Saturday, 14 December 2019 13:03

የዜማ ውበት፣ የድምፅ ጥበብ ከቤቲ አልበም - ወገግታ

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(2 votes)

     አገር ምድሩን በብርሃናማ ትርችቶች የሚያደምቅ፣ ንጋትን የሚያበስር እልል የሚያሰኝ የሃሴት ከፍታ ዘንድ ያደርሳል - “ብሩህ ጠዋት” በሚለው የፌሽታ ዘፈን፡፡
በወገግታ የሚጀምር፣ የዜማዎች ጣዕም ሽርሽር ነው - የቤቲ አዲስ አልበም። ብርቅ ድንቅ ዘፈኖችን የሚያጣጥሙበት የጥበብ አዝመራ። እና ደግሞ በአወንታ መንፈስ የተትረፈረፈ።

ከልብ የፈለቀ ከልብ የሚዘልቅ የአገር ትርጉም - ባወቀ አእምሮ
‹‹አገር›› ይላል ዘፈኑ፡፡ በተፈጥሮ ተዋድደው የተፈጠሩ በሚመስሉ ሦስት የዜማ ክፍሎች የተዘጋጀ ዕፁብ ድንቅ የዘፈን ጥበብ ነው - “ይሄ ነው አገር ማለት!› የሚያሰኝ። “ይሄ ነው የአገር ፍቅር ማለት” በሚል መንፈስ፣ ነፍስን ያድሳል፡፡ ህሊናን ይመረምራል፡፡
ምንም ሳያግደው የሚናኝና በሁለመና  ሰርጎ በሚዋሃድ ምርጥ የዜማ ፍሰት፣ በምርጥ የድምፅ ብቃት፣... ባወቀ አእምሮ፣ በተረዳ መንፈስ፣ ከሙዚቃው ሙያ ጋር በፍቅር በተዋሃደ የጥበብ ነፍስ የተሰራ ዘፈን ነው። “አገር” የተሰኘው የቤቲ ዘፈን ነው፡፡
አገርን በአድናቆትና በፍቅር እጅጉን በማወደስ ትጀምራለች... “የአምላክ ጥበብ… ባንቺ የታየ” እያለች። ከዚያስ? በጥያቄ ታባንነናለች፡፡
አገር
መስኩ ተራራው
ሸንተረር ጋራው
የአምላክ ጥበብ፣ ነው ባንቺ የታየ
ያየሩ ምቾት፣ ሁሌ ሚናፈቅ
ቅርሳቅርሱማ፣ ልብ የሚሰርቅ...
...ግን ይሄ ነው ወይ አገር ማለት?
ለዚህስ ብቻ ነው ወይ የሞቱለት?
ቤቲ፣ የመልክዐምድርና የቅርስ አድናቆትን ወደ የላቀ አድናቆት ለማምጠቅ፣ ከልብ በመቆርቆር በምታቀነቅነው ጥያቄዋ፣ መንፈሳችንን በሚቀሰቅስ ሃያል ዜማዋ የአእምሮ በራችንን ትቆረቁራለች፡፡ ህሊናን እያንኳኳች ታስከፍታለች።
የተፎከረው፣ የተለቀሰው፤
ያባቶቻችን፣ ደም የፈ-ሰሰው፤
ለቡናው ነበር ወይ?
ወይስ ለንጀራው?
ለአራዊቱ ላፈር ለሜዳው?
ኧረ ይሄ ነው ወይ አገር ማለት?
ለዚህስ ብቻ ነው ወይ የሞቱለት?
ኧረ ይሄ ነው ወይ አገር ማለት?
ለዚህስ ብቻ ነው ወይ ምንሞትለት?
