Saturday, 11 January 2020 12:23

ለምወዳችሁ ውድ ኢትዮጵያዊያንና የፖለቲካ መሪዎች

Written by  ኤፍሬም ይስሃቅ (ፕሮፌሰር)
Rate this item
(2 votes)

  እኔ በሀገረ አሜሪካ የምኖር ኢትዮጵያዊ ነኝ:: በአሜሪካ በኖርኩባቸው ጊዜያት ባገኘሁት የትምህርት እድል በጣሙን ተጠቅሜያለሁ:: ስለሆነም ምስጋናዬ የላቀ ነው፡፡ ይሁን እንጂ አሜሪካ ከደረስኩ ቀን አንስቶ እስከዛሬ ኢትዮጵያ በታሪክ የበለፀገች ምድር መሆኗን፣ ሰዎቿም ሰው ወዳድና አክባሪ መሆናቸውን፣ እንዲሁም ለህዝባችን ልማትና ሰላም ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ከማሳወቅ አልቦዘንኩም:: ስለዚህም ነው በአሁኑ ወቅት አላስፈላጊ በሆኑ የፖለቲካ ልዩነቶች በምወዳት ሀገሬ ላይ እየተከሰተ ያለውን ሞትና ውድመት ስሰማ ከሚታመነው በላይ የሚያመኝ፡፡ ጥሩና ምክንያታዊ ስርዓትን የተላበሰ አስተዳደር ሊኖር ግድ ይላል፤ የህዝባችንንና የሀገራችንን ብልጽግናና ደህንነት ማዕከል ያደረገ ቆራጥና ታጋሽ የሆነ የግጭት መነሻና መንስኤ ያልሆነ አስተዳደር ያስፈልገናል:: ሰላምና ፀጥታን እንዲሁም ደህንነትን የሚያስጠብቅ ጠንካራ የፖለቲካ አካል ሊኖረን ይገባል፡፡
ከዛሬ ስልሳ አመት አካባቢ በፊት እ.ኤ.አ በ1959 ዓ.ም የሰሜን አሜሪካ ኢትዮጵያዊያን ተማሪዎች ማህበር የመጀመሪያው ፕሬዝዳንት ሆኜ መመረጤን እንደተቀበልኩ ለመግለጽ ባደረግኩት ንግግር ላይ ስለ ህዝቦቻችን መልካምነትና እናት ሀገራችንን ለማስተዋወቅ እርስ በእርስ እየተረዳዳን በህብረት መስራት እንዳለብን እንዲህ ብዬ ነበር፡- “ሁላችንም ለውድ ሀገራችን ለኢትዮጵያ የተሻለ፣ የበለጠ ውጤታማ የሆነ ትብብርን አላማ እናድርግ…ሃብታም ሀገር አለችን፤ በአለምም ለም ከሆኑት አፈሮች ብዙ አለን - ቢያንስ 180 ሚሊየን ኤከር የሚሆን ድንግል ለም አፈር…ጥሩ መነሻ አለን፤ የምንኮራበት ጠንካራ ባህልና ታሪክ አለን፡፡ በመተባበር የሚያምን ህዝብ አለን፡፡ ስለዚህ ይህንን ግባችንን ዳር ለማድረስ ፈጣን ርምጃ የምንወስድ ከሆነና ለኃላፊነቶቻችን ታማኝ ከሆንን ለብዙዎች ለታረዙ፣ ለተራቡና ለተጠሙ፣ ለብዙ ታማሚዎችና ደካማዎች በውስጥም፣ በውጭም በክፍለ ሀገራችን፣ ባገራችን አልፎም በአህጉራችን ላሉት ዕረፍትም ሆነ ሰላም ላጡት ብዙ ፀጋዎችንና ትሩፋቶችን ልናመጣ እንችላለን፡፡” ከስልሳ ዓመት በፊት በተናገርኳቸው በነዚህ ቃላት ኩራት ይሰማኛል:: ዛሬ በግምት 110 ሚሊየን ከሚሆነው ጋር ሲነፃፀር፣ በዚያን ጊዜ የነበረው የኢትዮጵያ የህዝብ ብዛት 20 ሚሊየን ነበር፡፡ ለዚህ ነው ከነዚያ ዓመታት ሁሉ በኋላ እንኳን የተወሰኑ የፖለቲካ መሪዎች ዛሬም ለህዝባችን በዋናነት የሚያስፈልጉት የትምህርት፣ የጤና፣ የኢኮኖሚ ልማትና የስራ እድል ፈጠራ አገልግሎት እንደሆኑ መገንዘብ ተስኗቸው ሳይ የማዝነው፡፡ እነዚህን ጥያቄዎች ለመመለስ ከመስራት ይልቅ ጥላቻን እየሰበኩና ህዝባችን እርስ በእርሱ የፖለቲካ ጦርነት ውስጥ እንዲገባ እየደለሉ ለአካል ጉዳትና ለሞት ይዳርጉታል፡፡
ውድ ሀገራችንን ከቃላት በዘለለ በተግባርም ለማስተዋወቅ በማሰብ ጓደኞቼና እኔ ኢትዮጵያ የመሰረተ ትምህርት ኮሚቴን በ1966 (አ.ኤ.አ) አቋቋምን፡፡ ይህ ኮሚቴ የተቋቋመው የዚያን ጊዜውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ መሰረተ ትምህርት ዘመቻ ድርጅት ለማገዝ ነበር፡፡ ዋና ሰብሳቢ ሆኜ የተሾምኩበት ይሄው ኮሚቴ፤ በአሜሪካ የመጀመሪያው ከአሜሪካ ፌደራል ቀረጥ ክፍያ ነጻ የሆነ ድርጅት ሆነ፡፡ ከ1963-69 (እ.ኤ.