Print this page
Saturday, 11 January 2020 12:31

በሃሳብ መንገድ ላይ

Written by  ተመስገን
Rate this item
(1 Vote)

  ሰውየው በሺ ከሚቆጠሩት የእምነት ክፍሎች ያንደኛው ‹ፓስተር› ነበር፡፡ ‹ነቢያችን› እያሉ ይጠሩታል፡፡ ‹አጋንንት ያስለቅቃል፣ ሕሙማን ይፈውሳል› በማለት የሚመሰክሩለት ብዙ ናቸው፡፡ እሱ ግን ከዛም በላይ ሃይል እንዳለው ይሰማዋል - ሙታንን የማስነሳት፡፡ ‹‹እግዜር በህልሜ ተገልጦ ለዚህ ተግባር እንደ ተመረጥኩ ነግሮኛል›› ባይ ነው፡፡ እንደ ዕድል ሆኖ ይህን ችሎታውን የሚያሳይበት አጋጣሚ ድንገት ብቅ አለለት፡፡… በየሶስት ዓመቱ በታላቁ ስታዲየም የሚዘጋጀው ታላቅ ጉባኤ፡፡
የዚያን ቀን ፓስተራችን ስለ ታላቁ አምላክ ሃይልና ስልጣን በታላቅ መንፈስ ሰበከን:: ቀጥሎም ሙታንን የማስነሳት ተዓምር እንደሚከናወን አበሰረን፡፡ አዳዲስ አማኞች እንዳይደናገጡ ካሳሰበ በሁዋላም…
‹‹ከናንተ መሃል ሞቶ መነሳት የሚፈልግ እጁን ያውጣ›› ሲል ጠየቀ፡፡ በሺ የሚቆጠሩ ሰዎች ብድግ አሉ - ‹‹…‹እኔ!›፣ ‹እኔ!›… እያሉ፡፡ አራት የተመረጡ ምዕመን ወደ መድረኩ ወጡ:: ፓስተሩም ያዘጋጀውን መሳሪያ አስመጥቶ በየተራ ገደላቸው፡፡ ከአፍታ ጸጥ፣ እረጭ በኋላ ወደ መጀመሪያው አስከሬን ጣቱን ቀስሮ፡- ‹‹በየሱስ ስም ተነስና ቁም!›› በማለት አዘዘ፡፡… አልተነሳም፡፡ እንደገና ድምፁን ከፍ አድርጎ ተናገረ፡፡ አልተንቀሳቀሰም፡፡ ‹‹ምናልባት ዱዳ የነበረ ሰው ይሆናል›› … ሲል አሰበ፡፡ ወደ ሁለተኛው ሟች ተጠግቶ እንደ በፊቱ ተጣራ፡፡… አልሆነም፡፡ ሶስተኛውንና አራተኛውንም ሞከረ:: ያው ነው:: ሽጉጡን ወደ ራሱ አዙሮ ቃታ ሳበ፡፡ እሱም አልሰራም፡፡ ጥይቱ አልቋል፡፡ የተኩስ ድምፅ የሰሙ በጥበቃ ላይ የነበሩ ፖሊሶች ባይደርሱ ኖሮ፣ ‹ነቢያችን› እንደ ማርያም ጠላት ተቀጥቅጦ ይሞት ነበር - በተከታዮቹ፡፡… እንደ ሞሶሎኒ፡፡… ወስደው አሰሩት፡፡ እስር ቤት እያለ አንድ ቀን እግዜርን ህልሙ ውስጥ አገኘው፡፡
‹‹ምነው ‹ጉድ› አደረግኸኝ?››
‹‹ምን አጠፋሁ?››
‹‹ሙታንን ታስነሳለህ ብለኸኝ አልነበር?››
‹‹በደንብ እንጂ!››
‹‹ታዲያ ምነው አቃተኝ?››
‹‹የአንተ ጥፋት አይደለም››
‹‹ያንተ ነው?››
‹‹የኔም አይደለም››
‹‹እና?...››
‹‹… ጥፋት ሳይሆን ፍላጎት ነው፡፡… የመብት ጉዳይ!››
‹‹ማለት?››
እግዜር ትንሽ አሰበና የሆነውን ነገረው፡፡
‹‹ኦኬ፣ ኦኬ… አይሲ›› አለ ፓስተሩ… በመደነቅ፡፡ ‹‹… ታዲያ እኔ መታሰር አለብኝ?›› ለማለት አፉን ከመክፈቱ ባነነ፡፡ … የሆነው ነገር ምን ነበር?