አገር ማለት... ከዚህም በላይ በእጅጉ የላቀ መሆኑን ብንረዳ እንደሚበጀን ነው መልዕክቷን የምትነገረን። ግን፣ መልዕክቷን የምታስተላልፍልን፣ በዜማዋ የማሳመን ሃይል፣ በድምጿ ማራኪ ጥበብ፣ ወደ አድማጮች ህሊና እንደምትደርስ በመተማመን ነው።
የአገር ትርጉም፣... ላይ ላዩንና የቅርብ የቅርቡን ብቻ ሳይሆን፣ ውስጡን በጥልቀት፣ ከዳር እስከ ዳርም ስፋቱን እንድንረዳ፤ (አገር የሰዎች ትልቅ የስራ ውጤት ነውና) በአጭር ሳንታጠር የብዙ ምዕተዓመታት የህልውና መሰረቶችን፣ የታላቅነት ጀግኖችን፣ የእውቀትና የፈጠራ ሰዎችን፣... (አገር ለሰዎች ነውና) የወደፊቱንም ራዕይ ጭምር... እና ሌላም ሌላም ብዙ የአገርን ትርጉም አጥርተን፣ በአንድነት አዋድደን እንድንጨብጥ፣... ከመንፈሳችንም ጋር እንድናዋህድ... ነው?
የአገርን ትርጉም፤ በደንብ አውቀን ከራሳችን ጋር ያዋሃድን ጊዜ፣ የት እንደምንደርስና ምን እንደምናገኝ በእርግጠኛነት ታዜማለቻ። የአገርን ምንነት፣... እጅግ ሰፊና ጥልቅ፣ ውድና ድንቅ የአገር ትርጉም፣ በብዙ መፃሕፍት የሚተነተነውን የአገር ትርጉም አዋህዶ በአንድነት ማዋደድ!...
ይህንን ለመረዳት “ብዙ ነው ቋንቋው/ ግን አንድ ቤተሰብ” ብላ ያቀነቀችበትን ድምፅና ዜማ ልብ ብላችሁ ብታደምጡ ይሻላል። የአገርን ትርጉም እየተረዳን ስንሄድ... ያኔ በኑሮም በመንፈስም ከፍ ከፍ እንደምንል እንዳትጠራጠሩ አድርጋ ታዜማለች - ቤቲ።
እውነተኛ የልብ ቀና ምኞትን በድምጽ ብቃትና በዜማ ጥበብ ፍንትው አድርጎ ማሳየት እንደሚቻል (ቤቲ እንደምትችል) አድምጡ፡፡ “ሁሉም” ይለወጣል፡፡ መልካምም ይሆናል…” እያለች ዜማዋን የምትቀጥልበት፣ ከልብ ፈልቆ ወደ ልብ የሚዘልቅ የዜማ ስሜትን ከልብ ስሙ፡፡
ሁሉ ከእንቅልፉ ሲነቃ...
ሁሉ ባንድላይ ሆኖ ሲነሳ
ሁሉም ይለወጣል
መልካምም ይሆናል፡፡
ሁሉም ተርፎት ያድራል
ደስታችንም ይበዛል፡፡
ይጠፋል መጠላላት
አንዱ አንዱን ባሽሙር መውጋት፡፡
ሰው ለሰው መድሃኒቱ
የዛኔ እንደሆነ ሲገባን፣
ሃገር ነው ወገን፣ ወገንም ሃገር!
ብዙ ነው ቋንቋው፣
ግን አንድ ቤተሰብ!
የሚያስጨፍርና የሚመስጥ አስገራሚ ዘፈን - ቢራቢሮ
በዙሪያዋ ሁሉ፣ እፅዋት በርክተው፣ ልምላሜ ለብሰው፣ ውበትን የሚተነፍሱ፣ እሷን የሚጣሩ ቢመስላትና ብትቁነጠነጥ፣... ተፈጥሮዋ ነው:: አበቦች በህብር አምረው፣ በደማቅ ቀለማት ተንቆጠቁጠው ቢማርኳት፣ በመዓዛቸው የታወደውን ንፁህ አየር እየቀዘፈች እንደልቧ  መክነፍ ቢያሰኛት፣... ደግ አደረገች። ለመብረር የተፈጠረች ቢራቢሮ አይደለች?
