Saturday, 14 December 2019 12:06

ሰከን ያለ፣ ከልብ፣ ከአዕምሮና ከነፍስ የሚሰርፅ የኖቤል ሥነ ሥርዓት

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(3 votes)


            ጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ፣ ባለፈው ዓመት ባከናወኑት ስራ፣ እውን ባደረጉት ስኬት የተመሰገኑበትና የተከበሩበት የሽልማት ስነ ሥርዓት ነው፡፡ ግን ከዚያም ይልቃል፡፡ የወደፊቱ ከባድ ሥራ በጥሞና የሚታሰብበት ሥነ ሥርዓትም ነው - እጅግ ሰክን ያለ መንፈሳዊ ስነ ሥርዓት፡፡ ሰላምን፣ ከኑሮና ከነፍስ ብልጽግና ጋር በኢትዮጵያ የማስፈን የበርካታ ዓመታት ፈታኝ ጥረት፣ ከባድ ሃላፊነት እንደሆነ የሚያሳስብ የቃል ኪዳን ጥሞና ነው፡፡
ኢትዮጵያ ከከፍታ እጅጉን ብትወርድም፣ ትልቅ አገርነቷ የተተረከበት በመሆኑም፣ እጅግ በላቀ ሞገስ እንድናከብረው አድርጎናል፡፡ ከሁለት ሺ ዓመት በፊት፣ ከዚያም ወዲህ ለበርካታ ምዕተ ዓመታት፣ በዓለም ዙሪያ ሲፃፍና ሲነገር እንደነበረው ሁሉ፣ ኢትዮጵያ የተስፋ አገር መሆኗ ዛሬም ዳግም ተሰመስክሮበታል - የሽልማት ስነ ሥርዓቱ፡፡
አገራችን እንደገና ወደ ስልጣኔ ማማ የማቅናት ተስፋዋ በእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ጥረት ህያው ሊሆን እንደሚችል ያሳያልና፡፡ አንዱ የስልጣኔ መንገድ፣ ለሰዎች የላቀ ብቃትና የስራ ስኬት ተገቢውን ክብር የመስጠት ቀና መንገድ ነው፡፡
እንቁ ድምጻዊትና የሙዚቃ ጥበበኛ ቤቲ ጂ እና ድንቅ ስራዎቿ፣ የሚገባቸውን ያህል ክብር ያገኙበት ጥሩ አጋጣሚ ሆኗል - የኖቤል ስነ ሥርዓት፡፡ በአፍሪካ መድረክ ምርጥ አልበም ተብሎ ለሽልማት የበቃው የቤቲ ስራ፣ በዓለም መድረክም ተከበረ፡፡

Read 11234 times