Saturday, 21 December 2019 12:52

“ዳማከሴ ፊዚዮቴራፒ” ምን አዲስ ነገር ይዞ መጣ?

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

   - ዘመናዊ የሕክምና መሳሪያዎችን ከባለሙያው ጋር የማስተዋወቅ ዓላማ አለኝ
         - የተኛ ታማሚን ራሱ የሚያገላብጥ ፍራሽ አለ
         - በስትሮክ ለተጠቁ ድጋፍና እርዳታ የሚሰጡ መሳሪያዎች አሉን

      አቶ ሰለሞን ተሾመ ይባላሉ፡፡ በሜዲካል ኢንጂነሪንግና በባዮ ሜዲካል ኢንጂነሪግ ከሚኒሶታ ዩኒቨርስቲ ከተመረቁ በኋላ ለረዥም ዓመታት እዚያው አሜሪካ በሙያቸው ሰርተዋል፡፡ የእናታቸውን በስትሮክ መሞት ተከትሎ ብዙ በውስጣቸው የሚብሰለሰል ነገር እንደነበረ ይናገራሉ፡፡ በተለይም በኢትዮጵያ በስትሮክ፣ በመኪና አደጋና ከእድሜ መግፋት ጋር ተያይዞ በሚመጣ ህመም የተያዙ ሰዎች የመጨረሻ የሕይወት ዘመናቸው በጣም ከባድ እንደሆነ አስታውሰዋል፡፡ ይህንንም ችግር በአቅማቸው ለመቅረፍ ነው በመሀል አራት ኪሎ “ዳማከሴ ፊዚዮቴራፒ፣ ሪሀብና ሆም ኸልዝ ኬር” የተሰኘ ማዕከል ያቋቋሙት፡፡ ለመሆኑ በማዕከሉ
ምን ምን አገልግሎቶች ይሰጣሉ? የሰውን ሕይወት ቀላል የሚያደርጉ የቴክኖሎጂ ውጤቶች እንዳሉም ይገልጻሉ፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ ከአቶ ሰለሞን ተሾመ ጋር በአዲሱ ማዕከል ዙሪያ ተከታዩን ቃለ ምልልስ አድርጋለች፡፡

           በአሜሪካ ትምህርትዎን ካጠናቀቁ በኋላ በምን ሥራ ላይ ነበር የተሰማሩት?  
ብዙውን ጊዜዬን (ወደ 15 ዓመት ገደማ) በሕክምና ዘርፍ አሳልፌያለሁ፡፡ ስራዬ የሕክምና መሳሪያዎችን (Medical Divices) በማጥናት ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ አሜሪካ ውስጥ “South West Medical Equipments” የሚባል የራሴ ኩባንያ አለኝ፡፡ ኩባንያው በተለይ በሕክምና መሳሪያዎች ላይ ብዙ እንዳጠናና የበለጠ እውቀት እንዳገኝ እድል ሰጥቶኛል፡፡ አሜሪካን አገር ለሚገኙ ሆስፒታሎችና ክሊኒኮች ማንኛውንም የሕክምና መሳሪያ እናቀርባለን፡፡ በዚሁ ስራ ምክንያት ቻይናን ጨምሮ በርካታ የዓለም አገራት ተጉዣለሁ፤ ያልረገጥኩት አገር የለም፡፡
በአዲስ አበባ በቅርቡ የከፈቱት “ዳማከሴ ፊዚዮ ቴራፒና ሪሐብ ሴንተር” ምን አገልግሎት ይሰጣል?