ያጌጡ ክንፎቿን ከመቅፅበት ለመዘርጋት፣ እየዘመረች ወደ አበቦቹ  ለመብረር ልቧ ስቅል ብሎ፣ እመር ብላ ለመነሳት የጓጓች ህፃን ቢራቢሮ! ህልሟ፣…ጤናማ የሕያዋን ፍላጎትና የተቀደሰ ምኞት ነው!... ግን፣ ወዳሰበችው ለመሄድ፣ ወደ ከፍታ ለመድረስ መመኘት ማለት፣ ‹‹በአፍታ አብቦ ያለፋታ ለፍሬ መድረስ›› ማለት እንዳልሆነ አላወቀችም። ወድያው ተወልዶ እዝያው ባለክንፍ አይኮንም። ገና በሌለ ክንፍ መክነፍ፣ መች ይሆናል? ኩብኩባ መሆን፣ ማኮብኮብ ማለት አይደለም፡፡ የታለ የቢራቢሮነት መልክና ቅርፅ?
ገና ኩብኩባ፣ ገና ጀማሪ ቢራቢሮ፣... ገና ባዶ እጇ፣... የነጣች የገረጣች፣... በዚህ ሁኔታዋ፣ ያጌጡ ክንፎችን የማብቀል ምኞቷና ወደ አበቦች የመብረር ጉጉትዋ፣... ከሰማይ የራቀ፣ ያለተስፋ የቀረ ከንቱ ምኞት መስሎ ይታያት ይሆን?
ባለወኔ ንፁህ ነፍስ ናት። ችግሩ፣ ‹‹ምኞት ባንድ አፍታ›› አየር ባየር የሚገኝ መስሏታል፡፡ ይሄ አልሆን ሲል ደግሞ፣ “አሁኑኑ ካልበረርኩ፣ ወደፊትም ተስፋ አይኖረኝም” በሚል ስሜት፣ አንገት መድፋት? የጀማሪ ነገር፣... ትቸኩላለች፡፡ ከአንድ ስህተት ወደ ሌላ ስህተት?
ደግነቱ፣ የስኬት ሕልሟን በማክበር፣ የመብረር ጥረቷን በማድነቅ የምታበረታታ መካሪ አለችላት:: በቀና መንፈስ የተሞላችና ሁሌም ከውስጧ የማትጠፋ መካሪ ናት። ቀናዋ መካሪ መንፈስ፣... ከምር ነፍስ ዘርታ መጥታለች።
“የስኬት አላማና ጥረት፣... ምንኛ ከውድ እንቁም በላይ የከበሩ፣... በአድናቆትና በፍቅር፣ እጅግ ልንቆረቆርላቸው፣ ልንጠነቀቅላቸው፣ ልናስብላቸው እንደሚገቡ ከምር ያወቀች” መካሪ ናት። ይህች መካሪ፣ ይህች ብሩህና ቀና መንፈስ፣ በእውን ምን እንደምትመስል፣ በአካል የመዳሰስ ያህል የሚያሳይ ነው - “ቢራቢሮ” የተሰኘው የቤቲ ድንቅ ዜማ።
ባወቀ አእምሮ ብቻ የተዘፈነ አይደለም፡፡ እውቀትን ከማንነቷ ጋር አዋህዳ ስሜቷን የቃኘች የቤቲ የኪነ ጥበብ ነፍስ፣ በድንቅ የድምፅ ብቃቷና በዜማ ጥበቧ የተሰራችው ግሩም ዘፈን ነው።
ቢራቢሮ... ልትበር ቶሎ፤
ውብ አበባ... አይታ ኖሮ፤
አኮብኩባ... ልትነሳ፤
አላወቀች... ወይ ኩብኩባ።
የመዝሙር በሚመስሉ በእነዚህ ጥቂት ቃላት ነው ዘፈኑ የሚጀምረው - ግን ደግሞ በብልሃት የተሰናሰለ ሚስጥሩ የሚገለጥ ግጥም ነው። ከዚያማ፣ ቤቲ... እንዴት በተዋበ ዜማና በጥበበኛ ድምጿ ተዓምረኛ ሕይወት እንደምትሰጠው፣ ዘፈኗን እየሰሙ መደመም ነው። በገለፃ የሚሆን ነገር አይደለም። ዘፈኑን በማዳመጥ እንጂ! ዜማውን በማጣጣም እንጂ።
ቢራቢሮ...
