Saturday, 11 January 2020 14:51

በ27 የምግብ ምርቶች ላይ እገዳ ተጣለ

Written by  መታሰቢያ ካሣዬ
Rate this item
(1 Vote)

   ከረሜላዎች፣ የምግብ ዘይቶች፣ ቪምቶ፣ ጨውና የለውዝ ቅቤዎች እገዳው ከተጣለባቸው ምርቶች ውስጥ ይገኙበታል ድንገት በተደረገ ፍተሻ ከ500 ሚ. ብር በላይ የሚገመት ከባዕድ ነገር ጋር የተቀላቀለ ቅቤና ማር ተይዟል
            
            የኢትዮጵያ የምግብ የመድሃኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን፤ በተጭበረበረ ሁኔታ የሚመረቱና አድራሻቸው የማይታወቁ በመሆኑ በህብረተሰቡ ጤና ላይ የከፋ ጉዳት ያስከትላሉ ያላቸውን 27 ዓይነት የምግብ ምርቶች ህብረተሰቡ ከመጠቀም እንዲታቀብ አሳሰበ፡፡
በየደረጃው የሚገኙ የቁጥጥር አካላትም ምርቶቹን በአፋጣኝ ከገበያ እንዲያወጡ ትዕዛዝ አስተላልፏል፡፡
በባለስልጣን መ/ቤቱ ከተለዩትና ህብረተሰቡ እንዳይጠቀምባቸው እገዳ ከተጣለባቸው የዘይት ምርቶች መካከል ኢዛና፣ ጣና፣ ኦሊያድ፣ ሶኬት፣ በቅላ፣ አሚን፣ ቀመር፣ አለ፣ ሎዛ፣ ዘመን እና ዘቢብ ቃህ የምግብ ዘይቶች ይገኙበታል፡፡ ማኢዳ የለውዝ ቅቤና ሮዝ ክሬሚ የለውዝ ቅቤዎችም ክልከላው የሚመለከታቸው ሲሆን፤ አዋሽ የገበታ ጨው፣ ሳራና አሳራ፣ ሴፍ፣ ሸነጉ፣ ወዛቴ፣ ቃና እና አስሊ የገበታ ጨዎችም ባለስልጣን መ/ቤቱ ህብረተሰቡ እንዳይጠቀማቸው ማሳሰቢያ ከሰጠባቸው ምርቶች መካከል ይገኙበታል፡፡ በባለስልጣኑ እገዳ ከተደረገባቸው ምርቶች መካከል የህፃናት ከረሜላዎች የሚገኙበት ሲሆን ካርቶንስ ካንዲ ፍሩትስ፣ ሊዛ ሎሊፖፕና ክሬሚ ሎሊፖ ተጠቅሰዋል፡፡ ሲሳይ ንፁህ ማርና ቅቤ እንዲሁም ወለላ ማር እየተባሉ የሚጠሩትን ምርቶችም ሕብረተሰቡ ከመጠቀም እንዲታቀብ ማሳሰቢያ ተሰጥቷል፡፡
ባለስልጣን መ/ቤቱ ባለፈው ቅዳሜ ታህሳስ 25 ቀን 2012 ዓ.ም በመርካቶ አካባቢ ባደረገው ድንገተኛ ፍተሻ፣ ግምታቸው ከ500 ሚሊዮን ብር በላይ የሚሆን የተለያዩ የማርና የቅቤ ምርቶች ከባዕድ ነገሮች ጋር ተቀላቅለው ለገበያ ቀርበው መገኘታቸውንና ከዚህ ጋር በተያያዘም 72 የሚሆኑ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡ በአዲስ አበባው መርካቶ የገበያ ማዕከልና በአዲስ አበባ ዙሪያ በሚገኙ 13 የቅቤና የማር ምርት አቅራቢዎች ላይ በተደረገው ድንገተኛ ፍተሻ የተያዙትን ከባዕድ ነገሮች ጋር ተቀላቅለዋል የተባሉትን የቅቤና የማር ምርቶች በባለስልጣኑ መያዛቸውንና በ72 ተጠርጣሪዎች ላይ ምርመራ እየተካሄደ መሆኑም ታውቋል፡፡

Read 1917 times