በአገራችን ውስጥ በሕክምናውም ሆነ በባለሙያው ላይ ያለውን ክፍተት አውቅ ነበር፡፡ በዓለም ላይ ያለው የሕክምና ቴክኖሎጂ የሰውን ልጅ የሕይወት ደረጃ የሚያሻሽል፣ ብዙ ትልልቅ ሳይሆኑ ትንንሽ የሕክምና መሳሪያዎችን ፈጥሯል:: እዚህ አገር ላይ ደግሞ ያ የሕክምና መሳሪያና የጤና ባለሙያው በአግባቡ እንደማይተዋወቁ ብዙ ጊዜ እገነዘብ ነበር፡፡ ራሴንም ‹‹ለምን?›› እያልኩ እጠይቅ ነበር፡፡ ምክንያቱም በዚህ ዘርፍ ላይ ብዙ ጊዜዬን ስላጠፋሁበት፣ ‹‹አገሬ ላይ ይህ ቢኖር›› እያልኩ እቆጫለሁ፡፡ ለምን ካልሽኝ… እነዚህ የህክምና እቃዎች እዚህ ቢኖሩ፣ የሰውም ሕይወት ይሻሻላል፤ ሕክምናውንም በእጅጉ ያግዘዋል፡፡
እንዳስተዋልኩት፣ የዚህ አገር የባዮ ሜዲካል ኢንጂነሮች፤ የሕክምና መሳሪያውያን መጠገን እንጂ የሜዲካል እቃዎች ላይ አይሰሩም:: በሌላው ዓለም የባዮ ሜዲካል ኢንጂነሮች በሕክምና እቃዎች ላይ ጥናትና ምርምር በማድረግ፣ የህክምና እቃዎችን የማሻሻልና አዳዲስ ነገር የመፍጠር ስራ ላይ ነው የሚጠመዱት፡፡ እዚህ በተገላቢጦሽ ነው የሚሰራው፡፡ ይሄ መለወጥ አለበት፡፡ የሕክምና መሳሪያዎችና ባለሙያዎች በደንብ እንዲተዋወቁ ማድረግ ነው አላማዬ:: ማዕከሉን የከፈትኩበት አንዱ ምክንያቴ ይሄ ነው፡፡ ሁለተኛው፤ እናቴ በስትሮክ ምክንያት ነው የሞተችው፡፡ እናቴ በሞተች በሁለተኛው ዓመት አባቴ ሞተ፡፡ በዚያን ጊዜ የሚሰጠው ፊዚዮቴራፒ ብቃት እንደሌለው ተመልክቻለሁ:: ሌላው፤ የሰውን ሕይወት በህክምና ማሻሻልና ጥራት ያለው አገልግሎት አልነበረም፡፡ በእርግጥ እናቴ በታመመች ጊዜ 24 ሰዓት የሚጠብቋት፣ የቤት ለቤት እንክብካቤ የሚሰጧት… ባለሙያዎች ነበሩ፡፡ ነገር ግን እኔ አሜሪካ ደርሼ እስከመለስ ድረስ እናቴ ሳትገላበጥ እየዋለች፤ የሰውነቷ ቁስለት ደረጃ አራት የሚባለው ላይ ደርሶ ነበር። (ወደ መበስበስ ደረጃ የተቃረበ ልትይው ትችያለሽ፡፡) አንድ ሰው ታሞ ሲተኛ፣ የደም ዝውውር አይኖርም፤ ደም ይረጋል። ደም ሲረጋ ደግሞ ደሙ በረጋበት አካባቢ ቁስል ይፈጠራል። ያ ቁስል ቀስ በቀስ እያደገ አጥንት ድረስ ይደርሳል፡፡ ይሄ ሲሆን ደረጃ አራት ላይ ደረሰ ማለት ነው፡፡ እንግዲህ ነርሶች አጠገቧ ነበሩ፡፡ እሷን ለማገዝና ለመርዳት ነው የተቀመጡት፤ ግን አልረዷትም፡፡ ያልረዷት ደግሞ ሆን ብለው መርዳት ሳይፈልጉ ቀርተው አይደለም፡፡ ከእውቀትና ልምድ ማነስ ነው፡፡
ነርሶቹ ምን አይነት እርዳታና ድጋፍ ማድረግ ነበረባቸው?