ሲታይ መልክሽ... ...ሌላ ሆኖ፤
ተስፋሽ... ምነው ተመናምኖ፤
በችኮላ መብረር ተመኝታ ያልሆነላት ህፃን ቢራቢሮ፣ ገና ጌጠኛ ክንፍ እንደሌላት፣ መልኳ ገና ቢራቢሮ አለመምሰሉን እያየች፣ የራሷን ተፈጥሮ መጠራጠርና ተስፋ መቁረጥ እየሞካከራት ነው።  “ቢራቢሮ መሆንሽማ እውነት ነው” እያለች ለማስረዳት ትሞክራለች ብሩህዋ መካሪ። “ስሚኝ ዛሬ” እያለች ለማሳወቅ ትጣደፋለች፣ ዛሬውኑ፣ አሁኑኑ ለማስገንዘብ፣ ከመቅፅበት  በአንድ አፍታ ለማስተማር ትቻኮላለች - ብሩህዋ መካሪ።
ቢራቢሮዋ፣ በቀና መንፈስ ወደ ላቀ ከፍታ ለመብረር የምትቻኮል ገና ጀማሪ ቢራቢሮ!
ግን፤ መካሪዋም፣ በቀና መንፈስ በቅጽበት ለማቃናት የምትቻኮል ገና ጀማሪ ናት ለካ!
የሚመስጥ ጥልቅ ዘፈን ነው፡፡ ምኞትንና ውጤትን ብቻ ሳይሆን በመነሻና በመድረሻ መካከል፣ ቀና መንገድና የጥረት ጉዞንም ልብ እንድንል ያባብላል፡፡ ግን ደግሞ ዘና የሚያደርግ ዘፈን ነው:: በንፁህ መንፈስ ያስጨፍራልም እንጂ! በጥልቀት የሚመስጥ እና አዝናንቶ የሚያስጨፍር አስገራሚ የሙዚቃ ስራ ነው፡፡ የዘፈኑን ሃሳብ ስትመረምሩት ደግሞ፣ ይደንቃል፡፡
በምኞትና በውጤት፣ በአላማና በስኬት መካከል ያለውን የጥራት “ሂደት” መርሳት ወይም ቸል ማለት፣ ከጀማሪ እስከ መሪ፣ ከሊቅ እስከ ደቂቅ፣እንደየደረጃው ሁሉንም የሚፈትን ጉዳይ ነው። እንዲያውም፣ በጣት ከሚቆጠሩ ዋናዋና የፍልስፍና ጥያቄዎች መካከል አንዱኮ፣ ‹‹ተፈጥሮን የሚመጥን አላማ፣ ቀና መንገድና ውጤታማ ጥረትን›› የሚመለከት ነው፡፡ የስነምግባር (የኤቲክስ) ዘርፍ ይሉታል፡፡
የፖለቲካ፣ የጦር ሃይል፣ የትምህርት፣ የቢዝነስ፣ የእለት ተእለት ስራ ሁሉ…‹‹ትክክለኛ አላማ፣ ተገቢ መንገድና የስኬት ጥረት›› ከሚሉ ጥያቄዎች ውጭ የሚሆን ነገር የለም፡፡
ወታደራዊ ስትራቴጂ እና ታክቲክ፣ ስርዓተ ትምህርትና ዘዴ፣ የቢዝነስ እቅድ፣ የእግር ኳስ ቡድን አሰላለፍና ታክቲክ፣ ሁሉ የግብ፣ የዘዴና የተግባር ጉዞ ላይ የተመሰረቱ ናቸው፡፡ የሆነ ቦታ ለመሄድ ፈልገው አድራሻና አቅጣጫ ሲጠይቁ፣ በታክሲ ወይስ በአውቶቡስ ብለው ሲወስኑ ጭምር፣ ጉዳዩ ሌላ ነገር አይደለም፡፡
