Print this page
Saturday, 21 December 2019 13:02

የፖለቲካ ፓርቲዎችና መጪው ምርጫ - (ስጋቶችና ተስፋዎቹ)

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

   ኢንተርናሽናል ክራይሲስ ግሩፕ ከሰሞኑ በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ሰፋ ያለ የቅድመ ግጭት ማስጠንቀቂያን ያካተተ የጥናት ሪፖርት ከሰሞኑ ይፋ አድርጓል፡፡
ተቋሙ በኢትዮጵያ ያለው ወቅታዊ ሁኔታ ግጭቶች ያልተለዩት መሆኑን ገልጿል፡፡ እነዚህ የግጭት ሁኔታዎች በአስተማማኝ መልኩ እልባት ሳያገኙ ከቀሩ፣ ቀጣዩን ምርጫ ማካሄድ የከፋ ውጤት እንደሚያስከትል ሪፖርቱ ይተነብያል፡፡ በአመዛኙ ለምርጫ የሚቀርቡ እጩዎች የብሄር ቡድን ድምጽ ለማግኘት ፉክክር ስለሚያደርጉ ግጭቶች ሊከሰቱ ይችላሉ ያለው ተቋም ምርጫው መራዘም እንዳለበትም ሀሳብ አቅርቧል፡፡ አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች የዚህን ተቋም ስጋት ይጋራሉ፡፡ ነገር ግን መንግስት ምርጫ ለማካሄድ ከወሰነ እኛ ወደ ኋላ መቅረት ስለማንፈልግ እንሳተፋለን ይላሉ - ፓርቲዎቹ፡፡
በስድስት ወራት ጊዜ ውስጥ እንደሚካሄድ የሚጠበቀው ምርጫ፤ ለፖለቲካ ፓርቲዎች ብቻ ሳይሆን ለሌላውም ወገን ስጋትና ፈተና መደቀኑን መካድ አይቻልም፡፡ ለመሆኑ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ዘንድሮ ስለሚካሄደው ምርጫ ምን ያስባሉ? ከጅምሩ እስከ መቋጫው በሰላምና በሰለጠነ መንገድ ይካሄድ ይሆን? ምርጫውን ነፃና ፍትሃዊ እንዲሁም ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን የምናዳብርበት አጋጣሚ አድርጎ ለመጠቀም ከማን ምን ይጠበቃል? የአዲስ አድማሱ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ፤ በምርጫው ላይ ብቻ ትኩረት አድርጎ የሦስት ተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችን አነጋግሯል፡፡

                ‹‹ከምርጫው በፊት የአገሪቱ ሰላም መጠበቅ አለበት››
                     ዶ/ር ዘለቀ ረዲ (የሕብር ኢትዮጵያ ሕዝብ ግንኙነት ሃላፊ)


           ጥቂት ወራት የቀረው የዘንድሮ አገራዊ ምርጫ፣ በጊዜው የሚካሄድ ይመስልዎታል?
የኛ ፓርቲ በዚህ ላይ ሰፊ ግምገማ አድርጓል። በጎን ለምርጫው እየተዘጋጀን ቢሆንም፣ ጥሩ ምርጫ ማካሄድ የሚያስችል ነባራዊ ሁኔታ አልተፈጠረም፡፡ አንደኛ፤ በየቦታው  ያሉ  የጎበዝ አለቆች፣ ራሱ ገዥው ፓርቲ ተንቀሳቅሶ ሀሳቡን መግለጽ የማይችልበት ደረጃ አድርሰውታል፡፡ ከዚህ አንጻር ለገዥው ፓርቲ ራሱ ፈተና ነው:: ለምሳሌ፡- አንድ የገዥው ፓርቲ ተወካይ፤ በአሁኑ ወቅት ምዕራብ ወለጋ በሚገኝ አንድ ወረዳ ላይ ተንቀሳቅሶ፣ የምረጡኝ ቅስቀሳ ማድረግ አይችልም፡፡ ሁለተኛ ደግሞ በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች፤ ኦሮሚያ ክልል ወይም መቀሌ ሄደው ለመቀስቀስ ይቸገራሉ:: ሌላውም እንደዚያው፡፡ አሁን በአንጻራዊነት መንቀሳቀስ ይቻላል ተብሎ የሚታሰበው፣ አፋር፣ ሶማሌ ቤኒሻንጉል… ምናልባት ጋምቤላ  ነው፡፡ ከዚህ ውጪ ያሉት አካባቢዎች አስቸጋሪ ናቸው፡፡ ምርጫ ቦርድ፣ ሕግ ማዘጋጀትና ለምርጫው ሌሎች መሰናዳዎች ከማተኮር ያለፈ፣ የፖለቲካ ሜዳው ተስተካክሏል አልተስተካከለም የሚለው ላይመለከተው ወይም ትኩረት ላይደረግበት ይችላል፡፡ ነገር ግን ዋናው የፓርቲዎች ተግባር፤ በየቦታው በነፃነት ተንቀሳቅሶ፣ ሀሳባቸውን ለሕዝብ መንገር ነው:: ይሄን ማድረግ የሚቻልበት ነባራዊ ሁኔታ እንዳልተፈጠረ ግን የኛ ፓርቲ ገምግሟል፡፡
በምርጫ ቦርድ በኩል ያለው አደረጃጀትና የምርጫ ዝግጅት ምን ይመስላል?