ደም እንዳይረጋና ቁስል እንዳይፈጠር፤ በራሱ መንቀሳቀስ የማይችልን ሰው፣ ቶሎ ቶሎ ማገላበጥና ወዳልተኛበት ጎን ማዞር እንዲሁም የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን መፍጠር የግድ ያስፈልጋል። ነርሶቹ ይህንን የማይሰሩና የማያገላብጡ ከሆነ፣ ይህ ቁስለት እንዳይፈጠር የሚያደርግና ከተፈጠረም የሚቀንስ የሕክምና መሳሪያ አለ፡፡ እንደ ፍራሽ አይነት ሆኖ፣ ታማሚውን ራሱ የሚያገላብጥ ነው፡፡ አሁን ያ እቃ የታማሚውንም የአስታማሚውንም ሕይወት ያቀላል፤ ያሻሽላልም፡፡ ይሄ እቃ በሆስፒታል ደረጃ እንኳን ባይሆን ቤት ለቤት ቢኖር በጣም መልካም ነው፡፡ እቃዎቹ ብዙም ውድ አይደሉም እኮ! እውነት ለመናገር፣ ከታሰበበት በአገር ውስጥም መመረት ይችላሉ:: በአብዛኛው የስትሮክ ህመምተኞችን የሚገድላቸው ቁስል (ኢንፌክሽን) ነው፡፡
“ዳማከሴ” ለዚህ ምን መፍትሄ ይዞ መጣ?
ዳማከሴ ሁለት ዘርፎች አሉት፡፡ አንዱ “ዳማከሴ ፊዚዮቴራፒና ሪሀብ ሴንተር” ነው፡፡ ሁለተኛው፤ “ዳማ ከሴ ሆም ኬር” ወይም የቤት ለቤት እንክብካቤ አገልግሎት የሚሰጥ ነው፡፡ በማዕከላችን ያሉት የፊዚዮቴራፒ ባለሙያዎች፤ እስከ 17 ዓመት ልምድ ያላቸው፣ በዘርፉ በቂ እውቀት ያካበቱና በተለያየ ስልጠና ራሳቸውን ያበቁ ናቸው፡፡ ደረጃ በደረጃ ሂደቱን ጠብቀው ይሰራሉ፤ መሻሻሎችንና ለውጦችን እያዩ እንጂ፤ የመጣውን ሁሉ ዘለው ማሽን ውስጥ የሚከትቱም አይደሉም፡፡ አንድ የስትሮክ ተጠቂ፤ ሕክምናው ከየት ይጀምራል? በመሃል ምን ላይ ይደርሳል? መጨረሻውስ ምንድን ነው? የሚለውን በደረጃ አንድ… ሁለትና ሦስት እየሰሩ ነው የሚሄዱት፡፡ አንድ ሰው በስትሮክ ተጠቅቶ ሲመጣ፣ ከስትሮኩ ጎን ለጎን፣ ምን ተጓዳኝ ችግር አለ? የሚለውንም በደንብ ያያሉ፡፡ በጣም በጥንቃቄና ሙያን ማዕከል አድርገው የሰውን ልጅ ሕይወት ለማሻሻል የሚተጉ ናቸው፡፡
ተዘዋውሬ እንደጎበኘሁት፤ በርካታ አይነትና መጠን ያላቸው የሕክምና እቃዎች አሉ፡፡ እስቲ ጥቂቶችን ያብራሩልኝ?
