Print this page
Sunday, 29 December 2019 00:00

የወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ ቢሮ አንድ ይበለን!!

Written by  አያሌው አስረስ
Rate this item
(0 votes)


             ኢሕአዴግ ማነው? ቢቸግር እንጂ የማይታወቀውን ኢሕአዴግ ይበልጥ ለማሳወቅ ያነሳሁት ጥያቄ አይደለም፡፡ ድግግሞሹ ያሰለቻቸውን አስቀድሜ ይቅርታ እጠይቃለሁ:: ጥቂቶች ለመስማትና ለመቀበል ባይፈቅዱም፣ ኢሕአዴግ በሕወኃት የበላይነት እንደ እንዝርት ሲሾር የኖረ ድርጅት ነው። በትምህርት በሥራ ልምድና በብቃት ላይ ተመሥርቶ ሳይሆን ለድርጅት ያለ ታማኝነትን ዋና መስፈርት አድርጎ፣ ሥልጣንን በኮታ ሲያከፋፍል የኖረ ፓርቲ  ነው፡፡
እያንዳንዱ የኢሕአዴግ እህት ድርጅቶች፤ አባል የሚመለምሉት ዘርን ቀዳሚ መመዘኛ አድርገው ነው፡፡ በእሱም ቢሆን አባላት በቀላሉ ስለማያገኙ ወደ ሕዝብ የሚቀርቡት በአንድ እጃቸው ዱላ፣ በአንድ እጃቸው ካሮት ይዘው ነው፡፡ ከሥራው መፈናቀልና ጦም አዳሪ መሆን የማይሻው የመንግሥት ሠራተኛ፤ ካሮቱን ፈልጎ ይጠጋል፡፡ “ቤቱ የመንግሥት እኔ ደግሞ የሙያ ሰው፤ ምን አገናኘን” የሚለው ደግሞ የደመወዝ ጭማሪና የሥራ እድገት ስለሚከለከል ዱላው ሲበዛበት ከመሞት መሰንበት ብሎ ይገባበታል። በጥቃቅንና አነስተኛ የንግድ ተቋማት ያለውም ተመሳሳይ ነው፡፡ በግል ገንዘቡና ጉልበቱ የሚያድር ቢሆንም ከማን አለብኝ ዱላቸው ለመዳን ሲል አባል ይሆናል፡፡ በዚህ መንገድ የተሰባሰቡት የፓርቲው አባላት ቁጥር ሰባት ሚሊዮን መድረሱ ተነግሮናል፡፡ የገዥ ፓርቲው አባላት ይህን ያህል መድረስ የጤና እንዳልሆነ ለማወቅ ብዙ መመራመር አይጠይቅም:: በኢሕአዴግ መቃብር ላይ እየበቀለ ያለው የብልጽግና ፓርቲ፤ ይህን ዓይነቱን አሠራር ይለውጠዋል ወይስ ባለበት ያስቀጥለዋል? ለወደፊት የምናየው ጉዳይ ነው፡፡
መጋቢት 2010 ዓ.ም አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ፤ የኢሕአዴግ ሊቀ መንበርነቱንና የጠቅላይ ሚኒስትርነቱን ቦታ ሲለቁ፤ ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ተተኩ እንጂ ኢሕአዴግ አልተወጠም:: የኢሕአዴግ ምክር ቤትና ሥራ አስፈጻሚው ባለበት ነው የቀጠለው፡፡ ይሄ ደግሞ ለውጡ ወደ ታች እንዳይወርድና እላይ እንደተንጠለጠለ እንዲቀር አድርጎታል:: ችግሩ የታችኛው አካል አለመለወጥ ብቻ አይደለም፤የታችኛው አካል ለበላይ አካሉ ያለውን ታማኝነት ለማረጋገጥ አለመቻሉም ጭምር ነው፡፡ አሁን እየተጠጋገነ ቢሆንም በምስራቅ ኦሮሚያ ወለጋ ዞን ውስጥ የታየው የመንግሥት መዋቅር መፈራረስ ለዚህ ጥሩ አብነት ነው፡፡
ከታች ከቀበሌ ወረዳ ጀምሮ  ያለው የመንግሥት መዋቅር፣ በአመዛኙ የሚንቀሳቀሰው በሙያተኛ ሳይሆን በፓርቲ ታማኞች በመሆኑ፣ የላይኛውና የታችኛው አካል ግንኙነት በሚደናቀፍበት ወይም በሚቋረጥበት ጊዜ፣ በዚያ አካባቢ ሕግና ሥርዓት ማስከበር በእጅጉ እንደሚያስቸግር ታይቷል፡፡
