Print this page
Sunday, 12 January 2020 00:00

ሳልሳይ ወያኔ ‹‹ሕገ መንግሥቱ እንዲሻሻል እታገላለሁ›› አለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

 ከሰሞኑ መስራች ጉባኤውን በመቀሌ ከተማ ያደረገው ሳልሳይ ወያኔ ትግራይ (ሳወት)፤ ትግሌ የትግራይን ጥቅም ማዕከል ያደረገ ነው ብሏል፡፡ ለትግራይ ጥቅም በሚያደርገው ትግል ውስጥም በዋናነት ሕገ መንግሥቱ እንዲሻሻል እንደሚታገል አስታውቋል፡፡
ሶሻል ዴሞክራሲን ርዕዮተ ዓለሙ ያደረገው ፓርቲው፤ የትግራይ መንግሥት ምን መምሰል አለበት? የትግራይ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ጥቅሞች ምን መምሰል አለባቸው? በሚሉት ዋነኛ ጉዳዮችም ላይ የራሱን ፖሊሲዎችና ትንታኔዎች ማዘጋጀቱን አስታውቋል፡፡
የትግራይ ሕዝብ ዕጣ ፈንታ ምን መሆን አለበት? የሚለው ጉዳይም ዋነኛው የትግሌ ማጠንጠኛ ይሆናል፤ ለዚህም ከሕዝቡ ጋር እወያያለሁ ብሏል - ፓርቲው፡፡
አሁን በሥራ ላይ ያለው ሕገ መንግሥት ጠንካራ ክልሎች መፍጠር የሚያስችል ሆኖ መሻሻል አለበት የሚለው ሳልሳይ ወያኔ፤ ‹‹ይህ የማይሆን ከሆነ ግን የትግራይ ከኢትዮጵያ ጋር መቀጠል ትርፉ ኪሳራ ነው›› ብሎ እንደሚያምን ገልጿል፡፡
ሕገ መንግሥቱ ሲሻሻል በማዕከላዊ መንግሥቱ ተይዞ ያለው የፋይናንስ፣ የሃይልና የሥልጣን መጠን ለክልሎች መከፋፈል አለበት የሚል አቋም እንዳለው የገለፀው ፓርቲው፤ አሁን አገሪቱ ውስጥ ላለው ግጭትም ምክንያቱ የፌዴራል መንግሥቱ ያልተገባ የሥልጣንና የሃብት መጠን መያዝ ነው ብሏል፡፡
ፓርቲው በቀጣዩ አገራዊ ምርጫ በመላው ትግራይ ለመወዳደር ማቀዱንም አስታውቋል:: ሳልሳይ ወያኔ ትግራይ ከዚህ በፊት በተለምዶ ከነበረው የፓርቲዎች የአመራር አወቃቀር በተለየ መልኩ 25 አባላት ያሉት ‹‹ብሄራዊ አመራር›› የፈጠረ ሲሆን ይሄን ብሄራዊ አመራር በሊቀ መንበርነት እንዲመሩት አቶ ሃይሉ ጎደፋይ ተመርጠዋል፡፡


Read 10474 times