Saturday, 21 December 2019 11:57

የኤክሳይዝ ታክስ ረቂቅ አዋጅ እያወዛገበ ነው

Written by  መታሰቢያ ከሳዬ
Rate this item
(9 votes)

    በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለውይይት ቀርቦ ለገቢዎች በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴዎች የተመራው የኤክሳዝ ታክስ ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ እያወዛገበ ነው። አዋጁ በመሠረታዊ የፍጆታ ዕቃዎች ላይ ሳይቀር ከፍተኛ ተፅዕኖ የሚያሳድርና የአምራች ኩባንያዎችን ህልውና የሚፈታተን ነው ተብሏል፡፡
በአሁኑ ወቅት በሥራ ላይ የሚገኘው የኤክሳይዝ ታክስ አዋጅ 307/1995 ያሉበትን ክፍተቶች ለማሟላትና ለመንግሥትም ከፍተኛ ገቢ ለማስገኘት ያስችላል ተብሎ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለውይይት የቀረበውና ለገቢዎች በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴዎች የተመራው የማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ፤ በአገር ውስጥ በሚመረቱና ከውጪ አገር በሚገቡ የተለያዩ ምርቶች ላይ ተጨማሪ ታክስ የሚጥል ነው፡፡
በማሻሻያ ረቂቅ አዋጁ የቅንጦት ዕቃዎች ተብለው የተለዩትና ተጨማሪ የኤክሳይዝ ታክስ ከተጣለባቸው ምርቶች መካከል ዘይት፣ ስኳር፣ ጨው፣ ጣፋጭና ጨዋማ ምግቦች የአልኮል መጠጦች፣ የትምባሆ ምርቶች፣ የተሰፉ ልብሶች፣ የታሸጉና ጋዝ ያላቸው ውሃዎችን የለስላሳ መጠጦች፣ ይገኙበታል፡፡ የኤክሳይዝ ታክሱ በሕብረተሰቡ ጤናና በአካባቢ ደህንነት ላይ ችግር ያስከትላሉ በተባሉ የነዳጅ ምርቶች. ተሽከርካሪዎችና የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች እንዲሁም በመዋቢያ ቁሳቁሶች ላይ ተጥሏል፡፡
ረቂቅ የማሻሻያ አዋጁ መንግሥት ተገቢውን ታክስ እንዲሰበሰብ የሚያግዝ፣ ኮንትሮባንድና ሕገወጥ ንግድን ለመከላከል የሚያስችል እንደሆነም በዚሁ ረቂቅ አዋጁ ላይ ተገልጿል፡፡ የሕብረተሰቡን የጤና ሁኔታ የሚጎዱ፣ በማህበራዊ ሕይወት ውስጥ ችግር የሚያስከትሉና መሰረታዊ በመሆናቸው ምክንያት የገበያ ተፈላጊነታቸው የማይቀንስ ምርቶችና አገልግሎቶች ላይ ታክስ መጣል አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ረቂቅ አዋጁ መዘጋጀቱ ተጠቁሟል፡፡
በአዲሱ የኤክሳይዝ ታክስ ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ መሰረት፤ ዝቅተኛው የኤክሳይዝ ታክስ መጠን 10 ከመቶ ሲሆን ይሄ ታክስ ከሚጣልባቸው ምርቶች ውስጥ የፎቶና የቪዲዮ ካሜራዎች፣ የቲቪ መቀበያና መሰል ኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች ይገኙበታል፡፡  ትምባሆ 30 በመቶ የፕላስቲክ ከረጢት (ፌስታል) 40 በመቶ (በአንድ ኪሎ ግራም ፌስታል ላይ)፣ ስኳር 20 በመቶ፣ ሳቹሬቲድ ሰብ (ለጤና ጎጂ የሆነ ቅባትን የያዙ ዘይቶች ከ30-50 በመቶ፣ ዱቄት ለስላሳ መጠጦች፣ አልኮል አልባ የታሸጉ መጠጦች፣ ጋዝ ያላቸው የታሸጉ ውሃዎች ከ15-30 በመቶ፣ ቢራ ሙሉ በሙሉ በአገር ውስጥ በበቀለ ገብስ የተመረተ 35 ከመቶ እንዲሁም  የወይን መጠጥ ግብአቶች ከ30-40 በመቶ ኤክሳይዝ ታክስ ተጥሎባቸዋል፡፡
በኤክሳይዝ ታክስ ማሻሻያ ረቂቅ አዋጁ ላይ እንደተገለፀው ተሽከርካሪዎች እንደ አገልግሎት ዘመናቸው የሚጣልባቸው የኤክሳይዝ ታክስ መጠን የሚለያይ ሲሆን ከዜሮ ዓመት እስከ አንድ ዓመት ድረስ ያገለገሉ መኪናዎች 100 ፐርሰንት ፣ ከ7 ዓመት በላይ ያገለገሉ መኪኖች ደግሞ እስከ 500 ፐርሰንት የሚደርስ የኤክሳይዝ ታክስ ተጥሎባቸዋል፡፡
