Monday, 13 January 2020 00:00

የቶጎው መሪ ለ4ኛ የስልጣን ዘመን በምርጫ ሊወዳደሩ ነው

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 የቶጎው ፕሬዚዳንት ፋውሬ ጋሴንጊቤ “ደጋፊዎቼና ፓርቲዬ ጫና አሳድረውብኛል” በሚል ሰበብ ለ4ኛ የስልጣን ዘመን በምርጫ ለመወዳደር መወሰናቸውን በይፋ እንዳስታወቁ አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል፡፡
ዩኤንአይአር የተባለው የአገሪቱ ገዢ ፓርቲ ባለፈው ማክሰኞ ያደረገውን ስብሰባ ሲያጠናቅቅ ፓርቲውን ወክለው  በመጪው ወር በሚካሄደው አገራዊ ምርጫ እንዲሳተፉ ደጋፊዎቻቸው ጫና ስላሳደሩባቸው ለቀጣይ አስር አመታት ያህል በመንበራቸው ላይ እንዲቆዩ በሚያስችላቸው ምርጫ ለመወዳደር መወሰናቸውን ነው ፕሬዚዳንት ጋሴንጊቤ የተናገሩት፡፡
የአገሪቱ ፓርላማ ባለፈው አመት ባደረገው የህገ መንግስት ማሻሻያ አንድ ፕሬዚዳንት ከሁለት የስልጣን ዘመን በላይ ማገልገል እንደማይችል ቢደነግግም፣ ፕሬዚዳንት ጋሴንጊቤ ግን ዘንድሮና በ2025 በሚካሄደው ምርጫ ለመወዳደር ዝግጅት እያደረጉ መሆናቸውን ዘገባው አመልክቷል፡፡
እ.ኤ.አ በ1967 በተካሄደ መፈንቅለ መንግስት ስልጣን የያዙትና ለ38 አመታት ያህል አገሪቱን አንቀጥቅጠው የገዙት አባታቸው ጋሴንጊቤ ኢያዴማ በሞት በተለዩበት 2005 ከተካሄደ አወዛጋቢ ምርጫ አንስቶ አገሪቱን በማስተዳደር ላይ የሚገኙት ፋውሬ ጋሲንጊቤ፤ በ2010 እና በ2015 በተመሳሳይ አወዛጋቢ ምርጫ በማሸነፍ አገሪቱን በቀውስ ውስጥ ይዘዋት መዝለቃቸውን ያስታወሰው ዘገባው፣ ባለፈው አመት በተደረገው የህገ መንግስት ማሻሻያ በስልጣን ዘመናቸው ለፈጸሟቸው ወንጀሎች ሁሉ በህግ እንዳይጠየቁ ወይም እንዳይከሰሱ ከለላ እንዲሰጣቸው ማድረጋቸውንም አስታውሷል፡፡

Read 8529 times