Print this page
Saturday, 14 December 2019 13:09

‹‹እኔም ማሳየት የፈለግሁት ኢትዮጵያን ነው››

Written by  መታሰቢያ ከሳዬ
Rate this item
(1 Vote)

  (የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ መታሰቢያ ካሳዬ፤ በኦስሎው የኖቤል ሽልማት መድረክ ላይ ሥራዎቿን ካቀረበችው ብሩክታዊት ጌታሁን (ቤቲ ጂ) ጋር የአፍታ ቆይታ አድርጋለች)

            እንዴት ነበር ለኦስሎው የኖቤል መድረክ የተመረጥሽው?
የኖቤል ሽልማት ኮሚቴዎቹ ነበሩ የመረጡኝ፤ ሙሉ ዝርዝሩን እኔ አላውቅም፡፡ ከማናጄሬ ጋር ረዘም ላለ ጊዜ ውይይት ማድረጋቸውን አውቃለሁ፡፡ ዘፈንም እንዴት እንደምንመርጥ… ውይይት ያደርጉ ነበር፡፡ እና ኮሚቴዎቹ ናቸው የመረጡኝ፡፡
የኮሚቴ አባላቱን አግኝቼ ስለ ሁኔታው ጠይቄአቸው ነበር፡፡ እንዴት መረጣችሁኝ ብዬ ማለት ነው፡፡ የመለሱልኝ መልስ ግን ‹‹በምርጫችን በጣም ኮርተናል፤ በጣም ደስተኞች ነን›› የሚል ብቻ ነው፡፡ ለምን እንደመረጡኝና በምን ምክንያት እንደመረጡኝ ግልጽ ያለ ነገር አልነገሩኝም፡፡ ያው እንግዲህ የራሳቸው መስፈርት ይኖራቸዋል፡፡
አንቺ ግን እንዲህ አይነት መድረክ ላይ ለመዝፈን ዕድል አገኛለሁ ብለሽ አስበሽ ታውቂያለሽ?
ከልጅነቴ ጀምሮ እንዲህ አይነቶቹ ትላልቅ መድረኮች ላይ ለመዝፈን እመኝ ነበር፡፡ በዚህ ፍጥነት አደርገዋለሁ ብዬ ግን አላሰብኩም፡፡ ወደፊት እደርስበታለሁ ብዬ ነበር የማስበው:: በአሁኑ ወቅት እኔ ትልቅ ቦታ ላይ ደርሻለሁ፤ ይህንን ያህል ኃላፊነትን መወጣት እችላለሁ፤ እዚህ ቦታ ላይ ለመዝፈን ብቃት አለኝ ብዬ አላስብም ነበር፡፡ ከፕሮግራሙ በፊት ጠይቀሽኝ ቢሆን ኖሮ፣ ‹‹ገና ነኝ ለዚህ አልበቃሁም›› ብዬ ነበር የምመልስልሽ፡፡ ግን እግዚአብሔር ይመስገን… ተመርጬ ለመዝፈን በመቻሌ ብዙ ኃላፊነት ነው የሚሰማኝ፡፡ በዚያው መጠን ደግሞ ከፍተኛ ኃላፊነት እንደተጣለብኝ ነው የማምነው፡፡ ምክንያቱም ኢትዮጵያ ትልቅ አገር ነች፡፡ ገና ብዙ ሊተዋወቅ የሚገባው ብዙ ነገር ያላት አገር ነች፡፡ ብዙ አገራት ስለ እኛ ብዙም ነገር ሰምተው ስለማያውቁ፣ ለመስማት ለማወቅ በጉጉት የሚጠብቋት አገር ነች፡፡ እናም ከባድ ኃላፊነት ነው… ግን አንዴ ጀምረነዋል፡፡
መመረጥሽን ስትሰሚ… ምን አይነት ስሜት ፈጠረብሽ?
እንደተመረጥኩ ሳውቅ… በጣም ትልቅ ደስታ ነበር የተሰማኝ፡፡ ግን በፍጥነት የሄድኩት… ለዚህ ትልቅ ፕሮግራም ምን ይዤ ነው መቅረብ ያለብኝ ወደ ሚለው ጉዳይ ነበር፡፡ እዚያ መድረክ ላይ ተመርጬ ከቀረብኩ በኋላ መድረኩን የማሳመርም ሆነ የማበላሸቱ ኃላፊነት የእኛ ነው፡፡ ስለዚህም ብዙኃኑ ሊወደውና ሊቀበለው የሚችለውን ሥራ እንዴት ነው የማቀርበው የሚለውን ከማናጀሬ ጋር በስፋት ስንወያይና ስናስብ ቆይተናል፡፡ በመድረኩ ሥራ ላይ ግን በተለይም ወደ መጨረሻው ሰዓት አካባቢ… በቃ ልገልጸው የማችልለው ደስታና ፍርሃት ተሰምቶኝ ነበር፡፡ መድረክ ላይ ከወጣሁ በኋላ… ግጥሙስ ቢጠፋኝ? ሁሉ ብዬ አስቤ ነበር:: ምክንያቱም የምዘፍንበት መድረክ,፣ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን ባለቡት፣ የኖርዌይ ንጉሳውያን ቤተሰቦች