Saturday, 14 December 2019 12:21

በኖቤል ሽልማት ዙሪያ በየዘመኑ የተነሱ ውዝግቦች

Written by  (ከአብዱራህማን አህመዲን፤ የቀድሞ የፓርላማ አባል)
Rate this item
(2 votes)

 በዚህ መጣጥፍ ትኩረት የማደርግበት ጭብጥ በኖቤል ሽልማት ከተነሱ ውዝግቦች ውስጥ በስነ-ጽሑፍ፣ በኢኮኖሚክስና በሰላም ተሸላሚዎች ዙሪያ የተነሱትን ለመጥቀስ እሞክራለሁ፡፡ ከዚሁ ጋር በዶ/ር ዐቢይ ሽልማት ላይ የተነሱ አሉታዊ አስተያየቶችን በአጭሩ ለማየት እሞክራለሁ፡፡
ዶ/ር ዐቢይ አህመድ የዘንድሮውን የሰላም የኖቤል ሽልማት ውድድር ያሸነፉት ከመላው ዓለም ከቀረቡ 300 ተወዳዳሪዎች መካከል ተመርጠው ነው፡፡ የሰላም ሽልማቱ የተሰጣቸው “በዓለም አቀፍ ትብብር በተለይም ከጎረቤት ሀገር ኤርትራ ጋር የነበረውን የድንበር ውዝግብ ለመፍታት ላደረጉት አስተዋጽዖ” እንደሆነም ይታወቃል፡፡ ዶ/ር ዐቢይ ለሰላም የኖቤል ተሸላሚነት በመብቃታቸው እኔን ጨምሮ በርካታ ኢትዮጵያውያን ሽልማቱን ራሳችን ያገኘነው ያህል እንደተደሰትን ሁሉ በአንጻሩ በዶ/ር ዐቢይ የሰላም የኖቤል ሽልማት የተበሳጩና “አይገባቸውም” ብለው የሚቃወሙ ወገኖችም አሉ፡፡ አንዳንዶቹ “ሽልማቱ አይገባቸውም” ከማለት አልፈው ተሸላሚነታቸው እንዲሰረዝ በኢንተርኔት ፊርማ እስከ ማሰባሰብ ዘልቀዋል:: እነዚህ ወገኖች “ለዶ/ር ዐቢይ ሽልማቱ አይገባቸውም” የሚሉበት ምክንያት እርሳቸው ስልጣን ከያዙበት ጊዜ ጀምሮ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ከኖሩበት ቀዬ ተፈናቅለዋል፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ሞተዋል፣ በርካታዎች ቆስለዋል፣ ብዙዎች አሁንም በእስር ቤት ይገኛሉ በሚል ምክንያት ነው፡፡
በየዘመኑ የኖቤል ሽልማት “ይገባዋል - አይገባውም” የሚል ውዝግብ መነሳቱ የተለመደ ነው፡፡ በሁሉም ዘርፎች በየጊዜው ከተነሱ ውዝግቦች ውስጥ በስነ-ጽሁፍ፣ በኢኮኖሚክስና በሰላም የኖቤል ሽልማት ዙሪያ የተነሱ ውዝግቦችን አለፍ አለፍ ብዬ ልጥቀስ፡፡ ከ1902 - 1906 ባሉት ዓመታት ሩሲያዊው ሊዎ ቶልስቶይ፣በየዓመቱ እጩ ሆኖ ቢቀርብም አሸናፊ መሆን አልቻለም፡፡ ቶልስቶይ ውድድሩን ያላሸነፈው በነበረው የሃይማኖትና የፖለቲካ አቋም ምክንያት ዳኞቹ ሊስማሙ ባለመቻላቸው መሆኑ ይነገራል፡፡ በዚህም የተነሳ 42 ስዊድናዊ ደራሲዎች በኖቤል ኮሚቴው ውሳኔ ላይ ያላቸውን ተቃውሞ በመግለጽ ለቶልስቶይ ደብዳቤ ጽፈዋል፡፡
