Saturday, 14 December 2019 12:01

ኢትዮጵያውያን የተሸለሙበትና የነገሱበት ሣምንት

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

   ሳምንቱ የኢትዮጵያውያን ነበር፡፡ ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድን ሳይጨምር ቢያንስ አምስት ታላላቅ ኢትዮጵያውያን ባበረከቱት አስተዋጽኦና በጎ ተግባር ተሸልመዋል፤ ተከብረዋል፡፡ አንጋፋው ፖለቲከኛና የሰብአዊ መብት ተሟጋች ፕ/ር መስፍን ወ/ማርያም፤ በህይወት ዘመናቸው ለሰብአዊነት ያደረጉት ተጋድሎ ሚዛን የሚደፋ ነው ሲል ዕውቅና የሰጠው ‹‹ዲፌንድ ዲፌንደርስ›› የተሰኘው የሰብአዊ መብት ተከራካሪዎች ቡድን ነው፡፡
ፕ/ር መስፍን ወ/ማርያም በኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት እንዲከበር፣ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅትን በማቋቋም ከፍተኛ ጥረት ማድረጋቸውና ለሰብአዊነት የወገነ ሰብዕናቸው ለሽልማቱ እንዳበቃቸው ቡድኑ አስታውቋል፡፡
‹‹ዲፌንድ ዲፌንደርስ››፤ የፓን አፍሪካ የሰብአዊ መብት ተከራካሪዎች ኔትዎርክ፣ የህግ ባለሙያ ሴቶች ማህበርና የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ በጋራ የመሰረቱትና ዋና መቀመጫውን ኡጋንዳ ያደረገ የመብት ተሟጋቾች ቡድን መሆኑ ታውቋል፡፡
ሌላዋ በሰብአዊ ተግባሯ በዚህ ሳምንት አለማቀፍ ሽልማት ያገኘችው ኢትዮጵያዊቷ ፍሬወይኒ መብራህቱ ነች፡፡ ፍሬወይኒ፤ በገጠር የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ወጣት ሴቶችን ስለ ወር አበባና የንጽህና አጠባበቅ ግንዛቤ በመስጠት፣ የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶችን በነፃ በማደል ላበረከተችው ሰብአዊነት የተሞላበት ተግባር፣ ሴኤንኤን ‹‹የ2019 የአመቱ ጀግና›› ሲል ሸልሟታል፡፡ ለገጠር ታዳጊ ሴቶች እየታጠበ ጥቅም ላይ የሚውል ሞዴስ የሚያመርት ማሽን ሰርታ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑም ታውቋል፡፡
ለፈፀሙት ታላቅ የሰብአዊነት ተግባር ሽልማት ያገኙት ሌላው ኢትዮጵያዊ ደግሞ ታዋቂው የህግ አማካሪና ጠበቃ እንዲሁም የሰብአዊ መብት ተከራካሪ አቶ አመሃ መኮንን ናቸው፡፡
በተለይ ባለፉት አስር አመታት በፀረ ሽብርተኝነት ህጉ ለሚከሰሱ ወገኖች በነፃ ጭምር ጥብቅና በመቆም የሚታወቁት አቶ አመሃ መኮንን፤ የፀረ ሽብር ህጉ ሰብአዊነትን የሚደፈጥጥ እንደሆነ በመግለጽ የሰላ ትችት ሲያቀርቡ ከነበሩ ግንባር ቀደም ኢትዮጵያውያን መካከል ተጠቃሽ ናቸው፡፡
በፕ/ር መስፍንና በጥቂት ወዳጆቻቸው ከ27 አመት በፊት የተቋቋመው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ አባል እንዲሁም ዋና ሰብሳቢ በመሆን ያገለገሉት አቶ አመሃ፤ የ2019 የፈረንሳይ ጀርመን የሰብአዊ መብቶች ጥበቃ ሽልማትን አግኝተዋል፡፡
በተቀበሉት ሽልማት ዙሪያ ለአዲስ አድማስ አስተያየታቸውን የገለፁት አቶ አመሃ፤ ባለፉት 27 አመታት በአገሪቱ ውስጥ ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰት እንደነበር ጠቅሰው፤ ‹‹ይህ ድርጊት እንዲቀንስና እንዳይፈፀም በርካቶች ታግለዋል፤ እኔና እኔን የመሰሉ ሰዎችም በዚህ በኩል የሚቻለንን አድርገናል›› ብለዋል፡፡
‹‹መጀመሪያም ጉልበቴን ሳልቆጥብ ነበር የሰራሁት፤ ከዚህ በኋላም ለሰብአዊነት መረጋገጥ የምቆጥበው ጉልበት አይኖርም። አዳዲስ ፈተናዎችም እየመጡ ስለሆነ በነዚህም ላይ ከጓዶቼ ጋር ለመስራትና የጀመርነው የተስፋ መንገድ ተመልሶ እንዳይጨልም እታገላለሁ፤ አስተዋጽኦዬን እቀጥላለሁ›› ብለዋል አቶ አመሃ፡፡
የፖለቲካ አመራሮች በሚያደርጓቸው ንግግሮችና ቅስቀሳዎች በሰብአዊነት ላይ ጉዳት እንዳይደርስ መጠንቀቅ አለባቸው ያሉት አቶ አመሃ፤ ጉዳት ሲያጋጥምም ወገን ሳይለዩ በሰውነት ብቻ ማውገዝና ችግሩን መረዳት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
‹‹የ2019 በተፈጥሮ ሃብት ጉዳይ ተጽእኖ ፈጣሪ›› በሚል ከአለማቀፉ የደረጃዎችና ምዘና ኤጀንሲ በዚህ ሳምንት የተሸለሙ ሌላው ኢትዮጵያዊ ምሁር ደግሞ ዶ/ር መሃመድ አባኦሊ  ናቸው። በሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮ ሃብትና የስነ ደን ሃብት መምህርና ተመራማሪ የሆኑት ዶ/ር መሐመድ አባኦሊ፤ የምርምር ጽሑፋቸው ከ90 የአለም ሀገራት ከቀረቡ 5ሺ 278 እጩዎች መሃል በአንደኝነት ተመርጦ ነው ለሽልማት የበቁት፡፡   

Read 11542 times