Wednesday, 08 January 2020 00:00

የአለማችን 500 ባለጸጎች ሃብት በ12 ወራት በ1.2 ትሪሊዮን ዶ. ጨምሯል

Written by 
Rate this item
(3 votes)

   ዶ/ር ድሬ በ950 ሚ. ዶላር ገቢ የ10 አመታት ቀዳሚው ሙዚቀኛ ሆኗል

         የአለማችን ቀዳሚዎቹ 500 ባለጸጎች ባለፈው የፈረንጆች አመት 2019 ሃብታቸው በድምሩ በ1.2 ትሪሊዮን ዶላር ወይም በ25 በመቶ ጭማሪ በማሳየት 5.9 ትሪሊዮን ዶላር መድረሱን ብሉምበርግ ሲዘግብ፤ ፎርብስ በበኩሉ ዝነኛው ድምጻዊ ዶክተር ድሬ ባለፉት አስር አመታት ከአለማችን ሙዚቀኞች መካከል ከፍተኛውን ገቢ ማግኘቱን አስነብቧል፡፡
ባለፉት 12 ወራት የሃብት መጠናቸው በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል በሚል በአንደኛነት ደረጃ ላይ የተቀመጡት ፈረንሳዊው ቢሊየነር በርናንድ አርኖልት ሲሆኑ ባለጸጋው በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ 36.5 ቢሊዮን ዶላር ያህል ተጨማሪ ሃብት ማካበታቸውን ብሉምበርግ አስነብቧል:: ከፍተኛ የሃብት ጭማሪ ካሳዩት የአለማችን ቢሊየነሮች መካከል አብዛኞቹ በቴክኖሎጂውና በቅንጦት ቁሳቁስ ምርት ዘርፍ የተሰማሩ እንደሆኑ የጠቆመው ዘገባው፤ የፌስቡክ መስራችና ዋና ስራ አስፈጻሚ ማርክ ዙክበርግ የ27.3 ቢሊዮን ዶላር፣ የማይክሮሶፍቱ መስራች ቢል ጌትስ ደግሞ የ22.7 ቢሊዮን ዶላር የሃብት ጭማሪ በማስመዝገብ የሁለተኛና የሶስተኛ ደረጃ ላይ መቀመጣቸውንም አመልክቷል፡፡
በአመቱ በፍቺ ለተለያዩዋት የቀድሞ የትዳር አጋራቸው በካሳ መልክ የከፈሉትን 8 ቢሊዮን ዶላር ጨምሮ ሃብታቸው በ10 ቢሊዮን ዶላር የቀነሰባቸው የአማዞኑ መስራች ጄፍ ቤዞስ፣ ምንም እንኳን በ2019 የሃብት መጠናቸው በእጅጉ የቀነሰባቸው ሁለተኛው የአለማችን ባለጸጋ ቢሆኑም፣ አሁንም በ116 ቢሊዮን ዶላር ሃብት የአመቱ የአለማችን ቁጥር አንድ ቢሊየነርነት ክብራቸውን የነጠቃቸው የለም:: የማይክሮሶፍቱ መስራች ቢል ጌትስ በ113 ቢሊዮን ዶላር ሃብት የአለማችን ሁለተኛው ባለጸጋ ሲሆኑ፣ ፈረንሳዊው ቢሊየነር በርናንድ አርኖልት በበኩላቸው፤ በ106 ቢሊዮን ዶላር የሶስተኛነት ደረጃን መያዛቸውን ዘገባው አመልክቷል፡፡
ከአለማችን 500 ቢሊየነሮች መካከል በአመቱ የሃብት መጠናቸው ቅናሽ ያሳየባቸው 52 ባለጸጎች ብቻ ናቸው ያለው ብሉምበርግ፤ በአመቱ የ10.2 ቢሊዮን ዶላር ሃብት ያጡት በሚዲያው ዘርፍ የተሰማሩት አሜሪካዊው ቢሊየነር ሩፐርት ሙርዶክ ከፍተኛው የሃብት መቀነስ  ያጋጠማቸው ቀዳሚው የአለማችን ቢሊየነር መሆናቸውንም ጠቁሟል፡፡
በሌላ ዜና ደግሞ ባለፉት 10 አመታት ከፍተኛ ገቢ ያገኙ የአለማችን ዝነኛ ሙዚቀኞች ዝርዝር ከሰሞኑ ይፋ ያደረገው ፎርብስ መጽሄት፤ ታዋቂው የሂፖፕ ሙዚቃ አቀንቃኝ ዶ/ር ድሬ በ950 ሚሊዮን ዶላር ገቢ፣ በአንደኛ ደረጃ ላይ መቀመጡን ገልጧል፡፡ ባለፉት አስር አመታት በድምሩ 825 ሚሊዮን ዶላር ገቢ በማግኘት በሁለተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠቺው ታዋቂዋ ድምጻዊት ቴለር ስዊፍት ስትሆን ቢዮንሴ ኖውልስ በ685 ሚሊዮን ዶላር በሶስተኛነት ትከተላለች፡፡
ዩቱ የሙዚቃ ቡድን አባላት 675 ሚሊዮን ዶላር፣ ፒዲዲ በ605 ሚሊዮን ዶላር፣ ኤልተን ጆን በ565 ሚሊዮን ዶላር፣ ጄይዚ በ560 ሚሊዮን ዶላር፣ ፖል ማካርቲኒ በ535 ሚሊዮን ዶላር፣ ኬቲ ፔሪ በ530 ሚሊዮን ዶላር፣ ሌዲ ጋጋ በ500 ሚሊዮን ዶላር ገቢ እንደ ቅደም ተከተላቸው ከአራተኛ እስከ አስረኛ ያለውን ደረጃ መያዛቸውንም ፎርብስ በዘገባው አስታውቋል፡፡


Read 3273 times