እ.ኤ.አ በ2010 በስነ-ጽሁፍ ተሸላሚ የነበረው ማሪዮ ቫርጋስ ሎዛ ሊሰጠው አይገባም የሚል ጭቅጭቅ ተቀስቅሶ ነበር፡፡ ማሪዮ ውዝግብ የቀሰቀሰው “የፖለቲካ ዝንባሌው ቀኝ ዘመም ነው” በሚል ምክንያት ነበር፡፡ ውዝግቡ ከስነ-ጽሁፍ ይልቅ ፖለቲካዊ ገጽታ ተሰጥቶት ነበር፡፡ እ.ኤ.አ በ2009 የስነ-ጽሁፍ ሽልማት የተሰጠው ሔርታ ሙለር ለተባለ ሰው ነበር፡፡ በርካታ የአሜሪካ ሐያሲያንና የስነ-ጽሁፍ ምሁራን ለእጩነት ከመቅረቡ በፊት “ሙለር የሚባል ደራሲ አናውቅም” የሚል ትችት አቅርበው ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት የኖቤል ኮሚቴው “አውሮፓ ተኮር ነው” የሚል ቅሬታ ቀርቦበት ነበር፡፡
የዛሬ ሦስት ዓመት የስነ-ጽሁፍ የኖቤል ሽልማት የተሰጠው ቦብ ዲላን ለተባለ የሙዚቃ ግጥም ፀሐፊ ነበር፡፡ ሽልማቱ በዚህ ዘውግ ለመጀመሪያ ጊዜ የተሰጠ ሲሆን የልብ-ወለድ ደራሲዎችና ሐያሲን ሽልማቱ ተገቢ አይደለም የሚል ጫጫታና ተቃውሞ አሰምተው ነበር:: በኢኮኖሚክስ የኖቤል ሽልማት መስጠት የተጀመረው እ.ኤ.አ በ1969 ነበር፡፡ በዚህ ዘርፍ የሚቀርበው ዋነኛው ቅሬታ “ሽልማቱ ራሱ የአልፍሬድ ኖቤልን ፍላጎት የሚንያጸባርቅ ዘርፍ አይደለም” የሚል ነው፡፡ የአልፍሬድ ኖቤል ቤተሰቦች ጭምር ይህንን ቅሬታ ያሰማሉ፡፡ የአሜሪካው የቺካጎ ዩኒቨርስቲ በኢኮኖሚክስ ዘርፍ ዘጠኝ ጊዜ ተሸልሞ ስለነበር፣ ይህም ሁኔታ “አድሎአዊ አሰራር አለ” የሚል ቅሬታ ፈጥሯል፡፡
እ.ኤ.አ በ2008 ዓ.ም ፖል ክሩግማን የተባለ ኢኮኖሚስት “የንግድ ሂደትን በመተንተንና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ያለበትን ስፍራ በማመላከት” ላደረገው ጥናት ተሸላሚ እንዲሆን ሲመረጥ “ሽልማቱ የግራ የፖለቲካ ኃይሎች ግፊትና ጫና ያረፈበት ነው” የሚል ጭቅጭቅ ተቀስቅሶ ነበር፡፡ ታዋቂው ኢኮኖሚስት ሚልተን ፍሪድማን እ.ኤ.አ የ1976 የኢኮኖሚክስ የኖቤል ሽልማትን አሸነፈ ሲባልም ተመሳሳይ ቅሬታ ቀርቦ ነበር፡፡ ይህ የኢኮኖሚ ምሁር በፍጆታ፣ በሞኔታሪ ታሪክና ንድፈ ሃሳብ እንዲሁም የማረጋጊያ ፖሊሲን ውስብስብነት በተመለከተ ያቀረበው ጥናት ለሽልማት እንዳበቃው ሲነገር፣ ዓለም አቀፍ ተቃውሞን ቀስቅሶ ነበር፡፡ ቁጣው የተቀሰቀሰው በግራ ጽንፈኛ ኃይሎች እንደነበር ይነገራል፡፡
