Print this page
Sunday, 05 January 2020 00:00

ለተቃጠሉ መስጊዶችና የንግድ ተቋማት መልሶ ግንባታ ከ450 ሚ. ብር በላይ ያስፈልጋል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(4 votes)

     የሕዝበ ሙስሊሙ ጥያቄዎች በአፋጣኝ እንዲመለሱ ተጠይቋል

             በቅርቡ በሞጣ ከተማ የደረሰውን የመስጊዶችና የንግድ ተቋማት ጉዳት ሲመረምር የቆየው አጣሪ ኮሚቴ፤ የመጨረሻ ሪፖርቱን ያቀረበ ሲሆን የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ም/ቤት በበኩሉ የሕዝበ ሙስሊሙ ጥያቄዎች በአፋጣኝ እንዲመለሱ ጠይቋል፡፡
ከኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠ/ም/ቤት የተውጣጣውና ከሰሞኑ በሞጣ ከተማ ተገኝቶ ስለደረሰው ጉዳትና የጥቃቱ መንስኤ ሲመረምር የቆየው አጣሪ ኮሚቴ ባቀረበው ሪፖርት፤ በከተማዋ የሚገኙ ሶስት መስጊዶች ከእነ ሙሉ ንብረታቸው ሲቃጠሉ፣ በአንዳንዶቹ ላይ በከፊል ጉዳት መድረሱን አስታውቋል፡፡
መስጊዶች ላይ ከደረሰው ጉዳት በተጨማሪ በአካባቢው የሚገኙ 167 የንግድ ተቋማትና ቤቶች እንዲሁም የተለያዩ የእስልምና ቅርሶች መውድማቸውንና ቅዱስ ቁርአን መቃጠሉን ኮሚቴው ጠቁሟል፡፡
የተጎዱትን ንብረቶችና የእምነት ተቋማት መልሶ ለመገንባትም ከ450 ሚሊየን ብር በላይ እንደሚያስፈልግ የገለፀው ኮሚቴው፤ የክልሉ መንግሥት ለዚህ ተግባር አፋጣኝ ምላሽ መስጠት እንዳለበት አሳስቧል፡፡
ጥቃቱ ከደረሰ በኋላ የክልሉ መንግሥት በይፋ ይቅርታ መጠየቅ ሲገባው አለመጠየቁ እንዲሁም የደህንነት ዋስትናን በተመለከተ መጅሊሱ ላቀረበው ጥያቄ እስካሁን ምላሽ አለመሰጠቱ ቅሬታ መፍጠሩን ጠቁሞ፤ በአፋጣኝ ተገቢውን ካሳ እንዲከፍል ጠይቋል - ኮሚቴው፡፡
ታህሳስ 10 ቀን 2012 ዓ.ም በከተማዋ የተፈጠረው የእምነት ተቋማት ጥቃት ታቅዶበትና ተቀነባብሮ የተፈፀመ ድርጊት ነው ያለው ኮሚቴው፤ ለዚህም የፀጥታ አካላትና የከተማ አስተዳደሩ ትብብር ማድረጋቸውን ኮሚቴው በሪፖርቱ አስገንዝቧል፡፡
በዚህ ጥቃት ተባብረዋል ተብለው የተጠረጠሩ የከተማዋ የፀጥታ ሃላፊዎች እንዲሁም የአስተዳደር አካላት በሕግ ቁጥጥር ስር መዋላቸውን በማድነቅም ተገቢው ፍትህ እንዲሰጥም አሳስቧል፡፡
በሕዝበ ሙስሊሙ ላይ በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በተደጋጋሚ እየደረሱ ያሉ ጥቃቶችን በዝርዝር ያስቀመጠው መግለጫው፤ ማስተካከያ እንዲደረግባቸው ተደጋጋሚ ጥያቄ ቢቀርብም አዎንታዊ ምላሽ አለመገኘቱን አስታውቋል፡፡ ከተቀሰቀሱት ችግሮች መካከልም የመስጂድ ማፍረስና ቃጠሎ በአማራ፣ ደቡብ፣ አዲስ አበባና ኦሮሚያ መፈፀሙን፣ በአማራ ክልል ደግሞ በሕዝበ ሙስሊሙ ላይ በጦር መሳሪያ የታገዘ ጥቃት እንዲሁም የንግድ ተቋማትና መኖሪያ ቤት ውድመት ማጋጠሙን ጠቁሟል፡፡
የመስገጃ ቦታ እጦትና የመቃብር ቦታ አለማግኘት ደግሞ በትግራይ አክሱምና በአማራ ክልል እንዲሁም የመስጂዶች ይዞታ ሕጋዊነት ማጣት በአዲስ አበባና ደቡብ ክልል ማጋጠሙን ም/ቤቱ ጠቅሶ ፍትሃዊ የሚዲያ ዘገባና ሽፋን አለማግኘትም ከተዘረዘሩት ችግሮች መካከል ይገኙበታል፡፡
ከዚሁ ጋር በተያያዘ በሞጣ የደረሰውን ጥቃት በተመለከተ መገናኛ ብዙሃን፣ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽንና የሕዝብ እምባ ጠባቂ ተቋም ተገቢውን መረጃ ለሕዝቡ ባለማድረሳቸው ቅሬታ እንደተሰማው ም/ቤቱ አስታውቋል፡፡
መንግሥት በሕዝበ ሙስሊሙ ለሚነሱ ጥያቄዎች አፋጣኝና የማያዳግም ምላሽ እንዲሰጥ እንዲሁም  የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ተቋም የሆነው መጅሊስ ሕጋዊ ሰውነት በአጭር ጊዜ በአዋጅ እንዲቋቋም ጠይቋል፡፡

Read 10689 times