ምርጫ ቦርድ ምናልባት በማዕከል ደረጃ ተደራጅቶ ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን በክልሎች ያለው ነገር ምን ያህል ነው? ብዙ ጊዜ ቦርዱ እንደ ጥሩ ጥንካሬ የሚገልፀው፣ የሲዳማ ሕዝበ ውሳኔን ማስፈጸሙን ነው፡፡ ይሄ ትክክል አይደለም፡፡ አንደኛ፤ ሕዝበ ውሳኔው ሂደቱም ትክክል አልነበረም፡፡ ‹‹ሲዳማ ክልል ይሁን›› የሚለው በበላይነት ተይዞ፣ ‹‹ሲዳማ ክልል ባትሆን ይሻላል›› የሚለው አካል ጫና ተደርጎበት የተካሄደ ምርጫ ነው፡፡ የምርጫ ታዛቢዎችም ሂደቱን በስላቅ ነው ያዩት፡፡ ምርጫው ሳይካሄድ በፊትም ውጤቱ ይታወቅ ነበር ማለት ይቻላል። ከዚህ አንፃር ይሄ ለምርጫ ቦርድ የዝግጅት ጥንካሬ ጥሩ ምሳሌ አይሆንም፡፡ ስለዚህ ገና ብዙ ይቀረዋል ብለን እናምናለን፡፡
ከምርጫው ጋር በተገናኘ ዋናው ስጋታችሁ ምንድን ነው?
አንደኛው ስጋታችን የሰላም ጉዳይ ነው፡፡ ለምሳሌ ምርጫ ማለት አማራጭ ሀሳብ ማቅረብ ነው፡፡ ሀሳቡን ለገበያ አቅርቦ የመወዳደር ጉዳይ ነው፡፡ ይህ እውነት ባለበት ሁኔታ ግን ለምሳሌ በትግራይ መቀሌ ላይ በመሸጉ የህወኃት ባለሥልጣናት፣ የትግራይ ሕዝብ ታፍኖ ነው ያለው፡፡ በዚህ ሁኔታ የትግራይ ሕዝብ ሌላ አማራጭ ሳይቀርብለት፣ ምን አይነት ምርጫ ነው የሚኖረው? ሌላው በምዕራብ ኦሮሚያ አካባቢ መንግስት የሚልካቸው ሰዎች እንኳ ሳይቀሩ የሚገደሉበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ እዚያ አካባቢ ምርጫ እንዴት ነው የሚሆነው? በምርጫ ወቅት የአንዱ ፓርቲ አባል ቢገደል፣ ደጋፊዎች ወደ ብጥብጥ ሊገቡ ይችላሉ፤ ስለዚህ የሰላም መታጣቱ ብጥብጥን የበለጠ ሊቀሰቅስ ይችላል የሚለው ነው ዋናው ስጋታችን፡፡ ከዚህ አንፃር፤ በመጀመሪያ ሰላምን ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡ ይሄ የሚሆነው ደግሞ የትግራይ፣ የኦሮሚያ፣ የአማራ፣ የደቡብም፣ የሶማሌ… የሁሉም… የፖለቲካ ልሂቅ የሰከነ ውይይት ሲያደርጉ ነው አሁን ፉክክር እየተደረገ ያለው ‹‹የኔ ሀሳብ ይበልጣል›› በሚል ሳይሆን ‹‹እኔ ነኝ የምበልጠው›› በሚሉ ግለሰቦች ነው፡፡ ማንነታቸውን ለማሳየት ለውድድር እየቀረቡ ያሉት፡፡ ስለዚህ ይሄን የግለሰብን ውድድር፣ ወደ ሀሳብ ፉክክር ለማምጣት ተቀምጦ መነጋገር ያስፈልጋል፡፡ በዚህ መንገድ ብሄራዊ እርቅና መግባባት ከመጣ ብቻ ነው፣ በሃሳብ የበላይነትን ይዞ ወደ ውድድር መግባት የሚቻለው፡፡ ስለዚህ ውይይት፣ እርቅ፣ ብሄራዊ መግባባት መቅደም አለበት፡፡ ሰላም የሚመጣውም በዚህ መንገድ ነው፡፡
ምርጫ ቦርድ ምርጫው በእርግጠኛነት እንደሚካሄድ ገልጿል፡፡  በእናንተ በኩል ዝግጅት እያደረጋችሁ ነው?    
