Saturday, 14 December 2019 12:47

በሀሳብ መንገድ ላይ

Written by  ተመስገን
Rate this item
(1 Vote)

   “እርፍ ሳይጨብጡ ማረስ፣ ያለ ብዕር መፃፍ፣ ያለ ብሩሽ መሳል፣ ጦር ሳይሰብቁ ማሸነፍ ተችሏል፡፡ ያላዩትን ማፍቀር አይከለከልም፡፡ ላልተመለከቱት ማንጐራጐር፣ ያላዩትን መናፈቅ ይቻላል፡፡ “
             
               ሰውየው፤ “በእግዜር ነው በአላህ የምታምነው?” ተብሎ ሲጠየቅ፣
 ወደ ትልቅ መስታወት  ተጠጋና፣ ከምስሉ ጐን ቆሞ፡-
“የትኛው ነኝ አለ?” ጠያቂውን
“ሁለቱም አንተ ነህ”
ፈቀቅ ብሎ፡-
“አሁንስ?”
“ብቻህን ነህ”
“ቅድም ሁለቱም አንተ ነህ ብለህ ነበር፡፡ ሁለት ከነበርን አንደኛው የት ሄደ?”
“የትም፡፡ ያው ራስህ ነህ”
እንደገና ወደ ሌላ ቆሻሻ መስታወት ተጠግቶ ቆመና፡-
“አሁንስ ምን ይታይሃል?”
“አንተ ንፁህ ነህ፣ ያኛው ቆሻሻ ነው”
“ሁለት ነን ማለት ነው?”
“አይደላችሁም”
“እና?”
ዝም፡፡
አንድ የድሮ ቀልድ ነበረች፡፡ ሁለት እንስሶች እኔ እበልጥ፣ እኔ እበልጥ እየተባባሉ ሊስማሙ ባለመቻላቸው ለዳኝነት ጦጢት ዘንድ ቀርበው፤ “ማንኛችን ነን ቆንጆ?” ብለው ጠየቋት፡፡ ምን ያለች ይመስላችኋል?
***
ወዳጄ፡- የቀሽም ጥያቄዎች የመጨረሻ መልስ “ዝምታ” ነው፡፡ ጉተማ ቡድሃ፤ “ሰው የሚነሳና የሚወድቀው በራስ መተማመን ሲያቅተው ነው፣ ጽድቅና ኩነኔ የያንዳንዳችን ስራ ውጤት ነው፡፡” ብሎ ነበር፡፡
ወዳጄ፡- “ዝም” ማለት በሚያስፈልግበት ጊዜና ቦታ “ዝም” ማለት መቻል መልካም ነው:: መቻል “ማሰብ” ነው፡፡ እርፍ ሳይጨብጡ ማረስ፣ ያለ ብዕር መፃፍ፣ ያለ ብሩሽ መሳል፣ ጦር ሳይሰብቁ ማሸነፍ ተችሏል፡፡ ያላዩትን ማፍቀር አይከለከልም፡፡ ላልተመለከቱት ማንጐራጐር፣ ያላዩትን መናፈቅ ይቻላል፡፡
በቀደም በሸገር ሬዲዮ “Independent” በተባለው የነፃ አስተሳሰብ ቅኝት የተቀመሩ ሙዚቃዎችን ስሰማ ነበር፡፡ Post card from Mars, journey to the unknown እና ሌሎች በምናብ የሚያናውዙ ውብ ቅንብሮች፡፡ በኛም አገር ተመሳሳይ ይዘት ያላቸው ብዙ ዘፈኖች አሉ፡፡ እንደ “የህልሜ ጓደኛ” ዓይነቶች፡፡ ጥበብ በርቀት ማየትና በጥልቅ ማሰብ “መቻል” ነው:: “The true sense of art is imagination” ይላሉ ሊቃውንቱ፡፡
ወዳጄ? መቻል “መኖር” ቢሆንም፤ ሳይኖሩ… ፀሃይቱን ሳይሞቁ ግን በሰፊው የሚኖሩ ደግሞ ብዙ ናቸው፡፡ የሰው አእምሮ የፈጠራቸው:: “imaginary human beings” የሚሏቸው:: ጉዱ ካሳ አልነበረም፡፡ ሁሌ ግን ውስጣችን አለ፡፡ እኛ ብናልፍም እሱ ይቀጥላል፡፡ ዶን ኪፃቴና ሰንቾ ፓንዛ አልነበሩም፡፡ ነገር ግን የስፓኒያርዶች ጀግና ሆነው፣ በምናባዊ መልክ ተስለው ሃውልት ተቀርፆላቸዋል፡፡ የወደፊቱ ሰው፣ ታላቁ ሰው (Uberman, Superman) የተባለው ዛራ ቱስትራ አልነበረም፡፡ በዚህ ዘመን ግን መታየት ጀምሯል…እንደ ትንቢቱ፡፡
አዬ ኩዌ አርማህ “The beautiful ones are not yet born” የተባለውን መጽሐፉን ሲያሳትም ልዩና አስገራሚ (eccentric) ባህሪ አለው የተባለው ሰውዬም እንደተረገዘ አልቀረም፡፡ ጊዜዋን ጠብቃ ልትወልደው ፕላኔቷ እያማጠች ነው፡፡
