Print this page
Sunday, 05 January 2020 00:00

ጃፓን እንዴት ለኦሎምፒክ ሰለጠነች?

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

      የ32ኛው ኦሎምፒያድ 32 ሁኔታዎች

             202 ቀናት ቀርተዋል፤ 206 አገራት 11091 አትሌቶች፤12.6 ቢሊዮን ዶላር በጀት፤ 5 አዳዲስ የኦሎምፒክ ስፖርቶች፤5.9 ቢሊዮን ዶላር ገቢ፤ እንግዳ ተቀባይ ሮቦቶች እና ሾፌር አልባ ታክሲዎች ፤ 5ሺ የሱሺ ባሮች፤ ከ27 በላይ ቋንቋዎች የሚተረጉም አፕሊኬሽን፤ በአሮጌ የስልክ ቀፎዎች የተሰሩ ሜዳልያዎች፤ የኤሌክትሪክ ሃይል በሃይድሮጅን፤ በአልጌ ነዳጅ የሚሰሩ አውሮፕላኖች እና አውቶብሶች


  1. በጃፓኗ ከተማ ቶኪዮ ለሚካሄደው 32ኛው ኦሎምፒያድ 202 ቀናት ቀርተዋል:: ይህን የዓለማችን ግዙፉ የስፖርት መድረክ The 2020 Summer Olympics፤ XXXII Olympiad፤ 2020年夏季オリンピック Nisen Nijū-nen Kaki Orinpikku፤  第三十二回オリンピック競技大会 እና Tokyo 2020 በማለት በኦፊሴላዊ ደረጃ መጥራት ይቻላል፡፡
2. ለዝግጅቱ ከፍተኛ በጀት ወጭ ስለተደረገበት፤ በአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ስለተራቀቀ ፤ አዳዲስ የኦሎምፒክ ስፖርቶችና የውድድር መደቦችን ስለሚያስተዋውቅ፤ ሮቦቶች ስለሚሰማሩበት እና አዳዲስ ፈጠራዎችና ግኝቶች ስለበዙበት የዓለም  ሚዲያዎችን  ትኩረት እየሳበ መጥቷል፡፡
3. ቶኪዮ ለአዘጋጅነት የተመረጠችው ከ6 ዓመታት በፊት (በ2013 እኤአ) ዓለም አቀፉ ኦሎምፒክ ኮሚቴ በቦነስ አይረስ አርጀንቲና ባካሄደው 125ኛ ጠቅላላ ጉባኤ ሲሆን ተፎካካሪዎቿ ከተሞች ኢስታንቡል እና ማድሪድ ነበሩ፡፡  ጃፓን ኦሎምፒክን ለማስተናገድ የመጀመርያውን እድል በ1940 እኤአ አግኝታ ነበር፡፡  ይሁንና በሁለተኛው የዓለም ጦርነት በነበራት ተሳትፎ አዘጋጅነቱን ተነጥቃ የፊላንዷ ሄልሲንኪ ኦሎምፒኩን አስተናግዳለች፡፡ ከዚያ በኋላ የመጀመርያውን የኦሎምፒክ መስተንግዶ በዋና ከተማዋ ቶኪዮ በ1964 እኤአ ለማካሄድ  በቅታለች፡፡ ከ32ኛው ኦሎምፒያድ መስተንግዶ በኋላ ጃፓን በኤሽያ አህጉር ኦሎምፒክን ሁለት ጊዜ ያስተናገደች ብቸኛዋ አገር ትሆናለች፡፡ ከሁለቱ ኦሎምፒያዶች ባሻገር  ሁለት የክረምት ኦሎምፒኮችን  በ1972 በሳፖሮ እንዲሁም በ1998 በናጋኖ ከተሞች በማስተናገድ ከፍተኛ ልምድ አግኝታለች፡፡
4. በ2018 እኤአ የክረምት ኦሎምፒክን በደቡብ ኮርያ ፒዮንግያንግ መካሄዱና ከቶኪዮው 32ኛው ኦሎምፒያድ በኋላ ደግሞ በ2022 እኤአ ደግሞ የክረምት ኦሎምፒክ በቤጂንግ ቻይና መስተናገዱ ዓለም አቀፉ የኦሎምፒክ ኮሚቴ ለኤሽያ አህጉር የሰጠውን ትኩረት ያመለክታል፡፡
