Saturday, 07 December 2019 12:57

የጸጋዬ ገብረ መድኅን ሕይወትና ሥራዎች በድሕረ-ደርግ ዓመታት

Written by  ባየህ ኃይሉ ተሠማ bayehhailu@gmail.com
Rate this item
(1 Vote)

“-በጨካኝና አምባገነን ወታደራዊ ገዢዎች እግር የተተኩት አዲሶቹ ገዢዎች በኢትዮጵያ ዲሞክራሲን በመመስረት ፈንታ ከፋፋይና መሰሪ የዘር ፖለቲካን በማራመድ፣ አገሪቱን መውጫ ወደሌለው የብጥብጥ አዙሪት ውስጥ እንደሚከቷት ጋሼ ጸጋዬ ተረድቶት ነበር፡፡---”
                
         የደርጉ መንግሥት በ1983 ዓ.ም ሲወድቅ በደራሲያንና በጥበብ ሰዎች ዘንድ የንግግር፣ የመጻፍና በአጠቃላይ ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መሠረታዊ የሰብዓዊ መብት በኢትዮጵያ ሊከበር ይችላል የሚል ተስፋ ፈንጥቆ ነበር፡፡ በደርጉ ወንበር የተቀመጡት አዲሶቹ ገዢዎችም በኢትዮጵያ ዲሞክራሲን ስለ መመስረት፤ በተለይም የንግግርና የጽሑፍ ነጻነትን ለማወጅ እንዲሁም ሳንሱርን ለማስቀረት ተስፋ ስለ ሰጡ ይሄ ምኞት መሠረት ነበረው ለማለት ይቻላል፡፡ ብዙም ሳይቆይ የግል ጋዜጦችና መጽሔቶች ብቅ ብቅ ማለት ከመጀመራቸውም ሌላ ከመካከላቸው ጥቂት የማይባሉትም ለአዲሱ መንግሥት ያላቸውን ተቃውሞ በይፋ የሚገልጹ አስተያየቶችን ይዘው የሚወጡ ነበሩ:: እነዚህ የጽሑፍና የንግግር ነጻነት ምልክቶች በአገሪቱ መታየት መጀመራቸው በጥበብ ስራዎቹ የተነሳ ሲሰቃይ ለኖረው ጸጋዬ ገበረ መድኅን ሥራዎቹን በአዲስ መንፈስ እንዲሰራ መነቃቃትን ፈጥሮለታል፡፡
ጋሼ ጸጋዬ በዚህ ጊዜ ነበር የድኅረ-አብዮት ሥራዎቹ የሆኑት ‹‹ሀሁ በስድስት ወር››፣ ‹‹አቡጊዳ ቀይሶ››፣ ‹‹መልዕክተ ወዛደር›› እና ‹‹መቅድም›› ተከታይ የሆነውንና ‹‹ሀሁ ወይም ፐፑ›› ሲል የሰየመውን አዲስ ቴአትር ያዘጋጀው፡፡ ‹‹ሀሁ ወይም ፐፑ›› የኢትዮጵያ ተስፋ በሠላምና በአንድነት ወደ ዴሞክራሲ ‹‹ሀሁ›› እያሉ መሄድ ወይም ማለቂያ ወደሌለው የዘር ጥላቻና የመጠፋፋት አዙሪት መጨረሻ ‹‹ፐፑ›› እያሉ መጓዝ ነው ይላል፡፡ በሌላ በኩል፤ ይኸው አዲስ ቴአትር በ1983 ዓ.ም በመጣው የመንግሥት ለውጥ ሳቢያ የተቀሰቀሰው የዴሞክራሲና የሠላም መልካም ዕድልና ተስፋ፣ እንደ 1953 ዓ.ም የዴሞክራሲ ተስፋ ወይም እንደ የካቲት 1966 ዓ.ም አብዮት የዴሞክራሲ ተስፋ ለሶስተኛ ጊዜ ጨንግፎና መክኖ እንዳይቀር የቀረበ ተማጽኖ ነው፡፡  
