Saturday, 18 January 2020 13:52

ሞቴ - ትንሽ ቆየኝ

Written by  ድርሰት፡- ኪሩቤል ሳሙኤል
Rate this item
(5 votes)

  ፀጥታ ውስጥ ነኝ፡፡ ዝምታ፡፡ ከፊቴ የማየው የማይተነፍስ ቀለም ነው፡፡ ዝምታ፡፡ ወደየትም መሄድ አልፈልግም፡፡ መራመድ ሰልችቶኛል:: መራቀቅ፣ መራመድ፣ ማሰብ መተርጐም፤ መትፋት፤ መሞት፤ መታዘብ፤ መክሳት፤ መገኘት፤ ማግባት፤ መሳፈር፤ ማውራት፤ መፃፍ፤ማምለክ፣ መራቅ፣ መፍረድ፣ መግባት፤ መሳል፤ መታመም፤ እድሜን መተንፈስ፤ መተኛት፤ መፍራት፤ መዝፈን፤ መሳቅ፤ መርዘም፤ ማብራት፤ መታጠብ፤ ማጨስ፤ መግዛት፤ መስማት፤ መተንፈስ፤ መውለድ፤ መጨነቅ፤ መሳለም፤ መገመት፤ ማመን፤ ማወቅ፤ መፈላሰፍ፤ መተኛት፤ መፈላሰፍ፤ መተኛት፤ ማውራት፤ ማውራት፤ ማውራት፤ መተንፈስ፤ መተንፈስ፤ መኖር መሞት፤ መሞት መሞት…ፀጥታ … ዝምታ…
ከቤት መውጣት አልፈለኩም፡፡ ሆኖም መውጣት አለብኝ፡፡ አሞኛል፡፡ መድሃኒት መፈለግ አለብኝ፡፡ ከቤት መውጣት አልፈለኩም፡፡ ከሰዎች ጋር አይን ለአይን መተያየቱን አልፈለኩትም፡፡ መሰወሪያ ድግምት፤ እፀ መሰውር፤ ማናምን፤ ምናምን የሚባሉ ሚስጥራዊ እውቀቶችን እስክመረምር ድረስ የመሰወር፣ ያለመታየት፤ ያለመወራረስ፤ ያለመገማመት፤ ያለወሬ፣ የመኖር እድሜዬን ለመከወን ብዙ የእውቀት በሮችን ከፍቻለሁ፡፡ ያለሰዎች ግን መኖር አይቻልም፤ ሁሌም አሉ፤ ሁሌም ይገኛሉ፡፡ ይጠሩሻል፡፡ ስለሙሉ የቀን ታሪካቸው ትሰማለህ፣ ይደከምሃል፡፡ ሆኖም የወሬውን ሸክም በጆሮህ ሸቅሽቀህ ትከታለህ፡፡ የማሰቢያ ጊዜ የለህም፡፡ ጭንቅላትህን ወርሰውት ባንተ አዕምሮ ያስባሉ፡፡ ባፍንጫህ ይተነፍሳሉ፣ ባይንህ ያያሉ፣ ሀዘንህን ያለቅሱታል፣ ደስታህን ይስቁታል፡፡ ይሄ የመወራረስ፣ አብሮ የመዋል ጉዞ አሰልችቶኛል፡፡ የት ይሆን እረፍት ያለው…
ሆኖም ከቤት ወጥቼ መድሃኒት መግዛት አለብኝ፡፡ ሰው የሰራውን መድሃኒት፡፡ ሁሌ ከመውጣቴ በፊት የአከራዬን ፊት ላለማየት የግቢውን ድምጽ በትኩረት አዳምጣለሁ፡፡ የቅጠሎቹ ድምጽ ራሱ መሰማት የሚጀምረው ይህ ለእይታ በቂ ያልሆነው አከራዬ ሲተኛ ነው:: የሱን አለመኖር ካረጋገጥኩ በኋላ በቀስታ ከቤት እወጣለሁ፡፡ የመንደሩ ሰው ሰላምታ እንዳይሰጠኝ የኔ በምላት፤ እንኳን ሰው የፈሩ እንስሶች በማይሄዱበት መንገድ ጉዞዬን አደርጋለሁ፡፡ የሚሰማኝን ሰላም ልገልጽልህ አልችልም፡፡ ምንም እንኳን መንገዱ በግማትና አይንን በሚያጠለሹ እርምስማሽ የሰው ተረፈ ምርቶች ቢሞላም በውስጣቸው ሰውን ስላልያዙ በደስታና በኩራት እራመድባቸዋለሁ:: ፍቅር ከዚህ ይጀምራል፡፡ እውነት መተንፈሻ የሚያገኘው እዚህ ቦታ ነው፡፡ የፀጥታን የክብር ወለል የምትረግጠው እዚህ ነው፡፡ ግን አደራህን ይህች የኔ መንገድ ናት፡፡ ለመምጣትም ደግመህ እንዳታስብ፡፡
