Saturday, 28 December 2019 13:20

የእምነት ተቋማትን ጥቃትና ቃጠሎ የሚቃወሙ ሰላማዊ ሰልፎች ተካሄዱ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(7 votes)

         የሰብአዊ መብት ተቋማት ድርጊቱን አወገዙ

             በሞጣ ከተማ የደረሰውን የመስጊዶች ቃጠሎና የንብረት ውድመት የሚቃወሙ ሰላማዊ ሰልፎች በትላንትናው ዕለት በአገሪቱ የተለያዩ ከተሞች ተካሄዱ፡፡
በሰላማዊ ሠልፉ ላይ የተሳተፉ የእምነቱ ተከታዮች ለተቃጠሉ መስጊዶች አፋጣኝ ፍትህ እንዲሰጥ፣ አጥፊዎች በሕግ እንዲጠየቁ፣ የእምነት ተቋማት ክብር እንዲጠበቅ መጠየቃቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡
አዲስ አበባን ጨምሮ በወሎ፣ ደሴ፣ ወልዲያ፣ አዳማ፣ አርሲ ነገሌ፣ አፋር ሰመራ፣ ወሎ መርሳ፣ መካነ ሰላም፣ ሃርቡ፣ በደሌ፣ ጅማ፣ ስልጤና በሌሎች የአገሪቱ ከተሞችና አካባቢዎች የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፎች ተካሂደዋል፡፡
በሰላማዊ ሰልፎቹ ላይም መንግስት በእምነት ተቋማት ቃጠሎ የተሳተፉና ያስተባበሩ ግለሰቦችን በአፋጣኝ ለሕግ እንዲያቀርብ፤ መገናኛ ብዙሃንም ያለ አድልኦ ችግሩን እንዲዘግቡ ተጠይቋል፡፡
በተጨማሪም መንግስት ለተቃጠሉ የእምነት ተቋማትና ንብረታቸው ለወደመባቸው ግለሰቦች ተገቢውን ካሳ እንዲከፍል የሃይማኖትም ሆነ የፖለቲካ ጽንፈኞች ላይ ጠንካራ እርምጃ እንዲወስድ ሰልፈኞቹ ጠይቀዋል፡፡
በአዲስ አበባም በተለይ በፒያሳ ኑር መስጊድ ትላንት ከሶላት ስግደት በኋላ የእምነቱ ተከታዮች የተለያዩ መፈክሮችን በማሰማት ተቃውሟቸውን የገለፁ ሲሆን ካነገባቸው መፈክሮች መካከል “መስጊድ አቃጥለው የጨፈሩ ነውረኞች ለፍርድ ይቅረቡ››፣ ‹‹ጉዳት ለደረሰባቸው ሁሉ ይቅርታና ካሳ እንሻለን››፣ “የአማራ ክልል መንግስት የተቃጠሉ መስጊዶችን በአፋጣኝ ሊያስገነባ ይገባል” እንዲሁም “የክልሉ ሙስሊሞችን ችግር የሚፈታ ኮሚቴ ይቋቋም” የሚሉት ይገኙበታል፡፡
ትናንት በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የተደረገው ሰልፍ፤ በቤተ እምነቶች ላይ የሚደርሰውን ቃጠሎና ጥቃት ለመቃወም ያለመ መሆኑን በሰልፎቹ ላይ ከቀረቡ የተቃውሞ መፈክሮች መረዳት ተችሏል፡፡
በተመሳሳይ፤ በእምነት ተቋማት ላይ የሚፈፀሙ ጥቃቶች በአስቸኳይ እንዲቆሙ እንዲሁም የክልል መንግሥታት ሃላፊነት ወስደው ጥቃቱን እንዲከላከሉና አጥፊዎችን በተገቢው መንገድ ለሕግ እንዲያቀርቡ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማቱ አሳስበዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ፤ በእምነት ተቋማቱ ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን አስመልክቶ ባስተላለፉት ማሳሰቢያ፤ በማንኛውም የሃይማኖት ተቋም ላይ የሚፈፀም ጥቃት፣ የፈለጉትን ሃይማኖትና እምነት የመከተል ነጻነትን የሚጋፋ እኩይ ተግባር ነው ብለዋል፡፡
