Print this page
Saturday, 11 January 2020 13:47

ሶደሬ ቁጥር 2 ባለ ኮከብ ሪዞርትና ሆቴል ዛሬ ይመረቃል

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

        የቀድሞው ሶደሬ በ2 ቢ .ብር ማስፋፊያ እየተደረገበት ነው
                                       ሶደሬ ሆቴልና ሪዞርት እየተስፋፋ ነው
                                                 
              የሪፍት ቫሊ ዩኒቨርሲቲ ባለቤት በሆኑት አቶ ድንቁ ደያስ በ100 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነባው “ሶደሬ ሆቴልና ሪዞርት አፍሪካ ህብረት ቅርንጫፍ” ዛሬ ከቀኑ 6፡30 ጀምሮ የንግዱ ማህበረሰብ አባላት፣ የመንግስት ሃላፊዎችና ታዋቂ ግለሰቦች በተገኙበት እንደሚመረቅ የድርጅቱ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ አብዮት ተመስገን ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡ ባለ አራት ኮከብ ደረጃ ይኖረዋል የተባለው ሆቴሉ፤ ግንባታው 3 ዓመታትን የፈጀ ሲሆን 50 አልጋዎች፣ የመሰብሰቢያ አዳራሾች፣ ደረጃቸውን የጠበቁ ሬስቶራንቶችና በቂ የመኪና ማቆሚያዎች እንዳሉት ታውቋል፡፡
በሌላ በኩል በ2003 ዓ.ም ከመንግስት ይዞታነት ወደ ግል ባለቤትነት የተዛወረውና የአቶ ድንቁ ደያስ ንብረት የሆነው ሶደሬ ሆቴልና ሪዞርት፤ በ2 ቢሊዮን ብር ወጪ ከፍተኛ ማስፋፊያ እየተደረገለት መሆኑን የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ አስታውቀዋል፡፡ የማስፋፊያ ሥራው ሰው ሰራሽ ሀይቅ፣ ወተር ፓርክ፣ የእግር ኳስ ሜዳ፣ የመሮጫ መም (ትራክ)፣ ሰውን ከአንድ ተራራ ወደ ሌላ የሚያጓጉዝና 1ቢሊዮን ብር የሚወጣለት ኬብል ትሪ፣ ስድስት ሺህ ሰዎችን የሚያስተናግድ የስብሰባ አዳራሽ ሲሆን፤ አሁን ያሉትን 670 የመኝታ ክፍሎች ወደ 2ሺህ እንደሚያሳድግም ታውቋል፡፡
ባለሀብቱ በዘንድሮው አመት ከአፍሪካ ህብረቱ ሶደሬ ሆቴልና ሪዞርት ጋር ተመሳሳይ የሆነ ሆቴል በአዲሱ ገበያ እያስገነቡ ሲሆን፤ በ2013 ተጠናቅቆ አገልግሎት የሚሰጥ ሌላ ሆቴልም ቦሌ ከብርሃኔ አደሬ አፍሪካ ሞል ጀርባ ግንባታው በቅርቡ እንደሚጀምር ስራ አስኪያጁ ጨምረው ገልፀዋል፡፡ በተጨማሪም በ350 ሚሊዮን ብር ወጪ በ3 ዓመት ጊዜ ውስጥ ግንባታው የሚጠናቀቅ ‹‹ሶደሬ ቢሾፍቱ ሆቴልና ሪዞርትን›› በቢሾፍቱ ከተማ ለመገንባት ዝግጅቱ መጠናቀቁንም ለማወቅ ተችሏል፡፡
ባለሀብቱ በኢንዱስትሪው ዘርፍ “ሶደሬ” የታሸገ ውሃ ፋብሪካን፣ በኮንስትራክሽን ዘርፍ “ናኦል ደረጃ 1 ተቋራጭ”፣ በትምህርት ዘርፍ ‹‹ሪፍት ቫሊ›› ዩኒቨርስቲዎችን መስርተው እየመሩ ሲሆን ዛሬ የሚመረቀውን ሆቴል ጨምሮ በግንባታ በእቅድ ላይ ያሉት ሆቴልና ሪዞርቶች፤ ባለሀብቱ ለሆቴልና ሪዞርቱ ዘርፍ ትኩረት ሰጥተው እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን አመላካች  ነው ብለዋል - የድርጅቱ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ አብዮት ተመስገን፡፡ ዛሬ የሚመረቀውና በአፍሪካ ህብረት አቅራቢያ የሚገኘው ሶደሬ ቁጥር 2 ሆቴልና ሪዞርት ለ120 ሰዎች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር ተነግሯል፡፡

Read 2946 times