Print this page
Saturday, 07 December 2019 13:00

በሀሳብ መንገድ ላይ

Written by  ተመስገን
Rate this item
(2 votes)


                   “የሌሎችን ነፃነት አለማክበር የራስን ነፃነት ማጣት ነው”
                  
            እጠብቅሻለሁ
ተስፋ አልቆርጥም ከቶ
እኔ ራሴ እስከ ማልፍ
እንኳን ጊዜው ቀርቶ…
‹‹ትችላለች!!››
‹‹Yes, the can!!››
የገጠር ከተማ ነው፡፡ ልጅቱ ሃብታም የገበሬ ነጋዴ አባቷ እንደ ሞቱ፣ በጎረቤት ግፊት የከተማው ‹ባለውቃቤ›ን ልጅ አገባች፡፡ ሴት ልጅ ወለዱ፡፡ ቀስ እያለ የባሏ ባህሪ ተቀየረ፡፡ ሌላ የሚወዳት ሴት ነበረው። ሚስቱ ሰማች፣ ቀናች:: ውስጧ ተቃጠለ፡፡ ሲገባና ሲወጣ ጭቅጭቅ ሆነ፡፡ በዱላና በቅናት በለዘች፡፡ እርር፣ ኩምትር እንዳለች በጥቂት ቀናት ህመም ተገላገለች፡፡ … አረፈች፡። ከወራት በኋላ ሰውየው ሩቅ ቦታ ለሚኖሩ ዘመዶቹ ልጁን ጉዲፈቻ ሰጠ። ሌላዋን ሴት አግብቶ ሁለት ልጆች ወለደ፡፡ አሳደገ፡፡
ጉዲፈቻ የሰጣት የመጀመሪያ ልጁ፣ የአባትና የእናቷን ታሪክ በወሬ ወሬ ሰማች። እሱም እንደሰማች ሰማ። ወደሚኖርበት ከተማ ለመምጣት እየተዘጋጀ መሆኑን ሲያውቅ ታመመ፡፡ እየተሸከሙ ሃኪም ቤት ቢያመላልሱትም አልዳነም፡፡
ልጁ ከሰልስት በኋላ ደረሰች፡፡ ማንም የሚያውቃት አልነበረም። በተወለደችበት አካባቢ ባዳ ሆነች። ለእህትና ለወንድሟ ታሪኳን ነገረቻቸው፡፡ ‹‹አባታችን የነገረን ነገር የለም፣ አናውቅሽም›› አሏት፡፡ ወደ ሕግ ቦታ ሄደች፣ ፍትህ ፍለጋ፡፡ ለነሱ ተፈረደ፡፡ ወደ ለበላይ ይግባኝ አለች፡፡ አልተሳካም። ተስፋ አልቆረጠችም፡፡ ለጠቅላይ ፍ/ቤት አመለከተች:: እየተመላለሰች ስትከራከር የቴክኖሎጂ ዘመን ደረሰ፡፡ ፍ/ቤቱ የሷ ቤተሰቦች የዘረ መል ምርመራ እንዲደረግ አዘዘ፡፡ መቃብር ተቆፍሮ ከእናቷ ቅሪት በተወሰደ ናሙና ልጇ መሆኗ ተረጋገጠ፡፡ የአባቷ ግን አስደነገጣት። በአስከሬን ሳጥኑ ውስጥ የተገኘው የአባቷ ቅሪት ሳይሆን በሰው ቁመት የተጋደመ ግንድ ነበር፡፡ እንዴት ሊሆን ቻለ?
***
ወዳጄ፡- የፊታችን ማክሰኞ ዲሴምበር 10 ቀን 2019 ታላቅ ቀን ነው፡፡ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌ የታወጀበት፡፡ እ.ኤ.አ በ1938 በአንድ መቶ ሰባ አምስት አገራት ፀድቆ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስፈጻሚነት የሚተገበር ዋነኛ የሰው ልጆች ጉዳይ ሆኗል፡፡