የአላማና የስኬት፣ የመንገድና የጥረት ጉዳይ ነው - ነገሩ፡፡ ከምኞት ወደ ውጤት የሚያደርሱንን ሂደት አለመዘንጋት፤ የሁላችንም የሁልጊዜ ጉዳይ ነው፡፡
አስገራሚው ነገር፣ ይህንን ሁሉ ሃሳብና መንፈስ፣ በዜማ ማሳየት የሚቻል መሆኑ ነው፡፡  ማለቴ ቤቲ ችላለች። አሳምራ ዘፍናዋለች። የግጥሙ የቃላት አመራረጥም፣ ድርሻ አለው። ለምሳሌ፣ “ሂደት አለውና” የሚለው አገላለፅ፣ የመካሪዋ የጀማሪነት መንፈስን ለማሳየት ይጠቅማል። “ጀማሪ ለጀማሪ” የሚለውን መንፈስ፣ ስጋ አልብሳ ለማሳየት የቻለችው ግን፣ በዜማውና በአዘፋፈን ጥበቧ ነው። ዘፈኑን ፈጠን ወዳለ ሁለተኛ የዜማ ክፍል ታሻግረዋለች - ኧረ ቢራቢሮዬ... እያለች።
ኧረ፣ ቢራቢሮዬ፣ ስከኝ፣ ቀስ በይና፣
ባንዴ፣ መች ይበረራል፣ ሂደት አለውና፣
ኧረ፣ ቢራቢሮዬ፣ ስከኝ፣ ቀስ በይና፣
ባንዴ፣ መች ለውጥ፣ ይመጣል፣ ሂደት አለው ገና።
ቤቲ እነዚህን ስንኞች፣ ‹‹የጉራጊኛ›› ከሚመስል ምት ጋር፣ ሞቅ ደመቅ ባለ ዜማና አዘፋፈን ነው፣ ነፍስና ስጋ የምትሰጣቸው። ለመሆኑ የጀማሪዋ ቢራቢሮና የጀማሪዋ መካሪ መጨረሻ ምን ይሆን? “ባንዴ መብረር የለም››... “ሂደት አለው”። ሂደት ግን ሄዶ ሄዶ በዚያው አይቀርም። አፈር ላይ እየተንፏቀቁ፣ ጭቃ ላይ እየተላወሱ መቅረት የለም - መብረር አለ። ግን፣...
የቢራቢሮዋን የስኬት ምኞት እያደነቀች፣ ሲሰምር ራዕይሽ፣ ሲታይሽ ክንፍሽ፣ ሲበር በምናብሽ፣ የመለወጥ ህልምሽ እያለች ካወዳደሰች በኋላ... ትቀጥላለች። (የዘፈኑ ሃሳብና የዜማው ስሜት፣ በጥበብ ሲታጠፍ፣ ግጥምጥም ብሎ ሲሰምር (በsurprise twist)፣ ምርጥ መቋጫ ላይ ሲደርስ አድምጡ - በሦስተኛው የዘፈኑ ክፍል።)
ታዲያ “ቢራቢሮ
አይሆን ተቸኩሎ
ያልሆኑትን ሆኖ
ሂደቱ... ተጠልቶ”...
ብዬ የምነግራት
ልቧን ልመልሳት
ከድካም ከጥፋት፣...
እልፍ ብዬ ባያት
እቺ ቢራቢሮ
እኔ ሆኜ ኖሮ!
