Saturday, 14 December 2019 12:15

ሎዛ አበራ የሉሲዎቹ ግብ አዳኝ በማልታ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

ኢትዮጵያዊቷ ሎዛ አበራ በማልታ አንደኛ ዲቪዚዮን የሴቶች ሊግ ላይ በከፍተኛ አግቢነት እየተደነቀች ነው፡፡ የ22 ዓመቷ  ሎዛ  ወደ የማልታው ክለብ ቢርኪርካራ ቋሚ ዝውውር ካደረገች 4 ወራት ሊሞላት ሲሆን፤ በ7 ጨዋታዎች 17 ግቦችን አስቆጥራለች፡፡
በከንባታዋ ከተማ ዱራሜ ውስጥ የተወለደችው ሎዛ አበራ፤ በኢትዮጵያ እግር ኳስ በ10 ዓመታት ውስጥ በክለብ እና በብሄራዊ ቡድን የደረሰችበት ደረጃና እያስመዘገበች የምትገኘው ውጤት ተምሳሌት ያደርጋታል፡፡ በኢትዮጵያ እግር ኳስ በክለብ ደረጃ ለሐዋሳ፤ ለደደቢት እና ለአዳማ ሴት እግር ኳስ ክለቦች በመጫወት ባሳለፈችባቸው 7 የውድድር ዘመናት ተሳክቶላታል፡፡ በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚዬር ሊግ ለ4 ጊዜያት በሊጉ ሻምፒዮንነት የዋንጫ ክብሮችን ስትጎናፀፍ 3 ጊዜ ከደደቢት እና 1 ጊዜ ከአዳማ ሴት እግር ኳስ ክለቦች ጋር ሲሆን፤ በሊጉ በ4 ተከታታይ የውድድር ዘመናት  ኮከብ ግብ አግቢ ነበረች፡፡  በኢቢሲ የስፖርት ሽልማት በሴቶች እግር ኳስ ኮከብ ሆና የተሸለመችው ሎዛ ፤ በኢትዮጵያ ሴቶች እግር ኳስ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላት ልምድም በአርዓያነት የሚጠቀስ ነው:: በቱርክ ክለብ ክለብ የነበራት የ1 ወር ቆይታ፤  በስዊድን ክለቦች ያሳለፈችው የ4 ወራት የሙከራ ጊዜ እንዲሁም አሁን በምትገኝበት የማልታ ክለብ  በግብ አዳኝነት በማግኘት ላይ ያለችው ስኬት ይህን የሚያመለክት ነው፡፡ በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ሉሲዎች ታሪክ 23 ግቦችን በማስመዝገብ ከፍተኛው አግቢ መሆኗም ይታወቃል፡፡

በማልታው ቢርኪርካራ የጎል ማሽን በ7 ጨዋታዎች 17 ጎሎች
 ሎዛ አበራ ከ4 ወራት በፊት በአውሮፓዋ የደሴት አገር ማልታ በሚገኘውና በአገሪቱ  አንደኛ ዲቪዚዮን የሴቶች ሊግ ለሚወዳደረው ቢርኪርካራ ክለብ ለመጫወት የስምምነት ፊርማዋን ስታደርግ የክለቡ አመራሮች በጣም መደሰታቸውን ያወሳው ኦፊሴላዊ ድረገፃቸው ነበር፡፡ ሎዛ ለክለቡ ፊርማዋን ከማኖሯ በፊት ለበርካታ ሳምንታት ከክለቡ ጋር ልምምድ በመስራት እና ብቃቷን በማሳየት አሰልጣኞቹን አሳምና ነበር፡፡ ቢርኪርካራ ክለብ ከተመሰረተ ከ69 ዓመታት በላይ የሆነውና በደሴቲቷ አገር ማልታ ትልቁ በሆነው ቢርኪርካራ ከተማ የሚገኝ ነው:: የማልታ ደሴት በአውሮፓ አህጉር እንደመታቀፏ የሎዛ አበራ ዝውውር ለመጀመርያ ጊዜ ወደ አውሮፓ እግር ኳስ ያቀናችበት ሆኖ እንዲጠቀስ ምክንያት ይሆናል፡፡
ሎዛ  ወደ ማልታው ክለብ  ያደረገችውን ዝውውር አስመልክቶ ከወራት በፊት ለክለቡ ኦፊሴላዊ ድረገፅ አስ አስተያየቷን ስትሰጥ….
