Saturday, 07 December 2019 13:02

የማይደበዝዘው ኮከብ

Written by  ይነገር ጌታቸው
Rate this item
(4 votes)

      (የኤልያስ መልካ ሴት፣ ሀገር እና እግዜር!)
                   
             ብዙ ሰዎች የኤልያስ መልካ የሙዚቃ ግጥም እንዴት ያለ ነው? የሚል ጥያቄ ቢቀርብላቸው፣ አሉታዊ ነገርን የሚሸሽና አዎንታዊነት የሚሰብክ መሆኑን ይመሰክራሉ፡፡ ነገርዬው ጨለማን የሚፈራ፣ ብርሃንን የሚናፍቅ መሆኑን ያሳብቃል፡፡ ግን የኤልያስ ብርሃንን ሙጥኝ ማለት፣ ነገም ሌላ ቀን ነው በሚል ነባር  ብሂል የተተበተበ አይደለም፡፡ ይልቁኑ በጨለማ ውስጥ እየኖረ የነገን መልካምነት ያውጃል፤ የወደፊት ዓለሙን ራሱ ሊገነባ  ይሞክራል፡፡ ዘልማዳዊ የሆኑትን እሳቤዎችም ዳግም ለመበየንና ለመፈከር (redefine and interpret) ይጥራል:: የማይደበዝዘው ኮከብ እንዲህ ያለ በዘመን ላይ ማመፅ፣  ከፈረንሳዊው  የፍልስፍና ሰው አጊዩስት ኮምት ጋር እንድናመሳስለው ያደርገናል፡፡
ኤልያስ አውቆትም ሆነ ሳያውቀው የአግዮስት  ኮምንትን ወኔ የተላበሰ ሰው ነው ስል፣ አንድም ሁለቱም ሰዎች  ያለፉበት የዘመን አውድና ማኅበረሰባዊ የሞራል ግርግር  ተመሳሳይ መሆኑን ለመጠቆም፣  አንድም  ከዚህ ለመውጣት የሄዱበትን መንገድ ለማብራራት ነው፡፡ በሌላ በኩል፤ ኤልያስም ሆነ ኮምት ትናንትን ማፍረስ ግብ አይደለም በሚል አመለካከት፣ ሃይማኖታዊ በሆነ መንገድ  ሀገርና  ባህልን ዳግም በይነዋል (redefine እንዲሉ)፡፡ ተመሳስሏቸውን በውሉ ለመረዳት እንዲመቸን፣ ሁለቱን ግለሰቦች ለየቅል ለማየት እንሞክር፡፡
አግዮስት  ኮምንት የፈረንሳይ አብዮት ከፈነዳ ከጥቂት ዓመታት በኋላ የተወለደ የፍስፍና ሰው ነው፡፡ ኮምንት ያደገባት  ፈረንሳይ በህዝባዊ ፍላጎቶች ትርምስ ውስጥ የገባች፤ የሞራል ሁኔታዋ የተናጋ፤ አንድ ወጥ ሀገራዊ ህልም ያልነበራት፤ መጓዝን እንጂ መድረስን ግብ ያላደረገች ነበረች፡፡ የለውጥ ምጥ አስጨንቆ የያዛት ምዕራብ አውሮፓዊት ሀገር፤ ማኅበረሰቧ ከገዥዎቿ ጋር የተፋጠጠባት፤ በየቦታው ስርዓት አልበኝነት የነገሳባት፤ የደቦ ፍርድ የተለመደባት ከሆነችም ውላ አድራለች፡፡ ሽግግር በሚል የዳቦ ስም አዕላፍት በጅምላ የሚገደሉባት፣ ሴተኛ አዳሪነት የበዛባት፣ ሌብነት የገነነባት ሆናለች፡፡