ይሄውና፣ ዘፈኑና ዜማው፣ በጥበበኛ የእጥፋት ስምረት... ምርጥ መቋጫ ላይ ደረሰ። ጀማሪዋ የብሩህ መንፈስ መካሪ እና ጀማሪዋ ቢራቢሮ፣... አንዷ የሌላኛዋ ምስል ናቸው።
ከመቅፅበት አላማን ከስኬት ላይ የማድረስ ምኞት፣... ይሄ አልሳካ ሲል ደግሞ ተስፋ መቁረጥ፣... በምኞትና በስኬት መሃል ያለውን “ሂደት”፣... በአላማና በውጤት መካከል ያለውን ቁልፍ ነገር መርሳት (ምሁራኑ ስትራቴጂና የተሰናሰለ ተግባር የሚሏቸውን ነገሮች፣... ወይም ዘዴን እና ጥረትን መዘንጋት)፣ ሁሉንም ሰዎች የሚመለከት ቁምነገር ነው -ሁሌም፣ በሁሉም ጉዳይ ላይ። ይህንን እውነት የሚያሳይ በመሆኑም ነው፣ ጥበበኛው የእጥፋት ስምረት ትልቅ ትርጉም የሚኖረው (surprise twist፣ ሌጣው ሲሆን፣ ጥበብነትም ትርጉምም አይኖረውም)።
አይ ዘንድሮ (ከርዕሱ በላይ በላይ ልቆ የሄደ ትልቅ ዘፈን!)
ያማረ ውድ የምናብ ዓለም ነው የዘፈኑ መነሻ - የፍቅር ዓለም ጅምር፣ የፍቅር ኑሮ ውጥን። ለዘላለም የሚመስል፣ በፍቅር የተዋበ የምናብ ዓለም። ለዘላለምም መሆን ይችላል። በንፁህ ህሊና አስበው፣ በቀና የተነጋገሩት የትናንቱ ቃልኪዳን፣ ለይስሙላ አልነበረም። የምር ነበር እንጂ። ለዛሬም፣... ለነገም፣ ሁሌም የፍቅር ዓለም እየለመለመና እየደመቀ፣ ያማረ የፍቅር ኑሮ እንዲሆንላቸው ነበር ሃሳባቸው።
ግን፣ ቀናት አልፈው ወራት ሲተኩ፣... ያ በምናብ የወጠኑት የፍቅር ኑሮ፣ በእውን ሊይጨብጡት ሊይዙት ሲሞክሩ፣ በዚህና በዚያ እያመለጠ፣ አልሆን የሚላቸው ለምን ይሆን?
“የታል፣...
በበጎ በክፉም ጊዜ
ፍፁም ላንለያይ፣ ቃል የገባነው ያኔ”
ይሄ የዘፈኑ አጀማመር፣... ወደ እሮሮ የሚያመራ ከመሰላችሁ፣ ተረጋጉ። ለእሮሮና ለማማረር አይደለም። ወቀሳ መወራወርና ክስ መደርደር የለም:: በእርግጥ፤
 “ብርታት ጠፍቶ፣ መለያየት ደርሶ፣ ልባችን ተሰበረ” ከሚል የሀዘን መንፈስ ጋር ፣... “ስለፍቅር አለማወቃችን ጎዳን” የሚል የቁጭት ስሜትን ያዘለ ነው።
አወቅን የምንለው፣ ከጥቂት ቀናት በላይ በማይሰራ ቅንጣት እውቀት ብቻ ነው እንዴ?... ብርታትን የሚፈትን አጋጣሚ ሲፈጠር፣ በቀላል ሽውታ የሚደበዝዝ የአፍታ እውቀት ነው እንዴ የኛ እውቀት? ይህን ብሎ አዋቂነት!... በዚህ መንፈስ ነው፣ በቁጭት፣ “ፍቅር በመለያየት አያምንም” በማለት ስለፍቅር የምታዜመው፣... ስለ ፍቅር ስለ ራሱ!. “ፍቅር ፀንቶ ይቆማል”... እያለች!
“ፍቅር ይታገሣል
ቸርነትን ያደርጋል፣ እንዲሁ አይወድቅም ከቶ”፤
ስናበላሽ እንዲህ እያልክ...
ትመልሰኝ አልነበር፣ ለምን ልብህ ዛለ ቶሎ።
ፍቅር ፍቅር
አይ ዘንድሮ...
