Sunday, 05 January 2020 00:00

“የጋዜጠኞች ወግ” በጨረፍታ

Written by 
Rate this item
(4 votes)

  የመንግሥቱ ኃ/ማርያም ወዳጅ…
ጌታቸው ኃ/ማርያም የኢሠፓ አባል ነበር:: በስራው ላይ ግን ይህ ፍጹም አይንፀባረቅም ነበር፡፡ ጌታቸው እና ሊቀመንበር መንግስቱ ኃ/ማርያም ይቀራረባሉ፡፡ ትውውቃቸው የሚጀምረው ጅማ እንደነበርም ይነገራል:: ሊቀመንበሩ ጌታቸውን ያቀርቡታል፡፡ በጉዟቸው ሁሉ አብሯቸው ነው፡፡
በሀገር ውስጥም ሆነ በውጪ፡፡ በዓሉ ግርማ፤ ፀጋዬ ኃ/ማርያም በተሰኘው ገጸ ባህሪው ጋዜጠኛው ለሊቀመንበሩ ያለውን ፍቅር እንዲህ ገልጾታል፡- “ተርገብጋቢ ወንዳወንድ ድምጽ፤ እንደ መብረቅ ቦግ የሚል ከልብ የመነጨ ፈገግታ፤ ቅስምን ድንገት የሚሰብር ልባዊ ትህትና:: ሰውየው ባማረ ሚሊተሪ ዩኒፎርም ነበሩ፡፡ ሳያቸው በራስ የመተማመን ድፍረት ተሰማኝ:: የሀገር መሪዎች እንደ ማንኛውም ሰው ተራ ሟች መሆናቸው ቢታወቅም ሲያይዋቸው የሆነ ፍቅር፣ አክብሮትና ፍርሃት፣ እና ድፍረት ለምን በሰው ሆነው ይታዩኛል፡፡ ምናልባት የሀገርና የህዝብ ክብርና ኩራት ቃል ጠባቂና አስከባሪ ባለአደራ ስለሆኑ ይሆናል:: የሆነው ሆኖ በዚህ ምክንያትም ይሁን በሌላ ባለስልጣናትን ማክበር በጣም እወዳለሁ:: ይህንን ጸባዬን በማየት የሥራ ባልደረቦቼ “ይኼው እንግዲህ ባለስልጣን ሲያይ ጭራውን ሊቆላ ነው ይላሉ:: እኔ ግን ጭራዬን የምቆላ ሰው አይደለሁም፡፡ ቆልቼስ የት ልደርስ?”
ዝናቡ ዘነበ አልኩ እንጂ ሰማዩን
አላስለቀስኩት
ኢህአዴግ አዲስ አበባን በተቆጣጠረ ሰሞን መላው ጋዜጠኛ በማዘጋጃ ቤት ለግምገማ ይቀመጣል፡፡ ያ ዘመን ደግሞ የመገማገም፣ የመወነጃጀልና የመሰዳደብ ዛር የነገሰበት ነበር:: የኢህአዴግ ካድሬዎች በልባቸው የቋጠሩትን አላማ ይዘው፣ ተለጣፊና አለሁ ባይ ጋዜጠኞች ያቀበሏቸውን ወንጀሎች ሰንቀው ተሰይመዋል:: ጌታቸው ላይ አንድ ወንጀል ቀረበ፡፡ ከኮሎኔል መንግስቱ ኃ/ማርያም ጋር ውጪ ሀገር ሄዶ ሲዘግብ የነበረውን ሁኔታ አስታውሰው እንዲህ ሲሉ ወነጀሉት “ኮሎኔሉ ከአውሮፕላን ሲወርዱ ዝናብ ዘነበ የሚል ዘገባ ሰርተሃል፣ ምን ማለት ፈልገህ ነው?” ሲሉ ጠየቁት እሱም እንዲህ ሲል መለሰ የሚፈራ አለመሆኑን እያስረዳ ቀጠለ “እኔ ጌታቸው ኃ/ማርያም የዘነበውን ዝናብ ዘነበ አልኩ እንጂ ሰማዩን አላስለቀስኩት” ሲል