Saturday, 18 January 2020 13:03

ወደ መርሳ

Written by 
Rate this item
(7 votes)

ቀናቶቹ እንደ መጽሐፍ እየተገለጡ ጥር 27 ላይ ደረሰን፤ ድፍን ሃያኛ ቀናችንን አስቆጠርን:: 12፡30 ሲልም ጉዞአችንን ጀመርን:: ብዙም ሳንርቅ ውሃ እንድንይዝ በሚል ቆምን፤ መንገዴንም እያዘገምኩኝ ሳቅና ጢስ አባሊማ ደብረ ገነት መድኃኔዓለም ደብርን በመንገዴ አገኘሁኝ:: እግዚኦታ ሲደርስ በመስማቴም ተጠግቼ በመካፈል በሰላም ሲባል፣ በካህኑ መስቀል እግሮቼ ተሻሽተው እምነት ተቀብዬ ወጣሁኝ፡፡ በጸሎት ሰዓት ጓዶች ሲያልፉ አያቸው ስለነበር፣ በዛፍ የተሰመረውን ጠመዝማዛና ዳገታማ የአስፓልት መንገድ በሩጫ ተያያዝኩት፡፡ ውጫሌ የሚል ሰሌዳ ባለበት ከተማ ዳገታማ ቦታ ላይ ዕረፍት አድርገው አገኘኋቸሁ፡፡ ተያይዘንም ውጫሌ ከተማ ገባን፡፡ ብዙም ሳይቆዩ መንገድ ቆረጣውን ጀመሩት፡፡ ብቻዬንም አደባባዩን ይዤ ስሮጥ አላባቸው የተባለ የከተማዋ ነዋሪ አግኝቶኝ ሰላምታ ተሰጣጠን፡፡ “ደሴ ያረጋል” የተባለውን አይቶ አዝኖ እንደነበር ገልጾልኝ፤ “ብታገልልኝ” እያለ አጥብቆ ያዘኝ፡፡ ምን ማለት እንደሆነም ስጠይቀው፤ ለካስ ወደ ቤት ብትገባ ደስ ይለኛል፤ ዕረፍት አድርገህ ሂድ እንደ ማለት ነው፡፡ ጊዜ ቢኖረኝ ባደርገው ደስታው የኔው መሆኑን አስረድቼው በማመስገን፣ የተወሰነ ሸኝቶኝ የጓዶችን የአቋራጭ መውጫ አመልክቶኝ ተመለሰ፡፡
ዳገቱንም ጨርሴ በላሜራ የተሰራውን ሸቀጥ ሱቅ ተደግፌ ስጠባበቃቸው ቆይተው ደረሱ፡፡ “ድግስ አይተህ አትለፍ” የምትለዋን መመሪያ ተከትለው፣ ሰርግ እንደ ሰበሩ ፋሲሎ ነገረኝ፡፡ እኔም በተቀመጥኩበት ለስላሳ በዳቦ ተጋብዤ ለጉዞ ተነሳን፡፡ ውጫሌ መውጫ ላይም አቋራጭዋን ደገሟት፤ አሁን ፋሲሎ አብራኝ ነች፡፡ የተወሰነ እንደተራመድንም ከአዲስ አበባ 471 ኪ.ሜ ላይ የምትገኘዋን ውርጌሳ ከተማን አገኘናት፡፡ “እንኳን ደህና መጡ፤ ሰሜን ወሎ ሐብሩ ውርጌሳ” የሚለውን ማስታወቂያ እያየ፣ ድልድዩን አልፈን ዘለቅን፡፡ ይህች ከተማ ኮሚዲያን አለባቸው ተካ የተወለደባት ነች:: በመንገዳችንም ያሬድ፤ አምባሻና ሙዝ አቀብሎን እየነዳ አለፈን፡፡ መሐል ከተማዋ ላይ ስንደርስም ቀድመው የደረሱ ጓዶች ቢኖሩም፣ የቀደምናቸው ግን ብዙ ነበሩ፡፡
