Monday, 23 December 2019 00:00

ወደ ኋላ የማየት አባዜ መቼ ይቆማል?

Written by  አያሌው አስረስ
Rate this item
(1 Vote)


            የኢትዮጵያ አንድነት ጥያቄን የአማራ ሕዝብ ጉዳይ አድርገው የሚያዩና የሚያሳዩ ብዙዎች አሉ፡፡ ኢትዮጵያ ጠንካራ አገር መሆን አለባት ሲባል ተንደርድረው፣ ‹‹የአማራ የበላይነትን ለማምጣት ነው›› ብለው የሚለፍፉ ብዙ ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ አንድነት አስፈላጊና ጠቃሚነት ለአማራው ብቻ ሳይሆን ለሁሉም እንደሆነ መገንዘብም ይከብዳቸዋል፡፡ እነሱ እራሳችን ለራሳችን እንደሚሉት፣ አማራው ማለት እንደሚችልም አይገለጥላቸውም፡፡
የእነሱ ልጆች ወንዝ ተሻግረው ባሕር አቋርጠው፣ በአውሮፓና በአሜሪካ እንደተሰደዱት ሁሉ የአማራውም ልጆች ስደተኞች መሆናቸውንም አያስተውሉትም:: ሁሉም እየተገፋ ከሀገሩ የወጣውና በሀገር ውስጥም ያለው በድህነት የሚርመጠመጠው፣ በዚህች አገር ማቆሚያ ባጣው የእርስ በእርስ ትግልና መተላለቅ መሆኑን ማወቅ፣ እያወቁም አለመቀበልና ለማረም ባለመነሳት መሆኑን አስረግጦ መናገር ቢቻልም፤ የሚሰማ የተከፈተ ጆሮ የለም፡፡
ስድስት ወር ለሚሆን ጊዜ ቤት ዘግተው፣ ልባቸውን ከፍተው በሀገራቸው ጉዳይ ሲወያዩ የቆዩት “የኢትዮጵያ እጣ ፈንታ ጉባኤተኞች”፤ ሕዳር 23 ቀን 2012 ዓ.ም በውይይታቸው የደረሱባቸውን መደምደሚያዎች ይፋ አድርገዋል፡፡ ዛሬ ያለችበትን ተመልክተው ከሃያ ዓመታት በኋላ የሚፈልጓት ኢትዮጵያ ምን እንደምትመስል ያላቸውን የወደፊት ተስፋ ገልጠዋል፡፡
የየራሳቸውን እምነትና አስተሳሰብ ይዘው ወደ ውይይቱ የገቡት ሃምሳ “አመላም” ሰዎች፣ (አመለኛ ላለማለት) አንዱ ለሌላው አስረድቶ፣ የሌላውን ሃሳብ ሁሉም አፍ ከልብ አድምጠው፣ የደረሱበት ትልቅ መደምደሚያ ለሁሉም ማለትም ለሃምሳዎቹም፣ ዛሬ ያለችው ኢትዮጵያ የምታስፈልጋቸው መሆኗን ይህንንም አምነው መቀበላቸውን ለእየራሳቸው አስረግጠዋል፡፡ በአደባባይም ለአገር ምድሩ ተናግረዋል፡፡
ይህ የሃምሳ ሰዎች ውሳኔ ተራ ውሳኔ አይደለም፡፡ ለእኔ የሃምሳ ትናንሽ መሪዎች ውሳኔ ነው፡፡ ሲደመሩ ትልቅ የሚሆኑ ሰዎች ውሳኔ በመሆኑ ከፍ ብሎ የሚታይም ውሳኔ ነው፡፡ ይኸ ሃሳብ የማይገዛውና የኢትዮጵያን የግዛት አንድነት ለማፍረስ የሚያስብ ክፍልም ቆም ብሎ እንዲያስብ እንደሚያስገድደው አምናለሁ፡፡
በእኔ እምነት የጉባኤው መደምደሚያ፤ ከሁሉም በላይ ዋጋ ሊሰጠው የሚገባ የኢትዮጵያን አንድነትና ህልውና ማስቀጠል የአማራው ብቻ ሳይሆን የሁሉም ኢትዮጵያዊ የጋራ ጉዳይና የጋራ ኃላፊነት መሆኑን ማሳወቁ ነው፡፡ ለአማራዎችም ሆነ አማራ ላልሆኑት - ለኢትዮጵያ አንድነት ተቆርቋሪ አማራ ብቻ ሳይሆን ሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች መሆናቸውን እየነገራቸው ነው፡፡
