Monday, 20 January 2020 00:00

የአዲስ አድማስ የ20 ዓመታት ጉዞ፤ በጨረፍታ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

  “የግል ፕሬሱ ላይ የሚደረገው ተጽዕኖ፣ እንደ ወቅቱና እንደ ዓመቱ መልኩ ይለያያል”

            ከአዘጋጁ፡- አዲስ አድማስ ጋዜጣ የተመሰረተበትን 20ኛ ዓመት አስመልክቶ፣ ጋዜጠኛ ጌጡ ተመስገን ባለፈው እሁድ፣ ከጋዜጣው ምክትል ዋና አዘጋጅ ኢዮብ ካሣ ጋር ያደረገውን አጭር ቃለ መጠይቅ፣ ከፌስ ቡክ ገጹ ላይ ወስደን ለአንባቢያን አቅርበነዋል::  በዚህ አጋጣሚ፣ የአዲስ አድማስ 20ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ ፣ ጋዜጠኛ ጌጡ ተመስገንን ጨምሮ፣ ቃለ መጠይቅ ያደረጉልንን ሚዲያዎች እንዲሁም የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ያስተላለፉልንን አንባቢያን ሁሉ ከልብ ልናመሰግን እንወዳለን፡፡ ቃለ መጠይቁን እነሆ፡-
***
በኢትዮጵያ የግል ፕሬስ ታሪክ፣ ለ20ኛ ዓመት የምስረታ በዓል መድረስ ከባድ ነው አይደል?
በጣም እንጂ! የዛሬ 15 ዓመትና 20 ዓመት የነበሩትን ጋዜጦችና መጽሄቶች አሁን ካሉት ጋር ማወዳደር ትችላለህ፡፡ ያኔ በመቶዎች የሚቆጠሩ ነበሩ፡፡ አሁን ግን ያሉት በጣት የሚቆጠሩ ናቸው፡፡ ይሄ በራሱ የግል ፕሬሱን ፈተናዎች ያሳያል፡፡ ወደ 20 ዓመት የደረሱና የተጠጉ ጋዜጦች፣ የኛን ጨምሮ ከአራት አይበልጡም፡፡
ባለፉት 20 ዓመታት የአዲስ አድማስ ጋዜጣ ተግዳሮቶች ምን ነበሩ?
እንዴት መሰለህ --- በውጭው ዓለም 100 እና 150 ዓመት የሞላቸው ጋዜጦችን ታገኛለህ:: ዘ ኢኮኖሚስትን የመሰለ ምርጥ መጽሄትና ኒውዮርክ ታይምስን የመሰለ ድንቅ ጋዜጣ መጥቀስ ይቻላል፡፡ የአንባቢዎቻቸውን ቁጥር ደሞ አስበው፡፡ አንድ ጋዜጣ በቀን በ100ሺና በሚሊዮኖች የሚታተምበት ታሪክ ነው ያላቸው፡፡ እዚህ ጎረቤታችን ኬንያ ሳይቀር:: በዚህ የረዥም ዓመታት ታሪክ ሙያው፣ አሰራሩ፣ አመራሩ፣ ቴክኖሎጂው፣ የንባብ ባህሉ ምን ያህል እንደዳበረ ማየት ይቻላል፡፡ የሙያ ሥነ ምግባር ከፖለቲካ ነጻነት ጋር አብሮ ሲሄድ እንደዚህ ነው፡፡ ወደ እኛ ስትመጣ፣ የነጻ ፕሬስ ጋዜጠኝነት ዕድሜው ለጋ ነው - በሙያ ብቃትም ሆነ በሥነ ምግባር፡፡ ፖለቲካውን ደሞ ታውቀዋለህ:: ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የጋዜጠኝነት ትምህርት የተጀመረው በቅርቡ ነው፡፡ የንባብ ባህል ገና እንጭጭ ነው፡፡ የኢኮኖሚው ደካማ መሆን ራሱ መዓት ችግሮች አሉት፡፡ በአንድ በኩል፣ በቂ ማስታወቂያ የማግኘት ችግር በሌላ በኩል፣ የማተሚያ ዋጋ መናር ይፈጥራል፡፡ ይሄ ሳያንስ ደግሞ ፖለቲካው የሚያመጣቸው ጣጣዎችና የመንግስት ተጽዕኖ ይጨመርበታል::
የመንግስት ተጽዕኖ ያልከውን ልታብራራው ትችላለህ?