‹‹ሀሁ ወይም ፐፑ›› የተጻፈው የደርግ መንግሥት ከመውደቁ አንድ ዓመት ያህል ቀደም ብሎ እንደሆነ ከጋሼ ጸጋዬ ግለ ታሪክ የተገኘው መረጃ ይጠቁማል፡፡ ስለሆነም ቴአትሩ የተጻፈው ሽምቅ ተዋጊዎቹ አዲስ አበባን ለመያዝ የሚያደርጉትን ውጊያ ባጠናከሩበት ጊዜና የደርግ መንግሥት መውደቅ አይቀሬነት ከተገመተ በኋላ ነው ማለት ነው፡፡ ለቴአትሩ መጻፍ መነሻ የሆነው ብዙ ተስፋ የተጣለበት ሕዝባዊ አብዮት ፈሩን ስቶ ለጥቂት ወታደሮች የሥልጣን መገልገያ መሆኑ ያደረሰው ጉዳት ሳያንስ፤ ከወታደሮቹ መንግሥት ሥልጣኑን በግድ የሚረከበውም የኢትዮጵያን ሕዝባዊና አገራዊ አንድነት ለአደጋ የሚያጋልጥ ከፋፋይ ሌኒናዊ የሽምቅ ተዋጊዎች ኃይል መሆኑ የፈጠረው ስጋት ነው፡፡
‹‹ሀሁ ወይም ፐፑ››ን ያዘጋጀው ዓለሙ ገብረአብ ሲሆን ቴአትሩን ያጠኑት ደግሞ አማተር ወጣት ተዋናዮች ነበሩ፡፡ ቴአትሩ በብሔራዊ ቴአትር እንዲታይ ጥያቄ የቀረበው በ1984 ዓ.ም የመጀመሪያ ወራት ግድም ነበር፡፡ ጥያቄውን የተመለከተው የብሔራዊ ቴአትር አስተዳደር በመጀመሪያ መድረክ ለመፍቀድ ከተስማማ በኋላ ጥቂት ቆይቶ ቴአትሩ ‹‹በኮሚቴ መገምገም አለበት›› የሚል ውሣኔ አሳለፈ፡፡ የቴአትር ግምገማ የተባለው እጅ አዙር ሳንሱር መሆኑን አስቀድሞ የተረዳው ጋሼ ጸጋዬ ደግሞ ‹‹ቴአትሬ እዚህ አይገመገምም›› አለና ጉዳዩን ወደ ባህል ሚኒስቴር በመውሰድ የመስሪያ ቤቱ ከፍተኛ ባለሥልጣኖችና ባለሙያዎች በተገኙበት ቴአትሩን አሳይቶ የይለፍ ፈቃድ ለማግኘት ቻለ:: እንዲያም ሆኖ ቴአትሩ ለሕዝብ እንዳይቀርብ በርካታ መሰናክሎች በየጊዜው መፈጠራቸው አልቀረም፡፡ ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ ቴአትሩ በነሐሴ ወር 1984 ዓ.ም በብሔራዊ ቴአትር ለመጀመሪያ ጊዜ ለሕዝብ ሲቀርብ ከፍተኛ ተቀባይነት ለማግኘት ችሏል፡፡ ቴአትሩ በሳምንት ሶስት ቀናት ይቀርብ የነበረ ቢሆንም አዳራሹ ከአፍ እስከ ገደፉ በሰው እየተሞላ የመመልከት እድሉን ሳያገኝ የሚመለሰው ሕዝብ ይበዛ ነበር:: ይህንኑ አስመልክቶ ጋሼ ጸጋዬ ሲጽፍ ‹‹የአዲስ አበባ መድረክ የጥበብ ሞያተኞች ‹‹ሀሁ ወይም ፐፑ›› ን አዩ፡፡ አብዛኛዎቹ አነቡ፡፡ ተመልካቹም ሕዝብ ጭምር አነባ፡፡ የሃቅ ረሃብ፣ የሠላም ረሃብ የፈነቀለው የምሥራች እንባ ነው፡፡ እኛም እሰየው፤ ሁላችንንም እንኳን ለዚህ አደረሰን አልን፡፡ የኢትዮጵያ ክብርና ባህል ገፊም እንደ ልማዱ በግላጭ ተሳለቀ›› ብሎ ነበር፡፡