አ) በኢትዮጵያ መሰረተ ትምህርትን ለማበረታታት ለሚሰሩት ስራዎች የሚውል ወደ ግማሽ ሚሊየን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ አሰባስቦ ነበር፡፡ (በዚያን ጊዜ ይሄ በጣም ትልቅ መጠን ያለው ገንዘብ ነበር)፡፡ በመላው ሀገሪቱ ገጠራማ ቦታዎች መምህራንና ተማሪዎች ህዝቡን ማታ ማታ በበጐ ፈቃደኝነት ለማስተማር ተነቃቅተው ነበር፡፡ በሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ እያለሁ፣ የተከበሩ ጀነራል ታደሰ ብሩን ተክቼ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ መሰረት ትምህርት ዘመቻ ድርጅትን በኤክዚክዩቲቭ ዳይሬክተር ጀነራልነት እንዳገለግል በ1966 እ.ኤ.አ ተሾምኩ (1966-74)፡፡ የተለያዩ የኢትዮጵያ ሚዲያዎች (ቴሌቪዥንና ጋዜጦች) እንደዘገቡት፤ የደርግ የመሰረተ ትምህርት መርሃ ግብር ከመጀመሩ ብዙ ቀደም ብሎ ጀምሮ የኛ ድርጅት ከ1962-1974 (እ.ኤ.አ) ከሁለት ሚሊዮን የሚበልጡ ኢትዮጵያዊያንን ከመሃይምነት ነጻ አውጥቷል:: ስለሆነም ለአዎንታዊና መልካም ግብ ተባብሮ መስራት እንጂ ፖለቲካ ለህዝባችን እንደማይጠቅም እኔ እማኝ ነኝ፡፡ ግላዊ የፖለቲካ መጠላለፍ ለበለጠ ጥል ይዳርጋል እንጂ ህዝባችንን ኢምንት ያህል አይጠቅምም፡፡ (ደርግ የኢትዮጵያ ብሔራዊ መሰረተ ትምህርት ዘመቻ ድርጅት ከፍተኛ ተቀባይነት እንደነበረው ሲያውቅ ሁሉንም ቢሮዎቹንና ንብረቶቹን ወስዶ ኢትዮጵያ ትቅደም መሰረተ ትምህርት መርሃ ግብሩን እንደጀመረበት ተነግሮኛል፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ የተወሰኑት ቀደምት የፕሮግራሙ አስተዳዳሪዎች ኢትዮጵያ የመሰረተ ትምህርት ኮሚቴና የኢትዮጵያ ብሔራዊ መሰረተ ትምህርት ዘመቻ ድርጅት አባላት ነበሩ፡፡)
ታዋቂው የአሜሪካ ፈላስፋ ከመቶ አመታት በፊት አካባቢ አለ እንደሚባለው ታሪክን የሚረሱ እንዲደግሙት የተረገሙ ናቸው:: እኛም በርግጥ የፖለቲካ ታሪካችንን ልንረዳ የግድ ነው፡፡ ስለ ታሪካችን ድሎችና ትልቅነት ብቻ ሳይሆን በተለይም ባለፈው አንድ ምዕተ አመት ከግማሽ ውስጥ ለተሰሩትም ጥፋቶች እውቅና መስጠትና ስህተቶቻችንን መቀበል አለብን፡፡ የነዚያን አመታት ጠንካራ ጐኖች ማድነቅ እንዳለብን ሁሉ በዚያን ጊዜ የነበሩ ድክመቶችንና ውድቀቶችንም መቀበል አለብን፡፡ በዚህም ረገድ የዛሬ የኢትዮጵያ ወጣቶች ስላለፉ ውድቀቶቻችን በመጮህ ስህተቶች እንዲታረሙ የሚያደርጉትን ትግል አደንቃለሁ፡፡ የወደፊቱ የሀገራችን የፖለቲካ ሁኔታ ከማንም በበለጠ ወጣቶች ላይ ተጽእኖ ይኖረዋል፡፡ ወጣቶች ሀገር ተረካቢ ናቸው፡፡ ለነሱ ሲባልም የፖለቲካ መሪዎቻችን ሰላምና ስምምነት እንዲፈጠር መስራት ይኖርባቸዋል፡፡ ለምንድን ነው ከደሃው ህዝብ የወጡትና የተማሩት የፖለቲካ መሪዎች ፖለቲካ ረሃብተኞቻችንን እንደማይመግብ፣ ወጣቶቻችንን እንደማያስተምር ወይም ሆስፒታሎች እንደማይገነባ የማይገነዘቡት? ስለሆነም ከአክብሮት ጋር ይህ መልእክቴ ለመንግስታችንና ለፖለቲካ መሪዎቻችን ነው፡፡
አሁን የምኖርባት አሜሪካ ሀብታምና ሃያል ሀገር ናት፡፡ ነገር ግን ለምን ሃብታምና ሃያል ሆነች? ሁሉም ኢትዮጵያዊ፣ በተለይም የኛ የፖለቲካ መሪዎች፣ ይህን ጥያቄ እንዲጠይቁና ከዚያች ታላቅ ሀገር በመማር ሀገራዊ አቅማችንን በማያልቅ የፖለቲካ ጨዋታና ግጭት ማባከናቸውን እንዲያቆሙ እፈልጋለሁ:: ድህነትን ማስወገድ፣ የጤና አገልግሎትን ለህዝባችን ማዳረስ፣ ወጣቶቻችንን ማስተማር እንዲሁም በሳይንስና ቴክኖሎጂ ጥናትና ምርምር እንድንሳተፍ ከተመኘን ከአሜሪካ መማር ይኖርብናል፡፡