ይህ ነባራዊ ሁኔታ መንግስታዊና ህዝባዊ ሽብር ከዳር እስከ ዳር እንዲፈጠር በማድረግ ህዝባዊ ቀቢፀ ተስፋን ፈጠረ፡፡ ተስፋ የተጣለበት የስርዓት ለውጥ በወታደሮች መነጠቁም  የወል  እብደቱን (collective madness) አጦዘው፡ ኮምት የተወለደውም ሆነ ያደገው እንዲህ ያለው ማኅበረሰባዊ ምስቅልቅል በነገሰባት ሞንቴፔሌ  ቢሆንም፣  ከተስፋ ማጣት ጋር ግን ሊያብር አልፈለገም፡፡ በመሆኑም ፖዘቲቪዝም የሚባለውን አስተምህሮቱን ይዞ ብቅ አለ:: ፖዘቲቪዝም በአንድ በኩል የፈረንሳዊው የፍልስፍና ሰው የማኅበረሰብ የእድገት ደረጃ ምደባ ውስጥ የመጨረሻው ጥግ ተደርጎ የሚቀመጥ ሀሳብ ነው፡፡  ይህ ማለት  የዘመናዊው  ስነ-ማኅበረሰብ ጥናት (sociology) አባትና ተግባራዊ የፍልስፍና ሰው የሚባለው ኮምት፤ አንድ ህብረተሰብ  ቴዎሎጂካልና ሜታፊዚካል የዕደገት ደረጃን ካለፈ በኋላ ወደ ፖዘቲቪዝም መምጣቱ አይቀርም የሚል መከራከሪያ እንደነበረው ያስታውሳል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ  የኮምት ፖዘቲቪዝም  ብያኔ፣  እራሱን የቻለ ፅንሰ ሀሳብ  መሆኑንም ልብ ማለት ያሻል፡፡ የሞንቴፔሌው ተወላጅ፣  የሰው ልጆች የለውጥ ፍላጎት የማይገታ ቢሆንም፣ መዳረሻው ግን በውሉ መጤን እንዳለበት ያስተምራል፡፡ አብዮት በሚሉት ምንትስ ሀገሩ ያጣችውን መልካም ነገር በማስታወስም፣ የነገ መንገዳችን፣ ከትናንት በመመነን ብቻ ሳይሆን በመዋስም ሊሆን ይገባዋል የሚል ዕምነትን አራምዷል፡፡ ኮምት አንድ ማኅበረሰብ በጊዜ ሂደት ከሃይማኖት እሳቤ ሙሉ በሙሉ መውጣቱ አይቀርም የሚለው አስተሳሰቡ በርካታ ትችት እንዲሰነዘርበት ቢያደርገውም፣ የሕብረተሰቡ ሽግግር ግን ያለ ሃይማኖታዊ አስተምህሮት ሊሳካ እንደማይችል ለፍፏል፡፡ ይሁን እንጂ  ኮምት  ሃይማኖትን የሽግግር ድልድይ የሚያደርገው እንዳለ በመቀበልና በመስበክ ሳይሆን “ፖዘቲቪ ሃይማኖት” በሚል እሱ ለሚያስበው ማኅበረሰብ ግንባታ ጡብ እንዲሆነው አድርጎ በመቅረፅ ብቻ ነው፡፡ እዚህ ላይ የኮምት ፖዘቲቪዚም፣ በአንድ በኩል  ሃይማኖትንም ሆነ ሌሎች ነባር ልማዶችን ዳግም በመበየን የሚመራ ሲሆን በሌላ በኩል፣. የራስ ፈለግንም በማበጀት ይጠመዳል፡፡ የሞንቴፔሌው ብላቴና፤  ሀገር፣ ሃይማኖት፣ ሴት፣ ታሪክ ወዘተ--  የሚሉ ፅንሰ ሀሳቦችን ዳግም ሲበይንና ሲፈክር (interpret) የኖረውም በዚህ ምክንያት ይመስላል፡፡
ኤሊያስ እንደ ኮምት