የጋሼ ጸጋዬ ሥራዎችን በአጠቃላይ ‹‹ሀሁ ወይም ፐፑ›› ደግሞ በተለይ እንዳይታይ በወያኔ/ኢህአዴግ በኩል ፍላጎት እንዳለ ለመጀመሪያ ጊዜ የታወቀው በዚህ ጊዜ ነበር:: ስለዚሁ ጉዳይ በሐምሌ ወር 1985 ዓ.ም ታትሞ ለወጣው ‹ኢትዮጵያን ሪቪው› መጽሔት በሰጠው ቃለ መጠይቅ ጋሼ ጸጋዬ ሲናገር፤ ‹‹ከቴአትሩ (ከሀሁ ወይም ፐፑ) የመክፈቻ ቀን አሥር ቀናት ያህል ቀደም ብሎ ጀምሮ ዝግጅቱን እንዳቆም የሚያስጠነቅቁ የስልክ ማስፈራሪያዎች ካልታወቁ ሰዎች ይደርሱኝ ጀመር፡፡ ይህ እንግዳ ነገር ለእኔም ሆነ ለቤተሰቤ በፍጹም ያልተለመደ ነበር፡፡ ምንም እንኳን ባለፉት ሁለት መንግሥታት በርካታ ሥራዎቼ በመድረክ እንዳይቀርቡ ቢታገዱም፤ የወደቀው የደርግ መንግሥት ቴአትር ከማስጠናበት መድረክ ላይ በድንገት ጠልፎ ወስዶ ወደ ወህኒ ቢወረውረኝም፤ መጻፍ በጀመርኩበት ባለፉት አርባ ዓመታት ጊዜ ውስጥ እንደዚህ ያለ የሥነልቡና ጫና የሚያሳድር አስፈራሪ የስልክ ጥሪ ግን አጋጥሞኝ አያውቅም›› ብሎ ነበር፡፡
የወያኔ/ኢህአዴግ መንግሥት የሚከተለው መለያየትንና መጠራጠርን የሚያነግሥና አንድነትን የሚያኮስስ የመጠፋፋት ርዕዮተ ዓለም፣ ከጋሼ ጸጋዬ ዓይነት የወንድማማችነት፣ የአንድነትና የፍቅር ጠበቆች ቡራኬ እንደማያገኝ በዘር ፖለቲካ አራማጆች ዘንድ አስቀድሞ ታውቋል፡፡ በመሆኑም አገዛዙ ለሚከተለው የጎሣ ፖለቲካ እንቅፋት ይሆናሉ ያላቸውን የኢትዮጵያን አንድነት የሚያጎሉ፣ ፍቅርንና ወንድማማችነትን የሚያወድሱ፣ አርበኞችንና ጀግኖችን የሚያስታውሱ ሥራዎች በመድረክ እንዳይቀርቡ ስውር እገዳ ይጥልባቸው ጀመር:: በተጨማሪም ጎሠኝነትን ይቃወማሉ የተባሉ ደራሲያንንና የኢትዮጵያ ወዳጆችን ልዩ ልዩ ስም እየሰጡ ማሸማቀቅ እንዲሁም ከሥራ ማባረር በዚህ ጊዜ በስራ ላይ ከዋሉት ታዋቂ የማጥቂያ መሣሪያዎች ዋና ዋናዎቹ ነበሩ፡፡ ጋሼ ጸጋዬ ከመንግሥት ሥራው በጡረታ ስም እንዲሰናበት የተወሰነውም አዲሱ ቴአትሩ መታየት ከጀመረ ከአራት ወራት በኋላ ነበር፡፡ የሆነ ሆኖ ‹‹ሀሁ ወይም ፐፑ›› ለሕዝብ ለመታየት የበቃው አገዛዙ ዴሞክራሲያዊ ሆኖና ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት መከበር ተቆርቋሪ ሆኖ ሳይሆን በአንድ በኩል የአፈና መዋቅሩ ገና ሥር ስላልሰደደ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ዴሞክራሲያዊ መስሎ ለመታየት ጠቃሚ ሆኖ ስላገኘው ነበር::  አገዛዙ በ‹‹ሀሁ ወይም ፐፑ›› መታየት ደስተኛ ባይሆንም ቴአትሩ ያለምንም የተመልካች እጦት ከአንድ ዓመት በላይ ከቀረበ በኋላ በአዲስ አበባ ላይ የመታየት ፈቃዱ ታገደ፡፡ በቴአትሩ ላይ የተጣለው እገዳ ለጊዜው ከመዲናዋ ውጪ ያሉ ከተሞችን የማይመለከት መሆኑ ሲረጋገጥ 14 አባላት ያሉት አማተር የቴአትር ቡድን ‹‹ሀሁ ወይም ፐፑ››ን ይዞ መጋቢት 19 ቀን 1985
ዓ.ም ወደ ደቡብ አቀና፡፡ ቡድኑ ከአዲስ አበባ ውጪ የመጀመሪያው የሆነውን ዝግጅት ለዝዋይ ከተማ ነዋሪዎች ካቀረበ በኋላ ጉዞውን በመቀጠል ወደ ዲላ ከተማ አመራ፡፡ አስቀድሞ በወጣው ፕሮግራም መሠረት ቴአትሩ በዲላ ከተማ ለሁለት ቀናት ይታያል፡፡ የመጀመሪያው ቀን ፕሮግራም አልፎ አልፎ ካጋጠመ የመብራት መጥፋት ችግር በስተቀር ይህ ነው የሚባል የጎላ ችግር ሳይከሰት በተሳካ ሁኔታ ተጠናቋል:: የቴአትር ቡድኑ ለሁለተኛ ቀን ዝግጅቱን ሲያቀርብ ግን ከተመልካች መቀመጫ ላይ የተነሱ ታጣቂዎች ወደ መድረክ በመውጣት ተዋንያኑን በዱላና በሰደፍ መደብደብ ጀመሩ፡፡
በሕዝቡ ብርታት ተዋንያኑና የቡድኑ አባላት ከሞት ተርፈው በድብደባው የተጎዱት ለሕክምና ወደ ዲላ ሆስፒታል እንዲወሰዱ ተደርጎ ነበር::  የቴአትር ቡድኑ ከዲላው ጥቃት ካገገመ በኋላ ‹‹ሀሁ ወይም ፐፑ››ን በአዋሳ ከተማ ለማቅረብ ሲዘጋጅ የዲላው ጥቃት እንደማይደገም በመተማመን ነበር:: ይሁን እንጂ ቴአትሩ  በአዋሳ ከተማ መታየት ከጀመረ ከግማሽ ሠዓት በኋላ ከተመልካቾች መካከል አስቀድመው ቦታቸውን የያዙ የመንግሥት ታጣቂዎችና የአካባቢ ካድሬዎች ተኩስ ከከፈቱ በኋላ ዱላና ቆንጨራ ታጥቀው ወደ መድረክ በመውጣት ተዋንያኑን ያለርህራሄ መደብደብ ጀመሩ፡፡ በዚህ ጥቃት ተዋንያኑና የዝግጅት አስተባባሪዎች ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን በሕይወት ሊተርፉ የቻሉትም ብዙኃኑ ተመልካች ለነፍሱ ሳይሳሳ ባደረገው መከላከል የተነሳ ነበር:: በወቅቱ በአቅራቢያው