Print this page
Sunday, 19 January 2020 00:00

የዘንድሮው ምርጫ አደጋዎችና የሚያባብሱ ፈተናዎች፡፡

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(2 votes)

    • ሰላምና የሕግ የበላይነት ደልደል እስኪል ድረስ፣ ምርጫውን ማራዘም ይሻላል? ግን፣ ምርጫውን ለሚቀጥለው ዓመት ማሻገር፣ የሕግ የበላይነትን የሚጥስ ከሆነ ወይም ፓርቲዎች ባይስማሙበትስ?
    • እስካሁን፣ ብዙ ፓርቲዎች የተስማሙበት አንድ የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ሃሳብ አለ፡፡ በወንድ ፆታ የተፃፉ አንቀፆችን፣ የሴት ፆታንም በሚያካትት መንገድ
ለማሻሻል ይፈልጋሉ፡፡ ይሄ፣ ‹‹አገራዊ መግባባት›› ይባላል?
   • ምርጫው የሚራዘምበት ሕጋዊ መንገድ ከሌለ፣ ወይም ብዙ ተቀባይነት ካላገኘ፣ የምርጫ ዘመቻውን ለማሳጠር፣ ክርክሮችን ለመቀነስ ብዙዎቹ ፓርቲዎች
ቢስማሙ፣ መልካም ሊሆን ይችላል፡፡ ለምን?
    
            በብዙ የአፍሪካና የአረብ አገራት ውስጥ በተደጋጋሚ እንደታየው፣ በኢትዮጵያም፣ ‹የምርጫ ጊዜ፣ የአደጋ ጊዜ› ነው፡፡ ይህንን ‹‹የኋላ ቀር ፖለቲካ መዘዝ›› በቅጡ መገንዘብ አለብን፡፡  አደጋውን ለመቀነስና አስቀድመን ለመጠንቀቅ ከፈለግን ማለቴ ነው።
እንደ ኢትዮጵያ በመሳሰሉ አገራት፣ የፖለቲካ ምርጫ፣ አስፈሪ አደጋ የሚሆነው አለምክንያት አይደለም። ለስነምግባር፣ ለግለሰብ ነፃነትና ለሕግ ተገዢ ያልሆነ፣ ኋላቀር የፖለቲካ ቅኝት ነው፣ ዋናው የአደጋ መንስኤ። ክፋቱ ደግሞ፣ አደጋውን የሚያባብሱ ጥፋቶች፣ ባለፉት ጥቂት ዓመታት፣ እጅግ ተበራክተዋል።
አቶ ልደቱ አያሌው እንደተናገሩት፣ የፖለቲካ ምርጫ ይቅርና፣ የዩኒቨርስቲ ትምህርት እንኳ፣ በሰላም ማከናወን አስቸጋሪ ሆኗል። በእርግጥም፣ 35ሺ ተማሪዎች፣ የዩኒቨርስቲ ትምህርታቸውን አቋርጠዋል። ተማሪዎቹና ወላጆች፣ አይፈረድባቸውም። የበርካታ ተማሪዎች ሕይወት ጠፍቷል። ዩኒቨርስቲ - ለሕይወት አስፈሪ ሆኗል፡፡
የፖለቲካ ምርጫ ደግሞ አስቡት። የፓርቲዎች ፉክክርና የፖለቲከኞች ክርክር ሲጋጋል፣ የምርጫ ጩኸት ሞቅሞቅ ሲል፣ ‹ድንቅ የፖለቲካ ስልጣኔን› በእውን ለማየት የበቃን ሊመስለን ይችላል። ካሁን በፊት መስሎናል። ነገር ግን፣ ብዙም ሳይቆይ፣ ፉክክሩ፣ መያዣ መጨበጫ ወደሌለው እንካሰላንቲያ፣ ክርክሩም መቋጫ ወደማያገኝ ውዝግብ እንደሚለወጥ ነው ካሁን በፊት ያየነው፡፡