* * *
ካለፉት ሳምንታት ባንደኛው አዲስ አድማስ ርዕሰ አንቀጽ ያደረጋት አሪፍ ‹ታሪክ› ነበረች፡፡… ሰውየው ያጠፋው ወይም የበደለው ነገር የለም:: ሌሎች ሰዎች ግን ወደ እሱ እየጠቆሙ ‹‹እሱ ነው፣ እሱ ነው!›› በማለት ጣታቸውን ቀሰሩበት:: ሰውየውም መንገደኞቹን እየተመለከተ ‹‹ምናልባት ያጠፋሁትን ረስቼ ይሆናል እንጂ ይኸ ሁሉ ሰው እንዴት ይሳሳታል?›› በማለት አሰበና በማያውቀው ነገር ራሱን ጥፋተኛ አደረገ፡፡
ወዳጄ፤ ኢ-ፍትሃዊ በሆነው ቶታሊቴሪያን (Totaliteriam) ሥርዓት፤ እንደ ራስህ ሳይሆን እንደ ሌሎች እንድታስብ ትገደዳለህ፡፡ ታላቁ ፈላስፋ ባሩክ ስፒኖዛም በወጣትነቱ  የገጠመው ፈተናም ተመሳሳይ መንፈስ ነበረው፡፡
ሆላንድ በስደት የኖረው የአይሁድ ማህበረሰብ ዕምነት ተቋም (Synagogue) የልጃቸው ታላላቅ ሀሳቦች ተናነቃቸው፡፡ የውሸት ክስ ቀምመው ከጉባኤ መማክርቱ ፊት አቆሙት፡፡… እ.ኤ.አ አቆጣጠር በ1656 ዓ.ም፡፡ …ያኔ ሃያ አራት ዓመቱ ነበር፡፡
‹‹እግዜር እንደ ሰው የሰብዓዊ አካላት (Matter) ውቁር ሊሆን ይችላል፣ መላዕክቶች የቅዠት ምስል (Hallucination) እንጅ እውን ሆነው የሚገለፁ ፍጥረታት አይደሉም፣ ነፍስ የምንለው ህላዌ ሰብ ከስጋና በሕይወት ከመኖር ተነጥሎ ለዘለዓለም የሚቆይ ተዓምረ ክስተት አይመስለኝም፣ ከሞት በሁዋላ ሕይወት ስለመኖሩ በብሉይ ኪዳን የተጠቀሰ ነገር የለም›› ብለህ ለጓደኞችህ የተናገርከው እውነት ነው ውሸት ሲሉ ጠየቁት፡፡ ‹‹ምን እንደመለሰላቸው አልታወቀም፡፡›› ይልና ፀሐፊው፤ ነገር ግን ለወደፊቱ ግላዊ ሀሳቡን በውስጡ ይዞ፣ ቢያንስ በሌሎች ሰዎች ፊት ለአይሁዳዊ እምነት ታማኝ መስሎ እንዲታይ፣ ለዚህም በየዓመቱ አምስት መቶ ዶላር ምንዳ ሊሰጡት መወሰናቸውን እንዳሳወቁት ያትታል፡፡
ስፒኖዛ ግን የዕድል (fate) ጉዳይ ሆኖ አፈጣጠሩ ለአይሁድ ትልቅነት ሳይሆን ለዓለም በመሆኑ መደለያቸውን አጣጥሎ በፀናው ሀሳቡ ቆመ፡፡ ጉባኤውም ሕገ ደንባቸውን መሰረት አድርጎ ‹ይገለል› (Excommunicated ይሁን) የሚል ፍርድ አሳለፈበት፡፡