መለሰ፡፡ ሁሉም በድፍረቱ ተገረሙ፡፡ ውንጀላው ብዙዎችን አላሳመነም ከኢህአዴጉ ካድሬ ውጪ፡፡ ይሁንና ከሚወደው ሙያው ሳይወድ 1983 ላይ ተሸኘ፡፡ ተሰናበተ፡፡ የእሱ መሰናበት የጐዳው ጌታቸውን ብቻ አልነበረም፤ በሁለት እግሩ ለመቆም ይንገዳገድ የነበረውን የሀገራችንን የሚዲያ ዕድገትና ጋዜጠኞችን ጭምር እንጂ፡፡   
“ሞገደኛው ጋዜጠኛ”
መንግስቱ ገዳሙ ሞገደኛ የሚል ስያሜ የተሰጠው ከሙያዊ ሕይወቱ በመነጨ ሞጋች ስለነበር ነው፡፡ ጽሑፎቹ የሕዝቡን እውነተኛ ሕይወት የሚዳስሱ፣ ችግሩንና በደሉን ከፍላጐቱ ጋር የሚያመለክቱ ነበሩ፡፡ በተለይም የሥርዓቱን ንቅዘት በመዋጋት የሚደርስበት አሳርና መከራ ከሙያው አላገደውም፡፡ መንግስቱ “የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች የገና ዳቦ” ናቸው ሲል ብዙ ጊዜ ተናግሯል፡፡ የሞገደኛው ጋዜጠኛ መንግስቱ ገዳሙ ገድል ብዙ ነው:: በመንግስቱ ንዋይ መፈንቅለ መንግስት ወቅት የፒያሳን ሕዝብ በመኪና እየተዘዋወረ ቀስቅሷል:: ሁኔታው ሲለወጥ በሲዳሞ የአራት ወራት ግዞት ደርሶበታል፡፡ በአያሌ የሕዝብ አመጾች እየተሳተፈ ስላስቸገረም በየፖሊስ ጣቢያው ታስሮ የሻማ ከፍሏል፡፡
መንግስቱ ገዳሙ አንጋፋ ጠጪ በመባል የሚታወቅ ሲሆን ለምን እንደሚጠጣ ሲጠየቅ፤ “እኔ እኮ ለምን እንደምጠጣ እናንተ ደንቆሮዎች አይገባችሁም፤ የእኔ አእምሮ ከተራው ሰው አእምሮ በጣም የላቀ ነው፡፡ ስለዚህ ከእናንተ ጋር ለመነጋገር ያንን ከፍተኛ አእምሮዬን በአልኮል ኃይል ነው ወደ እናንተ ደረጃ ላወርድ የምችለው” በማለት መናገሩ ይታወሳል፡፡
ከጽሑፉና ከንግግሩ ባሻገር መንግሥቱ ገዳሙ በእለታዊ ድርጊቱ ስርዓቱን ይቃወም ነበር፡፡ ለምሳሌ አንዲት አህያ ጆሮዋ ላይ ብር ለጥፎ በየመጠጥ ቤቱ እየዞረ፣ አስተናጋጆቹ እንዲታዘዟት ያደርግ ነበር፡፡ በዚህም የጊዜው ባለስልጣኖች በገንዘብ እንጂ በአስተሳሰብ ከአህያ እንደማይሻሉ ለማስረዳት ያደረገው ነው ተብሏል፡፡ አህያዋን ይዟት በየቦታው ሲዞር “ምንድን ነች?” ብለው ሲጠይቁትም “የማስታወቂያ ሚኒስቴር ባልደረባ ነች” እያለ ይመልስ እንደነበር ይወሳል፤ በዚያ ዘመን ማስታወቂያውን በአህያ እየዞረ የሚያስነግረው ብሔራዊ ሎተሪ፤ በማስታወቂያ ሚኒስቴር ሥር ነበር፡፡ አህያዋም የባለስልጣኖች ተምሳሌት ነበረች፡፡ “