ከዚያም፣ የአሉባልታና የሃሰት ውንጀላው እየገነነ፣ ነገሩ ሁሉ፣ የፉከራና የዛቻ ድግስ ይሆናል። እነዚህ ጭፍን የቅስቀሳ ዘመቻዎች፣ አየር ላይ ተበትነው፣ በዚያው ብን ብለው የሚጠፉ አይደሉም።
በጭፍን ቅስቀሳዎች ማግስት የሚካሄዱ ‹ሰላማዊ ሰልፎች›፣… ሦስት አራቴ፣ ከሞላ ጎደል ሰላማዊ ሆነው ሊጠናቀቁ ይችላሉ። ግን ሰላማዊ ሆነው አይዘልቁም። ኋላ ቀር የፖለቲካ ቅኝት፣… ሞተር፣ መሪ እና ፍሬን እንደሌለው መኪና ነው:: በድንዛዜ ተወዝፎ በዝገት እየተበላ አመታትን ሊያስቆጥር ይችላል፡፡ ለመንቀሳቀስ የሚያስችል የሞተር አቅም የለውም፡፡ ሆይ ሆይታ፣ ውሽንፍር፣ ማዕበል፣ ናዳ የመሳሰሉ ነገሮች ሲመጡ፣ ያንገጫግጩታል፣  ይገለብጡታል፣ ያነሱታል፣ ይጥሉታል፣ ያንሸራትቱታል፣ ያንደረድሩታል፡፡ በራሱ አቅም አማካኝነት ባይሆንም ይነቀነቃል፡፡ ግን፣ አቅጣጫውን ማወቅ፣ መምረጥና መቆጣጠር አይችልም፡፡
ናዳ ወርዶበት፣ አውሎ ነፋስ ገፍትሮት፣ መሬት አንሸራርቶት ቁልቁል መውረድ ከጀመረ፣ ፍሬን እንደሌለው መኪና፣ ኋላቀር የፖለቲካ ቅኝትም እንዲሁ፣ ማቆሚያ በሌለው የጡዘት ምህዋር ይሾራል፡፡
ሰላማዊ ድጋፍና ተቃውሞ ተብሎ ይጀመርና፣  የአድማና የፍጥጫ ስሜት ይለኮሳል። ይራገባል። ግርግር በመፍጠርም ሆነ መንገድ በመዝጋት፣ ስራንና ኑሮን ማወክ ይመጣል። ንብረት መዝረፍና ማቃጠል ይጨመርበታል። የማፈናቀል ዘመቻና ግድያ እንደዘበት የሚበራከቱበት ሰበብ ይሆናል - የፖለቲካ ምርጫ።         
የኋላ ቀር ፖለቲካ መዘዝ ይኼው ብቻ አይደለም፡፡ ዝርፊያና ቃጠሎ፣ ስደትና ግድያ አገሪቱን ከዳር ዳር እያዳረሰ ሲያቃውሷት፣ ሁለት ክፉ ገጽታዎች ገዝፈው ይጋረጡብናል፡፡ በአንድ በኩል ‹‹ረግጬ ቀጥቅጬ ሰላምን አሰፍናለሁ›› ብሎ የሚመጣ ሕግ የማይገዛው አምባገነን መንግሥት (Tyranny)፤ ወይም ደግሞ፣ ሕግ የማስከበር አቅም ይጠፋና፣ በየቀዬው በየሰፈሩ እልፍ የመንደር አምባገነኖች የሚራኮቱበት፣ እጅግ ዘግናኝ የአገር ትርምስ (anarchy)… እነዚህ ናቸው - አስቀያሚዎቹ የኋላ ቀር ፖለቲካ ክፉ ገጽታዎች፡፡
ምን ለማለት ፈልጌ ነው? እንደ ‹‹ድንቅ የፖለቲካ ስልጣኔ›› ሲወደሱ የምንሰማቸው ‹‹ዲሞክራሲ እና ምርጫ›› የሚሉ መፈክሮች፣ ልካቸውና ቦታቸው እየተጋነነ አልፋና ኦሜጋ ሆነው በቁንጽል የሚገዝፉ ከሆነ፣ አደጋ ነው:: ከነጭራሹም ከእውነትና ከስነ ምግባር፣ ከግለሰብ ነፃነትና ከሕግ የበላይነት ስር ከመገዛት ይልቅ በተቃራኒው፤ ‹‹ዲሞክራሲና ምርጫ›› የቀዳሚ ቀዳሚ ከሆኑ፣ የጊዜና የመጠን ጉዳይ እንጂ፣ ጥፋትንና ቀውስን፣ ከዚያም አምባገነንነትን፣ አልያም፣ ይባስኑ፣ ሥርዓት አልበኝነትን አስከትለው እንደሚመጡ መገንዘብ አለብን።
