Print this page
Saturday, 11 January 2020 12:32

የአድማስ ትውስታ

Written by 
Rate this item
(4 votes)

   ከአዘጋጁ፡- የአዲስ አድማስ ጋዜጣ የተመሰረተበትን 20ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ ሚያዝያ 27 ቀን 1993 ዓ.ም በፊት ለፊት ገፅ ላይ የወጡ ሦስት አብይ ዜናዎችን ለትውስታ ያህል አቅርበናቸዋል አንብባችሁ ተገረሙ፤ ተደመሙ፡፡

                  የእፎይታ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ እንደኮበለለ ተነገረ

         የእፎይታ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ እንደኮበለለ ተነገረ
የእፎይታ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ የነበረው አቶ ተስፋዬ ገብረአብ ለወንድሙ ሠርግ በሚል ከአንድ ሳምንት በፊት ከኢትዮጵያ ውጭ ሄዶ በዚያው መቅረቱን ውስጥ አዋቂ ምንጮች ገለፁ፡፡
አቶ ተስፋዬ ገ/አብ ኢህአዴግ ሀገሪቱን ከተቆጣጠረ ከ1983 ዓ.ም በኋላ ለሁለት ዓመት ተኩል ያህል የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት መምሪያ ኃላፊ የነበረ ሲሆን፤ ከኢህአዴግ ከመቀላቀሉ በፊት የቀድሞው ሠራዊት የመቶ አለቃና የክፍሉም ካድሬ እንደነበር ይታወሳል ያሉት እነዚሁ ምንጮች፤ ኢህአዴግን የተቀላቀለው ደብረታቦር ላይ በ1982 በተደረገ ውጊያ ተማርኮ ነው ብለዋል፡፡ በምርኮኛ የጦር መኮንኖች የተቋቋመው የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ መኮንኖች አብዮታዊ ንቅናቄ (ኤዴመአን) የሚባል ድርጅት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል እንደነበር ምንጮች ጠቁመው፤ በወቅቱ የበረደች ጥይት እጁን መትታው የተማረከው አቶ ተስፋዬ ገብረአብ በቅርቡ በተካሄደው የካድሬዎች ኮንፈረንስ ላይ ለመገኘት ጠይቆ መከልከሉን ገልፀዋል፡፡
አቶ ተስፋዬ ገብአረብ “የቡርቃ ዝምታ”፤ “የቢሾፍቱ ቆሪጦች”፣ “ያልተመለሰው ባቡር” የተሰኙ መጽሐፎች ደራሲ ነው፡፡
(ሚያዝያ 27,1993 ዓ.ም)