ተጽዕኖ፤ እንደ ወቅቱና እንደ ዓመቱ መልኩ ይለያያል፡፡ በአንድ ወቅት ላይ በፓርላማ የምንሰማው የዛቻና የማስፈራርያ መግለጫ ሊሆን ይችላል፡፡ ሌላ ጊዜ ደሞ አንዳንድ ባለሥልጣን እየደወለ ቁጣውን ያወርድብሃል፡፡ “ነጻ ፕሬሱንና ተቃዋሚዎችን እንታገላቸዋለን” የሚል የመንግስት አቋም የሰማንበትም ጊዜ አለ:: አንዳንዴ የግል ህትመቶችን በዘመቻ መዝጋት ይሆናል፡፡ የሚብሰው ደሞ እያሰለሰ የሚመጣ የእስርና የክስ ዘመቻ ነው፡፡ ባለፈው የምርጫ ዘመን፣ የታክስ ኦዲት ተብሎ፣ በግል ፕሬሱ ላይ ዘመቻ ተከፍቶ ነበር፡፡ ጣጣው እስካሁን ዘልቋል፡፡ አሳዛኙ ደሞ ችግሩ የመንግስት ተጽእኖ ብቻ አለመሆኑ ነው፡፡ እስካሁን እንደምናየው፣ ነጻ ፕሬስ ማለት፣ ጭፍን ተቃዋሚና አክቲቪስት መሆን የሚመስላቸው አሉ፡፡ ይሄም በራሱ ለግሉ ፕሬስ ወደ ኋላ መቅረት ጉልህ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡
በእነዚህ ዓመታት የጋዜጣው አበርክቶ ምንድን ነው?
ነጻ ፕሬስ ነጻነቱን ጠብቆና የጋዜጠኝነት ሥነምግባርን አጽንቶ፣ ዕድሜ እንዲኖረው ማድረግ ቀላል አይደለም፡፡ አዲስ አድማስ በዚህ ከሚጠቀሱ የግል ፕሬስ ውጤቶች አንዱ ነው:: በሰለጠኑት አገራት እንደምናየው፤ ነጻ ፕሬስና ጋዜጠኝነት ፖለቲካ ብቻ አይደለም:: ይሄን በማሳየት አዲስ አድማስ በአርአያነት የሚጠቀስ ነው፡፡ ለንባብ ባህልና ለኪነ ጥበብ ያበረከተውን አስተዋጽኦ ማየት ትችላለህ፡፡ ያለ ማጋነን አዲስ አድማስ ላይ ያልጻፈ ደራሲና ገጣሚ ብዙ አታገኝም፡፡ ይሄ እንደ ጋዜጣው አዘጋጅነቴ ያኮራኛል፤ እርካታም ይሰጠኛል፡፡ ለረዥም ዓመታት የመጻህፍት ሂስና ዳሰሳ በማቅረብ፣ በሙዚቃ ሥራዎች ላይ ትንታኔ በመስጠትም ይታወቃል፡፡ በየሳምንቱ ወጥና ትርጉም አጫጭር ልብወለዶችን በማስነበብ፣ ምናልባት፣ ብቸኛው ጋዜጣ ሳይሆን አይቀርም፡፡ በየሳምንቱ ኪነ ጥባባዊ ዝግጅቶችን በመጠቆምና አዳዲስ መጻህፍትን በማስተዋወቅም ጉልህ ሚና ተጫውቷል፡፡
በሌላ በኩል፤ በጋዜጣው ላይ ትንታኔያቸውን የሚያቀርቡ ምሁራንን፣ ሃሳባቸውን የሚገልጹ ፖለቲከኞችን ማየት ትችላለህ፡፡ በየሳምንቱ የሚስተናገዱ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችን ተመልከት፡፡ ለምሳሌ የስኳር ፕሮጀክቶች፣ የሜቴክ የመሳሰሉት ከፍተኛ ቀውሶችና ችግሮች አምና ድንገት የተከሰቱ አይደሉም፡፡ በአዲስ አድማስ ጋዜጣ፣ ላለፉት 8 ዓመታት፣ የቀረቡና የታተሙ ዘገባዎች ናቸው፡፡ እንዲሁ በጭፍን ተቃውሞ ሳይሆን በተጨባጭ መረጃዎችና በጥልቅ ትንታኔ በተደጋጋሚ ቀርበዋል:: በአጠቃላይ አዲስ አድማስ፤ የፖለቲካና የኢኮኖሚ፣ የባህልና የኪነ ጥበብ ጉዳዮችን የሚዳስስ፣ የእርስዎና የቤተሰብዎ ጋዜጣ ነው ማለት ይቻላል፡፡
የአዲስ አድማስ መሥራችና ባለቤት አሰፋ ጎሳዬ ላንተ ምን ዓይነት ሰው ነበር?
እስካሁን የጠቀስኳቸውን ነገሮች ሁሉ የፈጠረልን አሰፋ ጎሳዬ ነው፡፡ በዚያን አስቸጋሪ ወቅት አዲስ አድማስን የመሰለ ጋዜጣ ለመፍጠር ብቻ ሳይሆን ጽኑ መሰረት ላይ ለማቆም፣ ምጡቅ ሃሳብና ራዕይ የነበረው ሰው ነው፡፡ በዕውቀትም በአርቆ አሳቢነትም፣ በብሩህ ራዕይና በጠንካራ ሰብዕናም የታደለ፡፡ የቅንነትና የትጋት ህያው አርአያችን ነው፡፡ የላቀ ህልምን በጥረትና በጽናት እውን የማድረግ፣ የ‹‹ይቻላል››፣ ተምሳሌት ነው ብዬ አስባለሁ፤ ለኛ ብቻ ሳይሆን ለአገርም ጭምር፡፡


Read 3245 times