በዚህ ላይ፣ አደጋውን በሚያከብዱ ፈተናዎች የበረከቱበት አስቸጋሪ ወቅት ውስጥ መሆናችንንም ጨምሩበት፡፡ ባለፉት ጥቂት አመታት፣ የስነ ምግባር ጥንካሬ እየመነመነ፣ የስነ ምግባር ድክመት ደግሞ ሲስፋፋ ታዝበናል፡፡
ከነባሮቹ ጥፋቶች በተጨማሪ፣ ለወትሮ ‹‹ነውር፣ ክፉ፣ ወራዳ›› ተብለው ይወገዙ የነበሩ ተግባራት፣ በግላጭ እየተፈፀሙና እየተላመድናቸው መጥተናል፡፡ አንዳንዶቹም የፖለቲካ ሰበብ እስከተላበሱ ድረስ፣ እንደ ሃላል ወደሚቆጠሩበት ዝቅታ አሽቆልቁለናል፡፡ ይህም ብቻ አይደለም፡፡  የአሉባልታና የዛቻ ማሰራጫ፣ እንዲሁም የጭፍን ጥላቻና የጥቃት ዘመቻዎችን እየቀሰቀሱ ለማሰማራት የሚያገለግል የሚዲያ አይነትና ብዛት፣ ዛሬ እልፍና ሚሊዮን ሆኗል፡፡
ከዚህ ጎን ለጎን፣ የአመፅና የትርምስ ዘመቻዎችን፣ እንደ ሰደድ እሳት በየአቅጣጫው ለማዛመት የሚያመቹ በርካታ ‹‹ማዕከላት›› ተፈጥረዋል፡፡ በተደጋጋሚ በተግባር ተሞክረውም አደገኛነታቸውን አስመስክረዋል:: ዩኒቨርሲቲዎችና ስቴዲዮሞችን መጥቀስ ይቻላል፡፡
ሌላ ፈተናም አለ፡፡ ነባሩ ኋላ ቀር የፖለቲካ ቅኝት አልተቀየረም፡፡ አደገኛነቱም አልተለወጠም፡፡ ይልቅስ፣ የተዋናዮቹ ቁጥር ጨምሯል - በዚያው ልክ አደጋውም ይብሳል፡፡  
በእርግጥ፣ አደጋውን ለማቃለል የሚያግዙ ነገሮችም አሉ፡፡ የመንግስት ተቀባይነት፣ አንዱ ጥሩ አዝማሚያ ነው፡፡ መጠኑን ከነክብደት ለክቶና መዝኖ ‹‹እቅጩን›› ለመግለጽ ቢያስቸግርም፣ ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ የሚመሩት መንግስት፣ ከቀድሞው የተሻለ ተቀባይነት እንዳለው ብዙ አያከራክርም::
ከፖለቲካ ተቀናቃኝነት እና ከውዝግብ በላይ ልቀው፣ የአገር ህልውናንና ቋሚነትን፣ የህግና ስርዓት ቀጣይነትን የማሳየት፣ ጽኑ ሰንደቅ የመሆንም ኃላፊነት የተረከቡት ፕ/ት ሳህለወርቅ ዘውዴ፣ በብዙዎች ዘንድ የተከበሩ ናቸው፡፡
የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳም እንዲሁ፣ በዋና ዋና ተቅናቃኝ ፓርቲዎችና ፖለቲከኞች ዘንድ ተቀባይነትን ብቻ ሳይሆን፣ ተመራጭነትንና ድጋፍን ያገኙ መሆናቸው፣ መልካም ነው፡፡