‹‹ዝውውሩ አስደስቶኛል፡፡ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ሊጉን በተከታታይ ያሸነፈ ክለብ በመሆኑ ለተጨዋችነት ዘመኔ ትልቁ ምዕራፍ መሆኑን አውቃለሁ፡፡ የአጥቂ መስመር ተጨዋች በመሆኔ ዋናው ኢላማዬ ግቦችን ማስቆጠር፡፡ በተለይ ለክለቡ ወሳኝ ውጤት የሚሆኑ ግቦችን፡፡ በያዝነው የውድድር ዘመን ክለባችን የሊጉን ሻምፒዮናነት አሳክቶ በአውሮፓ  ሴቶች ሻምፒዮንስ ሊግ መሳተፉን እንዲያረጋግጥ እፈልጋለሁ፡፡›› በማለት ተናግራ ነበር::
ሎዛ  ከ4 ወራት በፊት የማልታውን ክለብ ቢርኪርካራ  መቀላቀሏን በፊርማዋ ስታረጋግጥ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ዝውውሩ በህጋዊ መንገድ መፈፀሙን በዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ፌደሬሽኖች ማህበር ፊፋ እንደሚያውቀው የሚገልፅ መረጃ አውጥቶ እንደነበር ይታወሳል፡፡ በወቅቱ የሎዛ ዝውውር በኢትዮጵያ ሴቶች እግር ኳስ ከአገር ወጥቶ በተለያዩ ዓለም ክፍሎች ለመጫወት ያሉት እድሎችን ያነቃቃ ነበር፡፡
ሎዛ ቢርኪርካራ ክለብን ከተቀላቀለች በኋላ በማልታ አንደኛ ዲቪዚዮን የሴቶች ሊግ 7 ጨዋታዎችን አድርጋለች፡፡ የመጀመርያ ጨዋታዋ ኪርኮፕ ዩናይትድ ከተባለ ክለብ ጋር ተጫውተው 7ለ1 ያሸነፉበት ሲሆን በዚህ ጨዋታ ሁለት ጎሎች አስመዝግባ ነበር፡፡ ከዚያም ቢርኪርካራ  ከስዌይኪ ዩናይትድ ጋር ሲገናኙና 4ለ1 ሲያሸንፉ 1 ጎል፤ ከሞስታ ጋር ተገናኝተው 5ለ1 ባሸነፉበት ጨዋታ ሁለት ጎሎች እንዲሁም ራይደርስን 8ለ1 ሲረቱ ሁለት ጎሎችን ሎዛ ከመረብ አዋህዳለች፡፡ ባለፈው ሰሞን ደግሞ ቢርኪርካራ ከሂበርኒያንስ ጋር ተገናኝቶ 17ለ0 በሆነ ሰፊ ውጤት ሲያሸንፍ ሎዛ በአስዳናቂ ሁኔታ 7 ጎሎች ከማግባቷም በላይ 2 ለግብ የሚሆኑ ኳሶችን አቀብላለች፡፡ በአንደ ጨዋታ ሰባት ግቦችን ማስመዝገብ ከቻለች በኋላ ደግሞ ከፍተኛ አድናቆት ለማትረፍ ችላለች።
ይህን አስመልክቶ በትዊተር ገጿ ላይ ባሰፈረችው መልእክት ‘’ዛሬ በነበረን ጨዋታ በማልታ ሊግ ላይ በአንድ ጨዋታ ብቻ ሰባት ጎል በማስቆጠር ሌላ ታሪክ መፃፍ እና መስራት ስለቻልኩ በጣም ደስ ብሎኛል፤ ከዚህ በፊት ኢትዮጵያ ላይ በአንድ ጨዋታ ብቻ ዘጠኝ ጎል አግብቼ ነበር’’ ብላ ነበር፡፡
በማልታ አንደኛ ዲቪዚዮን የሴቶች ሊግ ሎዛ አበራ የምትገኝበት ቢርኪርካራ  በአሁኑ ወቅት 19 ነጥብ  እና 28 የግብ ክፍያ  መሪነቱን ተቆጣጥሮታል::  በዚህ ጥንካሬው በመቀጠል የውድድር ዘመኑን ከጨረሰ ደግሞ በማልታ ሻምፒየንነቱ በአውሮፓ የሴቶች ሻምፒዮንስ ሊግ እንዲሳተፍ የሚያስችለው ሲሆን፤ ይህ ደግሞ ሎዛ አበራ በትልልቅ የአውሮፓ ክለቦች በፕሮፌሽናል ተጨዋችነት የምታድግበትን እድል