Print this page
Saturday, 11 January 2020 12:27

የገብረክርስቶስ ደስታ ሥዕል!

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(1 Vote)

  ብሩሽና ብዕር ባንድ እጁ ጨብጦ፣ የጥበብን ጣዕም ያቃመስን ገብረክርስቶስ ደስታ፣ በገጣሚነቱ ሙዚቃ፣ በሰዓሊነቱ ቀለም የሚደመጥበት ይመስላል፡፡ ግጥሞቹ ውስጥ የሙዚቃ መሣሪያ፣ በሥዕሎቹ ነፍስ ውስጥ ምስል መፍጠር ይወዳል፡፡ ስለዚህም ይመስለኛል ምሠላዎቹ የስሜት ሕዋሳታችንን የሚቆነጥጡን!
ሣቅና ልቅሶው ጥልቅ፣ ዝምታው ሸለቆ ነው፡፡ ምናቡ የሩቅ ተጓዥ ነገር መዛዥም ነው፡፡ ፍልስፍናው የዘመኑን ቀለም ያጠቀሰ፣ አንደበቱ የማይፈራ፣ ቃሉ ደፋር ነው፡፡ “መንገድ ስጡኝ ሰፊ” የሚለው መጽሐፉን የፈተሸ ሰው፤ ገጣሚውንና ሰውየውን ገብረክርስቶስን በልኩ መረዳቱ አይቀርም፡፡ የልብ ስስነት፣ የሰዎች ናፍቆት፣ የሀገር ረሃብ፣ የጥበብ ግልቢያ፣ የቀጠነ መንገድ፣ የወፈረ ህልም ያለው ይመስላል፡፡
ሙዚቃ፤ የግጥም ልደት - ጓደኛ፣ የገጣሚ እንዝርት ለመሆኗ፣ ብዙ ቦታ፣ በብዙ የህይወት ገፆች፣ በተለያዩ የቃላት ነበልባል ገልጿታል፡፡ ሥዕልን በቀለም፣ በአረንጓዴ፣ ቢጫ፣ በመስክ፣ በተራራ፣ በመስከረም ምሥል ተርኳታል፡፡ ሥዕልን በግጥም ሲወዘውዛትም እናያለን፡፡ ግን በጣም ሩቅ፤ በጣም በጥልቀት ዐይኖቹን የሰደደ፣ ነፍሱን የኳላትም ይመስላል፡፡ ለነገሩ ግጥምን “A memorable speech” ይላት የለ!
አያልቅም ይህ ጉዞ…
ማስመሰል - መተርጐም
በቀለም መዋኘት፣     
    በመስመር መጫወት፣
    ከብርሃን መጋጨት፣
ለማወቅ ለመፍጠር ባዶ ቦታ መግባት
መፈለግ …..መፈለግ…
አዲስ ነገር መፍጠር፡፡
በዚህ አርኬ ቋንቋ፣ ሥዕል ጉዞ ነው፤ ግን መጨረሻ የለውም፡፡ አንድ ሰዓሊ ይጓዛል፣ ሳይደርስ ይሞታል፡፡ ሌላውም ሰዓሊ ሥዕል ይጀምራል፤ ሳይጨርስ ይጓዛል:: ይጓዛል… ይጓዛል…ይጓዛል፡፡ አያልቅም፣ ሥዕል ሕይወት ነው፤ ሕይወት ጉዞ ነው:: ማንም ጀምሮ አይጨርሰውም:: ማንም አገላብጦ አይደርስበትም፡፡ በውበቱ ተማርኮ፣ በአስጠሊነቱ በሽቆ፣ ተርኮ፣ ጠርዞ አይደመድመውም፡፡ ሕይወት መልኳም እንደ እስስት ነው፤ ይቀያየራል፣ ታሥቅና ታስለቅሳለች፡፡ ድንኳኗ ውስጥ ሺህ ዋንጫዎች አሏት፤ የማይቆጠር ዝባዝንኬ፤ ተነግሮ የማያበቃ ታሪክ፤ የማይፈታ እንቆቅልሽ! ሰዓሊው ብዕሩን ይዞ፣ ትንፋሹን ቋጥሮ የሚሮጠው በዚህ መም፣ በማያልቀው ሜዳ ነው፡፡