አሜሪካ የሚመሯት የፖለቲካ ፓርቲዎች አሏት፡፡ ነገር ግን አገሪቷን ሃያል ያደረጓት ፖለቲካም ሆነ ፖለቲከኞቿ አይደሉም፡፡ እርግጥ ነው በተለያዩ ጊዜያት የብሔር ግጭቶች በተለይም በነጮችና በጥቁሮች መካከል ይከሰታሉ፤ በቀኝ ዘመምና ግራ ዘመሞችም መሃከል እንዲሁ ግጭት ይከሰታል፡፡ ድህነትም ቢሆን ከአሜሪካ ጨርሶ አልጠፋም፡፡ ይሁንና አሜሪካ በጣም የበለፀገች ሀገር ናት፡፡ የፖለቲካ ልዩነት፣ ዘረኝነትና ፀረ - ሴሚቲዝም ቢኖሩም የአሜሪካዊያንን ኑሮ በበላይነት አይዙም ወይም ዋና የሞትና የጉዳት ምንጭ አይሆኑም፡፡ ለአሜሪካ ጥንካሬ መሰረቱ አገሪቱ ለኢኮኖሚ፣ ንግድ፣ ጤና፣ ትምህርትና ማህበራዊ አገልግሎቶች የሰጠችው ትኩረት ነው፡፡ የሆነ የፖለቲካ ችግር ቢፈጠር እንኳን የፋይንስ ሴክተሩ ባግባቡ ይሰራል፣ የንግድ ሂደቱም ይቀጥላል፤ ኢንዱስትሪውም አይስተጓጐልም፡፡ ባጠቃላይ ሃገሪቱ የበለፀገችና ጤናማ ነች፡፡
አሜሪካ ብዙ ከተለያዩ ቦታዎች፣ ብሔሮችና ሃይማኖቶች የመጡ ህዝቦች በሰላም ተከባብረው የሚኖሩባት ሀገር ነች፤ ቃልኪዳን አላቸው፤ እሱም የአሜሪካ ህገ መንግስትና የህግ የበላይነት ናቸው፡፡ ፖለቲከኞች ብዙ ጊዜ ይህን ቃልኪዳን በመተው የፖለቲካ ንትርክ ውስጥ እንደሚገቡ አውቃለሁ፡፡ በአሁኑ ወቅት እንኳን ለምሣሌ ብዙ ሰዎች የህገመንግስት ጥሰት ነው በሚሉት ጉዳይ ንትርክ አለ፡፡ አንዳንዴ ብዙ ሰዎች በፖለቲካ ተቃውሞ ሰልፎች ሊሳተፉ ይችላል፡፡ ነገር ግን ብዙው ህዝብ በስራ ላይ ነው፤ ወጣቱም ትምህርት ቤቶችና የትምህርት ተቋማት ውስጥ ነው፡፡ (ይሄ የምለው ሁሉ በሌሎችም እንደ ጀርመን፣ ስዊድንና ሌሎች ያደጉ አገራትም ይሰራል፡፡)
አሜሪካን ታላቅ ያደረጋት ፖለቲካ ሳይሆን በትምህርትና ኢኮኖሚያዊ ዘርፍ ያላት መሪነት ነው፡፡ የአሜሪካ በአለም ጦር ሃይልና ፖለቲካ መሪነት ራሱ በትምህርትና ኢኮኖሚያዊ ውጤታማነቷ ምክንያት እንጂ በልዩ ፖለቲካ አይደለም፡፡ ጠንካራ ገበሬዎቿ ናቸው አሜሪካን ታላቅ ያደረጓት፡፡ በቆሎ፣ ድንች፣ ሶያ፣ ስንዴና ሌሎች ቻይና፣ ጃፓን፣ አውሮፓና የተቀረው የአለም ክፍል የሚገዛቸውን የግብርና ምርቶች ያመርታሉ፡፡ አሜሪካን ታላቅ ያደረጓት መሃንዲሶቿና የሳይንስ ተመራማሪዎቿ ናቸው፤ ፖለቲከኞቿ አይደሉም፤ ብዙዎቹ ከተለያዩ የአለም አካባቢዎች በመምጣት የሲቪል፣ ሜካኒካል፣ ኤሌክትሪካል፣ ኬሚካል፣ ሶፍትዌርና የተለያዩ ሃብት የሚያስገኙ ምርቶችን ያመርታሉ፤ ይገነባሉ፡፡ አሜሪካን ታላቅ ያደረጓት ፖለቲከኞች ሳይሆኑ የተለያዩ እቃዎችንና አገልግሎቶችን የሚያቀርቡት ሰራተኞች፣ ግንበኞች አናጢዎች፣ ቀጥቃጮች፣ ቧንቧ ሰሪዎች፣ ሸክላ አንጣፊዎችና የተለያዩ ባለሙያዎች ናቸው፡፡ አሜሪካን ታላቅ ያደረጓት ከተለያዩ ሀገራት የመጡ ምጡቅ አእምሮ ያላቸው ተመራማሪዎችና እውቀት የሚመነጩባቸው ዩኒቨርስቲዎችና ዋና ዋና የትምህርትና የጥናት ምርምር ማዕከላት እንጂ ፖለቲከኞች አይደሉም፡፡ እንዲህ አይነት ውጤታማ ሰዎች ናቸው ለወጣቱ አርአያ የሚሆኑት፡፡ እደግመዋለሁ፤ አሜሪካን ውጤታማ ያደረጓት በስራ ፈጠራና ውጤታማ በሆነ ስራ ላይ በየቢሮአቸውና ፋብሪካዎች የተጠመዱ ባለሙያዎች፣ አስፈላጊ ሳይንሳዊና ባህላዊ ጥናት የሚያካሂዱ ፕሮፌሰሮች፣ ጤናን ለማዳረስ የሚለፉት ሃኪሞች፣ ሰዎች እርስ በእርሳቸው እንዲዋደዱና እንዲከባበሩ የሚያስተምሩት የሃይማኖትና መንፈሳዊ መሪዎች፣ ጊዜያቸውን በትምህርት ቤትና በእርቅ ላይ የሚያሳልፉት ወጣቶች ናቸው፡፡
አሜሪካን ታላቅ ሀገር ያደረጋት ስራና ተግባር እንጂ ወሬና ፖለቲካ አይደለም፡፡ በሚያሳዝን ሁኔታ እኛን ኢትዮጵያዊያንን የሚጐዳንና ደሃ ሆነን እንድንቀር ያደረገን የፖለቲካ ንትርክ ነው:: የጋናው ፕሬዚዳንት በፕሪንስተን ዩኒቨርስቲ በቅርቡ ባደረጉት ንግግር፤ አፍሪካ ትልቋ የአለም የንግድ ቀጠና ልትሆን እንደምትችል ገልፀዋል:: በተጨማሪም ካላት ሃብት አንጻር የአፍሪካ ለአፍሪካ ንግድ በጣም ዝቅተኛ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡ ኢኮኖሚያችንን በአግባቡ መምራትና መመሪያዎቹንና መተዳደሪያዎችን ማሳለጥ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ የምንወዳት ሀገራችን ኢትዮጵያን ትንሽ ያደረጓት አሉታዊ ፖለቲካና የ1960ዎቹን ማርክሲስት ሌኒኒስት ፖለቲካ የሚያቀነቅኑ ፖለቲከኞች እንደ አሸን መብዛት ነው፡፡ በግሌ እንደታዘብኩት፤ ይህ የፖለቲካ አመለካከት የህዝባችንን አስተሳሰብ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የመረዘ ነው፡፡ እኛን ትንሽ የሚያደርገንና ድሃ አድርጐ የሚያስቀረን የፖለቲከኞቻችን መሰዳደብ ነው፤ ሙሉ እውቀት ሳይኖር አቋም የመውሰድ የፖለቲካ በሽታ ነው፤ ስልጣን የተጠሙና ምቀኛ ፖለቲከኞች ናቸው:: በአጠቃላይ የጊዜውን ሁኔታ ከእውነተኛው ፖለቲካ ጋር በማመዛዘን ለሀገር የሚጠቅሙ ጉዳዮች ላይ የሚታትሩ በሳልና ብልህ ፖለቲከኞች መጥፋት ነው ትንሽ ያደረገንና ደሃ አድርጐ ያስረቀን፡፡
እርግጥ ነው ከዚህ በፊት እንዳልኩት ፖለቲካ ዋጋ የለውም አይባልም፡፡ ፖለቲካን እንደ ፖለቲካ አንጠላም፡፡ እኛ የምንጠላው ስልጣን ለመያዝና ስልጣንን ለሚሊዮኖች መበዝበዣና ለጥቂቶች መጠቀሚያ የሚያደርገውን ፖለቲካ፣ ህዝብን ለመከፋፈልና ለማዳከም የሚደረግን ፖለቲካ ነው፡፡ መልካም ፖለቲካና መልካም ፖለቲከኞች ያስፈልጉናል፡፡ መልካም ፖለቲካ ህዝቦችን ማቀራረብ፣ ማግባባትና በሰላምና በፍቅር እንዲኖሩ ማድረግ አለበት፡፡ በህገ መንግስቱ የተደነገገውን የሰዎች ሰብዓዊ መብትን ያማከለ ፍትሐዊ ፉክክር ለመልካም ፖለቲካ አስፈላጊ ነው:: ህዝቦች ጥቅማቸውን የሚያስጠብቁ የፖለቲካ መሪዎችን በመምረጥ የወደፊት እጣ ፋንታቸውን መወሰን አለባቸው:: ለዛም ነው ጥሩ ዴሞክራሲ የሚያስፈልገው:: ስለሆነም ሽማግሌዎቻችን ፖለቲከኞቻችን ጠንካራ አገልጋይና እንዲሆኑ ህዝቡን የሚያበቃ መልካም ፖለቲካ እንዲያራምዱ መማፀናቸው ትክክል ነው፡፡ ከዚህ ደሃ ህብረተሰብ የወጡት የተማሩ ፖለቲከኞች የፖለቲካ ንግግር ብቻውን የተራቡትን እንደማይመግብ፣ ወጣቱን እንደማያስተምርና ሆስፒታሎችን እንደማይገነባ የማይገነዘቡት ለምን ይሆን? ለምንድን ነው ፖለቲከኞቻችን በቅድሚያ በትምህርት፣ በጤና እንዲሁም በኢኮኖሚ ልማት ዘርፍ አስተዋጽኦ በማድረግ ትሁት አገልጋዮች መሆናቸውን ቢያሳዩና የፖለቲካ ተፎካካሪዎቻቸውን ቢያከብሩ የበለጠ የተከበሩና የተወደዱ  የፖለቲካ መሪዎች መሆን እንደሚችሉ የማይገነዘቡት?
የፖለቲካ መሪዎቻችንን ማክበርና እንዲሳካላቸውም መመኘት አለብን፡፡ በርግጥም ለዚህ ነው ብዙ በሀገር ውስጥም በውጪም ያሉ ሰዎች እንደሚያውቁት፤ የኛ የሰላምና ልማት ማዕከል በጊዜያዊ የሰላም ኮሚቴነት በ1989 እ.ኤ.አ የተቋቋመውና ከፖለቲካ መሪዎቻችን ጋር ለሰላም መስፈን ያላሰለሰ፣ በአክብሮት የታጀበ ውይይት ለማድረግ ሲሞክር የነበረው:: በነዚህ ባለፉት 30 ዓመታት ሽማግሌዎቻችን በህዝቦቻችን መሃከል ሰላምና ፍቅርን ለማስፈን ያለሙ ውይይቶችን ከሁሉም የፖለቲካ መሪዎች ጋር ለማድረግ ሲመላለሱ በርካታ መስዋእትነቶችን ከፍለዋል፡፡
ልፋታቸውንም በተለያዩ ጊዜያት፣ በተለይም ከ1989 ዓ.ም እስከ 2012 ዓ.ም ባሉት አመታት ፍሬ አፍርቷል፡፡ እናም የፖለቲካ መሪዎቻችን በሰሙን ጊዜ አምላካችንን አመስግነናል፡፡
ጊዜያዊው የሰላም ኮሚቴ በ1989 ዓ.ም ከተቋቋመ በኋላ የመጀመሪያ የነበረው ስራው በ80ዎቹ የነበሩትን የግጭቱን ተዋንያን ለሁለትዮሽ ውይይት ወደ ዋሽንግተን ዲሲ ማምጣት ነበር (1989-1991)፡፡ ሽማግሌዎቻችን በ1991 በአዲስ አበባ አፍሪካ አዳራሽ ለተደረገው ሰላምና ዲሞክራሲያዊ ሽግግር ኮንፈረንስ አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡ በኢትዮጵያና ኤርትራ መሃል በመመላለስም ስለ ሰላም ታትረዋል (1998-2000)፡፡ በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዘመንም በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ እስረኞችን ለማስፈታት ችለዋል (2007-2012):: ከዚያም በኋላም እስከ ቅርቡ 2018 ዓ.ም ድረስ ሰ.ል.ማ በየ3 ወሩ መንግስትን ሀ) ከኤርትራዊያን ወገኖቻችን ለ) ከኦነግ፣ ኦብነግ እና ከሌሎች የፖለቲካ አካላትና ፓርቲዎች እንዲሁም በውጪ ካሉት የኢትዮጵያ ዲያስፖራ አካላት ጋር እርቅ እንዲፈጥርና ዘላቂ ሰላምን እንዲያረጋግጥ መወትወቱን አላቆመም፡፡