ኤሊያስ ከአጊዮስት ኮምት ጋር ይቀራረባል ስል፣ ከላይ እንደጠቀስኩት፣ አንድም፣ ካለፈበት ዘመን የሞራል ግርግር ጋር አሰተሳስሬ ለማየት በመፈለሄ ሲሆን አንድም የእኛው የሙዚቃ ሰውም ፖዘቲቪዝም የተጠናወተው፣ በነገሮች ዳግም ፍካሬ የሚያምን ከመሆኑ ይመነጫል:: ኤሊያስ መልካ  አብዮቱ ከፈነዳ በኋላ ሀገር ቀይና ነጭ ሽብር በሚል የሀሳብ መስመር ተከፋፍላ፣ የማያበራ ዕልቂት ውስጥ በገባችበት ወቅት የተወለደ ሰው ነው፡፡ ፕሮፌሰር ዶናልድ ሌቪን፤ ይህን ዘመን የፈረንሳይን አብዮት ተከትሎ ከመጣው  የሞራል ግርግር ወቅት ጋር ያመሳስሉታል፡፡ በርግጥም የእኩልነት፣ የነፃነትና የወንድማማችነት ጥያቄን ያነገበው የሁለቱ ሀገራት አብዮት፤ ወታደሩ ስልጣን በመንጠቁ የወል አብደትን አስከትሏል፡፡ በፈረንሳይ በ1791 የተፈጠረው ቀውስ፣ በእኛ ሀገር በ1967 ዓ.ም ከሆነው ነገር ጋር ይቀራረባል፡፡ የባህር ማዶዋ ሀገር ሰዎች፣ ከአብዮቱ በፊት የነበረውን በጎ አስተሳሰብ ለማስቀጠል እንደከበዳቸው ሁሉ፣ የእኛም ሀገር እጣ ፋንታ ከዚህ የሚላቀቅ አልሆነም፡፡ ነገራችንን በውሉ ላጤነው ሰው ግን የማኅበረሰቡ የሞራል መመሰቃቀልና የፖለቲካ ጥያቄ፣ በአብዮት ዋዜማና ማግስት ብቻ ታይቶ የጠፋ ሳይሆን የዛሬውን የሰርክ ህይወታችንንም የሚፈታታን ነው፡፡ ጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ በቅርቡ ለንባብ ባበቁት “መደመር ”የተሰኘ መፅሐፍ፤ “ቀጣዩ የፖለቲካ ፕሮጀክት ነፃነትን፣ እኩልነትና ወንድማማችነትን መመለስ ነው” የሚሉንም ለዚህ ይመስላል፡፡ ይህ ደግሞ  ኤሊያስ እንደ ፈረንሳይ አብዮት፣ የሞራል እብደት ውስጥ በገባንበት ወቅት የተወለደ ብቻ ሳይሆን ሙሉ ዘመኑን በዚህ የስነ-ልቦና መናወጥ ውስጥ ያሳለፈ  መሆኑን ያረጋግጣል:: ይሁን እንጂ ኤሊያስ፣ እንደ አጊዮስት ኮምት፣ የወል ተስፋ ማጣት ውስጥ የገባን ማኅበረሰብ አስለቃሽ ሆኖ ለመኖር አልመረጥም፡፡  ይልቁኑ የማይደበዝዘው ኮከብ፣ የፖዘቲቪዝም እሳቤን አንግቦ፣ ጨለማን በብርሃን ሊረታ ግብግብ ይጀምራል፡፡ በእዮብ መኮንን እንደ ቃል አልበም ውስጥ የምንሰማቸው የኤሊያስ ስንኞች፣ የሰርኩን ዓለም የሚሸሹትና አዲስ ዓለምን የሚዋጁትም በአጋጣሚ አይመስልም፡፡
እያለሁ በትዕግስት
ስጠብቅ ደግነት  
ለካስ ለነገ ነው
ያለፍኩት ከትናንት
ይምሽልኝ ዛሬ ቀኑ
ያኔ ነው የሚታዬው ወጋገኑ፡፡
“የጠፋ ይገኛል” በተሰኘው የሃይሌ ሩትስ ስራ ውስጥ ያሉትን ስንኞች እንስማቸው፡-
ተስፋ ላጣ ለጨነቀው፤
ምን ሊበጅ አበቃ ቢለው
ካላላለ  ዙሪያው ያለ
ነገ መልካም  የተሻለ፡፡