ሕይወትን ለማስመሰል ይጥራል፤ ለመተርጐም ይቆፍራል፡፡ እንዳለ ለማሳየት፣ አሳይቶ ለመተርጐም ይደክማል፣ ይደክማል፣ ይደክማል፡፡ የሚያስመስለው በቀለም ነው፤ ስለዚህ ይዋኛል፡፡ በቀለም ውስጥ ሲዋኝ ደግሞ የራሱ መልክ ይጠፋዋል፤ ሰዓሊው የለም፡፡ ቀለም ውስጥ ተነክሮ ሲቀዝፍ ራሱን አይመስልም፤ በሥዕሉ አብዶ፣ በህልሙ እየደከረ ነው፡፡ ህልሙ አዲስ፣ ይሁን የተቀዳ፣ እዚያ ውስጥ ይባዝናል:: በመስመር ያወራል፣ በመስመር ይጫወታል፤ ከመሀል ወደ ዳር፣ ከዳር ወደ መሀል!...ከመስክ ወደ ጅረት፣ ከጅረት ተራራ፤ ከረቂቅ ወደ ተጨባጭ፣ ከተጨባጭ ወደ ረቂቅ፣ ይሄዳል፡፡ ከጨለማ ሳይሆን ክብርሃን ይጋጫል፡፡ ብርሃን - ጨለማን ይወጋል፤ ጨለማ፣ ህያው መሆን ሲሳነው ጥላ ይፈልጋል፡፡ በአካል ይደበቃል፤ በቁሳቁስ ይሠወራል፡፡ ሰዓሊው ያሳድደዋል፤ ያባርረዋል፡፡
ለማወቅ ለመፍጠር ባዶ ቦታ መግባት
መፈለግ…መፈለግ…
የገጣሚው ዓለም፣ የግጥም ባህርያት አንዱ ዘለላ ምናባዊነት ነው፡፡ እዚህ ጋ በምናብ ዕውቀት ፍለጋ፣ ያልተገኘ ታሪክ፣ ያልታየ አለም፣ ለማምጣት ሰዓሊው ስም - ድረ ገጽ ይሰወራል:: ይፈልጋል …ይፈልጋል፡፡ ሰው ብቻ አይደለም፡፡ ጽጌረዳ አበባ፣ የተሳለች እሾህ፣ ጥፍሩን የመዘዘ ጥላቻ፣ የሚያማልል የፍቅር ዛላ፣ የሳቅ ቀለም፣ የእንባ ጅረት፣ ትዝታ የሌለው ቀን፣ የሚደንስ ሬሣ፣ የደረቁ ወንዞችን ድምጽ! ምትሃትና ምትሃት!
አዲስ ነገር መፍጠር፡፡
ለዓለም አዲስ፤ ለሰው አዲስ፡፡ ያልተሸተቱ መዓዛ፣ ያልታየ  ውበት፣ ብርሃን አልባ ኮከብ፡፡
ከማይታየው ጋር ሄዶ መነጋገር፣
ሕይወትን መጠየቅ፣
ሐሳብን መጠየቅ፣
ዓለምን መጠየቅ
መሄድ ፣ መሄድ፣ መሄድ…
ከጨረቃ በላይ፣
    ከኮከቦች በላይ፣
    ከሰማዩ በላይ፣
መጓዝ ወደሌላ----ባዶ ቦታ መግባት፡፡
ከመላዕክት ጋር፣ ከሰማይ አጽናፋት፣ ከማይተኙ ነፍሶች፣ ከዜማ አልባ መዝሙሮች ሕይወትን መጠየቅ፣ ብዙ ፍልስፍና፣ የቀጠኑ ክሮች፣ የጠነኑ ሃሳቦች፣ መጠየቅ፣ መጠየቅ፤ ዓለምን መጠየቅ፣ ውስጧን ፈትሏን ማየት:: የጥለቷን ውበት፣ የጽልመቷን ድምቀት፣ የሳቆቿን ጉንጉን፤ የእሸቷን ዛላ፤ የዝምታዋን ውፍረት፣ የቀንበሯን ሕመም - መጠየቅ… መጠየቅ… መጠየቅ!