ሁሉም እስረኞች እንዲፈቱ፣ በጽንፈኛ ሃይማኖት መሪዎች መካከል ውይይትና እርቅ እንዲፈጠር፣ በምርጫ ወቅት በተለያዩ ፓርቲዎች መሃከል እርቅና ውይይት እንዲኖር እና አጠቃላይ የሰላም፣ የፍቅርና የእርስ በእርስ መከባበር መንፈስ በውዷ እናት ሀገራችን ይፈጠር ዘንድ ጥሪ ማስተላለፋችንን አላቋረጥንም፡፡ በሚያሳዝን ሁኔታ አንዳንዴ በበረሃ እንዳለች ብቸኛ ድምጽ የሆንን ያህል የተሰማን ጊዜም ነበር፤ በተለይ ከ2012-2018 ዓ.ም በነበሩ ጊዜያት ጩኸታችንን የሚሰማ ጆሮ አልነበረም፡፡
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይና ፓርቲያቸው እንዲሁም መንግስታቸው በህዝባችን መሃል ሰላምና ፍቅርን ሲያውጁና መሬት ያንቀጠቀጠ ለውጥ በቆራጥነት ሲያመጡ፣ የባልደረቦቼና የእኔ ትልቁ ተስፋችንና ህልማችን መሳካቱን ማየታችንን መናገር አያሻም፡፡
ለኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ሃይማኖትና ፖለቲካ ፓርቲዎች የሰላምን መለከት የነፉበትን፣ ከኤርትራ ጋር ሰላም ያወጁበትንና እስረኞችን የፈቱበትን ጆሮ - ግቡ ንግግራቸውን አደነቅን:: በሰኔ 19 ቀን 2018 ዓ.ም አንድ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣን “በቀጠናው ሰላምን ለማምጣት ያላችሁ ራዕይ በመልካም ሁኔታ ላይ ነው ያለው፤ ለእድሜ ልክ ጥረታችሁም እንኳን ደስ ያላችሁ፡፡” ብለው ሲጽፉልን ልባዊ ሃሴት ተሰማን፡፡
አሁን ግን እንደገና ስለ ብዙ ግጭቶች እየሰማን ነው፤ ባገራችን ስላለው ሞትና ውድመት እንዲሁም በማረሚያ ቤቶች ስለሚገኙ ብዙ ህዝባችን ስቃይ እየሰማን ነው፡፡ እንደገና ተከፍተናል፤ አዝነናል እናም የምንለው ጠፍቶናል፡፡ መቼ ነው ካለፈው የምንማረው? የሀገራችን ጤናና ብልጽግና፣ በትምህርትና በኢኮኖሚ እድገት፣ በብሔሮችና በሃይማኖቶች መሃል በሚፈጠር የእርስ በእርስ መከባበርና መፈቃቀር ላይ የተመሰረተ እንጂ በፖለቲካ ጨዋታና ዝረራ ወይም ለቁጣና ሞት አስተዋጽኦ በሚያደርገው ራስን እየኮፈሱ በሚጫወቱት የፖለቲካ ጨዋታ አለመሆኑን መቼ ነው የምንማረው?
ዛሬ አፍሪካ በምዕራቡ አለም በንቀት የምትታየው በኢኮኖሚ ጠንካራ ባለመሆኗ ነው፡፡ በተቃራኒው ግን አፍሪካ በተፈጥሮ ሃብት ከማንም በላይ ሃብታም ናት፡፡ በእርሻ፣ ቱሪዝም፣ ማምረቻ፣ ማዕድን ቁፋሮ፣ በውሃ ኤሌትሪክ ሃይል ማመንጫ፣ በፀሐይ ሃይል፣ በንግድ፣ በጠቅላላ ኢንዱስትሪና በፋይናንስ ቁጥር አንድ መሆን ትችል ነበር፡፡ ከፖለቲካ ይልቅ በስራና ኢንዱስትሪ ላይ ብናተኩር ኖሮ፣ ምርጥ ትምህርት ቤቶች፣ ሆስፒታሎችና ሆቴሎችን መገንባት እንችል ነበር::
እንዳለመታደል ሆኖ ግን በምዕራቡ አለም የተማሩትና ከአጠቃላይ የህዝብ ብዛታችን አንድ ፐርሰንት እንኳን የማይሞሉት መሪዎቻችን ትኩረታቸው ፖለቲካ ላይ በመሆኑና ያለንን ሃብት ለፖለቲካ ንትርክና መጠላለፍ ስለሚያውሉት ዛሬም ድሆች ነን፡፡
