Monday, 23 December 2019 00:00

የናይጀሪያ ባለስልጣናት 400 ቢ. ዶላር መዝረፋቸው ተነገረ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 አንጎላ በ2019 ብቻ ከመንግስት የተመዘበረ 5 ቢ. ዶላር ማስመለሷን ገልጻለች


            የናይጀሪያ የፍትህ ሚኒስትር አቡበከር ማላሚ፣ የአገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት፣ 400 ቢሊዮን ዶላር ያህል የህዝብ ገንዘብ ዘርፈው ወደ ውጭ አገራት ማሸሻቸውን እንዳስታወቁ ኦልአፍሪካን ኒውስ ዘግቧል፡፡ ሚኒስትሩ በተባበሩት አረብ ኤሜሬትስ በመካሄድ ላይ በሚገኘው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸረ ሙስና ጉባኤ ላይ ያደረጉትን ንግግር ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው፤ ባለስልጣናቱ በውጭ አገራት ከሚገኙ ታላላቅ ኩባንያዎችና አጋሮቻቸው ጋር በመተባበር፣ አገሪቱን 400 ቢሊዮን ዶላር ያህል ዘርፈዋታል፡፡
የአገሪቱ መንግስት ባለስልጣናት ከውጭ ሃይሎች ጋር በመተባበር፣ የሚፈጽሙትን መሰል ዘረፋ ለመከላከል ከመቼውም ጊዜ በበለጠ የተቀናጀ ስራ በመስራት ላይ እንደሚገኝ ሚኒስትሩ ማስታወቃቸውንም ዘገባው አክሎ ገልጧል፡፡ በሌላ ዜና ደግሞ አንጎላ ባለፉት 12 ወራት ጊዜ ውስጥ ብቻ በባለስልጣናት የተዘረፈ ከ5 ቢሊዮን ዶላር በላይ የህዝብ ሃብት እንዲመለስ ማድረጓን አልጀዚራ ባለፈው ረቡዕ ዘግቧል፡፡
የአገሪቱ የፍትህ ሚኒስትር ፍራንሲስኮ ኩየሮዝ እንዳሉት፤ የአገሪቱ መንግስት በተገባደደው የፈረንጆች አመት 2019 ብቻ ከመንግስት ካዘና የተዘረፈ ከ5 ቢሊዮን ዶላር በላይ ሃብት ከሃገር ውስጥና ከውጭ ለማስመለስ የተቻለ ሲሆን፣ በተለይም ፕሬዚዳንት ጃኦ ሎሬንሶ አገሪቱን ለ40 አመታት ያህል የመሩትንና ልጃቸውን ጨምሮ በሙስና እንደተጨማለቁ የሚነገርላቸውን ጆሴ ኤዱዋርዶ ዶስ ሳንቶስን ተክተው ስልጣን ከያዙ በኋላ ባለፉት 2 አመታት መሰል የህዝብ ሃብት ምዝበራንና ሙስናን ለመዋጋት እርብርብ እየተደረገ እንደሚገኝ ተገልጧል፡፡


Read 3209 times