የቦርዱ ሰብሳቢ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ፣ እርግጥ ነው ምርጫው ይካሄዳል ብለዋል፡፡ ይሄንን የቢሮአቸውን ዝግጅት ነው እንጂ መሬት ላይ ማውረድ እችላለሁ ያሉ አይመስለኝም:: ያንን ካሉ ስህተት ነው። ምክንያቱም ቢሮ ያለውና መሬት ያለው ነገር ይለያያል፡፡ እሳቸው ‹‹ዝግጅቴን እጨርሳለ፤ ታዛቢዎቼን አዘጋጃለሁ›› ያሉ ነው የሚመስለኝ፡፡ በኛ በኩል  በአገሪቱ ውስጥ በተቻለን አቅም ለመወዳደር ዝግጅት እያደረግን ነው፡፡ ትልቁ ችግር የሆነብን የሚዲያ ሽፋን አለማግኘት ነው፡፡ መግለጫችንን እንኳ በሥነ ሥርዓቱ የሚያስተናግድ ሚዲያ አጥተናል፡፡ ለምሳሌ ፋና ቴሌቪዥንና ኢቲቪ፤ ለአንዳንድ ፓርቲዎችን የግላቸው እስኪመስል ድረስ ሽፋን እንደልባቸው ይሰጣሉ፡፡ ለኛ ግን አይሰጡንም፡፡ ለዚያ ነው ያልተዘጋጀን የሚመስለው… እንጂ በስፋት ተዘጋጅተናል:: እንደውም በቅርቡ በወላይታና በጎፋ ሳውላ ሕዝባዊ ውይይት እናደርጋለን፡፡ በባህርዳር በቅርቡ ሰፊ ጉባኤ አድርገን ነው የመጣነው:: ሚዲያዎች ግን ‹‹ብልጽግናን›› በሚዘግቡበት ደረጃ ለእኛ ሽፋን አይሰጡንም፡፡ እንደውም ትልቅ አፈና ነው እያደረጉብን ያለው። እኛ ግን በአዲስ አበባ፣ በኦሮሚያ፣ አማራ፣ ደቡብ፣ ቤንሻንጉልና በሌሎችም አካባቢዎች ሰፊ እንቅስቃሴ እያደረግን ነው፡፡
ከመጪው ምርጫ ምን ትጠብቃላችሁ?
ከዚህ በፊት ከነበሩ ምርጫዎች የተለየ ይሆናል። ከቀድሞዎቹ ምርጫዎች በቁጥር የላቁ ወደ ፓርላማ ይገባሉ የሚል እምነት አለኝ:: ምናልባት አገሪቱ ወደ ዴሞክራሲ ልትሸጋገር ትችላለች፡፡ ጠ/ሚኒስትሩ የያዙት መንገድ ጥሩ ነው። ይሄን ማበረታታት፤ ማገዝ ያስፈልጋል፡፡ በዚያው ልክ ጠ/ሚኒስትሩም የሚታገዙበትን መንገድ መክፈት ይገባቸዋል፡፡ ለምሳሌ፡- እኛ እርቅ… ብሔራዊ መግባባት መኖር አለበት እንላለን፡፡ ይሄን ሊሰሙን ይገባል፡፡ ይሄ ከሆነ ቀጣዩ ምርጫ አንድ ደረጃ ወደ ዴሞክራሲ የምንራመድበት ይሆናል ብዬ አስባለሁ፡፡
ጠ/ሚኒስትሩ የነፃና ፍትሃዊ ምርጫ በአካሂደን፣ ውጤቱን በጸጋ ለመቀበል ዝግጁ ነን ብለዋል፡፡ በእናንተ በኩልስ?