እቃዎቹ እጅግ በርካታ ናቸው፡፡ ጥቅማቸውም በዚያው ልክ የተለያየ ነው። ለምሳሌ የወገቡ አጥንት ተጎድቶ የታከመን ሰው፤ አጥንት የሚያዳብርና ወገብ ላይ የሚታሰር፣ እዚህ አንድ እግሩ የተሰበረ ሰው በጀሶ ነው የሚታሰረው፡፡ ጀሶን የሚተኩ ጫማ የሚመስሉ ዘመናዊ መሳሪያዎች አሉን፡፡ አንድ ሰው በስትሮክ ሲጠቃ፣ በግራው በኩል ከሆነ የታመመው በቀኝ በኩል ያለው ሰውነቱ አይታዘዝም ወይም በቀኙ ከተመታ ግራው የሰውነቱ ክፍል አይታዘዝም፤ የማይታዘዘው እጅ ከእርምጃ መለማመጃው ጋር ይታሰርና፣ የሚታዘዘው እጁ ብረቱን ይዞ ያለ ሰው እርዳታ መራመድ የሚያለማምድም አሉ፡፡ የአንገት የትከሻ፣ የወገብ፣ የእጅ፣ የጎድን አጥንት… ብቻ ብዙ የአካላችንን ጉዳቶች በመደገፍ፤ ሕይወታችንን ከእርዳታ ጠባቂነት የሚያወጡ፣ ነገር ግን ትንንሽ መጠን ያላቸው መሳሪያዎች አሉ፡፡ እያየሻቸው ነው፣ ገና ከውጭም እየገቡ የሚገኙ አሉ፡፡
ማዕከላችን በአንድ ጊዜ አምስት ሰዎችን ማስተናገድ ወይም በቀን ከ30-40 ሰዎችን ይችላል። የፊዚዮቴራፒ፣ የሥነ ልቦና ግንባታ፣ የአመጋገብ ግንዛቤ፣ መሳሪያዎቹን ተጠቅመው ራሳቸውን በራሳቸው መርዳት የሚችሉበት ስልጠናና ልምምድ ያደርጋሉ - በማዕከሉ፡፡ የቤት ለቤት ድጋፍና አገልግሎት ለሚፈልጉም፤ የሰለጠኑ ባለሞያዎቻችን ሙያዊ አገልግሎት ይሰጣሉ። የታማሚ ቤተሰቦችም ስራቸው ሳይስተጓጎልና ሳይጨነቁ ሀሳባቸውን ባለሞያዎቻችን ላይ ጥለው፣ ያለ ስጋት ስራቸውን ያከናውናሉ፡፡
ማዕከሉ ገንዘብ ላላቸውና አገልግሎቱን ለሚፈልጉ ትልቅ አማራጭ ይመስለኛል፡፡ ግን ከፍለው መታከም የማይችሉ ደግሞ አሉ…
እኛ ይህንን ማዕከል ያቋቋምነው ትርፍ ለመሰብሰብ አይደለም፡፡ ነገር ግን በተለያየ ችግር ውስጥ ያሉ ህሙማን በተለይ በመጨረሻ ዘመናቸው ከህመም ስቃይ፣ ከስነ ልቦና ቀውስ ወጥተው የተሻለ ሕይወት ኖሯቸው እንዲቆዩ ለማድረግ ነው፡፡ እርግጥ ነው ማዕከሉ ራሱን ማስተዳደር አለበት፡፡ ኢንቨስትመንቱም ብዙ ነው፡፡ ቢሆንም ግን ማህበራዊ ሀላፊነታችንን መወጣት ደግሞ አለብን፡፡ አንደኛው፤ ይህንን ማዕከል መክፈትና ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት በራሱ ትልቅ ሃላፊነት ነው፡፡ ከዚያ ውጭ “የወደቁትን አንሱ” የተሰኘ የአረጋዊያን መርጃ ማዕከል አለ፡፡ እዚያ ማዕከል ውስጥ ብዙ ለአገር ውለታ የዋሉ ህሙማን አሉ - እርዳታና የማዕከላችን ህክምና የሚያስፈልጋቸው፡፡ ከማዕከሉ ሀላፊዎች ጋር ተነጋግረናል፡፡ እነሱ የሚልኩልንን ወይም መጥታችሁ አክሙልን ሲሉ፣ ያለ ክፍያ በነፃ እናገለግላለን፡፡ አቅማችን እያደገ ሲሄድ፣ ድጋፋችን ይቀጥላል፡፡ እነዚህን ሰዎች መርዳት፣ ስነ ልቦናቸውን መደገፍ፣ በሕክምና መሳሪያዎች ችግራቸውን ማቅለልና ማማከር ትልቅ ነገር ነው፡፡

Read 2438 times