ጥሬ ዞሮ፣ አልበሰልንም፣ “አዋቂ!” እኛን ብሎ።
ፍቅር አይታበይም
በደልንም አይቆጥርም
በመለያየት አያምንም፡፡
ፍቅር ይታገሣል
ቸርነት ያደርጋል፡፡
አይወድቅም ከቶ
ፍቅር ተስፋ ያደርጋል
ፀንቶም ይቆ...ማል!!
በጣም ምርጥ ዘፈን ነው። በድንቅ ድምጿ፣ በዜማዋ ብርታት፣ ይቅርን ማጽናት የምትችል ይመስላል፡፡ ዘፈኑ የዚህን ያህል ሃያል ነው፡፡
እውነት ለመናገር፣ ጥቅል ሃሳቦች የበረከቱበት እንዲህ አይነት ግጥም፣ ለዘፈን በጣም አስቸጋሪ ነው። ግን፣  ከድንቅ ዜማና ከተመጠነ ቁጥብ የሙዚቃ ቅንብር ጋር፣ ቤቲ በድምፅ ብቃቷና በጥበቧ... ምርጥ ዘፈን ሰራችበት - “ወይ ዘንድሮ” በሚል ርዕስ። እንዲያውም... ይሄው ዘፈን፣ የአልበሟ የምርጦች ምርጥ ዘፈን ነው ቢባል አይበዛበትም።
ግን ደግሞ፣ “አገር” የሚለው ዘፈን አለ። በዚያ ላይ “ቢራቢሮ” የተሰኘው ድንቅ ዘፈን አለ፡፡
“ጥልቅ ስሜት” የሚለውስ ዘፈን? የምርጦች አንደኛ ከመሆን ምን ያግደዋል?
“ዋጋ” የተሰኘው ዘፈንም ጉደኛ ነው።
“ሩጫም ለፈጣን፣ ውጊያም ለሃያላን፤ ሞገስ ለአዋቂ፣ ሃብትም ለጠቢባን...” መሆን አለበት፤ ብዙ ጊዜ እውን የሚሆን ባይመስልም፣ አይቀርም ይሳካል... እያለች የምታቀነቅንበት ዘፈን ነው - ‹‹ዋጋ›› የሚለው ዘፈን።
አዎ፣ ፈተናዎችን ለማለፍ ብዙ ጥረት ያስፈልጋል። ግን፣ ጥረት ሁሉ፣
ከንቱ ልፋት አይደለም። ዋጋ አለው... የሚል ነው ዘፈኑ። የታቀደው ወድቆ፣ የተጀመረው ከሽፎ፣ የተገነባው ፈርሶ፣ ባዶ እጅ የሚያስቀር አጋጣሚ ይኖራል፡፡ ከአንዴም ሁለት ሶስቴ ችግርና ፈተና እየተደጋገመ፣ ‹‹ምን ዋጋ አለው?!” የሚያስብል ቢሆንም እንኳ፣ ‹‹ጥረት ዋጋ አለው››…ብሎ አሳምኖ መዝፈን ቀላል ፈተና አይደለም፡፡
ዋጋ አለው ህይወት ስታልፍ መከራ
እንደወርቅ፣ እሳት ውስጥ ተፈትና ስትሰራ።
ዋጋ አለው መታገስ አይደለም ለከንቱ
እንቁ ሲታሽ ነውኮ የሚደምቀው ውበቱ።
እንቁ ዘፈን ነው፡፡ እውነትም፣ የምርጦች ምርጥ ዘፈን የትኛው እንደሆነ መናገር ያስቸግራል።
‹‹ኧረ ማነው?›› የሚለው ዘፈንም፣ ግሩም ነው፡፡
 “አስተውሎ መርምሮ፣ ጥሮ ሰርቶ፣ በፈተና በችግር ሳይረታ፣ ለስኬት የሚደርስ፣ ለአርአያነት የሚበቃ ጀግና የታለ? ኧረ ማነው?” እያለች በሌላ ዘፈን ትጣራለች፣ ታፈላልጋለች ቤቲ። የእውቀትና የጥበብ፣ የትጋትና የስኬት ጀግኖችን  የማየት ጉጉትና ረሃብ ነው - “ኧረ ማነው?” የሚለው በምርጥ ዜማና ድምፅ የተሰናዳ ዘፈን። ይሄስ፣ የምርጥ ዘፈኖች አንደኛ ለመባል ምን ያንሰዋል?