በፀጋ መቀበልና አለመቀበል የሚመጣው፣ በአሰራሩ ፍትሃዊነት ልክ ነው፡፡ አሰራሩ… አካሄዱ ፍትሃዊ ሊሆን ይገባል፡፡ በትክክል የሕዝብ ፍርድን ሁሉም ካከበረ፣ ማን ምን እንዳገኘ ሕዝቡ ራሱ ስለሚያውቅ፣ በጸጋ መቀበሉ ግዴታ ነው፡፡ እኔ እንኳ አልቀበልም ብል፣ ሕዝቡ  ‹‹ዞር በል ከዚህ ነው›› የሚለኝ፡፡ ስለዚህ ሂደቱን… አሰራሩን ነው ቆንጆ ማድረግ ነው፡፡ ሌላኛው ምናልባት ጠ/ሚኒስትሩ አገሪቱንና ሕዝቡን ለፍትሃዊ ምርጫ ሳያዘጋጁ፣ በኦሮሚያ በኦነግ ቢሸነፉ፣ በአማራ በሌላ ድርጅት ቢሸነፉ፣ በትግራይ በሕወኃት አፈና ቢሸነፉና እሳቸው ሥልጣን ቢለቁ፣ አገሪቱ ምን ውስጥ ነው የምትገባው የሚለውንም ማሰብ ይኖርብናል፡፡ በተረፈ ሕዝብ ሃሳባችንን ሳይገዛ ቀርቶ ብነሸነፍ፣ አመስግነን ለቀጣዩ ምርጫ የተለየ ሃሳብ ይዘን እንቀርባለን እንጂ ‹‹ለምን አልተመረጥንም›› ብለን አምባጓሮ አንፈጥርም፡፡

_____________________


                   ‹‹ለዴሞክራሲ ግንባታ መሰረት የሚጥል ምርጫ ነው መካሄድ ያለበት››
                           የሸዋስ አሰፋ (የኢዜማ ሊቀ መንበር)


            ጥቂት ወራት የቀረው የዘንድሮ ምርጫ በጊዜው የሚካሄድ ይመስልዎታል?  
ዋናው ጉዳይ፤ ይሄን ምርጫ ከባለፈው ምርጫ የተሻለ ለማድረግ የተዘጋጁ ተቋማት አሉን ወይ? ከሚለው ነው፡፡ ምናልባት ከዚህ በመለስ የመንግስትም፣ የሕዝብም የሌሎች ባለድርሻዎችም ሃላፊነት የሚሆነው፣ አገሪቱ ሰላምና መረጋጋት እንዲኖራት በማድረግ ረገድ ነው፡፡ በኛ ግምገማ፤ ይሄን ሁሉ ለውጥ ያመጣው፣ ከዚህ በፊት ሲደረጉ የነበሩ ምርጫዎች የይስሙላ መሆንና ከንጉሡም ከደርግም የተለየ አለመሆን ነው፡፡ እንደውም እየተባባሰ መጥቶ፣ በአንድ ፓርቲ መቶ በመቶ ፓርላማ የሚያዝበት ሁኔታ ላይ ስለተደረሰ ነው፣ በአገሪቱ ንቅናቄ ፈጥሮ፣ ሚኒስትሮችም ጠ/ሚኒስትሩም የተቀየሩት፡፡ ውጭ ሆነው ሲታገሉ የነበሩትም ወደ አገር ውስጥ የገቡት፣ ገዥው ፓርቲና አጋሮቹም ወደ ውህደት የመጡት በዚያ ምክንያት ነው፡፡ ይሄ ሁሉ የሕዝቡ ትግል ውጤት ነው፡፡ ስለዚህ በኛ እምነት፤ ይሄን ሁሉ ወደ ውጤት የሚያመጣ ምርጫ ነው የሚያስፈልገው። ያለፉትን  50ና ከዚያ በላይ አመታት፣ የሕዝብ ትግል፣ ለውጤት የሚያበቃ ምርጫ ነው መካሄድ ያለበት፡፡ ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ጥሩ ስረ መሠረት የሚጥል ምርጫ ነው መካሄድ ያለበት ብለን እናምናለን፡፡ ስለዚህ አሁን የሚታየው የሰላምና መረጋጋት ማጣት መስተካከል መቻል አለበት:: ይሄ ከተስተካከለ ምርጫውን ማካሄድ ብዙም አስቸጋሪ አይሆንም፡፡
በምርጫ ቦርድ በኩል ያለው ዝግጁነትስ እንዴት ትገመግሙታላችሁ?