ይህ የአንድነት አስፈላጊነት በተነገረ ቁጥር ወደ አማራ ጣታቸውን የሚቀስሩ፣ የነገር ሾተላቸውን ወደ ሰገባው እንዲመልሱ እንደሚያደርጋቸው አምናለሁ፡፡
ጉባኤው አማራውም ሆነ ሌላው ኢትዮጵያዊ ያልገባበትና ያልተሳተፈበት የኢትዮጵያን አንድነት የመጠበቅና የማስጠበቅ ተግባር ለእርሱ ብቻ የተተወ ሸክም አለመሆኑን የማወቅና የማሳወቅ ደረጃ ላይ የደረሰ መሆኑን መገንዘብ አስችሏል እላለሁ፡፡
አሁን የኢትዮጵያ አንድነት አደጋ ላይ መውደቅ፣ በአንድነት ዙሪያ ችግር መፈጠር… እንቅልፍ የሚነሳው “ነፍጠኛው” የሚባለውን አማራ ብቻ ሳይሆን ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ሆኗል ባይ ነኝ፡፡
ለስድስት ወር የዘለቀው “የዕጣ ፈንታ ጉባኤ”፤ ተሳታፊዎች ይፋ ያላደረጉት እንደ እኔ ያልተጠበቀ ውጤት አስገኝቷል - እንደኔ እምነት፡፡ ይኸውም የኦሮሞና የአማራ የፖለቲካ ድርጅት መሪዎች፣ ምሁራንና የሰብዓዊ መብት ተከራካሪዎች ተቀራርበው እንዲወያዩ እንዲመካከሩ ማድረጉ ነው፡፡ የዚህ ግንኙነት ውጤት ደግሞ በጥቅምት ወር 2012 ዓ.ም በኦሮሚያ ክልል በአንዳንድ አካባቢዎች ተቀስቅሶ የ86 ሰዎችን ሞት፣ የብዙዎችን አካል መጉደልና የንብረት መውደም ያስከተለውን ሁከት አይነት የጥፋት ድርጊቶች በጋራ ለማውገዝና በጋራ ሕዝብን ለማረጋጋት አቅም ይሰጣል፡፡
መሰል ግንኙነት አሁንም ቀጥሏል:: በቅርቡም የሁለት ቀን ስብሰባ አድርገው በሌላ በኩል  ሙሉ በአማራና ኦሮሚያ ክልል በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች፣ በተማሪዎች መካከል የሚቀሰቀሰውን ግጭት ለማስወገድና የመማር ማስተማሩ ሂደት በሰላማዊ መንገድ እንዲቀጥል ለማድረግ ተባብረው እንደሚሰሩ የገለፁ ሲሆን በቀጣይም በሌሎች አጀንዳዎች ላይም እንደሚወያዩ አሳውቀዋል፡፡
“የዕጣ ፈንታ ጉባኤተኞች” እንዲሁም የአማራና የኦሮሞ የፖለቲካ ኃይሎች ጊዜ ሳይወስዱ በር ዘግተው ሊመክሩበት፣ ጊዜያዊም ሆነ ዘላቂ መፍትሔ ሊፈልጉበት የሚገባው ሌላው ጉዳይ፣ አገር ወደፊት እንዳትራመድ ጠፍንጎ የያዛት የበዳይና የተበዳይ ትርክት ነው:: መቶ ዓመትና ከዚያ በላይ ዕድሜ ያላቸው ታሪኮች፣ የዛሬውን ኢትዮጵያዊ ሕይወት እያደፈረሱ፣ ሰላምና መረጋጋት እያሳጡና ወደፊት አርቆ እንዳያስብ እያደረጉት ነው፡፡
ባለፉት ሃምሳ ዓመታት ኢትዮጵያውያን በእርስ በርስ ጦርነት፣ ሀብታቸውን ሲያወድሙ፣ የሰው ኃይላቸውን ለአፈር ሲገብሩ፣ የበለጠ ድሃ እየሆኑ ሲኼዱ፣ በሌላ በኩል ሙሉ አቅማቸውን ለልማት ያዋሉት ቻይና፣ ሲንጋፖር፣ ደቡብ ኮሪያ አሁን በቅርብ ደግሞ ቬትናም በእድገት ጎዳና እየገሰገሱ ይገኛሉ፡፡
ኢትዮጵያና ሕዝቧ ወደ እድገት መገስገስ የሚችሉት ወደ ኋላ ማየትና ማሰባቸውን ሲያቆሙ ነው እላለሁ፡፡ አሁን ጥያቄው መቼ ነው ወደ ኋላ ማየት የሚቆመው? የሚለው ነው:: ይሄ አስቸኳይ መፍትሄ ይፈልጋል፡፡

Read 7511 times