Print this page
Saturday, 11 January 2020 14:56

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር የገና በዓል መልዕክት ማብራሪያ እንዲሰጥበት ተጠየቀ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(5 votes)

    የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ም/ቤት የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተመስገን ጥሩነህ የገናን በዓል አስመልክቶ ባስተላለፉት መልዕክት ላይ ማብራሪያ እንዲሰጠው ጠየቀ፡፡
ጠቅላይ ም/ቤቱ የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር የገናን በዓል ምክንያት በማድረግ በሰጡት መግለጫ እግረ መንገዳቸውን በሞጣ መስጂዶችና ሙስሊሞች ላይ የደረሰውን ጥቃት አስመልክት ያስተላለፉት መልዕክት ሚዛኑን ያልጠበቀ፣ ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖች ቁስል የሚያባብስ፣ ከመሆኑም በላይ በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ከአንድ ከፍተኛ የሕዝብ መሪ የማይጠበቅ ሆኖ አግኝቼዋለሁ ብሏል፡፡
ችግሩን ተከትሎ ጠ/ም/ቤቱ ሕዝበ ሙስሊሙን ለማረጋጋት እየተጫወተ የሚገኘውን ሚና የሚፃረር መግለጫ ነው ርዕሰ መስተዳደሩ የሰጡት ያለው ጠ/ም/ቤቱ በጉዳዩ ላይ ርዕሰ መስተዳደሩ አስቸኳይና ግልጽ ማብራርያ እንዲሰጡ ጠይቋል፡፡ መጅሊሱ በመግለጫው የሞጣን ጥቃት አስመልክቶ አምስት ጥያቄዎችን ያዘለ ደብዳቤ ለክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አድርሶ የነበረ ቢሆንም እስከ አሁን ድረስ ይፋዊ ምላሽ አለማግኘቱን አስታውቋል፡፡
ጠ/ም/ቤቱ ለጥያቄዎቹም አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጥ እንዲሁም በርዕሰ መስተዳድሩ ንግግር ላይም ማብራሪያ እንዲሰጥ ጠይቆ ‹‹ይህ ሳይሆን ቢቀር ግን ም/ቤቱ ሌሎች አማራጮችን ለመመልከት ይገደዳል›› ብሏል፡፡
አሁንም ከችግሩ ጋር ተያይዞ ሕዝበ ሙስሊሙን የማረጋጋት ተግባሬን አጠናክሬ እቀጥላለሁ ብሏል ም/ቤቱ በመግለጫው፡፡

Read 2427 times