Saturday, 14 December 2019 12:03

አስቸኳይ የብሔራዊ መግባባትና ዕርቀ ሠላም ጉባኤ እንዲጠራ ተጠየቀ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(4 votes)

  ህብር ኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ፤ አስቸኳይ የብሔራዊ መግባባትና እርቀ ሠላም ጉባኤ እንዲጠራ የጠየቀ ሲሆን፤ ጉባኤው ሀገሪቱን ወደፊት ለማሸጋገር ወሳኝ ሁነት እንደሚሆን አስታውቋል፡፡
ፓርቲው በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ሰሞኑን በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳመለከተው፤ ሀገሪቱ ከገባችበት ዘርፈ ብዙ ውስብስብ፣ ተደራራቢና ተመጋጋቢ ችግሮች፣ በዘላቂነት ልትወጣ የምትችለው በኢህአዴግና አጋሮቹ መዋሃድ ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ የብሔራዊ መግባባትና እርቀ ሠላም ጉባኤ ሲካሄድ ብቻ ነው ብሏል፡፡
የብሔራዊ መግባባትና እርቀ ሠላም ጉባኤው፤ በእውቀትና እውነት የቆመ አሻጋሪ ሃሣብ የሚፈልቅበት ሀገራዊ ሁነት በመሆኑ ለሀገሪቱ ፖለቲካ ወደፊት መሻገር ወሳኝ የለውጥ ምዕራፍ ነው ብሏል - ፓርቲው በመግለጫው፡፡
የሀገር መከላከያ ሠራዊትና የፀጥታ አካላት ከፖለቲካ ወገንተኝነት ነፃ ሆነው ተጠናክረው እንዲወጡ እንዲሁም የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሲቪክ ተቋማትና ማህበራት፣ ህዝባዊ አደረጃጀቶች፣ የሃገር ሽማግሌዎች፣ የፖለቲካ ልሂቃን፣ አክቲቪስቶች፣ አርቲስቶች፣ የሚዲያ ባለቤቶችና አጠቃላይ ባለድርሻዎች በሙሉ ከስሜታዊነትና ወገንተኝነት ተላቀው ስለ ሀገር ሠላም፣ አንድነትና ማህበራዊ ቁርኝት እንዲሰብኩ ጥሪ አቅርቧል - ህብር ኢትዮጵያ::
መንግስት አስቸኳይ ሁሉን አቀፍ የብሔራዊ መግባባትና እርቀ ሠላም ጥሪ እንዲያቀርብም ገለልተኛ ተቋማትና ፖለቲከኞች ግፊት እንዲያደርጉም ፓርቲው ጠይቋል፡፡   


Read 11010 times