ታህሳስ 10 ቀን 2012 የሞጣው ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን የእሳት ቃጠሎ አደጋ ደርሶበታል፡፡ ሞጣ ጊዮርጊስ  ከሦስት መቶ ዓመት በላይ እድሜ ያለው ታሪካዊ ቤተ ክርስቲያን ነው፡፡ የከተማው ነዋሪ - ሙስሊምና ክርስቲያኑ ተባብሮ እሳቱን ያጠፋዋል፡፡ ይህ በሆነ በጥቂት ጊዜ ውስጥ ከየት እንደመጡ የማይታወቁ ሕግ አልባ ግለሰቦች፤ ከተማው ውስጥ የሚገኙ ሦስት መስጊዶችን በእሳት ያያይዛሉ፡፡ ከዚያም አንድ መቶ የሚደርሱ የሙስሊሞችና የክርስቲያኖች ሱቆችንና ሕንፃዎችን መዝረፋቸውንና ማቃጠላቸውን ቀጠሉ፡፡ እነዚህ ወንጀለኞች ሰው ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሶ እርዳታ እንዳያደርግ፣ በተኩስ አካባቢውን ሲያውኩ እንደነበር ታውቋል፡፡   
በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ በአማራ ክልል የሰላምና ደህንነት ግንባታ ቢሮ ኃላፊ፣ በአቶ አገኘሁ ተሻገር የተመራ ስብሰባ ሞጣ ላይ ተካሂዷል። በስብሰባው ላይ የኢትዮጵያ ሃይማኖቶች ኅብረት ጉባኤ ተወካዮች ተገኝተዋል፡፡ ተሰብሳቢዎች የወንጀሉ ፈጻሚዎችና ተባባሪዎች ወደ ሕግ ቀርበው ተገቢ ቅጣታቸውን እንዲያገኙ ጠይቀዋል፡፡ ምርመራው የአካባቢውን ባለሥልጣናት ሁሉ መዳሰስ እንዳለበት አጥብቀው አሳስበዋል፡፡ ይህን ሲሉ ደግሞ ምክንያት አላቸው፡፡
በከተማው የሚገኘው የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጉባኤ፤ ወንጀል ሊፈጽሙ የተዘጋጁ ሰዎች እንዳሉ ስም ጠቅሶ ለሚመለከታቸው የዞኑ ባለሥልጣናት ቢያሳውቅም እርምጃ እንዳልተወሰደ ተነግሯል:: አቶ አገኘሁ በበኩላቸው፤ ‹‹ልዩ መርማሪዎች ከሌሎች አካባቢዎች አምጥተናል፡፡ በፖሊስም በአስተዳደር ሠራተኞችም ላይ ማጣራት ይደረጋል›› ሲሉ ቃል ገብተዋል፡፡ እስከ አሁንም በወንጀሉ የተጠረጠሩ ሃያ ሰባት ሰዎች መያዛቸው ታውቋል፡፡
ወደ ኋላ እንመለስ፡፡ ዶ/ር ዐቢይ ወደ ሥልጣን ከወጡ ወዲህ የዘር ግጭት በመቀስቀስ፣ ዘር ላይ ያተኮረ ግድያ፣ የአካል ማጉደልና የንብረት ማውደም ወንጀል በመፈፀም የተጠረጠሩ ከሁለት ሺህ በላይ ሰዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል:: ግን ተጠርጣሪዎቹ እነማን እንደሆኑ ለምን ለሕዝብ አይገለጽም? ሕዝብ ከተሰጠው መረጃ ተነስቶ ወንጀል ሠርተው ያመለጡትን ወይም የተደበቁትን ወደ ሕግ ለማቅረብ እንዳያግዝ መንገዱ ተዘግቶበታል፡፡
የዘገየ ፍትሕ ከተከለከለ ይቆጠራል ይባላል፡፡ እስካሁን በተያዙ ሰዎች ላይ አንድም አይነት ብይን አለመተላለፉ ሌሎች ወደ ወንጀሉ እንዲገቡ እያደረጋቸው ነው እላለሁ፡፡ መንግሥት ለተራ ሌባ ጊዜያዊ ችሎት እንደሚያቆም አውቃለሁ:: ለእንደዚህ አይነቱ የከፋ ወንጀልም አፋጣኝ ችሎት አቋቁሞ ተበዳዮች ፍትህ እንዲያገኙ፣ በዳዮችም ቅጣታቸውን እንዲቀበሉ ቢደረግ መፍትሄ ሊሆን ይችላል ብዬ አምናለሁ፡፡
ከዚህ አንጻር የወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ ቢሮ አንድ ሊለን ይገባል፡፡

Read 3187 times