5. ዋና  መርሁ Discover Tomorrow  ‹‹ነገን እናግኝ›› የሚል ሲሆን የውድድሩ የገድ ምልክት ደግሞ ቼከርስ ወይም ባለዳማ ዲዛይን የለበሰ Miraitowa የሚል ስያሜ ያለው አሻንጉሊት ነው፡፡
6. በ33 ስፖርቶች በ50 የተለያዩ መርሃ ግብሮች 339 ውድድሮች የሚካሄዱበት ሲሆን፤ 206 አገራትን የወከሉ 11091 ኦሎምፒያኖችን ይሳተፉበታል፡፡
7. 33 የስፖርት መሰረተልማቶች የኦሎምፒክ ጨዋታዎቹን የሚያስተናግዱ ሲሆን ከመካከላቸው 28ቱ ከኦሎምፒክ መንደሩ 8 ኪሎሜትር ርቀት የሚገኙ ናቸው፡፡
8. የውድድሩ ዋና መድረክ የሆነው አዲሱ የጃፓን ብሄራዊ ስታድዬም በአዲስ መልክ የተገነባው በ3 ዓመት ውስጥ  ሲሆን 68ሺ ተመልካቾችን የሚያስተናግድ ነው፡፡በ1964 እኤአ ላይ በኤስያ አህጉር የመጀመርያውን ኦሎምፒያድ ለማስተናገድ የበቃው ይህ ስታድዬም 1.4 ቢሊዮን ዶላር የወጣበት ሲሆን ከውድድሩ በኋላ ልዩ የጃፓን ቅርስ  እንደሚሆን እየተነገረ ነው፡፡
9. ከመላው ዓለም ከ204 ሺ በላይ  ለበጎፈቃደኝነት ያመለከቱ ሲሆን በኦሎምፒክ ሰሞን የሚሰማሩት ከ16ሺ እስከ 25ሺ ይደርሳሉ::
10. ለዝግጅቱ እስካሁን የወጣው በጀት በኦሎምፒክ ታሪክ ከፍተኛው ሆኖ የሚጠቀሰው 12.6 ቢሊዮን ዶላር ሲሆን በሚቀጥሉት 7 ወራት ወደ 18 ቢሊዮን ዶላር መድረሱ እየተገለፀ ነው::  ከ6 ዓመታት በፊት ጃፓን መስተንግዶውን ስታገኝ  ያቀረበችው የዝግጅት በጀት ለአራት ጊዜ የተከለሰ ሲሆን በአስር እጥፍም አድጓል፡፡ ዓለም አቀፉ የኦሎምፒክ ኮሚቴ ይህን ከፍተኛ በጀት ወደፊት ኦሎምፒክን ማስተናገድ የሚፈልጉ ከተሞችን ያሳቅቃል በሚል ነቅፎታል፡፡
11. የፈረንሳይዋ ከተማ ፓሪስ በ2024 እኤአ ላይ ለምተዘጋጀው ኦሎምፒክ 7.6 ቢሊዮን ዶላር በጀት እንደምታወጣ ስትገልፅ፤  ሎስ አንጀለስ በ2028 እኤአ የምታስተናግደው ኦሎምፒክ  አጠቃላይ በጀቱ ከ6.9 ቢሊዮን ዶላር እንደማያልፍ አስታውቃለች፡፡
12. 5 አዳዲስ የስፖርት ውድድሮች ኦሎምፒኩን የሚቀላቀሉ ሲሆን፤ እነሱም ቤዝቦል/ ሶፍት ቦል፤ ካራቴ፤ ስኬት ቦርዲንግ፤ ስፖርት ክላይምቢንግ እና ሰርፊንግ ናቸው:: በተጨማሪም በሁለቱም ፆታዎች በሚካሄዱ የተለያዩ ስፖርቶች 15 አዳዲስ የውድድር መደቦች ተፈጥረዋል፡፡
13. የሚያስገኘው ትርፍ ከ300 ሚሊዮን ዶላር በላይ እንደሚሆን ሲጠበቅ በ31ኛው ኦሎምፒያድ ሪዮ ዲጄኔሮ 250 ሚሊዮን ዶላር ትርፍ ተገኝቷል፡፡
14. ከስፖንሰር፤ ከሚዲያ መብትና ከቲኬት ሽያጭ የሚገኘው ገቢ  5.9 ቢሊዮን ዶላር ነው፡፡ ከአገር ውስጥ ስፖንሰሮች 3.3 ቢሊዮን ዶላር፤ ከትኬት ሽያጭ 900 ሚሊዮን ዶላር ነው የሚገባው፡፡
