣ ከ10 እና ከ15 ዓመት በኋላ የሚኖረው ውጤት፣ በሰዎች ምርጫና ተግባር አማካኝነት የሚወሰንና የሚቀየር ነገር ነው፡፡
አሁን፣ ዛሬ፣ በመጪዎቹ ሳምንታትና ወራት፣ ዘንድሮና በተከታዮቹ ዓመታት የምንቀርጻቸውና የምናፈርሳቸው፣ የምናስተጋባቸውና የምናጣጥላቸው ሀሳቦች፣ የምንፈጽማቸውና የምናሰናክላቸው ተግባራት፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ ውጤትና መዘዝ ይኖራቸዋል፡፡ ከ15 ዓመት በኋላ ለሚኖረው ስልጣኔና ኋላ ቀርነትም ጭምር!
ለክፉም ለደጉም (ለንጋትም ለፅልመትም ‹‹ሴናሪዮ››) የዛሬ ሃሳብና ተግባር፣ የ10 የ20 ዓመት ውጤትና መዘዝ አለው፡፡
የደስትኒ ኢትዮጵያ ሙከራ፣ ይህንን እውነት የተገነዘበ መሆኑ፣ አወንታዊ ገፅታው ነው፡፡
ከዚህ አወንታዊ ገፅታው የሚመነጩ ትክክለኛ ይዘቶችና ትንታኔዎችም አሉት፡፡ የትንታኔ ስህተቶችና የይዘት ጉድለቶች የሉትም ማለት ግን አይደለም፡፡ አሉት፡፡ በዝርዝር ፈትሾና በሰፊው ቃኝቶ፣ ጠቃሚ ሃሳቦችን ለመሰንዘር መጣር ይገባናል፡፡

Read 9207 times