Tuesday, 07 January 2020 00:00

ኢትዮጵያ በ2020 ከፍተኛ የምግብ አቅርቦት እጥረት ሊያጋጥማት ይችላል ተባለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(4 votes)

  ኢትዮጵያ በ2020 ከፍተኛ የምግብ አቅርቦት እጥረት ሊያጋጥማት እንደሚችል ያስጠነቀቀው የአለም የምግብ ፕሮግራም፤ መንግሥት ከወዲሁ ሕዝቡን ከችግሩ ለመታደግ ዝግጁ መሆን አለበት ብሏል፡፡
የሰብል አምራች በሆኑ አንዳንድ የአገሪቱ አካባቢዎች ከዝናብ ስርጭት አለመመጣጠን፣ የአንበጣ መንጋ ካደረሰው ጉዳትና ወቅቱን ካልጠበቀ ዝናብ መዝነብ ጋር ተያይዞ አገሪቱ የጠበቀችውን ያህል ምርት ላታገኝ እንደምትችል ከትናንት በስቲያ የዓለም የምግብ ፕሮግራም ባወጣው ሪፖርት አስታውቋል፡፡
በተለይ የሰሜን ምስራቅ አማራ፣ ትግራይ፣ ደቡብ፣ ምስራቅና ምዕራብ ሀረርጌ አካባቢዎች የምግብ ቀውስ ተጠቂዎች ሊሆኑ እንደሚችሉ የጠቆመው ድርጅቱ፤ በእነዚህ አካባቢዎች የክረምት ዝናብ እጥረት፣ የአንበጣ መንጋና ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ በሰብል ላይ ጉዳት ማድረሳቸውም በሪፖርቱ ተጠቅሷል፡፡
በሌላ በኩል ወቅቱን ያልጠበቀውና ከጥቅምት እስከ ታህሳስ የዘነበው ዝናብ አርብቶ አደር አካባቢ በሆኑት ሶማሌ ክልልና ሌሎች አካባቢዎች የእንስሳት ምርትንና የወተት ምርትን የሚጨምር መልካም አጋጣሚ መሆኑን ሪፖርቱ አመልክቷል፡፡
በአጠቃላይ በአገሪቱ ሊያጋጥም ከሚችለው የምግብ ሰብል እጥረት ባሻገር በየጊዜው የሸቀጦች ዋጋ ንረት የአገሪቱን ዜጎች የመግዛት አቅም እየተፈታተነ መሆኑንም ሪፖርቱ ጠቁሟል፡፡
በአሁኑ ወቅት የሸቀጦች የዋጋ ንረት (ግሽበት) ምጣኔው 20.8 በመቶ መድረሱንና ይህም በአገሪቱ እስከ ዛሬ የተመዘገበ ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት መሆኑን ያስታወቀው የዓለም ምግብ ፕሮግራም መንግሥት ለእነዚህ ሁሉ ችግሮች ዘርፈ ብዙ አማራጮችን እንዲፈትሽ መክሯል፡፡
የአገሪቱ መገበያያ ገንዘብ ብር ከዶላር ያለው ምጣኔም ባለፈው ወር ብቻ በየቀኑ የ0.35 በመቶ ውድቀት እያሳየ መቆየቱንም የጠቆመው ሪፖርቱ፤ ይህም ከውጪ ተገዝተው የሚገቡ ምርቶች ላይ የዋጋ ጭማሪ ማስከተሉን ጠቁሟል፡፡

Read 8037 times