Saturday, 21 December 2019 12:10

‹‹አይሮጡም ተብሎ ፈረስና በቅሎ አይሰግሩም ተብሎ ፈረስና በቅሎ እንዲያው በጥላቻ… ትመረጥ ይሆናል ኤሊ ለኮርቻ››

Written by 
Rate this item
(14 votes)


            ከዕለታት አንድ ቀን የሰፈር ባለቅኔዎችና ገጣሚያን አንድ ድግስ ላይ ተገናኙ፡፡ ቀጥለው ሙግት ገጠሙ፡፡
የመጀመሪያው ገጣሚ፡-
‹‹እባክሽ እናቴ ራቤን ተቆጭው
አንቺን ይፈራሻል አንጉተሽ ስትሰጪው››
ሁለተኛው ገጣሚ፡-
የትልቅነት ማቆሚያው እምን ድረስ ነው?
ሦስተኛው መለሰ፡-
የእኛ ልብ የፈቀደው ድረስ ነው
አራተኛው፡-
ተነሳ ወንድሜ መንገድ እንጀምር
እኔም ቅሌን ይዤ አንተም አገልግል
የመጀመሪያው ተበለጥኩኝ በሚል ስሜታዊ ትኩሳት፡-
አስቤ ጨረስኩት የፈረሴን ጉልበት
አንድ ቀን ደስ ብሎኝ ሳልቀመጥበት  
…ሲል ግጥም አዋጣ፡፡
ተወዳጅ የሆነው ግጥም ግን ሶስተኛው ሆነ፡፡
***
ተስፋችን ወደ ላይ እንጂ ቁልቁል ለማሽቆልቆል ከቶም አይገባውም፡፡ ምነው ቢሉ ኋላ ቀና ማለት እንዳይቸግረን ነው፡፡ አንዴ ያጣነውን እድል መልሰን እንዳናጣው፣ በጥንቃቄ መጓዝ ያለብን ያለ ጥርጥር አሁን ነው፡፡ በጭራሽ ታላቅ ነን እያልን ስንኩራራ፡-
‹‹ኩራትና ትዕቢት የሞሉት አናት
ሰይፍና ጎራዴ የመቱት አንገት
አይገላገሉም እንዲህ በቀላሉ
እመሬት ላይ ወድቀው ሳይንከባለሉ››
የትውልድን ተስፋና ምኞት ቀርፀንና አሳምረን፣ መማር ላለበት ተረካቢ ትውልድ በወግ በማዕረጉ ተገቢውን ርክክብ ለማድረግ ጥኑ ጥረት ይጠይቃል፡፡ ተረካቢው ትውልድ፤ በከባድ መራሄ - ግብር ውስጥ ለመጓዝ፣ የሕብረተሰባችንን ተቋማዊ መዋቅር፣ ተገቢውን አስተውሎት ለመቸር፣ ብርቱ ጥረት መፍጠርና መታገል መጀመር ይኖርባቸዋል፡፡
አካሄዳችንን ወደ ተቋማዊ መልክ ማፅዳት ያሻናል። ተቋማዊ ዕድገት ጥናት ይፈልጋል። ጥናቱ ደግሞ አጥኚ ይሻል፡፡
‹‹ሳይማር ያስተማረንን ሕዝብ›› ተገቢውን ምስጋና እናደርግለት ዘንድ አንድም የእኛን ቅንነት ይጠይቃል፣ አንድም ቀናነታችንን ከልቡ የሚያዳምጠን ቀና ጆሮ ያስፈልጋል፡፡ በሦስተኛ ደረጃ፤ ሥራዬ ብለው በአንድን ሕብረተሰብ ንቃተ ህሊና ለማበልፀግ ጥረት በማድረግ የሚታትሩ የተባ አዕምሮ ባለቤት ለመሆን የሚጓዝ ሞቅ ያለ ሀሳብ፣ በሳል የሆነ ንባብ፣ ውይይትና ሬኮርድ ወደ ማባዛት የመሄድ ጤናማ መንገድ ላይ ያሉ አሉ፡፡
‹‹ሳይማር ያስተማረንን ሕዝብ›› የሚለው አባባል፣ አንድ ሰሞን የፋሽን ያህል የሚጠቀስበት ዘመን ነበር፡፡ ዛሬም ከልብ ካሰብንበት ‹‹ሳይማር ያስተማረንን ሕዝብ›› ማስታወስ ጥንካሬን፣ ልባዊነትን፣ የበሰለ ትምህርትን፣ ብርቱ ንቃተ ህሊና ይጠይቃል፡፡
በገጣሚና ፀሐፌ ተውኔት መንግሥቱ ለማ ‹‹የባለ ካባና ባለዳባ መስመሮች እንደምድም፡-
‹‹ቀማኛን መቀማት ከሌባ መስረቅ
ለማቅለል ከሆነ የድሆችን ጭንቅ
በኔ ቤት ፅድቅ ነው አንድ ሰው ይሙት
አንድ መቶ ሺ ሰው ሲኖር በምፅዋት
በምናውቀው ስንሰቃይ የማናውቀውንም ፈርተን
በህሊናችን ማቅማማት ወኔያችንንም ተሰልበን
የነጋ ጠባ ሕይወት የመንቀሳወስ አቅሙ
የሕሊናችን ትርጉሙ የአዕምሮ ሚዛን ህልሙ
እያደር ከህሊናችን ይደመሰሳል ትርጉሙ››     

Read 13868 times