Saturday, 14 December 2019 11:57

ጥምቀት በዩኔስኮ 4ኛው የኢትዮጵያ የማይዳሰስ ቅርስ ሆኖ ተመዘገበ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

  ከ1ሺህ አምስት መቶ አመታት በላይ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ክርስቲያኖች ዘንድ በየአመቱ ጥር 11 የሚከበረው የጥምቀት በአል በሰው ልጆች ወካይ ቅርስነት መመዝገቡ ታውቋል፡፡
የአለም ቅርሶችን እያጠና በሚዳሰሱና በማይዳሰሱ ዘርፎች መዝግቦ እውቅና የሚሰጠው የተባበሩት መንግስታት የሣይንስ፣ የትምህርትና የባህል ተቋም (ዩኔስኮ) ረቡዕ ታህሳስ 1 ቀን 2012 ይፋ ባደረገው መረጃው፣ ጥምቀትን ጨምሮ አምስት የአለም ባህላዊ ቅርሶችን በማይዳሰሱ የአለም ቅርሶች ዘርፍ፣ ‹‹በሰው ልጆች ወካይ ቅርስነት›› መመዝገቡን አስታውቋል፡፡
የጥምቀት በዓል በዩኔስኮ ለማስመዝገብ በርካታ ጥረት ሲደረግ መቆየቱን ለአዲስ አድማስ ያብራሩት የኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃና ጥናት ባለስልጣን ም/ዳይሬክተር ረ/ፕሮፌሰር አበባው አያሌው በመጨረሻም ዩኔስኮ ረቡዕ እለት መመዝገቡን ይፋ አድርጓል ብለዋል፡፡
የጥምቀት በዓል ከኢሬቻ፣ ጫንበላላ እና የደመራ መስቀል በዓል ቀጥሎ ኢትዮጵያ ያስመዘገበችው አራተኛው የማይዳሰስ ቅርስ መሆኑ የሀገሪቱን የቱሪስት መስህብነት የበለጠ የሚያሳድግ ይሆናል ብለዋል ረዳት ፕሮፌሰሩ፡፡
“ጥምቀት በየአካባቢው ሲከበር በልዩ ልዩ መልኮች ነው” ያሉት ምሁሩ፤ በአለም እውቅና ማግኘቱ ቅርሱን የበለጠ የመጠበቅ ኃላፊነት ይጥልብናል ብለዋል፡፡
ለዩኔስኮ በአለም ዙሪያ 49 ያህል ተመሳሳይ ባህላዊ ሁነቶች በማይዳሰሱ ቅርስነት እንዲመዘገቡ ተጠይቆ የነበረ ቢሆንም ሚዛን ደፍተው የተመዘገቡት ጥምቀትን ጨምሮ አምስት ያህል ብቻ መሆናቸው ታውቋል፡፡

Read 2360 times