Sunday, 12 January 2020 00:00

“በቁመታችን ልክ” ምን ማለት ነው?

Written by  አያሌው አስረስ
Rate this item
(0 votes)

 ወደዚህ ጠያቂ ርዕስ የወሰደኝ ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና የተናገሩት ነው ተብሎ በማኅበራዊ ሚዲያ የተሠራጨው ሃሳብ ነው፡፡ ፕሮፌሰሩ “ዓላማችን በቁመታችን ልክ ቤተ መንግሥት መግባት እንጂ አገር ማፍረስ አይደለም” ብለዋል ነው የተባለው፡፡ ይህን ሃሳብ አዲሱ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ አባል አቶ ጁሐር ሞሐመድ ከኤልቴቪ ጋር በነበራቸው ቆይታ “በክልላችን ያለ ማንም ጣልቃ ገብነት ክልላችንን ማስተዳደር፣ በፌደራል ደግሞ በቁመታችን ልክ ተገቢ ውክልና ማግኘት” በማለት ከተናገሩት ጋር የሚስማማ ወይም የተጣጣመ ነው፡፡ በዚህም የተነሳ ሃሳቡን የድርጅት አቋምና መርህ አድርጐ መወሰድ ይቻላል ብዬ አስባለሁ፡፡
ፕሮፌሰር መረራን እኔ የማውቃቸው “አንድ ሰው አንድ ድምጽ” በሚለው መጽሃፍ “ለሁላችንም የምትሆን ኢትዮጵያን መመሥረት ይኖርብናል” በሚለው ሃሳባቸው ስለነበር ይሄ የአቋም ለውጥ ይሆን ብዬም እንዳስብ ገፋፍቶኛል፡፡ ለመሆኑ “በቁመታችን ልክ” ማለት ምን ማለት ነው? ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡
እንግዲህ ብሔረሰቦችን ብሔረሰብ ብለን የምንለየው በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ነው፡፡ በዚህ መሠረትም ብዙዎች አፍ የሚፈቱበት ቋንቋ ኦሮምኛ ሲሆን ሌሎቹ አማርኛ፣ ሶማሊኛ፣ ትግሪኛ ሲዳማኛ ጉራጌኛ ወላይታኛ ወዘተ እያለ እንደ ቅደም ተከተላቸው ይወርዳል፡፡
ዶ/ር መረራም ሆኑ ሌሎች የዚህ ሃሳብ ተጋሪ የኦሮሞ ልሂቃን “በቁመታችን ልክ” ሲሉ ከፍተኛ የሕዝብ ብዛት ያለው በዚህች አገር ኦሮሞ በመሆኑ አገሪቱ ያላትን ነገር በሙሉ አስቀድማ ማድረስ ያለበት ለኦሮሞ ነው ማለታቸው እንደሆነ መገንዘብ አይገድም፡፡
ፕሮፌሰር መረራም ሆኑ ሌሎች ለኦሮሞ “የሚገባውን በቁመቱ ልክ ማግኘት አለበት” ሲሉ ሌሎች ብሔረሰቦችን እንዴት አይተዋቸው ነው? ብሎ መጠየቅም ተገቢ ነው፡፡
ለእኔ ኦሮሞ በሕዝብ ብዛቱ በልጦ የሚታየኝ ኦሮሞ ከአማራ፣ ኦሮሞ ከትግሬና፣ ኦሮሞ ከሱማሌ ጋር ሲነፃፀር እንጂ ኦሮሞን ከአጠቃላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር አዳምሬ ሳይ አይደለም፡፡ እነሱም በዚህ መንገድ ቢያዩት፤ አተያያቸው ስህተት ያለበት መሆኑን እንደሚረዱት አምናለሁ፡፡
“በቁመታችን ልክ ቤተ መንግሥት መግባት አለብን” ማለት በብዙ ምክንያት በሌሎቹ ንዑሳን ላይ የበላይነትን ለመጫን ከመነሳት የተለየ ሆኖ ሊታይ አይችልም፡፡ አንዱ በብዛቱ ወደ ላይ ከወጣ፣ ሌላው በቁጥሩ ማነስ ወደ ታች የሚወርድ ከሆነ በእጅጉ የሚጎዱ ብሄረሰቦች እንደሚኖሩ በድፍረት መናገር ያሻል፡፡
ወይዘሮ አዜብ መስፍን ከ1997 አገር አቀፍ ምርጫ በኋላ አሉት የተባለው ነገር ትዝ አለኝ፡፡ የቅንጅት አሸናፊነት በጉልበት ተገለበጠና የአቶ መለስ መንግሥት በእግሩ ተንሸራቶ ከቆመ በኋላ ወ/ሮ አዜብ “ማን ታግሎ ባመጣው ወንበር ማን ይቀመጣል” አሉ፡፡ የሕወሓትን ስህተት የኦሮሞ ልሂቃን ገልብጠው ባይደግሙት መልካም ይሆናል፡፡
የኦሮሞ የፖለቲካ ሰዎች ሊያርሙት የሚገባ አስተሳሰብ እንዳለ ሁሉ፣ የኦሮሞ የፖለቲካ ድርጅቶች በርቱ የሚባሉበትም ጉዳይ አለ፡፡ ይኸውም ሶስቱ የፖለቲካ ድርጅቶች ማለትም፤ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) እና የኦሮሞ ብሄራዊ ፓርቲ (ኦብፓ) በአንድ ኅብረት ወይም ግንባር ለመሰብሰብ እየሠሩ መሆናቸው ነው፡፡ ይኼ ቀድመው መጀመር የነበረባቸው ከጀመሩት ዘንድም ሊያፋጥኑት የሚገባ ተግባር ነው፡፡
እንዳሉት በአገር አቀፍ ምርጫ ተወዳዳሪ ለመሆን ከተነሱ ግን ለፕሮፓጋንዳ ግብ ሲሉ በሕዝብ መሐል የዘሩትን እሾህ ፈጥነውና ተግተው መንቀል ይገባቸዋል፡፡   

Read 2814 times