የነበረው የፀጥታ ኃይል የቴአትር ቡድኑን ከጥቃት ለመከላከል የወሰደው ምንም ዓይነት እርምጃ አልነበረም:: የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን በሰሩት የዜና ዘገባ፤ በተዋንያኑ ላይ ጥቃት መድረሱን አምነው ጥቃቱ የተፈጸመው ግን ቴአትሩን በተቃወሙ ተራ ተመልካቾችና በተበሳጩ የቀድሞው ጦር አባላት እንደሆነ አድርገው ለማቅረብ ሞክረው ነበር፡፡  መንግሥት በዲላና በአዋሳ ከተሞች ላይ በታጣቂዎቹና በካድሬዎቹ የአማተር ቴአትር ቡድኑን አባላት በዱላና በቆንጨራ በማስደብደብ ለኪነ ጥበብ ማሕበረሰቡ ለማስተላለፍ የፈለገው መልዕክት ‹‹ሀሁ ወይም ፐፑ››ን ያየህ ተቀጣ የሚል ነበር፡፡
‹‹ሀሁ ወይም ፐፑ›› እንግዲህ ከደርግ መውደቅ ወዲህ የታየ የመጀመሪያውና በኋላም እንደታየው የመጨረሻው የጋሼ ጸጋዬ ቴአትር ይሆናል፡፡ የወያኔ/ኢህአዴግ መንግሥትም ፈቅጃለሁ ያለው የንግግርና የጽሑፍ ነጻነትም ቢሆን የይስሙላ አንደሆነ በተግባር ለመጀመሪያ ጊዜ የተፈተነው በዚህ ቴአትር ነው ለማለት ይቻላል፡፡ ከእንግዲህ ‹‹ሀሁ ወይም ፐፑ››ን ለሕዝብ ለማቅረብ የማይቻል መሆኑ ሲረጋገጥም የቴአትሩ ‹‹ስክሪፕት›› በመጽሐፍ መልክ ታትሞ በገበያ ላይ ውሎ በቴአትር አፍቃሪዎች ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት ለማግኘት ችሏል፡፡ ከዚህ ጊዜ በኋላም የጋሼ ጸጋዬ ነባርም ሆነ አዳዲስ ቴአትሮች በማናቸውም ሁኔታ ለሕዝብ እንዳይታዩ ስውር እገዳ ተጣለባቸው፡፡
ከመንግሥት በኩል ውሎ አድሮ በሥራዎቹ ላይ እገዳ እንደሚመጣ የሚጠቁሙ ምልክቶች ጋሼ ጸጋዬ ተመልክቷል፡፡ ስለዚሁ ሲናገርም ‹‹...እነሱ (ለወያኔ/ኢህአዴግ) ግን ‹የቴአትር ሥነ ጥበብ ዴሞክራሲ መናገር ከፈለገ ይጎዳናል› ስለሚሉ ከሁሉ በፊት ያንን ለማቀብ የኛን ብዕር ነው መዝጋት ያለባቸው:: በጡረታም ይበሉት ወይም ሌላ ስም ይስጡት እንደመጡ ነው መጋፋት የጀመሩን፡፡ ምክንያቱም ድሮም ያውቁናል፡፡ ‹በረሃ ሆነን ያንተን ቴአትር እናጠና ነበር› ብለውኛል፡፡ የበረሃ ጉዞአቸውን ጨርሰው ሲመጡ ግን ያንኑ ቴአትር ነው እንዳይታይ ያደረጉት›› ብሎ ነበር፡፡