ወዳጄ፡- ‹መቻል› የጊዜ ትርጉም ነው:: ‹ጂኒየስ› በመሆንና ‹ስቴት ኢንቴሌክቹዋል” በመሆን፣ በ“አውቶሪቲ” እና በነፃ አስተሳሰብ መሃከል ልዩነት እየሰፋ መጥቷል፡፡ ያውም የሰማይና የምድር ያህል፡፡ የማህበራዊነት አጀንዳና ግላዊ አስተሳሰብ ከተምታተበት መንግሥት ጋር ተከራክሮ የረታው፣ ቆሻሻውን የፍትህ መስታወት ጠርጎ፣ በእውነተኛ ገጽታዋ ማንነቷን ያሳየችው መሃንዲስም ብቅ ብሏል፡፡… ሃዋርድ ሮክ፡፡ የዓለምን ሞተር ማቆም የቻለው፣ የአሜሪካን ፕሬዚዳንት ንግግር ለማድረግ በተዘጋጀበት ሰከንድ፣ የሬዲዮ ፍሪኩዌንሲና የአየር ሞገዱን ሰብሮ በመግባት፣ ስለ ታላላቅ ሀሳቦች፣ ለዓለም ሕዝብ ንግግር ያደረገው ጆን ጋልትሞ ዕውን እየሆነ ነው፡፡ ታላቁ ይትስ፤ “ሁለተኛው መምጣት” (The second coming) የሚለውን ግጥም ሲጽፍ፤ መጪዎቹን ክርስቶሶቹ እያሰበ እንደነበር አትጠራጠር፡፡
ታላቁ ናፖሊዮን፤ ‹አይቻልም› የሚለው ቃል የሚገኘው በቂሎች መዝገበ ቃላት ውስጥ ነው ይል ነበር፡፡ እውነት ካለህ ትችላለህ፡፡ ቆራጥ ሁን ብቻ!!... ሰዎች የሚችሉት ወይም ውጤታማ እንዲሆኑ የሚያደርጋቸው ዋና ነገር፤ ግዞተኛ ወደነበሩበት ሁኔታ ላለመመለስ ሲቆርጡ ነው፡፡
ወዳጄ፡- ከሁለት ዓመትና ከዚያ በፊት ኖቤል ፕራይዝ ወደ አገራችን ይመጣል ብሎ ያሰበ ማንም አልነበረም፡፡ ግን መጣ፡፡ ኢትዮጵያ ቻለች፡፡ ቤሪ አንደርሰን፤ ‹‹ኢትዮጵያ የሰው ዘር መገኛ ነች፡፡ ሁላችንም ኢትዮጵያዊ ነን›› ብለው ተናገሩ፡፡ ዓለም አጨበጨበ፡፡ የሰለጠነ ሰው እንዲህ ያስባል፡፡ እኔና አንተ ግን…
ፍሬወይኒ መብራህቱ፤ የ2019 የCNN ጀግና ሆና ተመረጠች፡፡ ፍሬወይኒ ለአቅም አልባ ወገኖቿ እየታጠበ ጥቅም ላይ የሚውል ሞዴስ ማዘጋጃ ኢንዱስትሪ በመገንባት ለውጥ አምጥታለች፡፡ ‹Dignity for all› የሚል መርህ አላት፡፡ ልጅቷ በመቻሏ ኢትዮጵያ ከፍ አለች፡፡ እኔና አንተ ግን…
ወዳጄ፡- ሴቶቹ አልተቻሉም፡፡ የሰላሳ አራት ዓመቷ ሳና ማሪ፣ የፊንላንድ የመጀመሪያዋ ሴት ወጣት ጠ/ሚኒስትር ሆና ተመርጣለች፡፡ አዲሷ የአውሮፓ ኮሚሽን ፕሬዚዳንት፤ “ስራዬን የምጀምረው ኢትዮጵያን በመጎብኘት ነው” ብለው ባለፈው ቅዳሜ አገራችን መጥተዋል:: ፎንደር ላይን፡፡… ለሁሉም ባርኔጣችንን አንስተናል፡፡  
ወዳጄ፡- ኢትዮጵያ ቀልብ የምትስብ አገር እየሆነች ነው፡፡ ፊቷን ወደ ፀሐይ መውጫ አዙራለች፡፡ ወደ ህልሟ ሳትደርስ አትቆምም፡፡… እንደ ኪራ አርጋኖቫ!!
***
ወደ ቀልዳችን ስንመለስ፡- ሁለቱ እንሰሶች ጦጢት ዘንድ ቀርበው “ማንኛችን ነን ቆንጆ?” ብለው ሲጠይቋት ‹‹አንቺም፣ አንቺም አባቶቻችሁን ትመስላላችሁ›› ነበር ያለቻቸው:: ያኔ ዓለም በቴክኖሎጂ ሳይሆን በዲፕሎማሲ ነበር የምትመራው። ትናንት ሌላ፣ ዛሬ ሌላ!!
አንድ ጥያቄ ልጠይቅህ፡-
“As we look ahead to the next century, leaders will be those who empower others”   ያለው ማን ነበር?... ምርጫ ልስጥህ፡፡
ሀ) ዊሊያም አሳንጄ (ዊክሊክስ)
ለ) ጃክማ (አሊባባ)
ሐ) ቢል ጌትስ (ማይክሮ ሶፍት)
ሠላም!!


Read 2247 times