15. በወቅቱ የመዝናኛ ቴክኖሎጂ የሚራቀቅ እንደሚሆን እየተገለፀ ነው፡፡ በተለይ በኦሎምፒክ ታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ ኢስፖርት በከፍተኛ ደረጃ ይተዋወቃል፡፡
16. ከቶኪዮ ከባድ ሙቀት ጋር በተያያዘ ዓለም አቀፉ ኦሎምፒክ ኮሚቴ የማራቶንና የርምጃ ውድድሮችን  ከዋና ከተማዋ በስተሰሜን 800 ኪሎሜትር ርቀት ላይ ተዛውሮ እንዲካሄድ ወስኗል፡፡ ውሳኔው በኦሎምፒክ አዘጋጆቹ ተቀባይነት አላገኘም፡፡ አስቀድሞ በከተማዋ የተዘጋጀውን የመሮጫ ጎዳና ባለመጠቀም ከሚፈጠረው የገንዘብ ኪሳራ እንዲሁም አዲስ በተቀየረው ላይ ውድድሩን ለማካሄድ ተጨማሪ ወጪ በመጠየቁ ነው፡፡ የኦሎምፒኩ አዘጋጆች ለእንዲዚህ አይነቱ ጉዳት መቋቋሚያ 300 ሚሊዮን ዶላር ተጠባባቂ በጀት መመደባቸውን ገልፀዋል፡፡
17. ከተለያዩ ዓለም ክፍሎች ለሚመጡ ስፖርት አፍቃሪዎች እና ቱሪስቶች ምቹ መስተንግዶዎች ሮቦቶች ይሰማራሉ፡፡ ሮቦቶች በአየር ማረፊያ ሮቦቶች እንግዶችን የሚቀበሉ ሲሆን በኦሎምፒክ መንደር እና በመወዳደርያ ስፍራዎች ሮቦቶች የውድድር ሰዓቶችን በማስታወስና በማስተዋወቅ እንዲሁም የመንገድ ጥቆማ ሌሎች መረጃዎችን በመስጠት ያገለግላሉ፡፡
18. ወደ ጃፓን ኦሎምፒኩን ለመታደም የሚገቡ ቱሪስቶች እና ስፖርት አፍቃሪዎችን የሚያስተናግዱ  5ሺ የሱሺ ባሮች ይከፈታሉ፡፡
19. 882 የባቡር ጣቢያዎች እና 282 የምድር ስር የባቡር ጣቢያዎች በኦሎምፒኩ ሰሞን አገልግሎት የሚሰጡ ሲሆን ከእነሱ መካከል በሰዓት 601 ኪሜትር የሚጓዘው ሱፕርሶኒክ ባቡር ይገኝበታል፡፡
20. ዓለም አቀፍ አጋር ሆኖ የሚሰራው Intel ደረጃውንና ወቅቱን በጠበቀ ቴክኖሎጂ በመጠቀም ኦሎምፒኩን እንደሚያደምቅ መዘጋጀቱንም አስታውቋል፡፡ ለአትሌቶች፤ በመወዳደርያ ስፍራዎች ለሚታደሙ ለስፖርት አፍቃሪዎችና የቲቪ ተመልካቾች እንዲሁም ለኦሎምፒኩ አዘጋጆች የሚመች ነው ተብሏል፡፡ በተለይ የ5ጂ ቴክኖሎጂን በሁሉም ረገድ ተግባር ላይ ለማዋል መታቀዱ ልዩ ድመቀት ይፈጥራል::
21. የቶኪዮ ከተማ አስተዳደር እንዳስታወቀው ኦሎምፒያዱን በቴክኖሎጂ ለማስተሳሰር ከ2017 እኤአ ጀምሮ በተከናወኑ ተግባራት እስከ 51.4 ቢሊዮን ዶላር ወጭ መደረጉን ነው፡፡ ቴክኖሎጂዎቹ አትሌቶችን በአስተማማኝ ደህነነት እና ጥበቃ ውስጥ የሚያደርጉ በቂ ቁጥጥር አድርጎ ለማስተናገድ፤
22. ከስፖንሰሮቹ አንዱ የሆነው የጃፓኑ መኪና አምራች ቶዮታ  ከፍተኛ አስተዋፅኦ ለማድረግ የተዘጋጀ ሲሆን ከሮቦቶች እና ከተለያዩ መንቀሳቀሻዎች ባሻገር እስከ 7ሺ ተሳፋሪዎችን የሚያስተናግዱ 100 ሹፌር አልባ ተሽከርካሪዎችን ለትራንስፖርት አገልግሎት ያቀርባል፡፡