በጨካኝና አምባገነን ወታደራዊ ገዢዎች እግር የተተኩት አዲሶቹ ገዢዎች በኢትዮጵያ ዲሞክራሲን በመመስረት ፈንታ ከፋፋይና መሰሪ የዘር ፖለቲካን በማራመድ፣ አገሪቱን መውጫ ወደሌለው የብጥብጥ አዙሪት ውስጥ እንደሚከቷት ጋሼ ጸጋዬ ተረድቶት ነበር:: ይሁንና ይህን እኩይ የሆነ ጸረ-አገር ኃይል ከሚቃወሙ ኃይሎች ጎን በይፋ ለመቆምና የከፋፋዮቹን አጀንዳም ለማጋለጥ የወሰነው ግን ምናልባት ሥራዎቹ እንዳይታዩ ስውር እገዳ ከተጣለባቸው በኋላ ሳይሆን አይቀርም:: በዚህም መሠረት ከጥበብ ሥራው ጎን ለጎን አገርን ከጥፋት ለማዳን በተደረገው ርብርብ ላይ በየመድረኩ በንቃት ተሳትፏል፡፡ ዘረኝነትን እንጠየፍ፤ ኢትዮጵያን እናድን በሚል ጥሪው ሳቢያ በሕዝቡ ዘንድ የተከበረ የአገር ጠበቃ፤ በመንግሥት ዘንድ ደግሞ የሚፈራ የተቃውሞ ድምጽ ወኪል ሆኖ ተቆጠረ፡፡
ወደፊት መፈቀዱ ወይም መከልከሉ በውል ባይረጋገጥም ጋሼ ጸጋዬ የዊልያም ሼክስፒር ሥራ የሆነውን ማክቤዝ አሻሽሎ ለመስራት በ1990 ዓ.ም ከራስ ቴአትር ጋር ውል ተፈራርሞ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ የረጅም ዓመታት ቁራኛው የነበረው የስኳር ሕመም፤ በየጊዜው ከሚደርስበት የሥራ ጫናና ብስጭት ጋር ተደራርቦ በጤናው ላይ ያደረሰው ጉዳት በግልጽ እየታየ የመጣው በዚህ ጊዜ ሆነ፡፡ ይህ ወቅት ጸጋዬ በማክቤዝ ቴአትር ዝግጅትና በሌሎች ሥነ ጽሑፋዊ ሥራዎቹ የተዋጠበት ጊዜ ስለነበር እረፍት እንዲወስድና ራሱን እንዲያስታምም ከወዳጆቹ የሚቀርብለትን ጥያቄ ሊቀበለው አልፈለገም፡፡ በመጨረሻ የጤና ምርመራ ለማድረግ እንኳ ፈቃደኛ ለመሆን የቻለው በቤተሰቡና በቅርብ ወዳጆቹ ከፍተኛ ልመናና ግፊት ነበር፡፡ የጤና ምርመራ ሲደረግለት የተገኘው ውጤትም ቤተሰቡ ከገመተው በላይ አስደንጋጭ ሆነ፡፡ ልቡ መታመሙንና ሁለቱ ኩላሊቶቹም መድከማቸውን የሚጠቁም ነበር:: አሁን ተገቢውን ሕክምና በአውሮፓ ወይም በአሜሪካ በአፋጣኝ ማድረግ ካልጀመረ በሕይወት የሚቆይባቸው ጊዜያት በጣት የሚቆጠሩ ቀናት ሊሆኑ ይችላሉ፡፡
እንግዲህ ሩቅ አሳቢው ጋሼ ጸጋዬ ቅርብ አዳሪ ሆነ ማለት ነው፡፡ ውጥኑን ከዳር ሳያደርስ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለሕክምና ከኢትዮጵያ ውጪ መሄድ አለበት፡፡ ስለሆነም ከባለቤቱ ከወ/ሮ ላቀች ጋር በመሆን ወደ አሜሪካ አገር ተጉዞ በሐምሌ ወር  1990 ዓ.