ከእነዚህ በተጨማሪ፤ የምርጫ አደጋን ለማለዘብ የሚረዱ ሌሎች ነገሮችን መጥቀስ ይቻል ይሆናል፡፡ ባለፈው ክረምት ደህና ዝናብ መገኘቱና አዝመራው ለክፉ የማይሰጥ መሆኑ፣ ጥሩ እድል ነው፡፡ በቅርቡም፤ የአለም ገንዘብ ድርጅት ከ300 ሚሊዮን ዶላር በላይ ብድር፣ በፍጥነትና በአንዴ ለመስጠት መወሰኑ፣ ጊዜያዊ እፎይታን ያስገኛል፡፡
ግን ደግሞ፣ በተቃራኒው በዓመት ውስጥ ብቻ፣ ለውጭ እዳ ከነወለዱ፣ ከ2 ቢሊዮን በላይ ዶላር እየተከፈለ ነው፡፡ የውጭ ንግድ ከድንዛዜና ከማሽቆልቆል አለመላቀቁ፣ ከጐን ለጐንም የዋጋ ንረት በዓመት 20% እየጨመረ መሆኑ፣ ለኑሮ ብቻ ሳይሆን ለሰላምም አይበጅም፡፡
በአጠቃላይ፣ የምርጫ አደጋን ለማቃለል የሚጠቅሙ ጥቂት መልካም ለውጦች ቢኖሩም፤ አደጋውን የሚያባብሱ ፈተናዎች እጥፍ ድርብ ይበልጣሉ፡፡
እንግዲህ አስቡት፡፡ የምርጫ ጣጣ ተጨማምሮበት ይቅርና፣ በሌላ ጊዜም፣ የአገራችን ፖለቲካ፣ ሰላም የሚሰጥ አልሆነም:: በየእለቱና በየአካባቢው፣ ያለፋታ ሰላም የሚደፈርስ ከሆነ ደግሞ፣ ሕግ ከሞላ ጐደል የሚከበርበት ስርዓት ይላላል፡፡ ክፉ አዙሪት ነው፡፡ የሕግ የበላይነት ሲላላ፣ በተራው፣ ሰላምን ለሚያደፈርሱ ሰዎች ተጨማሪ እድል እየተፈጠረ፣ አገር ይታመሳል፡፡
በዚህ ላይ፣ የምርጫ ጣጣ ሲታከልበት ያስፈራል፡፡
ምርጫውን የማራዘም ሃሳብና የሕግ የበላይነት፡፡
ከሞላ ጎደል፣ ሕጋዊ ሥርዓትንና ሰላምን በተግባር ማደላደል ካልተቻለ፣ በዚህ ዙሪያና በሌሎች መሰረታዊ ጉዳዮች ላይም፣ ተቀናቃኝ ፓርቲዎች ሳይስማሙና ‹‹አገራዊ መግባባት›› ሳይፈጠር፣ ምርጫውን ማራዘም እንጂ፣ ዘንድሮ ምርጫ ማካሄድ አይበጅም የሚሉ አስተያየቶች መቅረባቸው አይገርምም፡፡ በእርግጥም፣ ያሳስባል።
በመሰረታዊ ጉዳዮችና በትክክለኛ ሃሳቦች ላይ፣ ተቀናቃኝ ፓርቲዎች ቢስማሙና ‹‹አገራዊ መግባባት››ን ቢገነቡ፣ ብዙዎች እንደሚናገሩትም፣ ሕገ መንግሥትን በሚያሻሽሉ ትክክለኛ ሀሳቦች ዙሪያ ሰፊ ተቀባይነትን ቢፈጥሩ መልካም ነው፡፡ አዎ፣ ብዙ መሻሻል የሚገባቸው የሕገ መንግሥት አንቀፆች አሉ፡፡
ነገር ግን፣ ብዙ ተቀናቃኝ ፓርቲዎችና ምሁራን የተሳተፉበት  ‹‹Destiny Ethiopia›› የተሰኘው ድንቅ የመግባባት ሙከራ ላይ እንደታየው፤ ‹‹የትኛው የሕገ መንግሥት አንቀፅ፣ በምን መንገድ ይሻሻል?›› በሚለው ጥያቄ ላይ፣ ይህ ነው የሚባል ስምምነት የለም፡፡ በአንድ ነገር ብቻ ላይ ነው ብዙ ፖለቲከኞች የተስማሙት፡፡ በወንድ ፆታ የተገለፁ የሕገ መንግሥት አንቀፆች፣ የሴት ፆታንም በሚያካትት መንገድ እንዲሻሻሉ ብዙዎች ተስማምተዋል፡፡ በቃ፡፡