ኤሊያስ፤ ኮምት እንዳደረገው ሁሉ ከትናንት መሸሽን ብቻ ሳይሆን ነገን ለመስራትም ይቃትታል፡፡ ይህ ግን በግብታዊነት ተከተሉኝ በሚል ስብከት የሚያደነቁር አይደለም፡፡ ከዛ ይልቅ ማኅበረሳባዊ ሽግግር ለማድረግ የሚረዱ ሦስት ጉዳዮችን ከግምት ውስጥ ያስገባ ነው:: የማይደበዝዘው ኮከብ፤ እንደ ፈረንሳዊው የፍልስፍና ሰው ኮምት ሁሉ ማኅበረ-ፖለቲካውን ለመቀየር ቀዳሚው ተግባር የልሂቃን መሰረቱን ማስተካከል እንደሆነ ተረድቷል፡፡
 በልዑል ኃይሉ “ቀዳሚና ተከታይ”  ሙዚቃ ውስጥ የምንሰማቸው ስንኞች ለዚህ ዋቢ ናቸው፡-
ፀጥ አልንና ሙት መስልናቸው መርዝ የጣፈጠን
ሊቅ ነን ሊሉ ቃርመው ያመጡትን ያኩትን ውጠን
……………
ቋንቋ አቡክተው ታሪክ ፈትፍተው ስንቅ
አጥፍተው
ዋሹን ህግ እያቀለሉ፣ ከጥንት አባቶች እያሉ
ሰው ባልሰማው ባላወቀው ባልኖረበት ዘመን
በራቀው
ከሚግባባት ቋንቋ አብልጦ ምን ያድርግ ነው
ጥንት አብልጦ
ዶናልድ ሌቪን፤ በኢትዮጵያ የጨነገፉ የለውጥ ጅምሮችን ሲያነሱ አንዱ ምክንያት፣ የልሂቃኑ ጥራዝ ነጠቅነት መሆኑን ያሰምራሉ፡፡ ኤሊያስ፤ ሀገር ወደፊት እንድትራመድ ከሁሉም በፊት ልሂቃኑ ኢትዮጵያዊ መሆን አለባቸው ብሎ ያምናል፡፡ ትችቱ ግን በዚህ አይገደብም:: የሀገረ መንግስቱንና የብሄር ግንባታ ትርክቱ መዛነፉን ይጠቁማል፡፡ የማይደበዝዘው ኮከብ፤ የምንፈልጋትን ኢትዮጵያ ለመገንባት ከሁሉም በፊት ለዚያ የሚመጥን የሞራል ልዕልና ያለው ማኅበረስብ እንደሚያስፈልግም ደጋግሞ ለፏል:: በኤሊያስ  ግጥም ውስጥ የምንሰማቸው ሃይማኖታዊ ጉዳዮች፤ በየትኛውም የእምነት ቅፅር ውስጥ ላለ ሰው የማይጎረብጡትም ለዚህ ይመስለኛል፡፡
ኤሊያስ መልካና እና አጊዮስት ኮምት የሚጋሩት ድንበር ሰፊ ቢሆንም፤ ከፖዘቲቪዘም ፍልስፍና አንፃር ግን ሦስት ጉልህ መልክን የተላበሱ ናቸው፡፡
የምንፈልገውን ሀገር ለመገንባት ከሁሉም በፊት ለዚያ ምቹ የሆነ የሞራል ልዕልና ያለው ማኅበረሰብ መመስረት አለብን ብለው ማመናቸው፡፡
ምንም ነገር በማኅበረሰብ ግንባታ ውስጥ አዎንታዊ ሚና የማይኖረው ከሆነ፣ የመጠቀም ፍላጎት የሌላቸው መሆኑ፡፡ (በኤሊያስ ሙዚቃዎች ውስጥ ውዝግብ የማያጣውን የሀገራችን ነገስታት ታሪክና ውዳሴን የማንሰማውም ለዚህ ይመስለኛል፡፡ “ያስተሰርያል” በተሰኘው የቴዲ አፍሮ የሙዚቃ አልበም ላይ በርከት ያሉ ስራዎችን ያቀናበረው ኤሊያስ መልካ፤ “ያስተሰርያል”ን ለምን አላቀናበርክም የሚለው ጥያቄም እዚህ ላይ ይነሳል፡፡)