ይፈጥርላታል፡፡ በአውሮፓ እግር ኳስ የመጀመርያ ልምዷን በትንሿ ማልታ ማግኘት የጀመረችውን ሎዛ በአፍሪካ የሴቶች እግር ኳስ እየገነኑ ከሚወጡ ምርጦች ተርታ የመደባት ዘታይምስ ኦፍ ማልታ ጋዜጣ፤ ለቢሪኪርካራ ክለብ 7 ግቦችን በማስቆጠር እና ሁለት ለግብ የበቁ ኳሶችን በማቀበል የነበራትን ጥሩ አጀማምሯን  በማውሳት ሰሞኑን ያቀረበው ዘገባ ነበር፡፡ የማልቲስን እግር ኳስ በአጭር ጊዜ እንዴት እንደተላመደችው ዘታይምስ ኦፍ ማልታ ሲጠይቃትም በማልታ እግር ኳስ መጫወት ቀላል አለመሆኑን የጠቀሰችው ሎዛ አበራ እግር ዓለምን የሚያግባባ ቋንቋ መሆኑ በቶሎ ለመላመድ እንደረዳት መልሳለታለች፡፡
‹‹ሁልግዜም አሰልጣኜን በደንብ መስማቴን እርግጠኛ ሆናለሁ፡፡ ምክንያቱም ለዚያ በሰጠሁት ትኩረት ሜዳ የምጋራቸውን ሌሎች የቡድን አጋሮቼን በደንብ ለመግባባት እችላለሁ፡፡ ተቀናቃኞችን ማክበር ተገቢ ቢሆንም እኔም ቡድኔም ያለምንም ፍርሃት መጨዋታችን አስፈላጊ ነው፡፡›› በማለትም ለታይምስ ኦፍ ማልታ ተጨማሪ አስተያየቷን ሰጥታለች፡፡

በኢትዮጵያ 3 ክለቦች፤ ከዚያም ለሙከራ  በስዊድንና  በቱርክ
4 ጊዜ የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚዬር ለግ ሻምፒዮንና 4 ጊዜ  ኮከብ ግብ አግቢ
ሎዛ ወደ እግር ኳስ ሙያዋ የገባችበትን የመጀመርያ ምዕራፍ የከፈተችው በትውልድ ከተማዋ ቡድን ውስጥ በመሰለፍ ነበር፡፡ ልዩ ችሎታዋ እና በእግር ኳስ ስፖርት ለማደግ የነበራት ውስጣዊ ፍላጎት የመልማዮችን ትኩረት ስላሰበ ገና በታዳጊ እድሜዋ ለሐዋሳ ሴቶች እግር ኳስ ክለብ የምትጫወትበትን እድል ፈጥሮላታል፡፡  ከሐዋሳ ጋር ክለብ ጋር ሁለት የውድድር ዘመናትን ስትቆይ በሴቶች ሊጉ ለሁለት ተከታታይ ዓመታት ሶስተኛ ደረጃን በያዙበት ታሪክ የክለቡ ከፍተኛ አግቢ በመሆን ስኬታማ ነበረች፡፡ ከሐዋሳ ሴቶች እግር ኳስ ክለብ በኋላ ያስፈረማት ደደቢት ሲሆን በዚሁ ክለብ አራት የውድድር ዘመናትን ስታሳልፍ ከፍተኛውን ስኬት በኢትዮጵያ የክለብ እግር ኳስ ለማስመዝገብ አስችሏታል፡፡ ሎዛ በደደቢት ክለብ ባሳለፈቻቸው 4 የውድድር ዘመናት የሴቶች ሊጉን በከፍተኛ አግቢነት ያደመቀችው ሲሆን ለ4 ተከታታይ ዓመታት ኮከብ ጎል አስቆጣሪ በመሆን ተሸላሚ ነበረች። በሶስት የውድድር ዘመናት ደግሞ ከደደቢት ጋር የሴቶች ፕሪሚዬር ሊግ ሻምፒዮን ሆናለች፡፡ ከፍተኛ ስኬት ያስመዘገበችበት የደደቢት እግር ኳስ ክለብ ከመፍረሱ በፊት  ለሎዛ አበራ ወደ ስዊድን ለፕሮፌሽናል የተጨዋችነት ሙከራ የምትጓዝበት አጋጣሚ ተፈጠረ፡፡ ከሌላዋ የኢትዮጵያ ሴቶች ብሄራዊ ቡድን አባል ቱቱ በላይ ጋር በመሆን በስዊድን እግር ኳስ የሙከራ ጊዜ ነበራቸው፡፡ ሎዛ እና ቱቱ በላይ በስዊድን ያሳለፉትን  ጊዜ ያመቻቸላቸው ላርስ የተባለ ስዊድናዊ ሲሆን፤ ሁለቱ ኢትዮጵያውያን በስዊድኖቹ ክለቦች ሮዘንጋርድ እና ፒቲያ አይ ኤፍ ተመዝግበው በስልጠና እና በሙከራ ጊዜያቸው ለአራት ወራት ሰርተዋል፡፡ የሙከራ ጊዜያቸውን ጨርሰው የስዊድን እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፈቃድ ያገኙ ቢሆንም የሚያስፈርማቸው ክለብ ግን አልተገኘም፡፡