ከዚህ ውጭ ግን፣ እስካሁን ሰፊ ተቀባይነት ያገኘ ሌላ የማሻሻያ ሃሳብ የለም፡፡ በሌሎች ጉዳዮች ላይም፤ በአገራችን ፓርቲዎችና ፖለቲከኞች ዘንድ፣ በአንድ ዓመት አይደለም፣ በአምስት ዓመትም ተዓምረኛ የመሻሻል ለውጥ ይመጣል ብሎ መጠበቅ ከባድ ነው:: እንዲያውም፣ የመበላሸት ለውጥ ካልመጣ፣ ‹‹ተመስጌን›› ነው፡፡
እናም፣ አቶ ልደቱ እንዳሉት፣ በትክክለኛ መሰረታዊ ሀሳቦች ላይ ‹‹አገራዊ መግባባት›› ቢፈጠር መልካም ነበር፡፡ እንዲህ፣ ትክክለኛ ሃሳቦች ላይ ባተኮረ ስኬት ነው፣ ወደ ስልጡን ፖለቲካ መጓዝ የሚቻለው፡፡ ምርጫ በማካሄድ ብቻ፣ ስልጡን ፖለቲካ አይፈጠርም፡፡ የምርጫ ድርሻ፣ የተወሰኑ የመንግሥት ሰራተኞችን መርጦ ከመቅጠር ያለፈ ብዙ ፋይዳ ሊኖረው አይገባም - በስልጡን የፖለቲካ ቅኝት፡፡
ለማንኛውም፣ በተቀናቃኝ ፓርቲዎች መካከል ስምምነትን፣ በትክክለኛ ሀሳቦች ዙሪያ ‹‹አገራዊ መግባባት››ን መፍጠር፣ በብዙ ዓመታት ከተሳካልን ጥሩ ነው፡፡
ሕጋዊ ሥርዓትንና ሰላምን፣ በተወሰነ ደረጃ የማደላደል ጉዳይ ግን፣ አጣዳፊ ነው፡፡ በአንድ በኩል ለምርጫው ያስፈልጋል፡፡
በተለይ በተለይ ግን፣ ከምርጫው፣… አገር በደህና፣ ዜጐችም በጤና እንዲተርፉ ከፈለግን፣ በተቻለ መጠን ሕጋዊ ስርዓትንና ሰላምን ማደላደል ይገባል፡፡
ችግሩ ምንድነው? ምርጫውን ማራዘም፣ ለዚህ ይጠቅማል ወይ?  በተለይ ደግሞ፣ ምርጫውን በሕጋዊ መንገድ የሚራዘምበት እድል ከሌለ፡፡ ‹‹በልዩ የለውጥ ወቅት ውስጥ ስለሆንን፣ ብዙ ሕጐች እየተጣሱ መሆናቸውም ተጨባጭ እውነታ ስለሆነ፣ ህጉ ባይፈቅድም፣ ምርጫውን ማራዘም ይገባናል›› ብንል ትክክል ይሆናል?
የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ እንደተናገሩት፣ የፍርድ ቤቶችን ስራ፣ ተገቢ መሆን አለመሆኑን የምንለካው፤ ‹‹በሕጋዊ መንገድና በሕግ ሚዛን ዳኝተዋል ወይስ አልዳኙም›› በሚል መለኪያ ነው፡፡
የምርጫ ቦርድ፤ ውሳኔና ተግባርም ሌላ መለኪያ ሊኖረው አይገባም፡፡
ከሕግ ሚዛንና ከሕግ የበላይነት ውጭ ሰንሄድ፣ ነገሩ ሁሉ መያዣ መጨበጫ ያጣል:: አንዱን ሕግ የመጣስ ስልጣን ከተሰጠን፣ ሌሎች ሕጐችን ላለመጣስ ምን ያግደናል በሚል ጥያቄም አንስተዋል - “Slippery slop” የተሰኘውን የጥንቃቄ ሃሳብ በሚጠቁም መንገድ፡፡
አቶ ልደቱም፣ ‹‹የሕግ የበላይነት›› ከዋናዎቹ መሰረታዊ ጉዳዮች መካከል አንዱ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
በእርግጥ፣ ምርጫው የሚራዘምበት ሕጋዊ መንገድ ካለ፣ በጥንቃቄ ቢፈተሽ መልካም ነው፡፡

Read 3224 times