እንደ አለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይ ኤም.ኤፍ) ሪፖርት፤ ከ2000 እስከ 2012 ዓ.ም ድረስ ኢትዮጵየ በጂዲፒ ልኬት ከአለም 3ኛ ፈጣን ኢኮኖሚ የነበራትና ለኢኮኖሚ እድገትም መልካም ምልክት ማሳየት የጀመረችበት ወቅት ነበር፡፡ አሁን ግን የአለም ባንክ ሪፖርት እንደሚያሳየው በንግዱ ዘርፍ ከ190 ሀገራት መሃል 159ኛ ስንሆን፣ የንግድ ጉድለትም ጫና ተጭኖናል:: የኢትዮጵያ የኤክስፖርት ንግድ ከ2012 ጀምሮ እያሽቆለቆለ ነው፡፡ በሃምሌ 2019 በጀት አመት እንኳን የ170 ሚሊዮን ዶላር ቅናሽ አሳይቷል:: ከቀደመው በጀት ዓመት ጋር ሲነፃፀርም በ9% ቀንሷል:: ዛሬ የህዝባችን 23% ያህሉ የቀን ገቢያቸው ከአንድ የአሜሪካ ዶላር በታች ነው:: ወደ 6.4 ሚሊዮን የሚጠጉት በተመጣጠነ ምግብ እጥረት የተጐዱ ናቸው:: ምግብና ውሃ ወለድ በሽታዎችን፣ ወባን እንዲሁም ተቅማጥን ባፋጣኝ ማስወገድ አለብን:: የጤና ተደራሽነትንና ንጽህናን ማሻሻል አለብን፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ወደ 60% የሚሆነው ህዝባችን ማንበብና መጻፍ አይችሉም፤ እድሜያቸው ለትምህርት ከደረሱ ህጻናት መካከል 31% ብቻ ናቸው ወደ ትምህርት ቤት የሚሄዱት:: የአለማቀፉ የምግብ ድርጅት (ደብሊው ኤፍፒ) ከህጻናቱ ውስጥ 38% የቀነጨሩ፣ 45% ደግሞ ባግባቡ ያልተመዘገቡ እንደሆኑ ግምቱን አስቀምጧል፡፡
ደግነቱ ጠንካራ ባህላዊና ኢኮኖሚያዊ መሰረት አለን፡፡ ስለሆነም ባገራችን አሁንም ደማቅ የተስፋ ብርሃን አለን፡፡ ለዚህም ነው ታላቂቱ ኢትዮጵያ ተፈጥራ ማየትን የምንሻ ሁሉ ተስፋ የማንቆርጠው፡፡ ደግ፣ ትሁት፣ ወዳድ፣ ለጋስ፣ አክባሪና ታታሪ በሆነው ህዝባችን ውስጥ ትልቅ ወረት አለን፡፡ ወደ ጥንት ዞር ብለን ያየን እንደሆነ ሴሚቲኮቹ፣ ኩሺቲኮቹ፣ ኦሞቲኮቹ፣ ናይሎቲኮቹና ሌሎቹም ብዝሃነት ያላቸው ህዝቦቻችን ለቀደመው የእርሻ፣ የጽሑፍ፣ የስነ ህንጻና የተለያዩ የአለም ስልጣኔዎች ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡ የግሪክና ሮማዊያን ታሪክ ፀሐፊ የነበረው ዲዎዶሮስ ሲኩለስ (መጽሐፍ 3) ከክርስቶስ ልደት በፊት በአንደኛው ምዕተ ዓመት “ኢትዮጵያዊያን” ብሎ ስላላቸው ህዝቦች በዝርዝር ሲጽፍ፤ “የመጀመሪያዎቹ የሰው ልጆች” ከማለቱም በላይ ጥንታዊያኑ ግብጻዊያን የነሱን በአማልክት የማመን ስርዓት፣ የተደራጀ የፖለቲካ ስርዓትና የተለያዩ ባህሎቻቸውን እንደወረሱ ጽፏል፡፡ ከኛ ጋር ስለሚዛመዱ ህዝቦች ነበር የሚናገረው:: ምንም እንኳን ዛሬ የማያባራ ግጭትና አፍራሽ ፖለቲካ ታሪካችንን ቢያጠለሸውም፣ የኛ ህዝቦች በታሪክ የሚታወቁት ሌሎች በሰላምና በአብሮነት እንዲኖሩ አርአያ ሆነው ነው፡፡
የፖርቱጋሉ ሂዩማኒስት ኤራስመስ ደቀመዝሙር የነበረው ሞሬስክ፤ በ16ኛው ክፍለ ዘመን ፌዴስ ሬሊጂዮ በተባለው መጽሐፉ ውስጥ “ኢትዮጵያ የሃይማኖት መቻቻል ያለባት ምድር” እንደሆነች ገልጿል፡፡ ከኢትዮጵያ ጋር በማነጻጸርም የራሱን አውሮፓ እንኳን የሃይማኖት መናናቅ እንዳለባት አንኳስሶ ጽፏል:: ዛሬም እንዟን የህዝባችን 99% በሰላም አብሮ መኖርን ይሻሉ፡፡ ለቤተሰቦቻቸው በትምህርት፣ በጤናና በብልጽግና የተሻለ ኑሮን ይፈልጋሉ:: ከስድስት መቶ ዓመታት በፊት የተጻፈው መጽሐፈ ብርሃን እንኳን “ሁሉም የኢትዮጵያ ህዝቦች እውቀትን ተጠምተዋል” ይላል፡፡ ስለዚህ ጉልህ የሆነ የባህልና ታሪካዊ ውርስ አለን፡፡
በኢኮኖሚ በኩል ብዙ ተፈጥሯዊ ሃብት አለን፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ የማዕድን ቁፋሮ ስራ በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን እንኳን ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ዛሬ በአለም ኢኮኖሚ ውስጥ የኢትዮጵያ የማዕድን ንግድ ኢምንት ነው፡፡ ባለፉት 20 ዓመታት ለምሳሌ የማዕድን ንግድ ለጂዲፒው ያለው አስተዋጽኦ ከ1% ያነሰ ነበር፡፡ የተለያዩ ህትመቶች እንደሚያመለክቱት፤ በኢትዮጵያ ውስጥ ለንግድ በሚሆን መጠን ወርቅ፣ ፕላቲኒየም፣ ኦፓል፣ አልማዝ፣ ሳፋየር፣ ከፍተኛ ደረጃ ያላቸው የከበሩ ድንጋዮች፣ ሊቲየም፣ ጂፕሲም፣ ማንጋኔዝ ኦር፣ ክሮም፣ ታንታለም፣ ኖራ፣ ሲሚንቶ፣ አሸዋ፣ ሸክላና የሸክላ ምርቶች፣ ፌልድስፓሮችና ኢንሃይድራይት፣ አለቶችና ጠጠሮች፣ እምነበረድ፣ የማዕድን ውሃ፣ በሃ ድንጋይ፣ ከሰል፣ ባልጩት፣ ብረት፣ ቤንቶናይት ፐርላይት፣ ዳይቶማይት፣ ሃይላይትና ነዳጅ ዘይት ይገኛሉ፡፡ በኢትዮጵያ ይገኛሉ ተብሎ ከሚታመኑ ሌሎች ማዕድናት ውስጥም ኒኬል፣ ብረት፣ ክሮሚየም፣ ዘይት፣ ከሰል፣ ዩራኒየም፣ ሰልፈር፣ አስቤስቶስ፣ ማይካ፣ ጋርኔት፣ ሞሊብዴናይትና ቫንዳኒየም ይገኙበታል:: አንድ ኒውጀርሲ የሚገኝ የነዳጅ ኩባኒያ ቦርድ አባል የሆነ የግል ጓደኛዬ እንደነገረኝ፤ ምናልባት ከአለም ትልቅ የሆነና ወደ አንድ ትሪሊየን ከግማሽ ኪዮቢክ ጫማ የሆነ መጠን ያለው የተፈጥሮ ጋዝ በምስራቅ ኢትዮጵያ ውስጥ እንዳለ ባንድ የብሪታንያ ኩባንያ ሪፖርት ተደርጓል፡፡ ከዚህም በላይ የፀሐይና የንፋስ ሃይልን ጨምሮ ኢትዮጵያ መጠነ ሰፊ የውሃ ኤሌክትሪክ ሃይል የማመንጨት አቅም አላት፡፡
በአጭሩ በመልካም አስተዳደርና ያላሰለሰ ጠንካራ ስራ ታጅበን የሀገራችንን የማዕድን ሃብት ብንመረምር፣ ኢትዮጵያ ከአለም ሃብታም ሀገራት ተርታ ትሰለፍ ነበር፡፡
በዋነኛነት ኢትዮጵያ ትልቅ የግብርና አቅም አላት፡፡ በ2010 ገደማ አዲስ አበባ ላይ ያገኘሁት አንድ የኬንያ መንግስት ሚኒስትር እንደነገረኝ፤ በኬንያ ለእርሻ የሚውለው መሬት ከ12% እስከ 15% ብቻ ሲሆን አብዛኛውም ለእርሻ ውሏል:: በኢትዮጵያ ግን 60% አካባቢ ከሚሆነው ሊለማ የሚችል መሬት ውስጥ ከ20% በታች የሆነው ነው የለማው፡፡ በ1970ዎቹ በሃርቫርድ በማስተምርበት ወቅት አንድ የተከበረ ፕሮፌሰር፤ ምንም እንኳ አሜሪካ በኬሚካል፣ ኤሌክትሪካል፣ በማዕድን ቁፋሮ፣ በአልባሳትና ሌሎች ተመሳሳይ ኢንዱስትሪዎች ከአለም ቀዳሚ ብትሆንም ትልቁ ሃብቷ ግን ከግብርና እንደሚገኝ ሲገልጽ በጣም ተገርሜ ነበር፡፡ የኛ ዋና ጠላታችን ሞሶሎኒ እንኳን “ኢትዮጵያ ለአውሮፓ የዳቦ ቅርጫት ትሆናለች” ማለቱ ይነገራል፡፡ ብዙ የፍራፍሬ ዛፎች ብንተክልና ትኩስ ፍራፍሬዎችን ለአውሮፓ ብቻ በቀዝቃዛው ወቅታቸው ብንልክ ብዙ ሚሊየን ዶላሮች ልናገኝ እንችላለን (ይሄንን ከመታት በፊት ከአንድ የአለም አቀፍ ምግብና ግብርና ድርጅት (ፋኦ) ኤክስፐርት ነው የሰማሁት)፡፡ የአለምን ህዝብ መመገብ የሚችሉ የግብርና ምርቶች ማምረት እንችላለን:: ከዚህም በተጨማሪ ሀገራችን በቱሪዝምም ከፍተኛ ደረጃ ሊያስመዘግቡ ከሚችሉ ሀገራት አንዷ ናት፡፡ የመስተንግዶ ዘርፉ ሊጐመራ ይችላል:: ኢንቬስተሮችም የውጪ ካፒታል ይዘው እንዲመጡ ሊሳቡ ይችላሉ፡፡
ስለሆነም አንድ ቀን ከጥቃቅን የፖለቲካ ንትርክ ወጥተን በኢኮኖሚ የበለፀግንና የተሳካልን ሀገር እንደምንሆን ተስፋ አለኝ፡፡ ያኔ ነው በኩራት የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ መሆናችንን መናገር የምንችለው፡፡ ዛሬ ላይ ህይወታችንን የተጫነን የፖለቲካ ቁርሾና ቁርቁስ ማቆም አለበት፤ እንዲህ ያለ መከፋፈል (ልዩነት) በሽታ ነው፡፡ የነጋችን መሰረት የሆኑትን ወጣቶች ማሳሳት ማቆም አለብን፡፡ ፖለቲካን ሳይሆን ጥሩ ትምህርትን፣ የኢኮኖሚ ዕድገትንና የተቀላጠፈ ልማትን ማስቀደም ይገባናል፡፡ ችግሮቻችንን፣ የህዝባችንን ብዝሃነትና ሃይማኖታዊ
አስተዋይነት ከግምት ውስጥ ያስገባ ርዕይ ያለው አስተዳደር ሊኖረን ይገባል:: ኢኮኖሚያችንን እንገንባ እንጂ ቀን ተቀን በሚፈጠሩ ንትርኮች አንዘናጋ፡፡ ተግዳሮቶቻችንን እናሸንፍ እንጂ አንዳችን ባንዳችን ላይ አንነሳ:: የጋራ ሰብአዊ አንድነታችንን በመፈለግና በአብሮነት የያንዳንዳችንን ባህላዊ እሴቶች በማክበር ለህይወት ዋጋ እንስጥ፡፡ እኛ ትልቅ ሀገራዊ ሃብት ያለን ጥንታዊ ህዝቦች ነን፡፡ በተደጋጋማ ታዳጊ ሀገር ልንባል ሳይሆን ያደገ ሀገር መባል አለብን:: ህዝባችን ህይወትን፣ ነጻነትንና ብልጽግናን እንዲመርጥ ጥሪዬን አቀርባለሁ፡፡