ይህ አስመልክቶ ከሳምንታት በፊት ለቢቢሲ አማርኛ ድረገፅ ሎዛ አስተያየቷን ስትሰጥ «በስዊድን ፊርማ ያኖርንለት ክለብ ግን አልነበረም። ልክ የስዊድን የሴቶች ‘ቶርናመንት’ ሲጠናቀቅ ተመለስን:: ከዚያስ…. ስዊድን የሴቶች ውድድር በሚጀምርበት ወር እኛ ግን ተመልሰን መሄደ አልቻልንም። ምክንያቱ ደግሞ ፋይናንስ ነው። ከአውሮፓ የምትመጣ ሴት ሲያስፈርሙ ተጨማሪ ወጪ የለባቸውም። ከሌላ አህጉር ለምትመጣ ተጫዋች ግን ቀረጥ [የስራ ፈቃድ ወጭ] መክፈል ግድ ነው። ክለቡ ይህንን ማድረግ አልቻለም። እንጂ የችሎታ ወይም የአቅም ማነስ ጉዳይ አልነበረም።» ብላለች፡፡
በነገራችን ላይ ሎዛ ከስዊድኖቹ ክለቦች የሙከራ ጊዜዎችዋ በፊት ለአንድ ወር ሙከራ ልምምድ ወደ ቱርኩ አንታልያስፖር ማቅናቷን ያወሳው የቢቢሲ ዘገባ የቱርኩ ክለብ ያቀረበላት ክፍያ ከኢትዮጵያም ያነሰ መሆኑ ዝውውሩን እንዳይሳካ አድርጎታል ብሏል:: በስዊድን ክለብ የሙከራ ጊዜያዋን በተሳካ መንገድ አሳልፋና በዚያው አገር ለመጫወት የሚያስችላትን  ፍቃድ አግኝታ ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሰች በኋላ ሎዛ አበራን የ2011 ዓ.ም የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚዬር ሊግ ከተጀመረ በኋላ አዳማ ከተማ አስፈርሟታል፡፡ የውድድር ዘመኑንም ከአዳማ ከተማ የሴቶች እግር ኳስ ክለብ ጋር በመሆን የሊጉን ሻምፒዮናነት ክብር ከመጎናፀፏም በላይ የፕሪሚዬር ሊጉም ኮከብ ግብ አግቢ ሆና ነበር የጨረሰችው፡፡

በ23 ጎሎች የሉሲዎቹ ከፍተኛ አግቢ
ሎዛ አበራ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ በሴቶች ብሄራዊ ቡድን ደረጃ አገልግሎት መስጠት የጀመረችው ከክለብም በፊት ነው፡፡ ለሉሲዎች ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ጋር በመጫወት ሲሆን ከዚሁ ቡድን ጋር ከ20 ዓመት በታች  ለዓለም ዋንጫ ለማለፍ ሶስቱን ማጣሪያዎች ሲያልፉ ሎዛ በከፍተኛ አግቢነት አስተዋፅኦዋ የላቀ ነበር፡፡  በኢትዮጵያ ሴቶች ብሄራዊ ቡድን ሉሲዎቹ በአፍሪካ ዋንጫ ዋና ውድድር እና ማጣርያዎች ፤ በኦሎምፒክ ማጣርያዎች እና በሴካፋ ሻምፒዮን በመጫወት ከፍተኛ ልምድ ያካበተችው ሎዛ ለብሄራዊ ቡድኑ 23 ጎሎችን አስመዝግባለች፡፡


Read 1599 times