የተቋማት ግንባታ ለምርጫው ወሳኝ ነው የሚለው ትልቅ እምነታችን ነው፡፡ ምርጫ ቦርድ ላይ ጥሩ ለውጦች ተደርገዋል የሰው ለውጥ ተደርጓል፤ የመዋቅር ለውጥ ተደርጓል፤ የሕግ ማዕቀፎች ተበጅተዋል፡፡ ግን ያንን ታች ድረስ ለማወረድ መሰራት አለበት፡፡ እርግጥ ነው ያንን ወደታች በጥሩ ሁኔታ ለማውረድ ጊዜ ይወስዳል ምናልባት አመታትንም ሊጠይቅ ይችላል፡፡ አሁን ባለው ግን ምርጫ ቦርድ በጥሩ ሁኔታ እየተዘጋጀ ያለ ይመስለኛል። ምርጫ ቦርድ በትክክል መዋቅሩ እስከታች ወረዳ ደረስ መዘርጋት ወሳኝ ነው፡፡ የተቋማት ጉዳይ ከተነሳ ሌላው ወሳኙ የፍትህ ተቋማት ገለልተኝነትና ጥንካሬ ነው:: ፍ/ቤቶች ወሳኝ ናቸው ሚዲያዎችም ወሳኝ ናቸው፡፡ አሁን እንደምናየው ከሆነ በሚዲያዎች በኩል በነፃነትና በልቅነት መካከል ድንበር ጠፍቷ የመንግስትን ሃላፊዎች መተቸትም ማዋረድም ይችላል በሚዲያ አገርን ማዋረድ ግን እጅግ ነውር ነው፡፡ ሕገወጥ ነው፡፡ የአገር ክህደትም ነው፡፡ ስለዚህ እነዚህን መስመር ማስያዝ ያስፈልጋል። የፍትህ፣ የጸጥታ፣ የሚዲያ ተቋማት ገለልተኝነት በእጅጉ ወሳኝ ነው፡፡
በዚህ ምርጫ ዋነኛ ስጋታችሁ ምንድን ነው?
በእርግጥ ነገሮች እየበረዱ ማን ምን መሆኑ እየታየ እየሄደ ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብም የሚታዘበውን እየታዘበ ዝርዝሮቹን እየቀነሰ ይሄዳል። በመጀመሪያ ለውጡ ዘገየ የሚሉ በዚያው ልክ ደግሞ የእነሱን ድርሻ የረሱ በአብዛኛው ግን ጥቅማቸው የቀረባቸውና ከሥልጣን አካባቢ የተባረሩ ሰዎች ችግር ይፈጥራሉ፡፡ ስለዚህ የመጀመሪያው ስጋት በእነዚህ አካላት የሚፈጠር የሰላም መደፍረስ ነው። የሰላምና አለመረጋጋት አለመኖር ደግሞ ድህነትና አለመማር ላይ ታክሎ ባለፈው በተዘራው ዘረኝነት ላይ ሲቆም ነገሩ የበለጠ የከፋ ይሆናል፡፡ የመጀመሪያው ስጋታችን ከዚህ ሰላምና መረጋጋት አለመኖር ጋር በተያያዘ ነው፡፡ ሁለተኛው ስጋታችን የተቋማት ገና በቅጡ አለመጠናከር ጉዳይ ነው፡፡ ተቋማት በእርግጥ በልምድ በሂደት በስራ እየተፈተኑ ነው የሚሄዱት፡፡ ያን ግን ማፋጠን ያስፈልጋል:: ሌላው ብሄርተኛ የሆኑ ድርጅቶች ገና ከወዲሁ አሸንፈናል በሚል ስሜት የአሸናፊነት ስሜት ይሰማቸዋል። የምርጫው ውጤት ግን ሌላ ሊሆን ይችላል፡፡ ምክንያቱም ምርጫው በፌስቡክ የሚመዘን አይደለም፡፡ ስለዚህ እዚህ ሌላ እዚያ ሌላ ሲሆንባቸው ባለመቀበል ብዙ መፍጨርጨር ሊኖር ይችላል፡፡
ምርጫው መካሄዱ አይቀርም ተብሏል በእናንት በኩል ለዚህ ምርጫ ዝግጅታችሁ አጠር ብሎ ሲገለፅ ምን ይመስላል?