አገራችን ኢትዮጵያም የድርጅቱን መርሆዎች ተቀብላ የውዴታ ግዴታዋን ለመፈጸም ተዋውላለች፡፡ በአዲስ አበባ ያለው ጽ/ቤትም አጋሮቹ ከሆኑት ከኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፣ ከኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ጉባዔ፣ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና የመሳሰሉት ጋር በመሆን ልዩ ልዩ ዝግጅቶችን አሰናድቷል፡፡ ቦሌ ፕላዛ አንደኛ ፎቅ ላይ በሚገኘው የድርጅቱ ጽ/ቤት የፎቶ ግራፍ ኤግዚቢሽን፣ በECA አዳራሽ ደግሞ የፓናል ውይይቶች፣ የአጭር ጽሑፍ  (Essay) ውድድርና መሰል ዝግጅቶችን አሰናድቷል፡፡
በዋናነትም የሴቶችንና የሕጻናትን ጥቃት ሲከላከሉና ሲታገሉ የነበሩትንና ያሉትን እንደ ዶ/ር ቦጋለች ገብሬ ዓይነቶች አርአያዎችን ይዘክራል፡፡ የዘንድሮው የሰብዓዊ መብት ቀን  ‹‹ትችላለች!!›› በሚለው መሪ ቃል እንዲከበር አጽንኦት ተሰጥቶታል፡፡… ትችላለች!!
ወዳጄ፡- ያለንበት ዘመን የሰው ልጅ አዕምሮ በከፍተኛ ደረጃ እያደገ የመጣበት ነው፡፡ ማንም ማንንም ለመጉዳት ቀርቶ ዞር ብሎ የሚገላምጥበት ጊዜ የለውም፡፡ …ደንቆሮ ካልሆነ!!
‹‹Your free domends where the other man nose begins›› እንደሚሉት፤ የሌሎችን ነፃነት አለማክበር የራስን ነፃነት ማጣት እንደሆነ ብዙዎች ተረድተዋል፡፡ ለሰለጠነ ሰው ጊዜው ራስን ለማብቃት፣ ብቁና ንቁ ለመሆንና እውነተኛውን የሕይወት መሰረት ለመረዳት እንኳ አይበቃውም፡፡
ካልተሳፈሩበት ቶሎ ተሽቀዳድሞ
ጊዜ ታክሲ አይደለም አይጠብቅም ቆሞ
የሰለጠነ ሰው ለጋራ ጥቅም ካልሆነ በቀር ‹በሱ› ጊዜ ሌሎች እንዲያተርፉበት አይፈቅድም። ለፍቅርና ለበጎ ተግባር ግን እንኳን ጊዜው ሕይወቱን ይሰጣል፡፡ ገጣሚው፡-
እጠብቅሻለሁ
ተስፋ አልቆርጥም ከቶ
እኔ ራሴ እስከ ማልፍ
እንኳን ጊዜው ቀርቶ… እንዳለው፡፡
ወዳጄ፡- ቴክኖሎጂ ሕይወትን ቀለል እንዳደረገልን ልብ ብለሃል? እንደ ቀድሞው ስልክ ቤት፣ ፎቶ ግራፍ አንሽ ቤት መሄድ ቀርቷል። ፖስታ ቤት መመላለስ፣ ኤሮግራም ለመግዛት ወረፋ መጠበቅ ተረት እየሆነ ነው:: አመጋገባችንና አለባበሳችንም ተለዋውጧል። አጭር መልበስ አያሳፍርም፣ በየመንገዱ መብላት ነውር አይደለም። ወልዶ መካድማ አይታሰብም፡፡… ጊዜው ተለውጧል፡፡
ቴያትር ቤት መሄድ፣ በየባንኩ ቤት መገተር፣ ሲኒማ ለማየት መሰለፍ፣ ለኳስ ሜዳ ትኬት መንከራተት፣ የውሃና መብራት ቢል ለመክፈል ፍዳ ማየት ቀንሷል፡፡ ላይብረሪዎች አይጨናነቁም፣ ትልልቅ መጽሐፍ መሸከም ‹Out dated› እንደ መሆን ይቆጠራል። ወዳጄ ጊዜው ተለውጧል!!  
መኖሪያ ቤትን በሶፋ፣ በቡፌ፣ በመደርደሪያና በኮሞዲኖ በማጨናነቅ የኑሮ መገለጫ ማድረግ ያለበትን ፋሺን ሆኗል፡፡ የኮተት ምንቸት ወጥቶ ‹Simplicity› ተተክቷል። የሰለጠነ ሰው የቦታና የአዕምሮ መስህብ ይፈጥራል። ቤቱን በአበባ፣ ግቢውን በዛፍ ያስውባል፡፡ እንስሳት ያለምዳል፣ አእዋፍ አትራክት ያደርጋል፡፡ የንጹህ አየርና የንፁህ ፍቅር ዋጋ ገብቶታል፡፡ ድንጋይ በድንጋይ ላይ ደርድሮ፣ በኤሌክትሪክ ሽቦ ታጥሮ፣ እራስን በራስ አስሮ መኖር አልተመቸውም። ፍርሃትና ነፃነት ከማጣት ስሜት መገላገል ይፈልጋል። ቤቱ በረንዳ ላይ ተቀምጦ ጸሐይ ስትወጣና ስትገባ ማየት ምቾት ነው… ጊዜው ተለውጧል!!  
