Saturday, 18 January 2020 12:54

‹‹አቶ ለማ መገርሳ ለመገናኛ ብዙኃን ሐሳባቸውን እንዳይገልጹ ተከልክለዋል መባሉ ሃሰት ነው››

Written by  መታሰቢያ ካሣዬ
Rate this item
(6 votes)

 የቀድሞው የኦሮምያ ክልል ፕሬዚዳንትና የኢትዮጵያ የመከላከያ ሚኒስትር አቶ ለማ መገርሳ በኢህአዴግ ውህደትና በጠቅላይ ሚኒስትሩ የመደመር ፍልስፍና እንደማያምኑ በመግለጽ ከአሜሪካ ድምጽ ጋር ያደረጉትን ቃለ ምልልስ ተከትሎ፣ ተፈጥሮ የነበረውን አለመግባባት በሰላማዊ መንገድ በንግግር መፍታታቸውንና አብረው ለመስራት መስማማታቸው የተገለፀ ቢሆንም፤ ስለ ጉዳዩ አቶ ለማ ለመገናኛ ብዙኃን ያሉት ነገር የለም፡፡ በዚህ የተነሳም አቶ ለማ ሐሳባቸውን ለመገናኛ ብዙኃን እንዳይገልፁ እገዳ ተጥሎባቸው እንደሆነ በማህበራዊ ሚዲያ ሲናፈስ ሰንብቷል፡፡ ይህ ሀሳብ ከእውነት የራቀ እንደሆነና አቶ ለማ አሁን በሃላፊነታቸው ላይ እንደሚገኙ የብልጽግና ፓርቲ የኦሮሚያ ቅርንጫፍ የከተሞች ፖለቲካ አደረጃጀት ኃላፊ አቶ ሳዳት ናሻ ትናንት ለቢቢሲ ተናግረዋል፡፡
በሁለቱ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት መካከል ተፈጥሮ የነበረው የሐሳብ ልዩነት በውይይትና በመግባባት መፈታቱን የጠቆሙት የፖለቲካ አደረጃጀት ኃላፊው፤ ልዩነታቸው መሰረታዊ እንዳልሆነና ቀላል አለመግባባቶች እንደነበሩ አስረድተዋል፡፡
አቶ ለማ ከአሜሪካ ድምፅ ጋር ባደረጉት ቆይታ በጉዳዩ ላይ የአቋም ለውጥ ካደረጉ ለመገናኛ ብዙሃን ቃለ ምልልስ ይፋ እንደሚያደርጉ ገልፀው ነበር፡፡  ልዩነቱ በውይይት ከተፈታና የአቋም ለውጥ ካደረጉ በኋላ መገናኛ ብዙሃን ማብራሪያ ይሰጣሉ ተብሎ ቢጠበቅም እስካሁንም ምንም አለማለታቸው ጥርጣሬ ማስከተሉን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡ በማህበራዊ ሚዲያዎችም አቶ ለማ ወደ መገናኛ ብዙሃን ወጥተው ሐሳባቸውን እንዳይገልፁ ክልከላ ተደርጐባቸዋል መባሉን በማንሳት፣ ቢቢሲ ለፖለቲካ አደረጃጀት ኃላፊው ጥያቄውን አቅርቧል፡፡
አቶ ሳዳት ናሻ በሰጡት ምላሽ፤ ‹‹ይህ ሃሳብ ከእውነት የራቀ ነው›› ሲሉ አጣጥለውታል፡፡
‹‹አቶ ለማ ካልተናገሩ በስተቀር የፓርቲው መግለጫ ስህተት ነው ብሎ ማሰቡ ትክክል አይደለም፡፡ በፓርቲው የተሰጠው መግለጫ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴውና የጓድ ለማ አቋም ሆኖ መታየት አለበት›› ብለዋል የፖለቲካ አደረጃጀት ኃላፊው፡፡
የመከላከያ ሚኒስትሩ በስራቸውና በኃላፊነታቸው ላይ እንደሚገኙ የገለፁት አቶ ሳዳት፤  በአሁኑ ወቅት በክልሉ እየተደረገ ያለው ሹምሽር ከዚህ ሁኔታ ጋር ፈጽሞ የሚገናኝ አይደለም  ብለዋል፡፡
‹‹የፓርቲው ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በሁለቱ ባለሥልጣናት መካከል የነበረውን አለመግባባትና የሃሳብ ልዩነት በውይይት የፈታው በመሆኑ አሁን በጋራ ስራቸውን በመስራት ላይ ናቸው›› ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል - አቶ ሳዳት ናሻ፡፡


Read 13569 times