Sunday, 05 January 2020 00:00

ጋዜጠኛ ፍቃዱ ማህተመ ወርቅ የ7 ዓመት ፍርዱ ጸናበት

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(3 votes)

 የ“ግዮን” መጽሔት ማኔጂንግ ዳይሬክተር ጋዜጠኛ ፍቃዱ ማህተመ ወርቅ፣ ከ6 ዓመት በፊት ከነበረ የታክስ ጉዳይ ጋር ተያይዞ በስር ፍ/ቤት ለተበየነበት የ7 ዓመት እስራት፣ ለፌደራሉ ከፍተኛ ፍ/ቤት የጠየቀው ይግባኝ ውድቅ ተደርጐ ፍርዱ እንደፀናበት ታውቋል፡፡
በ2006 ዓ.ም በ “እንቁ” መጽሔት ላይ በተከፈተው የታክስ ስወራ ክስ ምክንያት በፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት የ7 ዓመት እስራትና የ15 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት የተላለፈበት ጋዜጠኛው፤ ይግባኝ ጠይቆ ሲከራከር ቢቆይም ከትናንት በስቲያ ጉዳዩን የተመለከተው የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት 8ኛ ወንጀል ችሎት የስር ፍ/ቤት “ውሳኔ ተገቢ ነው” ሲል እስራቱን አጽንቶበታል፡፡
ጋዜጠኛው ላለፉት ሁለት ወራት በቃሊቲ ማረሚያ ቤት ታስሮ እንደሚገኝ የሚታወቅ ሲሆን፤ እስሩን ተከትሎም ሳምንታዊ የነበረችው “ጊዮን” መጽሔት ህትመት ተቋርጧል፡፡
አለማቀፍ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ቡድን (ሲፒጂ)፤ የጋዜጠኛው እስር ጉዳይ ግልጽ እንዳልሆነ በመጠቆም መንግሥት ተገቢውን ማብራሪያ እንዲሰጠው መጠየቁ አይዘነጋም፡፡


Read 9644 times