ም ኒውዮርክ ከተማ ደረሰ፡፡ ኒውዮርክን በረገጠ በአምስተኛ ቀኑ በቅዱስ ባርናባስ ሆስፒታል በተደረገለት ምርመራ፣ ሐኪሞች ሁለቱም ኩላሊቶቹ ከመዳከማቸው የተነሳ ለመስራት የማይችሉ መሆናቸውን አረጋገጡ:: ከእንግዲህ የኩላሊቶቹን ስራ በሚሰራ ‹‹ዲያሊሲስ›› ማሺን በሳምንት ለሶስት ቀናት እስከ ሕይወቱ መጨረሻ ሕክምና ይደረግለታል፡፡ በዚህ ጊዜ ለጋሼ ጸጋዬ ለመቀበል በጣም ከባድ የነበረው እድሜ ልኩን ሳይቋረጥ የሚደረግለት ሕክምና አስቸጋሪነት ሳይሆን ከምንም በላይ አስበልጦ ወደሚወዳት አገሩ ለመመለስ ያለው ተስፋ የመነመነ መሆኑ ነበር፡፡  
ጸጋዬ ከኢትዮጵያ ከመውጣቱ አምስት ዓመታት በፊት ለ‹‹ኢትዮጵያን ሪቪው›› መጽሔት በሰጠው ቃለ መጠይቅ የስደትን ነገር አስመልክቶ ሲናገር፤ ‹‹ምንም እንኳ ከአገሬ ወጥቼ እንድኖር የሚጋብዙ የተለያዩ ጥሪዎች እየመጡልኝ ቢሆንም በሰው አገር በስደት መኖርን በጭራሽ አስቤው አላውቅም:: ስደት በስተመጨረሻ የብዕርን ኃያል ጉልበት ይሰልባል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ስደት ለእነ ዶስቶቭስኪና ሶልዘንስቲን ዓይነቶቹ ታላላቅ ጸሐፍት እንኳን አልጠቀመም፡፡ ለኔ ብጤው ገራገርስ ቢሆን ምን የሚበጅ ነገር አለው?! ከሕዝቡ የእለት ከእለት ሐዘንና ደስታ፤ እንባና ሳቅ፤ ቅዝቃዜና ትኩሳት ርቆ የሚደረስ ግጥምም ሆነ ቅኔ ምንም ዓይነት መቅኖ አይኖረውም፤ ይህ ነው የሁልጊዜ ፍርሃቴ›› ብሎ ነበር፡፡
ጸጋዬ አሁን የሚኖረው ከሚወዳት አገሩ በሺዎች ማይል ርቀት ላይ ቢሆንም ውሎና አዳሩ ግን በኢትዮጵያ ላይ ነበር፡፡ ከእለት ወደ እለት እያሽቆለቆለ በመሄድ ላይ ባለ አሳሳቢ የጤና ሁኔታ ውስጥ ያለ ቢሆንም እንኳ ስለ አገሩ አለማሰብና ስለ አገሩ አለመጻፍን የሚቆጥረው ይቅርታ እንደማይደረግለት የአገር ክዳት ነበር:: ሕመሙ በአካሉ ላይ ካደረሰበት ጉዳት በበለጠ የሚያስጨንቀው የወያኔ/ኢህአዴግ መንግሥት በሚወደው ሕዝብና በሚያፈቅራት አገሩ ላይ በማን አለብኝነት የሚፈጽመው ወንጀል ነበር:: ስለሆነም አገርን ከጥፋት ለመታደግ በአሜሪካ በሚጠሩ ልዩ ልዩ ስብሰባዎች ላይ ከሕመምተኛ አልጋው ላይ እየተነሳ በመገኘት፤ ኢትዮጵያውያን በመሰሪ ከፋፋይ ገዢዎች ተታለው አንድነታቸው እንዳያላሉ ድምጹን ከፍ አድርጎ አሰምቷል:: በዚህ አስቸጋሪ ሕመም ላይ ሆኖም እንኳን ብቸኛውና ኃይለኛው የጸጋዬ ብዕር ለአንድም ቀን ሥራ ፈትቶ አያውቅም፡፡ በሕመሙ ወቅት ኒውዮርክ ከተማ በሚገኘው የስደት ቤቱ ተመላልሰው የጎበኙት ወዳጆቹ እንደሚናገሩት ጸጋዬ ስለ ኢትዮጵያ ያልተናገረበት ወይም ያልጻፈበት አንድም ቀን አልነበረም፡፡