አስቸጋሪ ዳገት እንዳጋጠማቸው ተማረው ያወሩ ነበር፡፡ ሰማኔ ላይ ሰርግ አግኝተን፣ በልተን ጠጥተን ስንጨርስ፣ በያሬድ ምርቃት አመስግነን ወጣን፡፡ የምርኩዜን ውለታ በማጤን “ኢትዮጵያ” የሚል ስም ልሰጣት በማሰብ የምፈለፍልበት መቅረጫ ካላቸው የጠየኳቸው ቢኒያምና አስቻለው የተባሉ የውርጌሳ ከተማ ነዋሪዎች፤ሚስማር ቀጥቅጠው አሹለው ሰጡኝ:: ወደ አባጌትዬ መርሳ ከተማ እየተጓዝን እንገኛለን፡፡ ውርጌሳንም እየተሻገርን ጓዶች አቋራጭ በመጠቀማቸው ጥቂት ርምጃዎችን ብቻዬን እንደተራመድኩኝ፣ መንገዱ አስፓልት የነበረና በቆይታ ብዛት ያገጠጡ ጠጠሮችን የፈጠረ በመሆኑ፣ ከዚህስ በገቡበት መግባት ሳይሻለኝ አይቀርም፤ ብዬ አቋራጩን ስይዘው መንገዱ ጠፋኝ፡፡ ብሽከረከረም በዛፍ ስለተሸፈነ ላገኘው አልቻልኩም፡፡ “ሰዎች” እያልኩኝ ስጣራ ሰሚ አግኝቼ፣ ሳንተያይ በድምጽ ብቻ መንገዱን አመለከተቺኝ፡፡ ባለቺኝ መስመር ሳቀናም ውሃ መውረጃ ያለው ወንዝ ሆኖ አገኘሁት፡፡ ወደ ኋላም ወደፊትም ለማለት ቸገረኝ፡፡ ፋሲሎ ጋር ስደውል ስልኳ አይሰራም፤ የቢኒያም ስልክ ቢጠራልኝ የሆንኩትን ስነግረውም፣ መራቃቸውንና ቴሌው ጋ መድረሳቸውን ነገረኝ፡፡ በሐሳብ እንደ ዋለልኩም የሰው ኮቴ በመስማቴ ተደስቼ ሳበቃ ልጅ ሆኖ አገኘሁት፡፡ ወንዙን መሻገር እንዳልቻልኩኝና እግሮቼን ውሃ እንዳይነካብኝ መፍራቴንም ነገርኩት፡፡ “ምን ይሻላል?” በሚል አብሮኝ ይጨነቅ ያዘ፡፡ አማራጭ ጠፋ፡፡ ስሙንም ስጠይቀው “ኢብራሂም” አለኝ፡፡ እኔም “ኢብሮ በቃ ተሸክመህ አሳልፈኝ” አልኩት:: “ኧረ አልችልክም” ብሎ ፈገግታ ሲያሳየኝ፣ ገና ሳልጠይቀው ልከብደው እንደምችል አውቄያለው፤ ግን ምን ላድርግ፤ ሌላ ሰው በአካባቢው ዝር አልል አለ፡፡ የ13 ዓመቱን ታዳጊ ግድ አልኩት፡፡ “እስቲ ሞክረኝ?” ስለውም፤ “እሺ” በማለት ጀርባውን አመቻችቶልኝ ዘፍ አልኩኝ፡፡ ሱሪውን ቢጠቀልልም መበስበሱ ግን አልቀረም፡፡ አንዲትም ጠብታ ውሃ እግሮቼን ሳይነካኝ፣ የጨቀየውንም መንገድ ጨምሮ አሻገረኝ፡፡ ግንባሩን ስሜው አንድ ቀን  ላገኘው እንደምችል ነግሬው ተሰነባበትን፡፡ እንደዚህ አይነት ከባድ ውለታዎች ሲያጋጥሙኝ እንባ ነው የሚቀድመኝ፡፡ የገባሁበትም አቋራጭ አሸዋና አፈራማ በመሆኑ ልስላሴው ተመችቶኛል፡፡ ነገር ግን አቅጣጫ ስቼ ወደ ጐን በመታጠፍ ዋናውን መንገድ በቶሎ ያዝኩኝ፡፡ የወጣሁበትንም ስፍራ ስጠይቅ “መሐል አምባ” እንደሚባል ተነገረኝ፡፡ በዚሁ መንደር ታሜ ቁጭ ብሎ ከአካባቢው ወጣቶች ጋር እያወጋ አገኘሁት፡፡
ተነስቶም እየተጓዝን ሳለ፣ የሁለተኞቹን የጉዞ አድዋ ማኅበር አርማ የተለጣጠፈበት መኪና፣ አጠገባችን ደርሶ ቆመ፡፡ ሹፌሩና በውስጡ የነበሩትም ወርደው “ኤርሚ እንዴት ነህ? ሰለሞን እባላለሁ” አለኝ፡፡ ደህንነቴንም ነግሬው እግሮቼን ሳሳየው፣ ተገርሞ በሀዘን ስሜት፤ “አይዞህ” ብሎኝ ፎቶ አብረን እንድንነሳ ጠየቀኝ:: ችግር እንደሌለው በመንገር ተነስተን፣ የመርሳ ጉዞአችን ቀጠለ፡፡
“ልክ ነው ያደረግከው” አለኝ ታሜ፡፡ “ምኑ?” ስለው “ማናገርህ! ከያሬድ ጋር ባላቸው ፀብ ተጓዥ መግባት የለበትም” ሲለኝ “ትቀልዳለህ? ከተጣላው ጋር ልጣላኮ አይደለም የተነሳሁት” ብዬው ሳበቃ አንድ የመኖሪያ ቤት ሲያይ ተጠግቶ ልጅቱን “የሚበላ ይኖርሻል?” ብሎ ጠየቃት:: ማባያ የሌለውን ደረቅ እንጀራ ተቀብሎ ቁጭ ብለን ካጋመስነው በኋላ፣ የተረፈውን በፌስታል ቋጠራት፡፡ ታሜ ውፍረቱ እንደ ልብ እንዲንቀሳቀስ ዕድል አይሰጠውም፡፡ ውፍረት እየቀነሰ መምጣቱ ሲነገረው በደስታ ይዘላል፡፡ ብዙ ጊዜም በዚህ ቃል አጽናናዋለሁ፡፡ መሮጥ እንደሚኖርብኝና “ከእኔ ጋር ስትዘገይ ሲያይ ኋላ ደግሞ ያሬድ ይናገረኛል፤ ስለዚህ ቅደም” በማለቱ ፍጥነቴን ጨምሬ ተጓዝኩኝ፡፡ በመጨረሻም አንድ ትልቅ የብረት ድልድይ አግኝቼ አጠገቡም “እንኳን ደህና መጡ ወደ መርሳ ከተማ” የሚል በማየቴ ተጽናናሁኝ፡፡ በአንድ የከተማዋ ነዋሪ አመልካችነትም ጓዶች ያረፉበትን ግቢ አግኝቼ ወደ አዳራሹ ገባሁ፡፡ የመርሳ ከተማ የመንግስት የስራ ኃላፊዎችም ደና ቀና ሲሉ አምሽተው፣ ጣፋጭ እራት ሰርተው እንድንበላ አደረጉ፡፡ ዘማች ሃናም ከማዕዱ አጐረሰቺኝ፡፡
 (በኤርሚያስ መኮንን ከተጻፈውና ሰሞኑን ከተመረቀው “የጉዞ አድዋ ማስታወሻዬ”፤
ጥር 2012፤ የተቀነጨበ)

Read 3844 times