እኛ በመጀመሪያ ለምርጫው በቂ ሁኔታ የለም ለሌላ ጊዜ ቢተላለፍ የሚል አመለካከት ነበረን፡፡ በዘንድሮ የፓርላማ መክፈቻ ላይ ንግግራቸውን ያቀረቡት ፕ/ር ሳህለ ወርቅ ዘውዴ በአንጻሩ ምርጫው ይካሄዳል የሚል አቋም ነው የገለፁት፡፡ ስለዚህ ምርጫው መካሄዱ የማይቀር ከሆነ በሚል  በከፍተኛ ሁኔታ ነው እየተዘጋጀን ያለነው፡፡ ድርጅታችን ተዋህዶ ከወጣ በኋላ በፋይናንስ እንዲደረጅ በአገር ውስጥም በውጪም ሰፋፊ እንቅስቃሴዎች አድርገናል። ከዚህም ባለፈ ደግሞ የፖሊሲ ሰነዶች ነው ያዘጋጀነው፡፡ በመጀመሪያ ዙር 18 የፖሊሲ ሰነዶች ነው ያዘጋጀነው አሁን ደግሞ ወደ 26 የፖሊሲ ሰነዶች እተዘጋጁ ነው፡፡ በ4 በመቶ የምርጫ ወረዳዎች ላይ በሚገባ ተደራጅተናል። በቀጣይም ዝግጅታችንን እናጠናክራለን፡፡ ምርጫ በፓርቲዎች አለመዘጋጀት ምክንያት መራዘም የለበትም፡፡ በተቋማት አለመዘጋጀት ነው ቢራዘምም መራዘም ያለበት፡፡ ስለዚህ ሁሉም ፓርቲ በዚህ ልክ ነው መረዳት ያለበት:: በቀጣይ ጊዜያትም ለሕዝቡ መተማመንን የሚያመጣ ዝግጅት እናደርጋለን፡፡
ጠ/ሚሩ ደጋግመው የምርጫውን ውጤት በፀጋ እንቀበላለን ብለዋል በዚህ ምን ያህል ትተማመናላችሁ ቃላቸውንስ ይጠብቁ ይሆን እናንተስ ውጤቱን በፀጋ ለመቀበል ምን ያህል ዝግጁ ናችሁ?
ኢዜማ የሕዝብን ድምፅ በማክበር በኩል አሁን ባለው ቁመናውና አስተሳሰቡ የሚታማ አይደለም፡፡ የሕዝብን ድምጽ እናከብራለን። አንዳንድ ወጣ ያሉ ቡድኖችና ሰዎች ወደ ሥርዓት ከገቡ በእርግጥ ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንሸጋገራለን የሚለው ተስፋችን ያለመልማል ማለት ነው፡፡ መንግስትም ቃሉን ይጠብቃል የሚል እምነት ነው ያለን፡፡

___________________________

                      ‹ሙሉ ለሙሉ ትኩረታችን አዲስ አበባ ላይ ይሆናል››
                             አቶ አዳነ ታደሰ (የኢዴፓ ፕሬዚዳንት)


              ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ በእርሶ ለሚመራው የኦዴፓ አመራር እውቅና መስጠቱን ገልጻችኋል በቀጣይስ ምን አይነት እንቅስቃሴ ነው የምታደርጉት?