በሰላም የኖቤል ሽልማት ዙሪያም ተመሳሳይ ውዝግቦች ይነሱ ነበር፡፡ ብዙዎቹ ቅሬታዎች የተሸላሚዎቹን ሁኔታ በማየት “የፖለቲካ እጅ አለበት፣ ሊያሸልመው የሚችል በቂ ምክንያት የለም ወይም ለሰላም የተደረገ አስተዋጽዖ ለሚለው ጽንሰ ሃሳብ የተሳሳተ ትርጉም ተሰጥቶታል” የሚሉ ናቸው፡፡ በ2012 የአውሮፓ ህብረት የሰላም ኖቤል ተሸላሚ መሆኑ ሲነገር ከፍ ያለ ማጉረምረም ተሰምቷል፡፡ ቀደም ሲል የሰላም የኖቤል ተሸላሚ የነበሩ የሰላም ሎሬቶች “የአውሮፓ ህብረት የሰላም ሻምፒዮን አይደለም” የሚል ተቃውሞ አሰምተው ነበር፡፡
እ.ኤ.አ በ2010 የሰላም ኖቤል ሽልማት እንዲሰጥ የተወሰነው በወቅቱ እስር ቤት ለነበረው ሊዩ ዣቦ ለተባለ ቻይናዊ የሰብአዊ መብት ተሟጋችና የሰላም ታጋይ ነበር፡፡ የቻይና መንግስት ራሱ በዣቦ ላይ ተቃውሞ ከማቅረቡም በላይ በዚሁ ምክንያት በቻይናና በኖርዌይ መንግስታት መካከል ዲፕሎማሲያዊ ግጭት ተፈጥሮ ነበር፡፡ አንዳንድ ወገኖች ደግሞ “ዣቦ አሜሪካ በቬትናም፣ በኮሪያ፣ በአፍጋኒስታንና በኢራቅ ያደረገቺውን ጣልቃ ገብነት ይደግፍ ስለነበር የሰላም ሽልማቱ አይገባውም” የሚል ተቃውሞ አቅርበው ነበር፡፡
እ.ኤ.አ በ2009 የሰላም የኖቤል ተሸላሚ የነበሩት ባራክ ኦባማ ነበሩ፡፡ የእርሳቸውም የኖቤል የሰላም ተሸላሚነት ትችትና ወቀሳ የተለየው አልነበረም፡፡ ኦባማን ተሸላሚ ያደረጋቸው “ለዓለም አቀፍ ግንኙነትና ለህዝቦች ትብብር ላደረጉት ልዩ አስተዋጽዖ” የሚል ነበር፡፡ ይህ ሽልማት ለኦባማ እንዲሰጥ የተደረገው የፕሬዝዳንትነት ምርጫ ባሸነፉ በዘጠነኛው ወር መሆኑ “ምንም ሳይሰሩ የተሰጠ ሽልማት ነው” የሚል ትችት ቀስቅሷል፡፡ ኦባማ ራሳቸው የተሰጣቸው ሽልማት ያልጠበቁት መሆኑንና ራሳቸውም ለሽልማቱ ብቁ ነኝ ብለው እንደማያምኑ የተናገሩ ቢሆንም ሽልማቱን ግን ተቀብለዋል፡፡ የኦባማን ሽልማት አስገራሚ ያደረገው በተመረጡ በዘጠኝ ወራቸው ለሽልማት መብቃታቸው ብቻ ሳይሆን ስልጣን በተረከቡ በ12ኛው ቀን ለሽልማት መብቃታቸው ጭምር ነው፡፡
የኖቤል ሽልማት ኮሚቴው ሊቀ መንበር ቶርጆር ጃግላንድ ስለ ኦባማ መመረጥ ተገቢነት ተጠይቀው፤ “አዎ ተገቢ ነው ብዬ አምናለሁ:: እንዳምን ያደረገኝ ኦባማ ስልጣን በያዝኩ በሦስት ወራት ውስጥ ከሩሲያ ጋር በኑክሌር የጦር መሳሪያ ጉዳይ ዙሪያ እደራደራለሁ ማለታቸው ነው፡፡ ከአልፍሬድ ኖቤል ዓላማዎች ውስጥ አንዱ ደግሞ “ለጦር ሰራዊት ቅነሳ” ለሚሰራ ሰው ሽልማት እንዲሰጥ የሚል ነው” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