የብልጽግናችን መሰረት ሰላም መሆን አለበት፡፡ የኛ ተግዳሮቶች ረሃብ፣ ደካማ የጤና አገልግሎትና ስርዓት፣ ወባን የማጥፋት፣ በምግብ ራስን የመቻል፣ መጠለያና መሃይምነት ናቸው:: እነዚህን ተግዳሮቶች ለማሸነፍ የፖለቲካ ጭቅጭቅ ሳይሆን የሰላም ባህል አስፈላጊ ነው፡፡
ዩኒቨርስቲ ስለተማሩ በርግጠኝነት ስራ አገኛለሁ ማለት አይቻልም፡፡ ነገር ግን የዩኒቨርስቲ ትምህርት የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም ግጭት መቀስቀሻ መሆን የለበትም፡፡ የተረጋጋ ፖለቲካ፣ ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት የሚረዳ የክህሎት ትምህርትና ለብልጽግና የሚያስጠጋን የቴክኖሎጂ እድገት እንፈልጋለን:: በሰው ሃብት ልማት ላይ ኢንቬስት ማድረግ እንጂ ግጭትን በሚያፋፍሙ የፖለቲካ እሰጥ አገባዎች ጊዜያችንን ማባከን የለብንም፡፡ እንደ አንዳንድ ፖለቲከኞች ትንሹን ሳይሆን ለትልቁ ማሰብ የግድ ይለናል፡፡
ወዳጆቼ፡- እኛ ኢትዮጵያዊያን በእውነት ምንድን ነው የምንፈልገው? የሚናገሩት ቋንቋ ምንም ይሁን ምን ለተራቡት በሚሊየን የሚቆጠሩ ህዝቦቻችን ምግብ ወይስ ስለማያውቋቸው የምዕራቡ አለም የፖለቲካ ርዕዮተ አለሞች እየታበዩ ለሚነግሩን ጥቂት ፖለቲከኞች የሚሆን ስልጣን? በሚሊዮኖች ለሚቆጠረው በሽተኛ ህዝባችን የሚሆኑ ሆስፒታሎችና መድሃኒት ወይስ ለጥቂቶቹ ልሂቃኖቻችን የሚሆኑ ዘመናዊ ልብሶችና ቅንጡ ቤቶች? ለሚሊዮኖቹ ህጻናቶቻችን ትምህርት ወይስ የውጪ ቋንቋዎች እውቀታቸውን ለሚቸረችሩብን ጥቂት ሰዎች የደለበ የባንክ ሂሳብ?
ሰላም ብልጽግናን፣ ፍቅርንና ደስታን ያመጣል፡፡ የእርስበርስ መከባበር ጥንካሬንና ሃብትን ያመጣል፡፡
ይህን መልእክት የምጽፈው ጨረቃ ላይ ሆኜ ቢሆን ኖሮ፣ ያችን ትንሽ ጐረቤታችንን ለመርገጥ የመጀመሪያው የሆነው አለን ሼፓርድ ከብዙ አመታት በፊት በተናገረው ንግግር እጀምር ነበር:: ንግግሩን ጠቅለል አድርጌ ሳቀርበው እንዲህ ይላል፡-
“ከዚህ ላይ ሆኜ አዘቅዝቄ ሳይ የውቅያኖስን ትንሽ ሰማያዊ፣ የአለምን ኮፍያዎች ትንሽ ነጭ እንዲሁም የመሬትን ትንሽ ቡናማ አያለሁ፡፡ ምድር ከዚች ጨረቃ በብዙ ጊዜ ትገዝፋለች:: ነገር ግን ከጨረቃ ላይ ተሁኖ ስትታይ በጣም ትንሽ ትመስላለች፤ ልክ እንደ ትንሽዬ ኮከብ፡፡
ታዲያ እዚያ ታች ያሉት ሰዎች በሰላም መኖር ለምን ተሳናቸው?”
***
ኤፍሬም ይስሃቅ የኢትዮጵያ ሽማግሌዎች ሰላምና ልማት ማዕከል መስራችና የቦርድ ሰብሳቢ ሲሆኑ በኒውጀርሲ በሚገኘው ፕሪንስተን ዩኒቨርስቲ የሴሚቲክ ጥናት ኢንስቲቲዩት ዳይሬክተር ናቸው፡፡ በፕሪንስተን ዩኒቨርሲቲ የበትለር ፌሎውም ናቸው፡፡ እንደ ሃርቫርድ የሽልማት ማስታወቂያ ፕሮፌሰር ይስሃቅ “በ1969 ገና በማቆጥቆጥ ላይ በነበረው የሃርቫርድ ዩኒቨርስቲው የአፍሮ አሜሪካን ጥናት የትምህርት ክፍል የመጀመሪያው ተሿሚ መምህር ነበሩ፡፡ በዚህም የተነሳ በትምህርት ክፍሉ ቀደምት ታሪክ ውስጥ ጉልህ ሚና ነበራቸው፡፡ እየተንሰራራ ለነበረው የትምህርት ዘርፋቸው በነበራቸው ቁርጠኝነት እስከ 1977 በአስተማሪነት አገልግለው በዛን ወቅት ገብተው ከነበሩት ተማሪዎች ውስጥ ግማሽ ያህሉን አስተምረዋል፡፡ በሃርቫርድ በነበራቸው ቆይታ (1969-1977) በአፍሮ - አሜሪካን ጥናት የትምህርት ክፍል በነበሩ ተማሪዎች በየአመቱ ምርጡ አስተማሪ እየተባሉ ይመረጡ ነበር፡፡ ዛሬ በአፍሪካ ቋንቋዎች ምጡቅ የሆነ ችሎታ ላላቸው የሃርቫርድ ተመራቂ ተማሪዎች “የኤፍሬም ይስሃቅ የአፍሪካ ቋንቋዎች የላቀ ችሎታ ሽልማት” ይበረከታል፡፡       

Read 942 times