የክልል መንግሥታት፣ የእምነት ተቋማትንና አማኒያንን ከጥቃት የመከላከል ሃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ያሳሰቡት ዶ/ር ዳንኤል፤ በደረሰው ጉዳት ላይ አስፈላጊውን ምርመራ በማድረግም አጥፊዎችን ለሕግ እንዲያቀርቡ አስገንዝበዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) በበኩሉ፤ በማንኛውም የእምነት ተቋም ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች በአስቸኳይ እንዲቆሙ ጥሪ አቅርቧል፡፡ የሃይማኖትና እምነት ነፃነት በሕገ መንግሥቱ በአግባቡ መቀመጡን ያወሳው ኢሰመጉ፤ ይህን የዜጎችን መብት የማስከበር ሃላፊነት ደግሞ በመንግሥት ላይ የተጣለ ነው ብሏል፡፡
መንግሥት ሕገ መንግሥት የማስከበር ሃላፊነቱን ባለመወጣቱ እስከ ታህሳስ 10 ቀን 2012 ዓ.ም በግምት ከምሽቱ 1፡30 ገደማ በአማራ ክልል ሞጣ ከተማ በሚገኙ አራት መስጊዶችና ንብረትነታቸው የሙስሊም ወገኖቻችን የሆኑ የንግድ መደብሮች፣ ሆቴሎች፣ የንግድ ድርጅቶች ላይ ቃጠሎ መፈፀሙን እንዲሁም የግለሰብ መኖሪያ ቤቶች መዘረፋቸውንና የንብረት ማውደም እንደተፈፀመባቸው ከአካባቢው ምንጮች ማረጋገጡን አስታውቋል፡፡ በዚያው እለት በመስጊዶች ላይ ከተፈፀመው ጥቃት ቀደም ብሎ በሞጣ ከተማ በሚገኘው የቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ላይ የቃጠሎ ሙከራ ተፈፅሟል ያለው ኢሰመጉ፤ ይህ ሁኔታም ለችግሩ መባባስ አስተዋጽኦ አበርክቷል ብሏል፡፡
በቅርብ ጊዜያት ውስጥም በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች መሰል የሃይማኖት ተቋማት ጥቃቶች መፈፀማቸውንና ጥቃቶቹ እየተበራከቱ መምጣታቸውን የጠቀሰው ኢሰመጉ፤ ድርጊቱም በእጅጉ አሳሳቢ ነው ብሏል፡፡ እነዚህ ድርጊቶች በሃይማኖት አባቶችና በእምነቱ ተከታዮች ሊወገዙ የሚገባቸው ናቸው ያለው ተቋሙ፤ መንግሥትም ሕግን የማስከበር ሃላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባ አሳስቧል፡፡
ችግሩ ሲፈፀም በቸልተኝነት የተመለከቱ የጸጥታ ሃላፊዎች፣ የወረዳ አመራሮች የከተማዋ ከንቲባና አስተዳደር ላይ ግምገማ ተደርጎ እርምጃ ይወሰዳል ብለዋል አቶ ተሻገር፡፡ ከዚህ በኋላ በክልሉ መሰል እንቅስቃሴ ለማድረግ በሚሞክሩ ሃይሎች ላይ ያለርህራሄ እርምጃ እንደሚወሰድም ሃላፊው አቶ አገኘው ተሻገር አስገንዝበዋል፡፡
በሞጣ ከተማ ድርጊቱ ከተፈፀመ በኋላ ባህር ዳርን ጨምሮ  በአማራ ክልልና በሌሎች የአገሪቱ ከተሞች ድርጊቱን የሚቃወሙ ሰላማዊ ሰልፎች የተደረጉ ሲሆን ሕብረተሰቡም በትብብር የወደሙ ንብረቶችንና የተቃጠሉ መስጊዶችን በጋራ ለመስራት ቃል ገብቷል፡፡

Read 13051 times