የህንዱ ማህተመ ጋንዲም በኖቤል ሽልማት ታሪክ ውስጥ በአወዛጋቢነት ተመዝግቧል:: ጋንዲ ከ1937 - 1948 ድረስ ባሉት ዓመታት አምስት ጊዜ የሰላም የኖቤል ሽልማት እጩ ሆኖ ቢቀርብም “አልፈልግም” በማለቱ ተሸላሚ ሊሆን አልቻለም፡፡
በ1948 ስድስተኛው የእጩነት ደብዳቤ ለጋንዲ ተልኮ ምላሹ እየተጠበቀ ባለበትና የምላሽ መቀበያው ጊዜ ሊጠናቀቅ ሁለት ቀናት ሲቀሩ ጋንዲ ተገደለ፡፡ ጋንዲ በተላከለት ደብዳቤ መሰረት ሽልማቱን መቀበል አለመቀበሉን ባለመግለጹ ምክንያት የኖቤል ኮሚቴው የጋንዲን እጩነት ውድቅ አደረገው፡፡ ከአሰርት ዓመታት በኋላ የኖቤል ኮሚቴው ጋንዲን ባለመሸለሙ የተሰማውን ጸጸት ገልጿል፡፡ በወቅቱ የኖቤል ሽልማት ዋና ጸሐፊ የነበሩት ጌይር ሉንደስታድ፤ “የኖቤል ሽልማት ለጋንዲ ትርጉም የለውም፡፡ በአንጻሩ ጋንዲን ያልሸለመ የሰላም የኖቤል ሽልማት ኮሚቴ ትርጉም አለው ወይ? ነው ጥያቄው” ብለዋል፡፡
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ጭምር ሽጉጥ ታጥቀው የሚሄዱት ያሲር አራፋት በአንድ ወቅት ባደረጉት ንግግር፤ “በአንድ ወገን ሰላምን የሚያመለክት የወይራ ዝንጣፊ፤ በሌላኛው ጎን የነፃነት ታጋይ በመሆኔ ሽጉጥ ታጥቄያለሁ” ብለው ነበር፡፡ ይህንን ንግግር ካደረጉ ከሃያ ዓመታት በኋላ፣ እ.ኤ.አ በ1994 አረፋትና የእስራኤል መሪዎች ሺሞን ፔሬስና ይስሃቅ ራቢን “በመካከለኛው ምስራቅ ሰላም እንዲፈጠር ላደረጉት አስተዋጽዖ” በማለት የሰላም የኖቤል ሽልማት እንዲሰጥ ተወሰነ፡፡ ይህ ሽልማት ለሦስቱ ሰዎች የተሰጣቸው እ.ኤ.አ በ1993 በኦስሎ በተፈራረሙት የሰላም ስምምነት ምክንያት ነበር፡፡ ስምምነቱ በእስራኤልና በፍልስጤም መካከል እርቅ ለመፍጠር ነበር፡፡ ይህ ሽልማት በይፋ ከተገለጸ በኋላ ከአምስቱ የኖቤል ሽልማት ኮሚቴ አባላት ውስጥ አንዱ “ያሲር አራፋት አሸባሪ ነው” በማለት ከኮሚቴ አባልነታቸው ለቀቁ፡፡ ይህንንም ተከትሎ “ለያሲር አረፋት ሊሰጠው አይገባም” የሚል ተቃውሞ በጋዜጦች በስፋት ይዘገብ ነበር፡፡
