Saturday, 21 December 2019 11:53

አዲስ አበባ ራሷን የቻለች ክልል እንድትሆን ተጠየቀ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(10 votes)

  አዲስ አበባ ራሷን የቻለች ክልል እንድትሆን የኢትዮጵያውያን አንድነት ዲሞክራሲያዊ ድርጅት ጠየቀ፡፡ ድርጅቱ ለአዲስ አድማስ በላከው መግለጫው፤ በፓርቲነት ከተቋቋመበት 1992 ዓ.ም ጀምሮ በዋናነት የአዲስ አበባን ሕዝብ ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ጥያቄ እስከ ክልል መሆን እንቅስቃሴ ሲራምድ መቆየቱን አስታውቋል፡፡
በአዲስ አበባ ውስጥ ዘላቂ ሰላምና ዋስትና ያለው ዴሞክራሲ እንዲሰፍን፤ በፖለቲካው በኢኮኖሚውና ማህበራዊው ዘርፍ እድገቷ እንዲፋጠን፤ የተወላጁና ነዋሪው የእኩልነት መብታቸው በእኩል እንዲጠበቅ አዲስ አበባ ራሷን የቻለች ክልል መሆን አለባት ብሏል - ድርጅቱ፡፡
ይሄንኑ ጥያቄውንም ለብሄራዊ ምርጫ ቦርድ በደብዳቤ ማቅረቡን ገልጿል፡፡ አዲስ አበባ የ89 ብሄር ብሄረሰቦች ክልል እንዲሁም የፌደራል መንግስቱ ርዕሰ ከተማ እንደሆነች ያወሳል፡፡
በሕዝብ ብዛትም ከሁሉም ክልሎች በ3ኛ ደረጃ መቀመጧን የገለፀው ድርጅቱ፤ ከሕዝብ ብዛቷም ሆነ ማህበራዊ መስተጋብሯ አንፃር ራሷን የቻለች ክልል መሆን ይገባታል ብሏል፡፡
አዲስ አበባ ራስ ገዝ ሆነ የራሷን ክልላዊ መንግስት እንድታቋቁም፣ የራሷን ክልል ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ የልማት ፖሊሲና ስትራቴጂ እንድትወጣ፣ የራሷን ሃብትና መሬት በራሷ እንድታስተዳድር እንዲሁም ራሷን በራሷ የማስተዳደር አላማን መሰረት ያደረገ ክልላዊ መስተዳድር እንዲዋቀርላት ድርጅቱ በደብዳቤው ጠይቋል፡፡
አዲስ አበባ የራሷን ግብር ለራሷ የምትሰብስብ፣ ፀጥታና ሰላሟን በራሷ ፀጥታ ሀይል የምትመራ፣ በፌደሬሽን ም/ቤት ውስጥ የራሷ ተወካይ ያላት እንድትሆንም የጠየቀው ፓርቲው፤ ‹‹የአዲስ አበባ ክልላዊ መንግስት››ን ማስተዳደር የሚገባው የአዲስ አበባ ተወላጅና ቀደምት ነዋሪ መሆን አለበት ይላል - በመግለጫው፡፡     

Read 11266 times