ሁሌ ከመውጣቴ በፊት ይህን ነበር የማደርገው፡፡ አሁን ግን ምን እንደሆንኩኝ እንጃ፡፡ ባዶ ህልም ሽፋሽፍቴ ላይ አክራሞቱን አጠንክሮ ከአየር የሳሳ የደስታ ስሜትና ከአለት የጠነከረ መሰላቸት ውስጥ ከቶኛል፡፡ ሆኖም ዛሬ አሞኛል፡፡ ግዴታ መዳን አለብኝ፡፡ ምንም እንኳን ሞት የህይወት ብቸኛው ትርጉም እንደሆነ ብረዳውም ግድ የለም የህይወትን ኩሽና ገና በርብሬ አልጨረስኩም…
ከአልጋዬ ላይ ተነስቼ ጫማዬን አደረኩኝ:: ሁሌም እንደማደርገው ያለምንም ፀሎት፤ ያለምንም ምስጋና፣ ያለምንም አክብሮት፤ ያለምንም ስሜት ውስጥ ሆኜ ጓደኛዬ በእርሳስ ስሎ ያመጣልኝ የክርስቶስ ምስል ላይ አፈጠጥኩበት፡፡ ስዕሉን ሲሰጠኝ የመጀመሪያው ቀን ደብሮኝ ነበር፡፡ አሁን ግን እሱ ከሞተ በኋላ ያለኝ ወዳጄ የእርሳሱ ቀለም አድኖ ያገኘው ምስል ነው፡፡ እኔም ወዳጄም የማናውቀው ሆኖም መሆን የምንፈልገው የሰው ምስል፡፡ የክርስቶስ ምስል፡፡
ፊት መታጠብ ስለማልወድ ጫማዬን እንዳረኩኝ ቤቴን ለቅቄ ወጣሁ፡፡ ከቤቴ ከወጣሁ ሁለት ወራቶች አልፈዋል፡፡ በነዛ ሁለት ያለሰው የቆየሁባቸው ወራቶች እንዴት ውብ እንደሆኑ አትጠይቀኝ፡፡ ልክ እንደ ህፃን ልጅ የመጀመሪያ ፈገግታ እንደውሾች ናፍቆት እንደ እፉዬ ገላ መንከባለል ብቸኝነት ሁሉም ውብ የሆኑ ነገሮች ጥርቅም ውጤት ነው፡፡
የምኖርበት ቦታ ኮተቤ የሚባል አዲስ አበባ ውስጥ ያለ አንድ መንደር ውስጥ ነው:: ኮተቤ ጠዋት ላይ ስትወጣ የሚያጋጥምህ ነገር ቢኖር…እንቅልፉን በቅጡ ያልጨረሰ ሰራተኛ በብርድ እየተቆላ ሰልፍ ይዞ ታክሲ ሲጠብቅ፤ የቀን ሰራተኛው የመሳሪያ እቃውን እና ኩንታል ተስፋውን ተሸክሞ እንደ በጐች ተጠጋግቶ አንድ ቦታ ላይ ሰፍሮ ከሆነ መኪና ውስጥ ወደሱ የሚጠቁም ጣት ፍለጋ ለአይኖቹ እግሮች ተክሎላቸው ሲያራውጣቸው፤ ጉሊት ቸርቻሪዎች መደቦቻቸውን እያስተካከሉ እነሱም ሆኑ የምድር ፈጣሪ ባልገባው ነገር ሲሰዳደቡና ሲዛዛቱ ታያለህ፡፡ ሁሉም ሱቆች በጊዜ ነው የሚከፈቱት ሆኖም ከታክሲ ሰልፈኛው ቀጥሎ የምትመለከተው ዘይት ወይም ስኳር ለመግዛት የሚሰለፈው ሰው ሳይሆን የሚበዛው ጫት የሚገዛው የጐረምሳ ግሪሳ ነው፡፡ ኮተቤ ውስጥ ጫት ሀይማኖት ነው፤ ሀይማኖቱ የሚጣሰው በአረቄ እና በሴተኛ አዳሪዎች ነው፡፡ ይህ ሁሉ ያስፈራኛል…ይቀፈኛል…እውነታውን መግደል ብችል ምን ያህል እድለኛ በሆንኩኝ ነበር፡፡ ሆኖም አንድ ሰው ብቻ ነኝ፡፡ ከዚህ በላይ ከፍ እንደማልል ነው የገባኝ፡፡