በታላቅ ስነ ሥርዓት የተከናወነው የዚህ ፍርድ ሂደት እስራኤልን፣ አምላኳንና ሕገ መጽሐፏን ለመጠበቅ የተደረገ ውሳኔ መሆኑን ይዘረዝራል:: በፈላስፋው ላይ ከተላለፈው የእርግማንና የውግዘት መዓት በተጨማሪ ከማንኛውም እስራኤላዊ ጋር በጽሑፍም ሆነ በቃል ግንኙነት እንዳያደርግ፣ ማንኛውም ዓይነት አገልግሎት እንዳይሰጠው፣ ከማንም የማህበረሰቡ አባል ጋር በአንድ ጣራ ስር እንዳይኖር፣ እሱ ካለበት ቦታ ቢያንስ አራት ሜትር መራቅ እንደሚገባና ጽሑፎቹን ማንበብ ክልክል እንደሆነ ይደነግጋል::
ስፒኖዛ በታላላቅ ሀሳቦቹ ምክንያት ከሚወዳቸው ወገኖቹ ተገለለ፣ ራቀ፣ ከስራ ተፈናቀለ፣ ብቸኛ ሆነ፡፡ ይህም ሳይበቃ በአንድ የማህበረሰቡ ሥነ መለኮት አጋፋሪ የግድያ ሙከራ ተደረገበት፡፡ ተረፈ እንጂ፡፡
‹‹There are few Places in this world where it is safe to be a philosopher›› በማለት የጻፈው ያኔ ነው፡፡ ፍሬደሪክ ኒች፤ ኢየሱስን ‹‹የመጨረሻው ክርስቲያን በመስቀል ላይ የሞተው ነው›› ብሎ ሲጽፍለት ብዙ ሊቃውንት ስፒኖዛን እንዴት ‹ረሳው?› በማለት ተገርመዋል፡፡   
ወዳጄ፡- በዚህ ዘመን ሕገ ደንብ፣ ሕገ መንግሥት ወዘተ በሚል ሽፋን ታላላቅ ሀሳቦችን ለማኮላሸት መሞከር አይቻልም፡፡ የአንዱንና የሁሉን ዜጋ መብት የማያከብር ሕግም ሆነ ደንብ አለም አቀፋዊ፣ ሰብዓዊ፣ ተፈጥሯዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን ባገናዘቡ ሕጎች ሊሻሻል ወይም ሊተካ ግድ ነው፡፡ በሰብዓዊ መብት ጥሰት የተከሰሱ ተጠርጣሪዎች ፍ/ቤት ቀርበው ‹‹ወንጀሉን የፈፀምነው ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ለመጠበቅ ነው›› የሚል አስደንጋጭ መልስ ሲሰጡ ሰምተን አፍረናል፡፡ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት ምን ማለት እንደሆነ አልገባቸውም።
* * *
ወደ ጨዋታችን ስንመለስ፡- አስከሬኖቹ ያልተነሱት በዚህ አጭር ዕድሜ በክልል ተፈርጀን፣ እየተጨቃጨቅን ከምንኖር እስከ ዕለተ ምፅዓት ሁሉም እኩል በሆነበት መካነ መቃብር መቆየት ይሻለናል በማለታቸው ነበር፡፡
በነገራችን ላይ ‹‹ብዙ ጠንቋዮችና አዋቂ ነን ባዮች ጋ ሄጄ የተለያዩ ነገሮችን ነግረውኛል:: ማናቸውም ግን ፖሊስ መሆኔንና ላስራቸው እንደመጣሁ ሊያውቁ አልቻሉም፡፡›› በማለት የፃፈልን ማን ነበር?
ሰላም!!

Read 1467 times