ከማን አንሼ” በምትሰኝ መጽሐፉ ላይ አንድ ሰው እጅ እንዲነሳት የተደረገችው ክራቫት ያሰረች አህያ፤ የወቅቱን የፓርላማ አባላት ለመሳደብ ሆን ብሎ ያዘጋጃት ናት ይባላል፡፡
***
“ዜና እያነበብኩ በጥይት ተመታሁ…”
ወቅቱ 2008 ክረምት ላይ ነበር፣ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የተቃውሞ ድምጾችና ግርግሮች በብዛት የሚታዩበት ሰሞን፡፡ ከእነዚህ ቦታዎች አንዱ ደግሞ ጐንደርና አካባቢው ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንም በአብዛኛው ማህበረሰብ ዘንድ ከፍተኛ ተቃውሞ የገጠመው በዚሁ ጊዜ ነበር፡፡ “ኮለኔል ደመቀ ዘውዱ በቁጥጥር ስር ውሏል” የሚል ዜና እና መግለጫ የእለቱ ዋና ዜና ሆኖ ጊዜ ተመድቦለታል:: የእለቱ ተረኛ ዜና አንባቢ ደግሞ መሰለ ገ/ህይወት፡፡
ዜና ማንበቡን ጀመረ፡፡ ወዲህ ደግሞ ደባርቅ ከተማ ላይ አንድ አርሶ አደር ዜናውን በከፍተኛ ንዴት ትኩረት ሰጥቶ መከታተሉን ቀጠለ፤ መሰለም ይህንን መግለጫ ማንበቡን ቀጥሏል:: አርሶአደሩ ግን የመሰለን ዜና መስማትና መቋቋም አቃተው፡፡
ክላሹን አነሳ፤ አቀባበለ፤ ወደ ቴሌቪዥኑ ተኮሰ፡፡ መሰለን ያገኘ ያክል እፎይታ ተሰማው:: ዜናው ተቋረጠ፡፡ “ይህንን የነገረኝ አንድ የቅርንጫፍ ባልደረባችን ነው:: በዚህም ምን ያክል ኢቲቪ ይጠላ እንደነበርና ለእኛ ያላቸው አመለካከት ከባድ እንደሆነ ተረድቻለሁ፡፡ ይህንን ጉዳይ ስሰማ በጣም ነው የደነገጥኩት፡፡ መሰለ በጥይት ተመታ እየተባለም ረጅም ጊዜ ይወራ ነበር፡፡
***
“ለ8 ቀን ኒሻን የሸለሙኝ አርበኛ”
እነዚህ የተቃውሞና የጥላቻ ድምጾች እንዳሉ ሁሉ፣ በተቃራኒው ደግሞ አድናቆቱም ከፍተኛ ነበር፡፡ “አንድ አባት አርበኛ በጣም እንደሚያደንቁኝ ከነገሩኝ በኋላ የሚሰጡኝ ግራ ሲገባቸው፣ በጣሊያን ወረራ ላይ የተሸለሙትን ኒሻን “ለስምንት ቀን አድርገህ መልስልኝ” ብለውኛል፡፡
የተለያዩ ስድቦችና በፎቶሾፕ የተሰሩ አስቂኝ ፎቶዎች…በተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያዎች እከታተል ነበር፡፡
ኢቲቪ የመንግስት አፍና የስርዓቱ ማንጸባረቂያ ስለሆነ ህዝቡ ዜናውን እኛ የምናዘጋጀው ይመስለው ነበር፡፡” እኔ ተቋሙ የቀጠረኝ የተሰጠኝን ማንኛውንም ዜና ለማንበብ እንጂ መርጬ “ይሄን አላነብም፤ ይሔኛው ደግሞ ይቅርብኝ” የማለት መብት የለኝም፡፡…