ለነገሩማ፣ “እንጃ” የሚለው ዘፈንምኮ፣... አሪፍ ነው።
“እንጃ” የሚለው የግድ የለሽነት ቃል፣ ፍቅርን ሲሸረሽር የሚያሳይ ዘፈን ነው፡፡ ‹‹እንጃ›› የሚለው ቃል፣ ፍቅርን የሚበላ አስቀያሚ ዝገት መስሎ ይታያችኋል - ዘፈኑን ስትሰሙ። ‹‹እንጃ እንጃ ተው አትበል ስለኛ›› እያለች በተንጠፈጠፈ የፍቅር ተስፋ ትጣራለች፡፡ ‹‹እንጃ፣ እንጃ›› ዘንድሮስ እኔ እንጃ›› እያለች ትሰጋለች - እንጃ የሚለውን ቃል ዞር አድርጋ:: ... ያው፣... ይሄም፣ በድንቅ ብቃት የተሰራ ዘፈን ነው። “እንጃ”፣ ምርጥ ነው (ዘፈኑን ማለቴ ነው። ዝገቱን ማለቴ አይደለም)።
የፌሽታ ዘፈን፣ የአዲስ አመት ብስራት!!
“ብሩህ ጠዋት” የሚለው ዘፈን ደግሞ አለላችሁ! በብርሃናማ ርችቶች አገርን የሚያደምቅ፣ ንጋትን የሚያበስር ዘፈን ነው - ለአልበሙ ልዩ ክብር የሚያጎናፅፍ የመጨረሻ ዘፈን!
ብርሃን ብርሃን፣ ለጨለማ
ብርሃን ብርሃን ይሁን ዛሬ
ብርሃን ብርሃን ይብራ ፋና
ብርሃን ብርሃን ይሁን ለኔ
እልልታ በመሰለ እጅግ ፈጣንና ደማቅ ዜማ፣ አገሬውን ፏ አድርጋ ታበራዋለች።
ብቻ ማናለፋችሁ? የቤቲ አልበም፣ በዜማ ጣዕም የተንበሸበሸ የጥበብ አዝመራ ነው። ከምኞትም በላይ በርከትከት ብሎ የተሟላ። ለቤቲ የላቀ ብቃት የሚመጥኑ ዜማዎችን በማዘጋጀት፣ ለምርጥ የድምጽ ጥበቧ ቅድሚያ የሚሰጥ ቁጥብ ሙዚቃ በማቀናበር ልዩ ጥበብን አሳይቷልና አቀናባሪው ያምሉ የተባረከ ባለሙያ ነው፡፡ ቤቲ ደግሞ፣ በላቀ ብቃት፣ ለጥበብ በቆረጠ ልብ፣ ከስራ በሚገኝ የሃሴት ብርታት፣ ጥንቅቅ አድርጋ ሰራችው።
የምትዘፍንበት ድምፅ እና ስሜት አስገራሚ ነው። የድምፅ ብቃትና የሙዚቃ ሙያ ፍቅር... ከዚህም ጋር፣ የእያንዳንዱን ግጥምና ዜማ ይዘት፣ የሃሳብና የስሜት መልዕክት፣ ከመነሻ እስከ መድረሻ፣ ዜማውና ፍስሰቱን፣ ጠልቆ መገንዘብ፣ መረዳት፣ ከራስ ጋር ማዋሃድንም ሁሉ ያሟላላችለት አልበም ነው፡፡
 ቤቲ ምን ያህል ዘፈኖቿን ከራሷ ጋር አዋህዳ እንደዘፈነቻቸው ሲታይ፣ የዘፈኖቿ ግጥሞችና ዜማዎች አብረዋት የተወለዱና ከራሷ ፈልቀው የተቀረፁ ነው የሚመስሉት።Read 877 times