በቀጣይ እንደ ፓርቲ የምናደርጋቸውን እንቅስቃሴዎች በተመለከተ በቅርቡ ስራ አስፈጻሚው ተሰብስቦ ውሳኔ የሚያሳልፍ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ባለፈው ሀምሌ ባደረግነው የብሄራዊ ም/ቤት ስብሰባ የተወሰኑት ውሳኔዎች ተግባራዊ ወደማድረግ እንቅስቃሴ እንገባለን፡፡ አሁን ሙሉ ለሙሉ ወደ ፖለቲካው ገብተናል፡፡ ስለዚህ በአገሪቱ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ሁሉ እንሳተፋለን፡፡ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይም መግለጫ መስጠት በሚያስፈልገን መግለጫ እንሰጣለን፡፡ ሌላው ፓርቲው ትኩረት የሚያደርገው 7ኛውን ጠቅላላ ጉባኤውን ማካሄድ ነው፡፡ ሌላውና ዋናው ፓርቲያችን ትኩረት የሚያደርገው የምርጫ ጉዳይ የማይቀር ከሆነ ሙሉ ለሙሉ ወደ ምርጫው እንቅስቃሴ እንገባለን፡፡
ወደ ምርጫው ለመግባት የሚያስችላችሁ መዋቅር አላችሁ?
አዎ! ምርጫ ቦርድም ጽ/ቤቶቻችንና ንብረታችን እንዲመለስ አዟል ስለዚህ የነበረንን መዋቅር አጠናክረን እንቀጥላለን ማለት ነው፡፡ በዚያ መዋቅር ወደ  ምርጫው እንገባለን፡፡
ምርጫ ለማካሄድ የሚያስችል ሁኔታ አለ የሚል እምነት አላች ማለት ነው?
ቀደም ብለንም በሰጠነው መግለጫ አሁን አገሪቱ ለምርጫ ዝግጁ እንዳልሆነች አሳውቀናል። በሶስት ምክንያቶች አገሪቱ ዝግጁ አይደለም፡፡ አንደኛ የሰላም እጦት ነው፡፡ ይሄ ምርጫው ላይ እንቅፋት ይሆናል የሚል ግምገማ ነው ያለን፡፡ ሁለተኛው ምርጫ ቦርድ በራሱ እንደ ተቋም በተገቢ መንገድ ዝግጁ አይደለም የሚል ግምገማ አለን፡፡ ሶስተኛ የመንግስት ሰላምና የሕግ የበላይነትን የማረጋገጥ አቅም በጣም ደካማ ነው ብለን እናስባለን። እነዚህ ሁኔታዎች ባሉበት ምርጫውን ማካሄድ ይቻላል ብለን አናምንም፡፡ ምርጫውም ቢካሄድ ከምርጫው በኋላ የምርጫውን ውጤት ተከትሎ ሰላምና መረጋጋት ይፈጠራል ብለን አናምንም፡፡ ስለዚህ ቢቻል ምርጫው የሚራዘምበት ሁኔታ ቢኖር ጥሩ ነው፡፡
ምርጫው መካሄዱ እንደማይቀር ተገልጿል… እናንተ በዚህ ምርጫ በምን መልኩ ትሳተፋላችሁ?
ምርጫው የሚካሄድ ከሆነ ኢዴፓ ባለፉት ሶስትና አራት አመታት ድርጅታዊ ስራ ሲሰራ ስላልነበረ በድርጅት መዋቅር ረገድ ደካማ ሁኔታ ውስጥ ነው ያለው ስለዚህ በዚህ ደካማ መዋቅር  ውስጥ ሆነን በመላ አገሪቱ አባላትን አሰማርተን እጩዎች አዘጋጅተን ምርጫ ውስጥ እንገባለን ብለን አጉል ጉራ መንዛት አንፈልግም፡፡ ግን በተለየ ሁኔታ አዲስ አበባ ላይ ብቻ ትኩረት አድርገን፤ ሙሉ አቅማችንን አዲ አበባ ላይ አድርገን እንሰራለን፡፡ የአዲስ አበባ ህዝብ አሁን ባለው የፖለቲካ ሁኔታ በቂ ውክልና አለው ብለን አናምንም፡፡ ስለዚህ የአዲስ አበባ ሕዝብ ወኪል ለመሆን በሙሉ አቅማችን እንሰራለን፡፡
በዚህ ምርጫ ላይ ዋነኛ ስጋታችሁ ምንድን ነው?
