Thursday, 09 January 2020 00:00

የቀድሞው የአንጎላ መሪ ልጅ በሙስና ያገኙት 1 ቢ. ዶላር ታገደ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

   የእስራኤሉ ጠ/ሚ ፍ/ቤት እንዳልቀርብ ከለላ ይሰጠኝ አሉ


           የቀድሞው የአንጎላ ፕሬዚዳንት ኤዱዋርዶ ዶስ ሳንቶስ ልጅ የሆነችውና የአባቷን ስልጣን መከታ በማድረግ ባካበተችው ሃብት የአፍሪካ ቁጥር አንድ ቢሊየነር እንደሆነች የሚነገርላት ኤልዛቤል ዶስ ሳንቶስ፤ ያላግባብ አፍርታዋለች የተባለው አንድ ቢሊዮን ዶላር ያህል ሃብት እንዳይንቀሳቀስ መታገዱን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
አገሪቱን ለ40 አመታት ያህል ያስተዳደሩትን ኤዱዋርዶ ዶስ ሳንቶስ ተክተው ከ2 አመታት በፊት ወደ ስልጣን የመጡት ፕሬዚዳንት ጃኦ ሎሬንኮ፤ ብሔራዊ የጸረ-ሙስና ዘመቻ መጀመራቸውንና 2.2 ቢሊዮን ዶላር ያህል ሃብት እንዳላት የሚነገርላት የቢሊየነሯ ኤልዛቤል ዶስ ሳንቶስ ሃብት እንዳይንቀሳቀስ፣ ከሰሞኑ በፍርድ ቤት የተላለፈው ውሳኔም የዚህ ዘመቻ አካል እንደሆነ ዘገባው አመልክቷል፡፡
የአገሪቱ መንግስት የነዳጅ ኩባንያ ዋና ስራ አስፈጻሚ የሆነቸው የ46 አመቷ ኤልዛቤል ዶስ ሳንቶስ፣ ግዙፉን የቴሌኮም ኩባንያ ዩኒቴልን ጨምሮ በበርካታ ኩባንያዎች ውስጥ ከፍተኛ የሃብት ድርሻ እንዳላቸው ያስታወሰው ዘገባው፣ የአባቷን ስልጣን መከታ በማድረግ በሙስናና በምዝበራ ሃብት አፍርታለች በሚል ክስ ቢቀርብባትም፣ ምንም አይነት ወንጀል እንዳልፈጸመች ስታስተባብል መቆየቷንም ገልጧል፡፡
ፍርድ ቤቱ ውሳኔውን ማስተላለፉን ተከትሎ ኤልዛቤል በትዊተር ድረገጽ ባስተላለፈችው መልዕክት፤ ውሳኔውን በፖለቲካ ጫና የተላለፈብኝ ነው ስትል መቃወሟን የጠቆመው ዘገባው፣ የቀረቡብኝን የሃሰት ክሶች በህግ ተከራክሬ ነጻ ለመውጣት ዝግጁ ነኝ ማለቷንም አመልክቷል፡፡ የቀረበባትን የሙስና ክስ በማጣራት ላይ የሚገኘው ፍርድ ቤቱ  ባስተላለፈው ውሳኔ፤ ኤልዛቤል በባንክ ውስጥ ያላት ገንዘብና በግዙፍ ኩባንያዎች ውስጥ ያላት የሃብት ድርሻ እንዳይንቀሳቀስ ከማገዱ በተጨማሪ የባለቤቷ ሲንዲካ ዶኮሎ ሃብትም እንዳይንቀሳቀስ ማገዱን ዘገባው አክሎ ገልጧል::
በሌላ በኩል ደግሞ የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ በቀረቡባቸው የሙስና፣ የእምነት ማጉደልና የማታለል ክሶች ፍርድ ቤት እንዳይቀርቡ የህግ ከለላ ይሰጠኝ ሲሉ ለፓርላማው ጥያቄ ማቅረባቸውን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡ ከዚህ ቀደም ሶስት የወንጀል ክሶች የተመሰረቱባቸውና ምንም አይነት ወንጀል አልፈጸምኩም በማለት ምላሽ ሲሰጡ የቆዩት የ70 አመቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታኒያሁ ባለፈው ረቡዕ ለአገሪቱ ፓርላማ በላኩት ደብዳቤ፤ለተወሰነ ጊዜ ፍርድ ቤት እንዳይቀርቡ የህግ ከለላ እንዲሰጣቸው መጠየቃቸውን የጠቆመው ዘገባው፤ጥያቄያቸው ተቀባይነት ሊያገኝ የሚችለው ከፓርላማው አባላት ከግማሽ በላይ ድጋፍ ሲያገኝ መሆኑንም አመልክቷል፡፡
ኔታኒያሁ ቀጣዩ የአገሪቱ ምርጫ እስከሚካሄድበት ጊዜ ድረስ የፍርድ ሂደቱ እንዳይጀመር ለፓርላማው የህግ ከለላ ጥያቄ ማቅረባቸውን ተከትሎ፣ የተቀናቃኝ የፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮች ከፍተኛ ተቃውሞ ማሰማታቸውንና ሰውዬው የህግ ከለላው እንዳይሰጣቸው ተግተው እንደሚታገሉ በይፋ አስታውቀዋል፡፡ እስራኤል በአንድ አመት ውስጥ ባካሄደቻቸው ሁለት ምርጫዎች ኔታኒያሁም ሆኑ ተቀናቃኛቸው ቤኒ ጋንዝ መንግስት ለመመስረት የሚያስችላቸውን ድምጽ ማግኘት ባለመቻላቸው ለሶስተኛው ምርጫ ዝግጅት በመደረግ ላይ መሆኑን ያስታወሰው ዘገባው፤ የኔታኒያሁ የህግ ከለላ ጥያቄም የተከሰሱበት ወንጀል በፍርድ ቤት የሚታይበት ጊዜ ከምርጫው በኋላ እንዲጀመር ከመፈለግ የመነጨ ነው ብሏል፡፡


Read 5410 times