ይህ ሁሉ ግን በቀለም ነው፤ በብሩሽ ነው:: በሸራው ምድጃ ላይ መጥበስ፣ መቀቀል፣ መቀባት፣ ማሳሳት፣ ማወፈር፡፡ የራበውን ዐይን መጥራት፣ ከበሮ መደለቅ፣ ነጋሪት መጐሰም፣ ምስጢሯን ማሳበቅ፣ መፈተሽ… መፈተሽ፡፡
ሰዓሊ ባለ ምናብ ነው፤ እንደ ገጣሚው፣ ገጣሚው በቃላት፣ ሰዓሊው በብሩሹ ከንፈር!! ሙዚቃና ቅኔ! የነፍስ ዳንስ ውበት! ጥያቄ… ጥያቄ… ጥያቄ፡፡
“አያልቅም ይህ ጉዞ” - ድንበሩ ዘላለም ነው:: ዘላለም ድንበር የለውም፡፡ ዘላለም ባንዲራ የለውም፡፡ ዘላለም ድፍን ፍሬ ነው፡፡ ዘላለም ቁመናው ግምት ነው፡፡ ቀኖቹ ሥንጥሮች ናቸው፡፡ ጫማው የሰው ምናብ ነው፤ ጉዞው ፍተሻ ነው፡፡ ቀለሙ ውቅያኖስ ነው፤ አያልቅም፤ አይደርቅም፤ መንገደኛ ነው፡፡
መሄድ ነው - መሄድ ነው፡፡
መሄድ፣ መሄድ፣ መሄድ…
ተሂዶ አይደረስም፡፡ ደርሶ መቆም የለም:: አዳም ሄዶ ሄዶ ቆሟል፡፡ ሔዋንም ቆማለች፡፡ ማቱሳላም ቆሟል፡፡ ከጨረቃ በላይ
ከኮከቦች በላይ፣
ከሰማዩ በላይ፣
መጓዝ ወደሌላ - ባዶ ቦታ መግባት፡፡
ከብርሃን ምንጮች በላይ መሄድ፤ ወደምንም የትም! ከሰማይ በላይ፤ ከዚያም በላይ፣ ክልክል የሌለበት፤ መንግስት የሌለበት፡፡ ሀገር የሌለበት፣ ፖሊስ የሌለበት፣ ምንም የሌለበት፡፡ ምንም ምንም! ወደ ሌላ ቦታ!...ዝም ብሎ መጓዝ፡፡ ጠረፍ ጠባቂ የለም፡፡ ፓስፖርት አይጠየቅ! ዜግነትም የለም፤ ሰዓሊው መብቱ ነው፤ የህይወቱ መንገድ - የነፍሱ ምርጫ ነው፡፡ በሥዕል ውስጥ በአየር ላይ፣ ያለ ሞተር፣ ያለ ክንፍ፣ ዝምምም ብሎ መሄድ! ወደ ሌላ ቦታ! ዝም ብሎ መግባት፡፡ ጥያቄ… ብቻ፤ ወደፊት ብቻ!..ትናንትም ዛሬም፡፡
የብርሃነ ሥላሴ ከበደ ግጥም፤ የትናንቱን ርዕዮት በስንኞቹ እንዳጣቀሳቸው፤ የገብሬ ግጥም ቀለም አጥቃሹን ጉዞ ወረቀት ላይ ፈትፍቶታል፡፡
ከባዕድ ሰማይ ስር
ጉም እንደጨለፈ፣
የነሌኒን ምርኮ
ያ ትውልድ አለፈ፡፡
አወይ ምስኪን ቧጋች
ሕልሙን የተቀማ
ራዕይ መሣይ ቅዠት
ደጋግሞ እየሰማ፡፡
መልስ አልባ ጥያቄ
ከንቱ እንደጠየቀ
ይኼኛውም ያልፋል
ከራሱ እንደራቀ፡፡
የገብረክርስቶስ ግጥም ጩኸቱ ይሄ ነው፤ የዜማውም ድንበር ያ ነው፡፡ መሄድ ብቻ! ጀምሮ… አለመጨረስ! ቋጭቆ ያለማብቃት:: ፈልጐ ያለማግኘት፤ ግን መፈለግ… መፈለግ… መፈለግ፡፡ እንዳለፈው ትውልድ፣ የያዙትን ዘር ድንጋይ ላይ በትኖ፣ እርቃን እርሻን ማንበብ! በደም ውስጥ መጫወት! ሥዕል እንደዚያ ነው፡፡ በነፍስ መቃተት፡፡
    በሐሳብ መደበቅ፣
        መፈለግ…ማስገኘት፡፡
    አያልቅም ይህ ጉዞ፡፡
ድብብቆሽ…አኩኩሉ…ፍለጋ…መፋጠጥ!- መዳማት…መጋጨት! ከብርሃን - ከሰማይ…ከህይወት! በብሩሽ - በቀለም - በዜማ!
የገብረክርስቶስ ደስታ “ለሥዕል” አጭር ግጥም፣ የማያልቅ ጉዞ መዝሙር፣ የህይወት ጓሎች ፈትል ናት፡፡ ዝብርቅርቁን ዓለም፣ በተኳለ ዐይን ለመፈተሽ ቅንድቧን የከረከመች ውብ!
ዐሰነኛኘቷ ግሩም ነው፡፡ የሕይወትን ደረት ለማየት አዝራሮቿን መፈልፈል የጀመረች ናት:: እሰየው!!   

Read 1923 times