የራሳቸውን  ደቀ መዛሙርት ፈጥረው አዲስ ሀገር፣ አዲስ ማኅበረሰብ ለመፍጠር መትጋታቸው፤ አጊዮስት ኮምት  ከመላው ፈረንሳይ የተውጣጡ ካህናትን ሰብስቦ፣ በሃይማታዊ አስተህምሮት ውስጥ ያሉ መልካም ጉዳዮችን በማጉላት የተሻለ ማኅበረሰብ ለመፍጠር ጥሯል:: እዚህ ላይ የፈረንሳዊው የፍልስፍና ሰው ኮመት፣ ካህናት ሃይማኖታዊ ብቻ ሳይሆኑ የስነ-ማኅበረሰብ ለውጥ አቀንቃኞች መሆናቸውን ልብ ማለት ያሻል፡፡ በኤሊያስ “ቤተ-መቅደስ” በገና ስቱዲዮ ውስጥ የሚውሉ ሙዚቀኞችም እንዲህ ያለ ሚና የነበራቸው መሆኑ የሚያከራክር አይደለም፡፡ ልዑል፣ ቤሪ፣ ጌቴ፣ኃይሌና እዮብ እያልን የምንጠራቸው ድምፃዊያንም፣ ከዚህ አንፃር የማኅበረሰብ አንቂና የሰርክ ህይወትን ፈታሽ እንጂ ድምፃውያን ብቻ አልነበሩም፡፡ እንዴት የሚል ጥያቄን በማንሳት የኤሊያስን የሙዚቃ ግጥሞች ከፍታ፣ ከአጊዮስት ኮምት የጠያቂነትና የፖዘቲቪዝም ፍልስፍና አንፃር ለመመልከት እንሞክር:: ለዚህም ሴት፣ ሀገር እና እግዜር የሚሉ አንፃሮችን እንመልከት፡፡
ሴት
ሴትነት በህዝባዊ  ባህል  ውስጥ ሁለት መልክ ያለው ነው፡፡ ተጠቃሚነት እና የወሲብ ቁስነት፡፡ የኢትዮጵያ ሙዚቃ ከዚህ አንፃር ሴትነትን ከሞላ ጎደል የወሲብ ቁስ አድርጎ የሚመለከት ነው:: የሙዚቃ ግጥም ፃሀፊዎቻችን ሴትን በወንድ ህሊና ውስጥ የምትኖር ፍጡር አድርገው መቀበላቸው ብቻ ሳይሆን ሴት አድማጮችም ይህን አምነው መኖራቸው የሚገርም ይመስለኛል፡፡ አዲስ ማኅበረሰብ ለመፍጠር የሚታትረው ኤሊያስ ግን ይህን የሰርክ መንገድ ይንዳል፡፡ ሴትነትን ከፍ አድርጎ እስከ ፈጣሪ ተወካይነት ያደርሳል፡፡ ይህ መንገዱ አንድም በፈጣሪና በሰው መካከል ሌላ አገናኝ የለም ከሚለው ግላዊ  ፍልስፍናው የሚቀዳ ሲሆን አንድም ሴትን የማኅበረሰባዊ ሞራላዊ ሽግግር  ዋና መሪ ናት ብሎ ከማመኑ ጋር ይተሳሰራል፡፡ እዮብ ያዜመላት ሴት ለዚህ ዋቢ ትሆናለች ፡፡
ወኪል ነሽ ከላይ
ደግነቱን እንዳይ
……..
የእሱ ምርጫ ነሽ
ለእኔ መርጦ የሸለመሽ  
ኤሊያስ በሙዚቃችን ውስጥ የተለመደውን ሴትን የወሲብ ቁስ የማድረግ እሳቤ፤ በጌቴ አንለይና  በኃይሌ ሩትስ ሙዚቃ ውስጥም ፊት ለፊት ለመናድ ሞክሯል፡፡ “መልክሽ አይበልጥሽም” የሚለው ሙዚቃም በጌቴ ውስጥ ጎልቶ ይሰማ እንጂ ሁሉንም በእሱ ስራዎች ውስጥ የምንሰማቸው ሴቶች ይወክላል:: ኤሊያስ ሴትን  እንዲህ ናት ብሎ  ስለዘመረላት ብቻ አርነቷን እንደማታውጅ የገባው ይመስላል:: በዚህ የተነሳም ሴቶች የምንለው ማንን ነው? የሚል ቁልፍ ጥያቄ ያነሳል፡፡ እዚህ ላይ ሰርቶ ባጠናቀቀው የታዲዎስ አልበም ውስጥ ሴትነትን ያየበት መንገድ ስለሚገርምኝ፣ ግጥሙን ከመተረክ ወጥቼ ሀሳቡን ብቻ ልናገር፡፡ ብዙ ወንዶች ሲገናኙ፤ ሴቶች የሚል ጥቅል ድምዳሜን በመዋስ የራሳቸውን ፍረጃ ይሰጣሉ፡፡ ኤሊያስ ወንዶች ሴቶች እያሉ የሚወቅሱት ማንነው የሚል ሙግት፣ ከራሱ ጋር ይጀምራል፡፡ ከዛም ሴቶች ብለን የምናወግዛቸው፣ የምናማቸው፣ በአሉታዊ ጎን የምንጠራቸው፣ የራሳችንን ፍቅረኛና የትዳር አጋር መሆኑን እንዴት ልብ ለማለት ተሳነን፣ በሚል አዲስ የሃሳብ ግዛትን ይመሰርታል፡፡
ሀገር
ኢትዮጵያዊነት በሙዚቃችን ውስጥ ግዙፍ ጭብጥ ሆኖ  የኖረ ነው፡፡ የመጀመሪያው ጉዳይ ሀገርን በመልክአ ምድር ውስጥ ለመበየን መሞከር ነው፡፡ ተራራው፣ አየሩ፣ ሸንተረሩ የሚለውን አድናቆት የምንሰማውም በዚህ የተነሳ ይመስለኛል፡፡ እንዲህ ያለው ከሰው ይልቅ መልክአ ምድርን ማግነን እንደ ዓለማየሁ ፋንታ ባሉ ድምፃዊያን ሙዚቃ ውስጥ የጦርነት ድላችን ሳይቀር፣ በእነሱ ውልታ የመጣ መሆኑን እስከ መግልፅ የሚደርስ ነው:: ሌላው መልክ ሀገርን በማይጨበጡ ሀቲቶች ማወደስ ነው:: መንፈሳዊና ታሪካዊ እሳቤዎችን ጨምሮ ብዙ ጉዳዮች በዚህ ውስጥ ይወድቃሉ:: ያልተደፈረችና የማትደፈር ሀገር እንዲሁም የቃል-ኪዳን ምድር መባሉም ዘወትሯዊ ሆኗል፡፡
ኤሊያስ የሞራል መደላድል እየፈጠረላት ያለችው ሀገር፤ ከላይ የተገለፀችው አይደለችም:: እዚህ ላይ የኤሊያስን መልካን ኢትዮጵያ ያሳያሉ ያልኳቸውን ሁለት አንፃሮች ልጥቀስ፡፡ የመጀመሪያው ነባሩን መናድ ሲሆን ሁለተኛው በአዲስ ሀሳብ መዋጀት ነው፡፡
የዳን አድማሱ  “ኢትዮጵያ” ሙዚቃ ለመጀመሪያው ጥሩ ማሳያ ስለሚሆን እሱን ላንሳ፡-
ምስጢር ላንች ብቻ የሚልክ
ያዳላልሽ  ሌላን ግን  ሲንቅ
አለ ያልሽን ቅን አምላክ ሰማይ
ሁሉን የፈተተ ነው ወይ
ኤሊያስ ብሉያዊ የሚመስለውን የኢትዮጵያ የሙዚቃ ጭብጥ በዚህ መልክ ይንደዋል:: ኢትዮጵያ የቃል ኪዳን ሀገር ናት የሚለውን ሀቲት ያፈርሳል፡፡ ኤሊያስ በዚህ አያበቃም፤ ሀገር መልክአ ምድር ነው የሚለውን አመለካከትንም ለመናጥ አርፎ አይቀመጥም፡፡  
የልዑል ኃይሉ “አንችው ነሽ አካሌ” ላይ የምንሰማት ኢትዮጵያ፤ የኤሊያስን እውነተኛ የሀገር ትርጓሜ የምናገኝበት ይመስለኛል፡፡ ሙዚቃው ትርጉም በሌለው ቋንቋ ይጀምራል:: ትዕምርቱ ጣናና ዳሎል ትርጉም አልባ መሆናቸውን ይጠቁማል፡፡  ከዛም ኢትዮጵያ ማለት መሬቱና ውኃው አይደለም፤ ሰው እንጂ የሚል ሀሳቡን ይሰነዝራል፡፡
መሬቱ አይደለም ሀገር ጣራው
ነፍስሽ ነው ቤቱ የሀገር ስፍራው
አንችው ነሽ ሀገሬ ኦያ
ነፍስ ያለሽ ህይወቴ አያ
.......