23. Voicetra የተባለ የፅሁፍ መልዕክትን በተለያዩ ቋንቋዎች ተርጉሞ የሚያቀርብ አፕሊኬሽን ተዘጋጅቷል፡፡ ከ27 በላይ ቋንቋዎችን የሚተረጉም ነው፡፡ በሌላ በኩል ፓናሶኒክ አንገት ላይ የሚንጠለጠል የቋንቋ መተርጎሚያ ለማቅረብም አስቧል፡፡ ይህች መሳርያ ጃፓንኛን ወደ 10 ቋንቋዎች ትተረጉማለች፡፡
24. ከሃይደፍኔሽን ቴሌቭዥኖች በ10 እጥፍ ጥራቱ የሚልቅ ስርጭት የሚያሳዩ 8ኬ ቴሌቭዥኖች በጃፓንና በመላው ዓለም ለመጀመርያ ጊዜ በኦሎምፒኩ ይተገበራሉ፡፡
25. አውሮፕላኖችና አውቶብሶች  የሚጠቀሙት ከአልጌ የተሰራ ነዳጅ ይሆናል:: በኦሎምፒኩ ላይ ይህን ተግባራዊ ለማድረግ ከ40 በላይ ድርጅቶች ተባብረው ሰርተዋል፡፡
26. በኦሎምፒክ መንደር ሙሉለሙሉ ሃይድሮጅን የኤሌክትሪክ ሃይል ጥቅም ላይ የሚውል ሲሆን እስከ 300 ሚሊዮን ዶላር ኢንቨስት ተደርጎበታል፡፡
27. በመክፈቻው ስነስርዓት ላይ የክዋክብት ዝናብ ከሰማይ ላይ ለማውረድ የታቀደ ሲሆን እስከ 4 ሚሊዮን ዶላር ወጭ ሆኖበታል፡፡
28. ከ1ኛ እስከ 3ኛ ደረጃ በማግኘት ለሚሸለሙት ኦሎምፒያኖች የተዘጋጁት ሜዳልያዎች የተሰሩት ኤሌክትሮኒክ ሳይክሊንግ  ፕሮግራም በተባለ እንቅስቃሴ ነው፡፡ የወርቅ፤ የብርና የነሐስ ሜዳልያዎቹን  ከጃፓን ህዝብ በልዩ ዘመቻ በተሰበሰቡ እና እስከ 8 ቶን በሚመዘኑ አሮጌ የስልክ ቀፎዎች ነው የሰሯቸው::
29. ግሬስኖት ስፖርትስ ስታትስቲካዊ ትንታኔ በዓለም የስፖርት ሊጎች ላይ የሚሰራ ተቋም ነው፡፡ ግሬስ ኖት ኦሎምፒኩ ዛሬ ቢጀመር ብሎ ባቀረበው የሜዳልያ ትንበያ አሜሪካ በ1ኛነት እንደምታጠናቅቅ ያመለከተው  51 የወርቅ፤ 34 የብርና 41 የነሐስ በአጠቃላይ 126 ሜዳልያዎች ትሰበስባለች በማለት ነው፡፡ ቻይና  81  ፤ ራሽያ 65 ፤ በብሪቲን 43፤ አውስትራሊያ 43፤ ፈረንሳይ 41፤ ጀርመን 38፤ ሆላንድ 34ና  ጣሊያን 32 አጠቃላይ የሜዳልያ ስብስብ በማስመዝገብ እስከ 10ኛ ደረጃ አከታትለው ይወስዳሉ፡፡
30. በግሬስ ኖት ለኢትዮጵያ በተሰራው የሜዳልያ ትንበያ 9 ሜዳልያዎችን 2 የወርቅ፤ 4 የብርና 3 የነሐስ ሜዳልያዎችን በመሰብሰብ 31ኛ ደረጃ እንደምታገኝ የተጠቆመ ሲሆን  የቅርብ ተቀናቃኟ ኬንያ 12ኛ ደረጃን በ17 ሜዳልያዎች 8 የወርቅ፤ 3 የብርና 6 የነሐስ ሜዳልያዎች ታገኛለች ተብሏል፡፡
31. ቤስትስፖርትሰ የተባለ ድረገፅ ከሳምንት በፊት ባወጣው ትንበያ ደግሞ ኢትዮጵያ 8 ሜዳልያዎችን 3 የወርቅ፤ 1 የብርና 4 የነሐስ ሜዳልያዎችን እንደምትሰበስብ ገምቷል
32. ኦሎምፒክ ፕሪዲክሽን ድረገፅ ደግሞ ለኢትዮጵያ የተነበየው 10 ሜዳልያዎችን 3 የወርቅ፤ 3 የብርና 4 የነሐስ ሜዳልያዎችን ነው፡፡


Read 877 times