Monday, 23 December 2019 00:00

በሙዳይ በጎ አድራጎት ድርጅት “የገና ስጦታ” የተሰኘ የስጦታና የሥዕል ኤግዚቢሽን ይከፈታል

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

 ከ600 በላይ ሕጻናትንና ከ450 በላይ እናቶችን በመደገፍና የበጎ  አድራጎት ስራዎችን በመስራት የሚታወቀው ሙዳይ በጎ አድራጎት ድርጅት ለአስር ቀናት የሚቆይ ‹‹የገና ስጦታ›› የተሰኘ የስጦታና የሥዕል አውደ ርዕይ የፊታችን አርብ ታህሳስ 17 ቀን 2012 ዓ.ም ኮተቤ ብረታ ብረት አካባቢ በሚገኘው ግቢው ከረፋዱ 4፡00 ጀምሮ ይከፍታል፡፡
እስከ ታህሳስ 27 ማለትም እስከ ገና ዋዜማ በሚቆየው በዚህ የስጦታና የስዕል ኤግዚቢሽን ሳምንት በድርጅቱ ለሚደገፉ ሕጻናትና እናቶች የሚውል ምግብ፣ የንፅህና መጠበቂያ ዕቃዎች፣ አልባሳት፣ የመማሪያ ቁሳቁሶችና ልዩ ልዩ ድጋፎችን እየያዙ ማዕከሉን እንዲጎበኙ የድርጅቱ መስራችና ዋና ሥራ አስኪያጅ ወ/ሮ ሙዳይ ምትኩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
‹‹የገና በዓል በተለየ ሁኔታ ሰዎች ስጦታ በመለዋወጥ ፍቅራቸውንና ወዳጅነታቸውን የሚገልጹበት ነው›› ያሉት ሥራ አስኪያጇ በመሆኑም ሁሉም የሕብረተሰብ ክፍል የቻለውንና የፈቀደውን ስጦታ ለተረጂዎቹ ይዞ በመምጣት ፍቅሩንና ወዳጅነቱን እንዲገልጽ፣ እግረ መንገዱንም በተለያዩ ሰዓሊያን የተሳሉና ለእይታ የሚቀርቡ ስዕሎችን እንዲጎበኙ ጥሪ አቅርበዋል፡፡  
ሙዳይ በጎ አድራጎት ድርጅት ከ1 ሺህ በላይ ሕጻናትንና እናቶችን ትምህርት በማስተማር የአልባሳትና የምግብ እንዲሁም የመኖሪያ ወጪን በመሸፈን ለበርካታ አመታት እየሰራ የሚገኝ በጎ አድራጎት ድርጅት ሲሆን፣ ከ1 ሺህ በላይ እናቶችን በሽመና፣ በሸክላ ሥራ፣ በልብስ ስፌት፣ በጫማና በጌጣ ጌጥ ስራ አሰልጥኖ ራሳቸውን እንዲችሉ አድርጓል፡፡
በመክፈቻ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ለድርጅቱ ድጋፍ ሲያደርጉ የቆዩ ሚዲያዎችና ግለሰቦች እንደሚሸለሙም ታውቋል፡፡

Read 7821 times