ነፍስሽ ነች ህይወቴ ሆያ ሆዬ
ነፍሴ ነች ህይወትሽ ሆያ ሆዬ
.......
ካንች አይብስ ምንጊዜም
ዳሎልም ተከዜም
ለፍቅር እንጂ ማዜም
ኤሊያስ፤ በጌቴ አልበም ውስጥ የሚያነሳው  የቀይ ጥቀር ጠይም ሀሳብ ግን ከፍታውም በሀገር የሚወሰን አይመስልም፡፡ ኢትዮጵያን በሌላ የፍልስፍና አውድ ውስጥ ያነሳታል፡፡
አለች ቆጣ ቆጣ ፊቷን ከፋውሳ
የሩቅ አርገው ቢያሙት ጠይም ሰው ለራሷ
ጥቁርስ ቢታማ እንዴት አያማትም
ጠይም ናት ልጅቷ ባዕድ ሰው የላትም  
ኤሊያስ ኢትዮጵያን ሲያስብ ከእነ ኢትዮጵያዊ መልኳ ነው፡፡ “ከምን ነፃ ልውጣ” የሚለው የቤሪ ሙዚቃ፤ ከራስ ጋር ሙግት የፈጠረው የእሱ ስራ ይመስለኛል፡፡ ጫፉ ግን ሀገር ላይ ብቻ ሳይሆን እግዜር ደጃፍ ይደርሳል፡፡
እግዜር
የኤሊያስ ጠያቂነት የፈጣሪን ደጃፍ ያንኳኳል፡፡ የእግዛብሄርን መኖር ጠይቆ እንጂ አምኖ የተቀበለ አይመስልም፡፡ በፍልስፍና ውስጥ ተደጋግመው ከሚሰሙ ሙግቶች መካከል በፈጣሪና በሰው መካከል ማነው ተወካይ  የሚለው ነው፡፡ ዘርያቆብ አሁን እኔን ፈጣሪ ይሰማኛል ብሎ ጠይቆ  “ጆሮን የሠጠኝ አምላክ እንዴት አይሰማም ብዬ አሰብኩ” ሲል ለራሱ ይመልሳል፡፡ ኤሊያስ በዘሪቱ ከበደ  ዜማ ውስጥ ለእንዲህ ያለው ፍልስፍና ባሪያ መሆኑን አረጋግጧል፡፡   
አንዱ በዝቶበት ሲቸገር መምረጥ
ሌላው ምንም አጥቶ ላይ ታች ሲራወጥ
ላዘነው ሰው ምነው ቢያካፍለው  ቢያቻችለው
ለተረፈው ምነው በቃ ቢለው ይብቃህ ቢለው  
ለመኖር ሲጓጓ ለማየት የፊቱን
ግን ሳይወድ ይሄዳል ሳይደርስ ምኞቱን
ኦ ምን አለፋኝ
መልሱ ከጠፋኝ
እሱ አይሳሳት
ሁሉ በምክንያት
የእኔም አይን አይቷል እሱ ያበራው
ሰሪ አይበልጥም ወይ
ኦ ከተሰራው
(በግጥሙ ላይ ዘሪቱ እንደተሳተፈች ቢታወቅም፣ ፅንሰ-ሃሳቡ የኤሊያስ መሆኑን ለመረዳት ግን ከዚያ በኋላ የወጡ ስራዎቹን ማየቱ በቂ ይመስላል፡፡)
የማይደበዝዘው ኮከብ፤ በሙዚቃ ታሪካችን ውስጥ አንድን  ሀሳብ ተከታታይ በሆኑ ስራዎች በተለያየ አንፃር እንድንመለከተው ሲያደርግ የኖረ ሰው ነው፡፡ ደራሲ ብርሃኑ ዘሪሁን፤ የአብዮቱ ዋዜማ፣ መባቻና ማግስት ብሎ ሦስት ተከታታይ መፅሐፍትን በአንድ ርዕሰ ጉዳይ ላይ እንዳስነበበን ሁሉ፤ ኤሊያስም ስለ ፈጣሪና ተፈጣሪ  በበርካታ ሙዚቃዎቹ ውስጥ መላልሶ ያነሳል፡፡ በሃይሌ ሩትስ አልበም ተራ ቁጥር አምስት  ላይ የምንሰማቸው  ስንኞች፤ ከላይ ካነሳነው የሙዚቃ  ግጥም ጋር የሚመሳሰሉትም ለዚህ ነው፡፡  