በዋናነት ምርጫ ለማካሄድ ጥሩ አውድ መኖር አለበት፡፡ የተሟላ ሰላም መኖር አለበት:: አሁን ያ የለም፡፡ የምርጫ ቅሰቀሳ በመላ አገሪቱ ተንቀሳቅሶ ማካሄድ የሚቻልበት ሁኔታ የለም:: ሰው ተረጋግቶ መዝኖ አመዛዝኖ ድምጹን የሚሰጥበት ምቹ ሁኔታ የለም፡፡ ስለዚህ ዋነኛ ስጋታችን የሰላምና መረጋጋት እጦት ነው፡፡ ጠ/ሚኒስትሩ በሕገ መንግስቱ የተሰጣቸውን ፓርላማውን በትኖ እስከ ስድስት ወር ወደፊት ምርጫውን መግፋት የሚችሉበትን መንገድ አስበው ከሆነ ምርጫው ይካሄዳል እየተባለ ከሆነ ጥሩ ነው ነገር ግን በቀጣዩ 6 ወር ውስጥ ብቻ በሚደረግ ዝግጅት ምርጫ ማድረግ እንዴት እንደሚቻል አይገባንም፡፡ ፓርላማውም በዚህ ጉዳይ መክሮ ውሳኔ ማሳለፍ አለበት:: መጀመሪያ መቅደም ያለበት ምርጫ ሳይሆን የአገር ህልውና ነው፡፡ ከዚህ አንጻር መንግስት የአገሪቱን ሁኔታ ገምግሞ ማራዘም ቢችል የሚለው ቀዳሚ ምርጫችን ነው፡፡
ይሄን ምርጫ ከዚህ በፊት ከነበሩት የተለየ ያደርገዋል የምትሉት ጉዳይ ይኖር ይሆን?
በብዙ መልኩ የተለየ ነው፡፡ በሽግግር ወቅት ያለ ምርጫ መሆኑ በራሱ ከባድና በጥንቃቄ ሊደረግ የሚገባው አስቸጋሪ ምርጫ ያደርገዋል:: ሁለተኛው በጦር መሳሪያ ሲታገሉ የነበሩ በሰላማዊ ምርጫ ተሳትፎ አድርገው የማያውቁ ፓርቲዎችም የሚሳተፉበት ነው። ሌላው ደግሞ የማህበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ያለበት ምርጫ ነው:: በሌላ በኩል በከፍተኛ ደረጃ ኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነት ተዳክሞ የብሄር ፖለቲካ ገኖ የወጣበት ነው፡፡ ስለዚህ ምርጫውን እንደ አገር ሲታሰብ ስኬታማ የሚያደርገው ነገር የለውም:: በምርጫው ውጤት ሳቢያ የሚከፈተው ከዚህ በፊት ከነበረው  የከፋ ነው ሊሆን የሚችለው:: ስለዚህ ይሄኛው ምርጫ በአገሪቱ ህልውና ላይ የራሱን ወሳኝ ሚና የሚጫወት ነው፡፡
ጠ/ሚሩ ምርጫውን ውጤታማ ለማድረግና ውጤቱንም በፀጋ ለመቀበል ይገልጻሉ ይሄንን እናንተ እንዴት ነው የምትረዱት? በእናንተ በኩልስ ውጤትን በመቀበል በኩል ምን ያህል ዝግጁ ናችሁ?
ኢዴፓ በባህሉ በምርጫ የሚመጣን ውጤት ተቀብሎ በምርጫ ሂደት ያለን እንከን የሚነቅፍ ነው፡፡ ስለዚህ በዚህ በኩል አይታማም:: ጠ/ሚሩ በፀጋ ለመቀበል ዝግጁ ነን ሲሉ ምናልባት በሳቸው በኩል ያለን ዝግጅነት ነው እየገለፁ ያሉት ሌላው አካል ውጤቱን በቀላሉ ለመቀበል ዝግጁ ነው ወይ ነው ጥያቄው፡፡ አሁን በምናየው የፖለቲካ ውጥረት ውስጥ ሁኔታዎች በፖለቲከኞች ሳይሆን በአክቲቪስቶች መስመር እየሳተ ነው ይሄ ምርጫውን በቀላሉ የሚቀበል አካል ለመፍጠር አዳጋች ይሆናል የሚል ግምገማ ነው ያለን፡፡         


Read 1509 times