Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 23 June 2012 08:56

ዶ/ር እሌኒ ከኃላፊነታቸው ለቀቁ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ  (ECX)  መስራችና ዋና ስራ አስፈፃሚ የነበሩት ዶ/ር እሌኒ ገ/መድህን፣ የስራ ማስፋፊያ ዕቅዳቸው ተቀባይነት ማጣቱን ሮይተርስ የዘገበ ሲሆን ስራ አስፈፃሚዋ  ከነበራቸው ሃላፊነት ለቀዋል፡፡ ዶ/ር እሌኒ በምርት ገበያ መስራችነታቸው ዓለማቀፍ ዕውቅናና ሽልማቶች እንዳገኙ የሚታወቅ ሲሆን ድርጅቱን ለመመስረትና ለመምራት አብረዋቸው እንዲሰሩ በዓለማቀፍ መመዘኛ ቀጥረዋቸው የነበሩ ዘጠኝ ከፍተኛ ባለሙያዎችም ከሳቸው ጋር ለቀዋል፡፡ የድርጁትን ስራ ለማስፋፋት ከመንግስት ጋር ውይይት ሲያካሂዱ መቆየታቸውን የተናገሩት ዶ/ር እሌኒ፣ አንዳንድ ዋና ዋና እቅዶች እንደከሸፉ ለሮይተርስ ገልጸዋል፡፡

በቡና ግብይት ስራ የጀመረው የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ፣ በሰሊጥ በበቆሎና በመሳሰሉ ግብይቶች ስራውን ለማስፋፋት መሞከሩ የሚታወስ ሲሆን የእርዳታ እህሎችን ጨምሮ የስኩዋር ሽያጭም በማካተት ስራውን ለማሳደግ ስራ አስፈፃሚዋ ያወጡት ዕቅድ እልባት ሳያገኝ ነው የለቀቁት፡፡ በቺካጎ ኮሞዲቲ ኤክስቼንጅ አሰራር ውስጥ እንደሚታየው፣ የመጪውን አዝመራ ተመርኩዞ ከወዲሁ የሚካሄዱ ግብይቶችን (Future Trading) የመጀመር ሃሳብ የዶ/ር እሌኒ ትልቁ እቅድ ነበር፡፡ እቅዱን ለመተግበር ከመንግስት ጋር ሲደራደሩ ቢቆዩም አልተሳካም - “ይሄን ነገር አትችሉትም” የሚል የስጋት ጩኸት ከውጭ አገር መበርከቱም ለእቅዱ መክሸፍ አንድ ምክንያት ሆኗል ብለዋል ዶ/ር እሌኒ፡፡    በዶ/ር እሌኒ ምትክ የአቢሲኒያ ባንክ ም/ፕሬዚዳንት የሆኑት አቶ አንተነህ አሰፋ የተሾሙ ሲሆን፣ ኩባንያው ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ ሲሰሩና ልምድ ሲቀስሙ የነበሩ የአገር ውስጥ ተቀጣሪ የማኔጅመንት ባለሙያዎች፣ አመራሩን ተክተው ይሰራሉ ተብሏል፡፡ ዶ/ር እሌኒ እስከ መጪው መስከረም አጋማሽ ድረስ በአማካሪነት እንደሚሰሩ ታውቋል፡፡ የዓለም ባንክን ጨምሮ በታላላቅ ዓለም አቀፍ ተቋማት በከፍተኛ የኢኮኖሚ ባለሙያነት የሰሩት ዶ/ር እሌኒ፣ በአሜሪካ በተካሄደ የጂ8 ስብሰባ ላይ በባራክ ኦባማ ከተጋበዙት ሁለት ከፍተኛ የአፍሪካ የቢዝነስ መሪዎች መካከል አንዷ ሲሆኑ በአፍሪካ የፋይናንስ ኢንዱስትሪ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ላበረከቱ ባለሙያዎች ሽልማት በሚሰጠው አፍሪካ ዲቨሎፕመንት ባንክ ባለፈው ግንቦት ወር ተሸልመዋል - የኢትዮáያ ምርት ገበያን ለማቋቋም ባበረከቱት አስተዋፅኦ፡፡

 

 

 

Read 19760 times Last modified on Saturday, 23 June 2012 11:38