እውቀት መልካም ነው መመራመር
የሰሪውን እጅ ሳይዳፈር
የሳይንሱን ዛፍ መርጠው ካልበሉ
የሞት ፍሬ አለው በየመኸሉ
ፅሁፌን ከመቋጨቴ በፊት አንድ ጥያቄን ማንሳቱ ተገቢ ይመስለኛል፡፡ የኤሊያስ እግዚአብሄር ማነው? ኢትዮጵያዊው አጊዮስት ኮምት፣ ሃይማኖትን ዳግም በመበየን፣ አዲስ ሀገራዊ የሞራል መደላድን ለመፍጠር የጣረ ሰው መሆኑን ጠቅሻለሁ፡፡ ይህ የሞራል መደላድል የምናስባትን ኢትዮጵያ ከመፍጠራችን በፊት ለዚያ ዝግጁ የሆነ ማኅበረሰብን መገንባት መሆኑንም ጠቁሜያለሁ፡፡ የኤሊያስ የሰርክ ልማድ እንዲህ ከሆነ፤ የእሱ እግዚአብሄር በክርስትና ውስጥ ብቻ የታጠረ ነው ብሎ መገመቱ የዋህነት ነው፡፡ የማይደበዝዘው ኮከብ፤ ቅዱስ ቁርአንን በውሉ አንብቧል፡፡ በፕሮስቴንት ቤተ-ክርስትያን ውስጥ አግልግሏል፡፡ የጆብሃ የዕምነት አስተምህሮንም በወጉ አጥንቷል:: ኤሊያስ ከዚህ ሁሉ በኋላ ነው እንግዲህ ተቋማዊ የሆነውን እግዚአብሄር ሸሽቶ፣ እሱ የሚያምነውን  እግዚአብሄር መከተል የጀመረው:: ይህ በእኔ ግምት የኤሊያስን እግዜር ግላዊና ፅንሰ ሀሳባዊ ያደርገዋል፡፡ ግላዊነቱ መፅሐፍ ቅዱስ ላይ ያለውን እግዚአብሄር፤ትክክል ነኝ ባለበት መንገድ መረዳቱ ሲሆን ፅንሰ ሃሳባዊነቱ የወል ካለመሆኑ ጋር ይተሳሰራል ፡፡ ለእኔ ይህ መልኩ በሀገራችን ታሪክ፣ በተራራቀ ዘመን፣ ህልው የሆኑትን አቡነ ኤውስጣጢዎስና ደቂቀ እስጢፋኖስ ያስታውሰኛል፡፡ ጥቂት በማይባሉ ቦታዎች ላይም ከዘርዓያቆብ ጋር ይጎራበትብኛል::
ኤሌያስ ድንቅ የዜማ ደራሲ፤ እንደ ተወርዋሪ ኮከብ የሚታይ አቀናባሪ መሆኑን ማንም ይስማማበታል፡፡ ይሁን እንጂ በሙዚቃ ታሪካችን ውስጥ የፈጠረው ሥነ-ግጥምን ለላቀ ፍልስፍናው ሰረጋላ ማድረጉ  ከሁሉም የላቀ ሚናው ይመስለኛል፡፡ ከዚህ አንፃር ጠያቂው ኤሊያስ፣ ሞጋቹ ኤሊያስ፣ ብቻውን ሀገር ለመስራት የቃተተው ኤሊያስ --- ላይመለስ መሄዱ፣ ኪነ-ጥበቡን ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያን እንደ ሀገር  አጉድሏታል ብሎ በድፍረት መናገር ይቻላል፡፡
(ይህ ፅሁፍ፤ በኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ፣ የብላቴን ጌታ ህሩይ የኪነ-ጥበብ ማዕከል የቀረበ ነው)
***
ከአዘጋጁ፡- ጸሀፊውን በኢ-ሜል አድራሻቸው፡- mar.getachew @gmail.com ማግኘት ይችላሉ፡፡Read 2452 times