ጋሼ ጸጋዬ ኒውዮርክ ከሚገኘው የስደት ቤቱ ሆኖ በኢትዮጵያውያን ለሚዘጋጁ ድረ ገጾች፣ ሬዲዮና ቴሌቪዥኖች እንዲሁም ልዩ ልዩ የሕትመት ውጤቶች ስለ ኢትዮጵያና ሕዝቦቿ ባህል፣ አንድነትና ፍቅር እንዲሁም መሰሪ ልጆችዋ ስለደቀኑባት የመበታተን አደጋ ሳይታክት ቃለ-ምልልስ ሰጥቷል:: በአገር ቤት በዋነኝነት በጦቢያ መጽሔት ላይ የሚሰጣቸው ቃለ ምልልሶች በብዙኃን አንባቢዎች ዘንድ በጉጉት የሚጠበቁ ነበሩ፡፡ በተለይ በዚሁ መጽሔት ላይ ‹‹ኢትዮጵያዊነት›› በሚል ቅጽ በተከታታይ እትሞች ይወጡ የነበሩት የጋሼ ጸጋዬ ግጥሞች ሳይጠቀሱ የማይታለፉ ናቸው፡፡ በተለይ ‹‹ኢትዮጵያዊነት›› በሚለው ቅጽ ውስጥ ከተካተቱት የባለቅኔው ሥራዎች መካከል ይድረስ ለኛ፣ ይድረስ ለተቃዋሚዎች፣ ይድረስ ለመለዮ ለባሹ፣ ይድረስ ለመራጩ ዜጋ፣ ይድረስ ግንቦት ሰባት ይድረስ፣ ምርጫና ቃጠሎ . . . ወዘተ የተሰኙት ምንጊዜም የማይዘነጉ ታላላቅ ሥራዎቹ ነበሩ፡፡
እንግዲህ የድኅረ-ደርግ ዓመታት ጋሼ ጸጋዬ ተስፋ እንዳደረገው፣ ነባርና አዳዲስ ስራዎቹ ለሕዝብ በስፋት የቀረቡበት ሳይሆን እንዲያውም ካሳለፋቸው ሁለት መንግሥታት በከፋ ደረጃ ሥራዎቹ የስውር እገዳና ክልከላ ሠለባ የሆኑበት ነበረ፡፡ ከዚህም በላይ ዘመኑ የግል ጤናው ክፉኛ ተቃውሶ ሕይወቱ ወደ ሞት አፋፍ የደረሰበትና በዚህም ምክንያት ከሚወዳት አገሩ ተለይቶ ለስደት የተዳረገበት መጥፎ ጊዜ ሆነ:: ይሁንና ሳንሱር፣ እገዳ፣ አሳሳቢ የጤና ችግርም ሆነ ስደት ጸጋዬ ለጥበብና ለአገሩ ያለውን ፍቅር አላደበዘዘበትም፡፡ እንግዲህ ባለቅኔውን ጸጋዬ ገብረ መድኅንን የምናስታውሰው ከአምባገነን አገዛዞች ጋር እየታገለ ትቶልን ባለፈው ዘመን አይሽሬ የጥበብ ሥራዎቹ ብቻ ሳይሆን፤ ለአፋኝ አገዛዝና ለሕመም ሳይንበረከክ በኢትዮጵያ እውነተኛ ዴሞክራሲና ሠላም እንዲሰፍን ያደረገውን ተጋድሎ እየዘከርንም ጭምር ነው፡፡
በባዕድ አገር ምሕረት በሌለው ደዌ ተይዞ እየተሰቃየ እንኳን የሚወዳት አገሩንና ሕዝቦቿን ለአንዲት ደቂቃም እንኳን ሳይዘነጋ በብዕሩ ለዴሞክራሲና ለነጻነት ያደረገው አንጸባራቂ ተጋድሎ ለዘላለም ሲታወስ የሚኖር ነው፡፡

Read 1833 times