በሚታደሙበት ቦታ ላይ በመሆኑ ከባድ ነበር፡፡ በዚያ ላይ ደግሞ እኔ ከዚህ በፊት የማውቀው የኮንሰርት መድረክ ነው፡፡  እዛ ላይ ተመልካቹ አብሮ እየዘፈነ… አብሮ እየጨፈረ… ስለሚሰራ መድረኩ ቀላል ነው፡፡ እዚህ ጋ ግን እርግት ብሎ የሚያዳምጥ ሰው ስለሆነ… ብሳሳት ያውቁብኝ ይሆን? ይሰሙብኝ ይሆን? የሚለው ጭንቀት በራሱ አስፈሪ ነበር፡፡ ሁለቱም መድረኮች የየራሳቸው ውበት ቢኖራቸውም፣ ይኼኛው ትንሽ ጭንቀት ጨምሮብኝ ነበር፡፡ ግን ከስራው በኋላ ዩቲዩብ ላይ የተቀረፀውን ሳየው… የአቅሜን ተወጥቻለሁ የሚል ስሜት ነው የተሰማኝ፡፡ የሰራሁት ነገር በጣም አስደስቶኛል፡፡
የኦሮምኛ የአንገት ውዝዋዜውን እንዴት ሰራሽው? ማለት አልከበደሽም?
ከፕሮግራሙ ሁለት ሳምንት በፊት ጀምሮ በደንብ ስለማመደው ነው የቆየሁት፡፡ ሥራው በጣም ከባድ ነው፡፡ መጀመርያ ላይ ቁጭ ብዬ ነው ስለማመድ የነበረው… በጣም ያዞረኝ ነበር፡፡ አንገቴን ሁሉ ስትራፖ አሞኝ ነበር፡፡ በኋላ ደግሞ ቆሜ መለማመድ ጀመርኩ፡፡ በዚህ አጋጣሚ ይህንን ውዝዋዜ የሚሰሩ ባለሙያዎችን በጣም ማክበርና ማድነቅ እፈልጋለሁ፡፡ ምክንያቱም እኔ ለዚያች በትንሹ ለሰራኋት ሥራ ምን ያህል እንደከበደኝ አይቼዋለሁ፡፡ እነሱ ግን ምቱም እየፈጠነ… እነሱም እየፈጠኑ… ለረጅም ሰዓት ይጫወቱታል፡፡ ሁልጊዜም በመድረክ ስራዎች ላይ እጠቀማቸዋለሁ ወይም እጫወታቸዋለሁ ብዬ ከማስባቸው የአገሬ ውዝዋዜዎች መካከል አንዱ ነው፡፡ ወደፊትም ይህንን ጭፈራም ሆነ የጉራጊኛ፣ የወላይታ፣ የትግርኛና ሌሎች የአገሬን ውዝዋዜዎች በመድረክ ላይ እጫወታለሁ:: ምክንያቱም የአገራችን የጭፈራ አይነቶች አንዱ ካንዱ የተለየ፣ ሁሉም በጣም የሚያምርና ለሚያየው ሰው ‹‹ይሄ ሁሉ አለ ወይ›› የሚያስብል ነው፡፡ በዚህ አጋጣሚ ልክ ይሄ ነገር ሲሳካልኝ በጣም ነው ደስ ያለኝ፡፡
አንቺና የሙዚቃ ባንዱ አባላት በመድረክ ላይ ስራችሁን ከማቅረባችሁ በፊትና ካቀረባችሁ በኋላ በተጠናና ሥርዓት ባለው መልኩ ለእንግዶች እጅ ስትነሱ
በኖርዌይ በእንዲህ ያሉ ፕሮግራሞች ላይ የመድረክ ሥራቸውን የሚያቀርቡ ባለሙያዎች፤ ለንጉሳውያኑ ቤተሰቦች እጅ መንሳት የተለመደ ነገር ነው፡፡ ይህ ባህል ደግሞ ለእኛ ለኢትዮጵያውያን አዲስ ነገር አይደለም፡፡ ስለዚህም አሰልጣኞቻችን ይህንን ነገር ሲያሰለጥኑን፣ እኛ አላስቸገርናቸውም፤ ምክንያቱ ደግሞ ጉዳዩ ለእኛ አዲስ ነገር አለመሆኑ ነው፡፡ ደግሞም አክብረው ሥራሽን ለማየት የተቀመጡትን ሰዎች፤ አንቺም በዚያ መልኩ የአክብሮት ምላሽ ስትሰጪ ደስ ይላል፡፡
ከመድረክ ስራው በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድን ለማግኘት ዕድል ገጥሞሽ ነበር…?
አዎ አግኝቻቸው ነበር፤ በጣም ደስ እንዳላቸው ነግረውኛል፡፡ ‹‹በጣም ጎበዝ ነሽ፤ በርቺ›› ብለውኛል፡፡
እዚያው ኖርዌይ እያለሽም ሆነ አሁን ከመጣሽ በኋላ ከአድናቂዎችሽ ምን ምላሽ አገኘሽ?
ብዙዎች በጣም ጥሩ ሰርተሽዋል ነው ያሉኝ:: ሰው ሁሉ ‹‹አኮራሽን›› ሲለኝ ነበር፡፡ ይሄ በጣም ያስደስታል፡፡ እኔም ማሳየት የፈለግሁት ኢትዮጵያን ነበር፡፡ ኢትዮጵያዊ አድናቂዎቼ ደግሞ በመኩራታቸው በጣም ደስተኛ ነኝ:: ምክንያቱም ኃላፊነቴን ተወጥቼአለሁ ማለት ነው፡፡  


Read 2379 times