Saturday, 28 December 2019 14:04

ዘመን ባንክ የትርፍ መጠኑን ወደ 86 በመቶ አሳደገ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

   ቅርንጫፍ ባንኮቹን ወደ 43 አሳድጓል
                                        
              ዘመን ባንክ ባለፈው የበጀት ዓመት የትርፍ መጠኑን ወደ 86 በመቶ ማሳደጉን አስታወቀ፡፡ ባንኩ በ2011 ዓ.ም የበጀት ዓመት ከሰጣቸው የአገር ውስጥና የውጭ አገር የባንክ አገልግሎት ዘርፎች ከ1.5 ቢ ብር በላይ ያገኘ ሲሆን ሊያገኝ ካቀደው የ1 ቢ. 492 ሚ.ብር ገቢ አንጻር፣ የ6 በመቶ ብልጫና ከ2010 ዓ.ም አንፃር የ39 በመቶ ብልጫ ወይም የ447 ሚ.ብር እድገት ማሳየቱን ባንኩ በላከው መግለጫ አስታውቋል፡፡
ለትርፉ ማደግ እንደ ምክንያት ከተቆጠሩት መካከል የወጪ ቅነሳ፣ የብድር አቅርቦትና በአገልግሎት ዘርፍ የተመዘገበው መልካም አፈፃፀም ዋና ዋናዎቹ እንደሆኑ የጠቀሰው ባንኩ፣ በበጀት ዓመቱ 1 ቢ. 84 ሚ. ብር ወጪ ይኖረዋል ተብሎ የነበረ ቢሆንም በአመቱ ውስጥ በተሰሩ የወጪ ቅነሳ መርሃ ግብሮች አጠቃላይ ወጪው 947 ሚ.ብር እንዲሆን በማድረግ ትርፋማነቱን ለማሻሻል  እንደረዳውም ተገልጿል፡፡
ባንኩ በበጀት ዓመቱ ከታክስ በፊት 635.9 ሚ. ያልተጣራ ትርፍ ያስመዘገበ ሲሆን ይህም ከቀዳሚው 2010 ዓ.ም የ86 በመቶ ወይም የ293.5 ሚ. ብር ብልጫ ማሳየቱንና ከዕቅዱ ደግሞ የ55 በመቶ ብልጫ ያለው አፈፃፀም ሆኖ መመዝገቡን አስታውቋል፡፡
ባለፈው የበጀት ዓመት ለተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች የሰጠው ብድር 7.6 ቢሊዮን ብር የደረሰ ሲሆን ይህም ከቀዳሚው አመት የ50.7 በመቶ እድገት የተመዘገበበት እንደሆነ ባንኩ ጨምሮ ገልጿል፡፡ ባንኩ በበጀት ዓመቱ ካገኘው ከ1.5 ቢ. ብር በላይ ገቢ ውስጥ 1.ቢ 15 ሚሊዮን ከወለድ፣ ከአለም አቀፍ ባንክና ከሌሎች አገልግሎቶች ያገኘው እንደሆነም አስታውቋል፡፡
የዘመን ባንክ አጠቃላይ ሀብት እ.ኤ.አ በ2019 ዓ.ም መጨረሻ 14.7 ቢሊዮን የደረሰ ሲሆን ይህም ከቀዳሚው አመት በ18 በመቶ ወይም በ2.2 ቢሊዮን ብር ጭማሪ ማሳየቱ የተገለፀ ሲሆን፣ በ2010 ዓ.ም ከነበረው የ10.2 ቢሊዮን ብር ተቀማጭ ገንዘብ፣ በ2011 ዓ.ም ወደ 11.6 ቢሊዮን ብር ማደጉም ታውቋል፡፡
በሌላ በኩል፤ ባንኩ በ2011 ዓ.ም የበጀት ዓመት የደንበኞቹን የባንክ አገልግሎት ፍላጎት ለማሟላትና በቅርበት ለማገልገል ባደረገው ጥረት፣ የቅርጫፎቹን ብዛት ኪዮስኮችን ጨምሮ ወደ 43 ያሳደገ ሲሆን በተያዘው አዲስ የበጀት ዓመትም ይህንኑ የቅርንጫፍ ቁጥር የማሳደግ ስራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቋል፡፡

Read 4058 times