በሌሎችም የሽልማት ዘርፎች ተመሳሳይ ውዝግቦች ነበሩ፡፡ ለግንዛቤ ያህል ከላይ የተጠቀሱት ይበቃሉ ብዬ አስባለሁ፡፡ የሰላም የኖቤል ተሸላሚዎች ዝርዝር ሊሸለሙ የሚገባቸውን ብቻ ሳይሆን አንዳንድ ጊዜ ያልተጠበቁ ሰዎችንም ይዞ ብቅ የሚልበት አጋጣሚ አለ፡፡ በዚህም ምክንያት ውዝግብና ጭቅጭቅ የተለመደ ነው፡፡ አንዳንዶቹ ሽልማቱ ከተሰጣቸው በኋላ “ይመልሱ” የተባሉበት ሁኔታ ታይቷል፡፡ ለምሳሌ የበርማዋ አን ሳን ሱቺ፣ በሮሂንጃ ሙስሊሞች የጅምላ ጭፍጨፋ ሲካሄድ ዝም በማለቷ ብዙ ሰዎች ሽልማቷ እንዲሻር ጥሪ አቅርበዋል፡፡ በኢንተርኔት የተቃውሞ ፊርማ ተሰብስቦም ነበር፡፡ በእኛው ጠቅላይ ሚንስትር በዶ/ር ዐቢይ አህመድ የሰላም የኖቤል ተሸላሚነትም ላይ የተቃውሞ ድምፆች ተሰምተዋል፡፡
ዘ ጋርዲያን የተባለው ጋዜጣ “የዶ/ር ዐቢይ አህመድ የኖቤል የሰላም ተሸላሚነት ውሳኔ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አክብሮት፣ ላመጧቸው አስገራሚ ለውጦች እውቅና የሰጠ ነው፡፡ ግን የአገሪቷ የመሻሻል ሁኔታ አሁንም ቀድሞ በነበረበት ነው” ብሏል፤ በቅርቡ ባወጣው እትም፡፡ የጀርመን ድምጽ ሬዲዮ ጋዜጠኛ ሉድገር ሻዶምስኪ ደግሞ፤ “ለዶ/ር ዐቢይ አህመድ የተሰጠው የሰላም የኖቤል ሽልማት የተሳሳተ ውሳኔ ነው የሚል አስተያየት አለ” ይላል፡፡ “ሎሬቱ በርግጥም የለውጥ ሰው ነው፡፡ ይሁን እንጂ እውቅና ያገኘው በዋናነት ከሀገሩ ውጪ ባለ ጉዳይ ነው፡፡ የኖቤል ኮሚቴው የመረጠበት እሳቤ ትርጉም ያለው ቢሆንም የተሳሳተ ምርጫ ነው፡፡ ከባራክ ኦባማ ጋር ተመሳሳይ “symbolic meaning” ያለው ነው” ብሎ ነበር ጋዜጠኛው፡፡
ዶ/ር ዐቢይ ያደረጓቸውን ማሻሻያዎችና ሥር ነቀል ለውጦች የሚደግፏቸው ብቻ ሳይሆኑ በጽኑ የሚቃወሟቸው መኖራቸውም መታወቅ አለበት፡፡ እናም በኖቤል ሽልማት ሂደት “ይገባዋል - አይገባውም” ከሚለው ውዝግብ በተጨማሪ ሽልማቱ “ይመለስ” የሚል ተቃውሞም ቀርቦባቸው ነበር፡፡ ይሁን እንጂ የኖቤል ሽልማት የሚሰጠው ከሽልማቱ በፊት በነበሩት ጊዜያት ለተሰሩ ስራዎች በመሆኑ ከዚያ በኋላ በሚፈጠር ሁኔታ ሽልማት እንዲመለስ አይደረግም፤ ተመልሶም አያውቅም፡፡
ለማንኛውም በኖቤል ሽልማት ዙሪያ ተቃውሞ መቀስቀሱ የተለመደ ስለሆነ በዶ/ር ዐቢይ ላይ ብልጭ ድርግም እያለ የሚነሳውን ተቃውሞ፣ በሳቅ በፈገግታ ማለፉ መልካም ነው እላለሁ፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጸሃፊውን በኢ-ሜይል አድራሻው፡- This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል::

Read 12319 times