***
“ከመንግስቱ ኃ/ማርያም ኮበለሉ…”
ግንቦት 13/1983 ዓ.ም በኢትዮጵያ ራዲዮ ለሚገኙ ጋዜጠኞች እንደማንኛውም ቀን ሆና የቆየችው እስከ ረፋዱ 5፡00 ሰዓት ድረስ ብቻ ነበር፡፡ ምንም አዲስ ነገር አልነበረም፡፡ ምንም እንኳን ጦርነቱ በአዲስ አበባ ዙሪያ እንደቀጠለ ቢሆንም፡፡
በወቅቱ የማስታወቂያ ሚኒስትር የነበሩት አቶ አብዱልሀሺዝ ይባላሉ፡፡ ወደ ኢትዮጵያ ራዲዮ መጡና ጌታቸው ኃ/ማርያምን አናገሩት:: እንዲህም አ፡- “ዛሬ፤ በተለይም ራዲዮ ዜና አንባቢዎች የትም አትሄዱም፤ የሚጠበቅ ዜና አለ” ብለው ተናግረው ወጡ:: ግቢው ግራ ገባው:: ጋዜጠኞቹም ይህንን አዲስ ዜና ማን ያነበው ይሆን? እያሉ መጠባበቅ ጀመሩ:: ምናልባትም የራሳቸውን የሞት ፍርድ ማንበብም ሊሆን ይችላል፤ ግን ደግሞ የሆነ መሬት አንቀጥቅጥ ዜና እንዳለ አምነዋል፡፡ የዚህ ዜና ታሪክ አካል መሆን ሁሉም ይፈልጋሉ:: ሰዓቱ እየሄደ ነው፡፡ ከቀኑ 6፡00 ሰዓት ሆነ፡፡ “ጣቢያው እንዳይዘጋ፤ ጠብቁ” የሚል ትእዛዝ ድጋሚ ተላለፈ፡፡
አለምነህ ይህን ዜና ለማንበብ ከሁሉም በላይ ጓጓ፡፡ ዳሪዮስ ሞዲ ልምድ ስላለው እሱ ሊያነበው ይችላል በሚል ፍርሃት አለምነህ ዳሪዮስ ሞዲን በቅርብ ርቀት ይከታተለው ጀመር፡፡ ነጋሽ መሐመድም ቢሆን ሊያነበው እንደሚችል ሲያስብ ይበልጡን ፈራ፡፡
አለምነህ ዋሴ ሁሉንም በአይኑ ሲፈልግ ዳሪዮስ ሞዲን አጣው፡፡ በአካባቢው አለመኖሩንም ሲያይ ደስታው ወደር አልነበረውም፡፡ ሰዓቱ 6፡30 ሆኗል፡፡
ዜናውን የሚያመጡት ሰዎች ገቡና በቀጥታ ወደ ስቱዲዮ መውረድ ጀመሩ፡፡ አለምነህ ተከትሎ ገባ፤ እሱ ሊያነበው እንደሚችልም እርግጠኛ ሆነ፡፡ ነገር ግን ወደ ስቱዲዮ ሲጠጉ፣ ዳሪዮስ ሞዲ ከስቱዲዮ ሆኖ ቀድሞ ገብቶ “አድማጮች ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ በጉጉት የሚጠበቅ ዜና አለ” ብሎ እያስተዋወቀ ነበር:: ይሄንን ታላቅ ዜና አለምነህ በልምድ ማነስ ምክንያት (ዳሪዮስ ስቱዲዮውን ቀድሞ ይዞት ኖሮ) ለማንበብ ሳይታደል ቀረ፡፡ “የሚያስቅ ሀዘን” ብሎ ይገልጸዋል ይህንን ልዩ አጋጣሚም - አለምነህ ዋሴ፡፡ ዜናውም “መንግሥቱ ኃ/ማርያም በዛሬው እለት ከስልጣን ወርደው ከኢትዮጵያ ውጪ ሄደዋል” የሚል ነበር፡፡ (እንግዳ፣ ኢትዮጵያ ቴሌቪዥን)
ምንጭ፡-
(“የጋዜጠኞች ወግ” በግዛቸው አሻግሬ)

Read 3136 times