Wednesday, 15 January 2020 00:00

በኮንጎ አደገኛ የኩፍኝ ወረርሽኝ ከ6 ሺህ በላይ ሰዎችን ገደለ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

  በዲሞክራቲክ ኮንጎ ባለፈው ሰኔ ወር የተቀሰቀሰው፣ በአለማችን እጅግ የከፋውና በፍጥነት በመስፋፋት ላይ የሚገኘው የኩፍኝ ወረርሽኝ ከ6 ሺህ በላይ ሰዎችን ለህልፈተ ህይወት መዳረጉን የአለም የጤና ድርጅት ባወጣው መግለጫ ማስታወቁን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
የኩፍኝ ወረርሽኙ ከተቀሰቀሰበት ጊዜ አንስቶ በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች 310 ሺህ ያህል ሰዎችን ሳያጠቃ አልቀረም መባሉን የጠቆመው ዘገባው፤ ወረርሽኙ ተስፋፍቶ መቀጠሉን ተከትሎ ባለፈው መስከረም የአገሪቱ መንግስትና የአለም የጤና ድርጅት በትብብር አስቸኳይ የክትባትና የህክምና ዘመቻ ቢጀምሩም፣ በአገሪቱ ያለው የጤና አገልግሎትና የተቋማት ደረጃ ዝቅተኛ በመሆኑ የተፈለገውን ለውጥ ለማምጣት አለመቻሉን አመልክቷል፡፡
በአሁኑ ሰአት ወረርሽኙ ወደ አገሪቱ 26ቱም ግዛቶች መስፋፋቱን የጠቆመው ዘገባው፤ ባለፈው የፈረንጆች አመት 2019 ብቻ ከ18 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ የአገሪቱ ህጻናት የኩፍኝ ክትባት መሰጠቱንም አስታውሷል፡፡
የአለም የጤና ድርጅት ወረርሽኙን ለመቆጣጠርና ክትባቱን በመጪዎቹ ስድስት ወራት ለህጻናትና ታዳጊዎች በስፋት ለማዳረስ ለተያዘው አገራዊ ፕሮግራም ማስፈጸሚያ ተጨማሪ 40 ሚሊዮን ዶላር ያህል እንደሚያስፈልግ በመጥቀስ፣ ለጋሾችና አለማቀፉ ማህበረሰብ ድጋፉን እንዲያደርግ ጥሪ ማስተላለፉንም ዘገባው አክሎ ገልጧል፡፡
በነሃሴ ወር 2018 የተቀሰቀሰው አስከፊ የኢቦላ ወረርሽኝ ከ2 ሺህ 230 በላይ ዜጎቿን የገደለባት ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ አሁን ደግሞ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ በአደገኛ የኩፍኝ ወረርሽኝ መመታቷ ወደ ከፋ ቀውስ ሊያስገባት ስለሚችል አለማቀፉ ማህበረሰብ እርብርብ ማድረግ እንደሚገባውም ዘገባው አመልክቷል፡፡

Read 6700 times