ወዳጄ፡- መሰልጠን መንቃት ነው፡፡ ላለመኖር ጊዜ የለም፡፡ የወጣትነት ዕድሜ ሲባክን፣ ያለ ፋይዳ ሲበን ሁለት ጉዳት አለው፡፡ ሳይኖሩ ማርጀትና ሲያረጁ መፀፀት፡፡ ታላቁ በርናንድ ሾው እ.ኤ.አ ጁላይ 29 ቀን1946 በታተመ ኒውስ ዊክ መጋዘን ላይ ‹‹Youth is wasted on the young›› በማለት ጽፎ ነበር፡፡ በኛ አገር ወድደ ‹At› ያንሰዋል፡፡
ወዳጄ፡- ባለፈው ሰሞን በለንደን ጎዳናዎች የታየ ድራማ ነበር‹‹… አስቂኝ፡፡ ‹‹ኢኮኖሚክስ አላማውንና ሳይንሳዊ መሰረቱን ስቶ ትሪኮኖሚክስ ሆኗል›› ይላል፡፡ በኛ አገር ስሌት ‹‹High grade›› ይገባቸዋል አያሰኝም? ምክንያቱም ከሰባ አምስት በመቶ በላይ የሆነው ሕዝባችን በክፉ ድህነት እየማቀቀ=@ ሃያ ሰባት ዓመት ሲነገረን የነበረው አገር እያደገች መሆኗ=@ ስለ ሁለትና አንድ ዲጂት የዕድገት ቀመር ነበር፡፡ መሬት ላይ ከሚታየው እውነታ ጋር የሚቃረን፡፡
ወዳጄ፡- ዛሬ ግን ታላላቅ ኢንቨስትመንቶች ወዳገራችን እየገቡ ነው፡፡ የተሻለ ነገ ይታያል:: ‹‹የሚያጠግብ እንጀራ ከምጣድ ላይ ያስታውቃል›› እንደሚባለው፤ ለኛ ባይሆን ለልጆቻችን ተስፋ አለ፡፡ ወጣቶች አገራቸውን ለመቀየር ራሳቸውን መቀየር አለባቸው። ሁሌም እንደምንለው፤ አገር ለማሳደግ አዕምሮ ማደግ አለበት፡፡… ‹‹First things first›› እንዲሉ፤ ታላቁ ቤከን ወጣቶች ወደ ህልማቸው የሚደርሱት ከሁሉም በላይ ለሕግና ለሰላማዊ ሥርዓት ተገዢ ሲሆኑ ነው ይላል፡፡ ‹‹The growing citizen must be thought obedience to the law››› በማለት፡፡
ወዳጄ፡- ፖለቲክስም ፖሊትሪክስ እንዳይሆን ተጠንቀቅ!!
***
ወደ ትረካችን ስንመለስ፤ በልጅቷ አባት አስከሬን ሳጥን ውስጥ ግንድ የተገኘበትን ምክንያት ፖሊስ እንዲመረምር ታዘዘ፡፡ ፖሊስም ምርመራውን በሁለቱ ልጆችና በአማቶቻቸው ላይ አተኮረ፡፡ ጉዳዩ በጥልቅ ሲጣራ የልጅቱ አባት ‹‹በጠና ታምሞ ሞተ›› የተባለው ሲያስመስል እንጂ የእውነት አልነበረም፡፡ የልጅቱን ውርስ ለማስቀረት የተጫወተው ‹ድራማ› ነበር፡፡ ሰውየው በድብቅ ወደ አዲስ አበባ መጥቶ ቀደም ሲል በገዛው ቤት መኖር ጀምሯል፡፡ ቤተሰቦቹም በተለያየ ጊዜ እየመጡ ይጠይቁታል፡፡ ከተያዘ በኋላ የልጅቱ አባት ስለመሆኑ ከሱ በተወሰደው ናሙና ተረጋገጠ፡፡ ፍርድ ቤቱ ትክክለኛ ወራሽ ስለመሆኗ ሕግን መሰረት ያደረገ፣ የማይቀለበስ ፍርድ ሰጠ። አባትና ልጆች እንደ ጥፋታቸው ክብደት ተቀጡ፡፡ ልጃችን በሕግ ባለሙያ ሴቶች እገዛ ‹‹ቻለች››፡፡ አንቺም ትችያለሽ፡፡ እሷም ትችላለች፡፡ …. ጊዜው ተለውጧል!!
ሰላም!!


Read 1748 times