የህወሓት ካድሬዎች እንዲወያዩበት ቀረበ የተባለ የአቶ መለስ ዜናዊ ጽሑፍ፤ የሊበራል ዲሞክራሲ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ መርሆች ጠቃሚ ቢሆኑም በኢንዱስትሪ ለበለፀጉ አገሮች ብቻ የሚሰሩ ናቸው፤ ለኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት አብዮታዊ ዲሞክራሲ ነው እንደሚል ተገለፀ፡፡
የመፃፍ፣ የመደራጀትና ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ የዜጐችን መብት እናከብራለን የሚለው ይኸው ጽሑፍ፤ ተቃዋሚዎችንና ነፃ ፕሬስን በማፈን ሳይሆን በህብረትና በህግ በጽናት እንታገላቸዋለን የሚል ነው ተብሏል፡፡
የህግ የበላይነት መከበር አለበት፤ የዜጐች መብትና በህግ ፊት እኩል መሆናቸው መጠበቅ አለበት እንዲሁም የመንግስት ስልጣን በህግ አውጪ፣ አስፈፃሚና ተርጓሚ ተከፋፍሎ እርስ በርሱ የሚቆጣጠር መሆን ይገባዋል የሚሉ መሰረተ ሃሳቦች ዋነኛ የሊበራል ዲሞክራሲ መርሆች እንደሆኑ የዘረዘረው የአቶ መለስ ጽሑፍ፤ አብዮታዊ ዲሞክራሲ እነዚህን መርሆች እንደ መነሻ በመውሰድና ወደ ላቀ ደረጃ በማድረስ፣ ህዝባዊና አብዮታዊ ባህርዮችን ያላብሳቸዋል ይላል፡፡
ጽሑፉ፤ “አብዮታዊ ዲሞክራሲ በግለሰቦች መብት መከበር ላይ ብቻ ሳይገታ የህዝባችን መብት ማለትም የብሔር ጥያቄንም በሚገባ ይመልሳል፤ በዚህም ኢትዮጵያን ከመበታተን አደጋ አድኗል” ካለ በኋላ፤ አሁንም ትምክህተኝነትና ጠባብነት አለ፤ እንዲያውም በአንዳንድ በኩል ተባብሷል በማለት ኢትዮጵያዊነትን የመፍጠር ስራ መጠናከር አለበት ሲል ይገልፃል፡፡
በኢኮኖሚ በኩል ሊበራል ዲሞክራሲ ነፃ ውድድርን በማስፈንና መንግስት ሙሉ ለሙሉ ከኢኮኖማው እንዲወጣ በማድረግ፣ ብልጽግና እንደሚያመጣ የተነተነው ይኸው ጽሑፍ፤ “ሊበራል ዲሞክራሲ በኢንዱስትሪ ለበለፀጉ አገሮች እንደሚጠቅም ግልጽ ቢሆንም መርሁን ከኢትዮጵያ ሁኔታ ጋር ማጣጣም ያስፈልጋል፡፡ ነፃ ገበያ ሊሸፍናቸው የማይችሉ ቀዳዳዎችን ለመድፈን መንግስት ኢኮኖሚው ውስጥ መግባት አለበት” የሚል ሲሆን፤ የባለሀብቶች አቅም እየዳበረ ሲሄድ የመንግስት ተሳትፎ እየቀነሰ እንደሚሄድ፤ ይህም የአብዮታዊ ዲሞክራሲ መርህ እንደሆነ ያብራራል፡፡
የአብዮታዊ ዲሞክራሲ አስተሳሰብ የበላይነት እንዳላገኘ እንረዳለን የሚለው የአቶ መለስ ጽሑፍ፤ ተቃዋሚዎችንና ነፃ ፕሬስን በህግና በህብረት እንታገላቸዋለን በማለት አላማውን ገልጿል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት ጋዜጠኞችን በማሰርና የፕሬስ ነፃነትን በማፈን በአለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተከራካሪዎች በግንባር ቀደምትነት ዘወትር የሚወቀስ ሲሆን ሰሞኑን ፈረንሳይ አገር የሚገኝ ድንበር የለሽ የጋዜጠኞች ማህበር የፕሬስ ነፃነትን ያፍናሉ በማለት ከዘረዘራቸው የዓለም መሪዎች መካከል ጠ/ሚኒስትር መለስ ዜናዊን አንዱ አድርጓቸዋል፡፡
(ሚያዝያ 27,1993 ዓ.ም)
***
የተማሪዎች ህብረት ፕሬዚዳንትን ጨምሮ በርካታ ተማሪዎች የደረሱበት አልታወቀም
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ጥያቄ በኋላ ወደ 3ሺህ የሚጠጉ ተማሪዎች ለ8 ቀናት ሰንዳፋ ቆይተው ቢመለሱም የተማሪዎች ህብረትን ሲያንቀሳቅሱ የነበሩ ተማሪዎች ግን የት እንዳሉ እንደማይታወቅ አንዳንድ ተማሪዎች ገለፁ፡፡
ከሚያዚያ 1 ቀን 1993 ዓ.ም ጀምሮ የተማሪዎቹን የመብት ጥያቄ ሲያቀርቡና ሲያስተባብሩ የነበሩ ተማሪዎች ከስጋት የተነሳ ራሳቸውን ደብቀው እንደሚገኙ ተማሪዎቹ ተናግረዋል፡፡
የቀድሞው የተማሪዎች ህብረት ፕሬዚዳንት የነበረው ተማሪ ተክለሚካኤል አበበ በፖሊሶች ከፍተኛ ክትትል እየተደረገበት መሆኑን አብረውት የሚማሩ ተማሪዎች ጠቅሰው፤ ፖሊሶች የተክለሚካኤል የትውልድ ቦታ ወደሆነው አሩሲ ነገሌ በሄሌኮፕተር በመሄድ ፈልገው ሲያጡት፣ ታላቅ ወንድሙን አፈወርቅ አበበን ይዘው አዲስ አበባ እንዳመጡት ገልፀዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት የተማሪ ተክለሚካኤል ወላጆች በከፍተኛ ስጋት ላይ እንደሚገኙ የጠቆሙት የተክለሚካኤል ጓደኞች፤ ለማረጋገጥ ባይቻልም ወደ አንድ ኤምባሲ ለመግባት ጠይቆ ተፈቅዶለት እዚያ እንደሚገኝ ወሬ መስማታቸውን ተናግረዋል፡፡
ከ1992 ዓ.ም ጀምሮ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች ህብረት ፕሬዚዳንት የነበረውና የህግ ፋኩሊቲ የ4ኛ ዓመት ተማሪ የሆነው ተክለሚካኤል አበበ፤ “የተማሪው ህገ መንግሰታዊ መብት መጠበቅ አለበት” በሚል በመታገሉና በሚያቀርባቸው ሐሳቦች ብዙ ተማሪዎች ይደግፉታል ሲሉ የቅርብ ጓደኞቹ ይናገራሉ፡፡
ከዚህ ቀደም የደህንነት አካላት መኝታ ክፍሉ ድረስ በመምጣት ዛቻና ማስፈራሪያ ያደርሱበት እንደበር ብዙዎቹ ተማሪዎች ያውቃሉ የሚሉት የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች፤ በፖሊሶች አድራጐት ይማረር እንደነበር፤ ሚያዝያ 8 ቀን 1993 ዓ.ም የትምህርት ሚኒስትሯ ወ/ሮ ገነት ዘውዴ ተማሪዎችን ባወያዩበት እለትም ይህንኑ ተናግሮ ነበር ብለዋል፡፡
ተማሪ ተክለሚካኤል “ህሊና” በሚል ስያሜ መታተም ጀምሮ የነበረውን የተማሪዎች ህብረት ጋዜጣ ከሚያዘጋጁ ተማሪዎች መካከል አንዱ ነበር ሲሉ ጠቁመዋል፡፡
አሁንም በዩኒቨርሲቲው ትምህርት ያልተጀመረ ሲሆን፤ አንዳንድ የስድስት ኪሎ ተማሪዎች እንዳሉት “የመሰብሰብ ነፃነት አላችሁ” ተብለን ስንሰባሰብ በፖሊሶች ታፍሰን የምንወሰድ ከሆነ ለህይወታችን ሥጋት አለን ብለዋል፡፡   
(ሚያዝያ 27,1993 ዓ.ም)

Read 848 times
Administrator

Latest from Administrator