ይህም ማለት የአገልግሎት ዘመናቸው ከ2012 በፊት ባሉ መኪኖች ላይ የሚጣለው የ500 በመቶ የኤክሳይዝ ታክስ ምጣኔ የመኪኖቹን ዋጋ በአራትና በአምስት እጥፍ የሚያሳድገው ይሆናል፡፡
ፖሊስ ክበብ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ካሉ የመኪና መሸጫ ማዕከላት የአንዱ ባለቤት የሆኑት አቶ ቴዎድሮስ የማነ እንደተናገሩት ፣ በአሁኑ ወቅት ከ400 ሺ ብር ባልበለጠ ዋጋ እየተሸጡ ያሉ እንደ ቪትዝ ያሉ አነስተና መኪኖች በዚህ በአዲሱ የኤክሳይዝ ታክስ ማሻሻያ መሰረት፣ ከአንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ብር በላይ የሚሸጡ ይሆናሉ፡፡ ይህ ደግሞ የሕብረተሰቡን የመግዛት አቅም ሙሉ በሙሉ የሚገዳደር በመሆኑ እኛም ከዘርፉ ለመውጣት እንገደዳለን ብለዋል። በተሽከርካሪዎች ላይ የተጣለው የኤክሳይዝ ታክስ ያገለገሉ የእርሻ ትራክተሮችንም የሚመለከት ሲሆን እነዚህ ትራክተሮችም እስከ 400 በመቶ የሚደርስ የኤክሳይዝ ታክስ ተጥሎባቸዋል፡፡ ይህ ሁኔታም አገሪቱ ከተያያዘችውና ግብርናችንን በማዘመን በምግብ ራሳችንን የመቻል እቅድ ጋር በእጅጉ የሚቃረንና በሚገባ ታስቦበት ያልተወሰነ መሆኑን አስተያየት ሰጪዎች ይገልጻሉ፡፡
እንደ ስኳር፣ ዘይት፣ ጨውና ውሃ ባሉ መሰረታዊ የፍጆታ ዕቃዎች ላይ ሊጣል የታሰበው የኤክሳይዝ ታክስ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ የሚታየውን የኑሮ ውድነት በእጅጉ የሚያባብስና የብዙሃኑን ሕዝብ ኑሮ የሚፈታተን መሆኑን የተናገሩ አስተያየት ሰጪዎች ፣ መንግሥት የማሻሻያ አዋጁን ከማጽደቁ በፊት ቆም ብሎ ሊያስብበትና ሁኔታውን በአግባቡ ሊመረምር ይገባል ብለዋል፡፡
በቢራ ምርቶች ላይ ሊጣል የታሰበውን የ35 በመቶ የኤክሳይዝ ታክስ ኢንዱስትሪውን ሙሉ በሙሉ አደጋ ላይ የሚጥልና አገሪቱ ከዘርፉ የምታገኘውን የታክስ ገቢ የሚያሳጣ እንደሆነ የቢራ አምራች ፋብሪካዎች ማህበር ገልጻል፡፡ ከማህበሩ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው የኤክሳይዝ ታክስ አዋጁ በዘርፉ በሚያስከትለው ከፍተኛ ጫና ሳቢያ የዋጋ ጭማሪ ለማድረግ
የሚገደዱ ሲሆን ይህም የሽያጩን መጠን በእጅጉ ይቀንሰዋል፡፡ በዚህ ምክንያትም ፋብሪካዎቹ ሰራተኞቻቸውን ለመቀነስ ይገደዳሉ፡፡ ለፋብሪካዎቹ ግብአት የሚሆን የቢራ ገብስ አምራች ገበሬዎችም ምርታቸውን የሚቀበላቸው ባለመኖሩ ምክንያት ለኪሳራ ይዳረጋሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም አገሪቱ ከዘርፉ የምታገኘውን ግብር የምታጣ ሲሆን የቢራ አምራች ፋብሪካዎቹም እያደረጉ ያሉትን የማህበረሰብ ድጋፎች በእጅጉ ሊቀንሱ እንደሚገደዱ  ከቢራ አምራች ፋብሪካዎች ማህበር የተገኘው መረጃ ያመለክታል። እንኳንስ ኤክሳይዝ ታክሱ ተጨምሮበት የአልኮል መጠጦች በሚዲያዎች እንዳይተዋወቁ በመደረጉ ሳቢያ በሽያጩ ላይ ቀላል የማይባል ጉዳት መድረሱን ያመለከተው ይኸው መረጃ አዲሱ የማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ ከጸደቀ በዘርፉ ሊሰማሩ በዝግጅት ላይ ያሉትንም ሆነ አሁን በሥራ ላይ የሚገኙትን የቢራ ምርት ኢንቨስትመንቶች በእጅጉ የሚጎዳ ይሆናል ብሏል፡፡  መንግሥት ሁኔታውን በሚገባ ሊያጤነውና በአንድ ጊዜ ለመጣል ያሰበውን የኤክሳይዝ ታክስ በየአመቱ በትንሹ እየጣለ ካሰበበት ሊደርስ እንደሚችል ተጠቁሟል፡፡
አዲሱ  የኤክሳይዝ ታክስ ረቂቅ አዋጅ በአንድ ጠርሙስ ቢራ ዋጋ ላይ የዘጠኝ ብር ጭማሪ ይደረግበታል ተብሏል ፡፡
ሰዎች ከሚጠቀሙባቸው የቅንጦት ዕቃዎች ላይ ገቢ በመሰብሰብ በድህነት ላይ ለሚገኙ ዜጎች ለመደጎም እንዲያስችል ታስቦ የተጣለው የታክስ ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ ለዝርዝር እይታ ለገቢዎች በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ተመርቶ ውይይት እየተደረገበት ይገኛል፡፡

Read 13449 times