ማንም የማይደፍራትን መንገድ ይዤ በመሄድ ላይ እንዳለሁ ድንገት አንድ ግቢ ላይ ተንጠልጥሎ ያለ ማስታወቂያ ቀልቤን ሳበው:: ምናምን የባህል ህክምና ይላል፡፡ ወደ ስልሳ የሚደርሱ ምናልባትም ወደፊት ሊመጡ ይችላሉ ተብለው የተገመቱም በሽታዎች ሊሆኑ ይችላሉ ብቻ የበሽታ አይነቶቹ ባነሩ ላይ ተጠግጥገው ተመለከትኩኝ፡፡ የባህል ሀኪሞች አብዛኞቹ በግምት መዳኒት እንደሚሰጡ ሰምቻለሁ:: ይሄን እድል ተጠቅሜ ለምን የመሞት እድሌን አልጠቀምም ብዬ ድንገት ማሰብ ጀመርኩኝ:: ከዚህ በኋላ ከድምጽ ተለይቼ…ከስልክ፣ ከመብራት፣ ከቤት፣ ከምግብ፣ ከውሃ፣ ከእጽዋት፣ ከእንስሳት በተለይ በተለይ ከሰው ተለይቼ የምኖርበት ቦታ ሞት ውስጥ እንደሆነ ድንገት ተከሰተልኝ፡፡ ስሜቱ አስደሳችም አስፈሪም ነው፡፡ ልቤ ቦታ ለመቀየር ይመስል ከግራ ወደ ቀኝ በኩል ተወርውሮ ለማምለጥ ደረቴ ውስጥ ያገኘውን ነገር እየገፈታተረ ሲመታ ይታወቀኛል፡፡ አንድ ጊዜ አየር ስቤ ተነፈስኩኝ:: እብድ በለኝ ከፈለክ በቆምኩበት ልክ ሰው እያናገረኝ እንዲመሰለኝ አድርጌ ኦናው አየር ላይ ፈገግ አልኩኝ፡፡ የገዛ ፈገግታዬ አቅለሸለሸኝ፡፡ ራሴን የባህል ህክምና ያለበትን ግቢ እያንኳኳው አገኘሁት፡፡
በሩ በዝግታ ተከፍቶ የአንድ ሰው ጭንቅላት ብቅ አለ፡፡ እንድገባም በትህትና በእጁ ምልክት ሰጠኝ፡፡ የሰየውየው መረጋጋት ያስፈራል፡፡ በዚህ ዘመን ውስጥ ስሜቱን ማድመጥ የማይቻል ሰው ማግኘት ከባድ ነው፡፡ ሁሉም ስሜታዊ በሆነበት ሀገር ውስጥ እንዲህ ያለ ከውሃ ሚስጥር በላይ የሆነን ሰው መመልከት የግል ፈተና ውስጥ ይከታል፡፡ በቤቱ ውስጥ አስገባኝ፡፡ በግድግዳው ላይ ከጊዜ መቁጠሪያ ካላንደር ውጭ ምንም የተለጠፈ ነገር የለም፡፡ የቤቱ ፀጥታ ከዚህ ቀደም ከነበሩት አስር ሺህ አመታት በፊት ሰው ዝር ያለበት እንዳይመስል አድርጐታል፡፡ ሁሉም የቤቱ እቃዎች በስርዓት ተደርድረዋል፡፡
ሰውየው እኔን በሳሎኑ ውስጥ አስቀምጦ ወደ ሌላኛው ክፍል ገብቶ ጥቂት ቆይቶ በእጁ የሆነ የሚጨስና በእሳት የተቀጣጠለ እንጨት ይዞ መጥቶ የቤቱን አራቱንም አቅጣጫ እየተዟዟረ የጭስ ውቅያኖስ በቤቱ ውስጥ መስራት ጀመረ፡፡ አታጭስብኝ ልለው ነበር…ወይም እንጨቱን ተቀብዬው ከሳሎኑ ውጭ መወርወርም አምሮኝ ነበር ሆኖም እጅም ቃላት ሊጠጉት የማይችሉት የስሜት ከፍታ ውስጥ መግባት ጀመርኩኝ፡፡ ከልቤ ላይ ተንጠልጥላ የነበረችው ነፍሴ ከእስር ተለቃ የራሴኑ እጅ ይዛ ወደ ጥልቁ ህዋ ልትወስደኝ በለስላሳ ጣቶቿ ስትዳብሰኝ ተሰማኝ፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ ሰውነቴ ልክ እንደተከራየሁት ቤት የኔ አልመስልህ አለኝ:: እኔ ነኝ ስለው የነበረው ማንነቴ የሚናገረውና የሚያስበው ጠፍቶት የህልም ክንፎቼ ውስጥ ተደብቆ ተመለከትኩት፡፡ ልክ ዛፍን አልብሶት እንዳለ የልጥ ድሪቶ የኔም ማንነት ወደተለያዩ ማንነቶች እየተበታተነ እኔም ያልተረዳሁትን እኔን መጐብኘት ውስጥ ገባሁኝ፡፡ አይኖቼ ይከደኑ ይገለጡ የማውቀው ነገር የለም …ብቻ እየሄድኩኝ ነው፡፡ ወደ ራሴ ወደ እኔነቴ ብቻ የማልዳብሰውን ማንነቴን እየተመለከትኩት በሄድኩ ቁጥር እርስ በራሱ እያባዛ ወዳለ ጨለማ ውስጥ ገባሁኝ፡፡
የማይቆጠር ዘላለም ውስጥ ስማስን ቆይቼ ድንገት አይኖቼን ከፈትኳቸው፡፡ እመነኝ አንተ የኔ ቦታ ሆነህ ቢሆን ኖሮ ቀጥታ መጮህ ነው የምትፈልገው፡፡ የጩኸትህ ዋነኛው ምክንያቶች ከሚሆኑት መካከል የመጀመሪያው ለምን ካለሁበት የህልም አለም ወጣሁ ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ የት ነው ያለሁት የሚለው ክፍልፋይ ሀሳቦች ናቸው፡፡
አንድ ክፍል ውስጥ ከፊት ለፊቴ ግዙፍ ቴሌቪዥን ተከምሮ እኔ ደግሞ ምቾት ያለው ሶፋ ላይ ተቀምጬ ነው የነቃሁት፡፡ ደመነፍሴ በራሱ ድምጽ እንዳወጣ አስገደደኝ፡፡
“እዚህ ቤቶች የት ነው ያለሁት?...ተጣራሁ፡፡ ብዙም አልቆየም ያ ፂም አልባው የባህል ሀኪም መጥቶ ከፊት ለፊቴ ቆመ፡፡
“የት ነው ያለሁት ጌታ? ምን አድርገህብኝ ነው እንደዚህ እስክሆን ድረስ ራሴን የሳኩት?”
“ራስህን አልሳትክም…ይልቁኑስ ከማንኛውም ጊዜ በላይ ወደራስህ የተጠጋህበት ጊዜ ዛሬ ነው::” አለኝ በተረጋጋ አንደበት፡፡
“ምን እያልከኝ ነው አንተ ሰውዬ? ወደ ቤቴ መሄድ እፈልጋለሁ፡፡ የሆነ አደጋ ውስጥ ገብቼ ከሆነ አሁኑኑ ንገረኝና በምንደራደርበት መንገድ እንደራደር?”
ይህን ስናገር እስከዛሬ ድረስ እንደ ጥገኛ ህዋስ ነፍሴን ሲበላው የነበረውን ጥቁር ጥላቻ የሚያወድም ብርሃናዊ ፈገግታ አንድ ጊዜ ለገሰኝ:: ስለፈገግታው ባመሰግነው ደስ ባለኝ ነበር ሆኖም ካለሁበት ግራ መጋባት የሚያድነኝ የሱ ፈገግታ ሳይሆን ምን አድርጐብኝ እንደነበር ሲነግረኝ ብቻ ነው፡፡
“አትደናገጥ ዮሴፍ፡፡ መልሶችህ ያሉት በኔ ዘንድ ሳይሆን አንተው አንደበት ውስጥ ናቸው:: ምንም እንኳን የታሰርክ መስሎ ቢሰማህና ነፍስህን ያሰራትን ሰንሰለት መበጠስ ብትፈልግ ቁልፉን ማን ጋር እንዳለ የምነግርህ እኔ ሳልሆን አንተው ራስህ ነህ፡፡”
“እና አሁን ምን እንዳደርግ ነው የምትፈልገው? በሽታዬ ምን እንደሆነ ሳልነግርህ ገና በጭስ አፍነህ ልትገለኝ ያልከውን ሰው እንዴት አድርጌ ነው የማምንህ?”
ሰውየው በተረጋጋ መንፈስ ውስጥ ሆኖ መለሰልኝ፡፡
“ሁለት አማራጭ አለህ፡፡ በቅድሚያ በዚህ ቴሌቪዥን ውስጥ ያለውን ምስል መመልከት አለብህ፡፡ ቀጥሎም መምረጥ ትጀምራለህ፡፡ ካየኸው ነገር መልስ ያገኘህ መስሎ ከተሰማህ በተዘጋጀው የጓሮ በር በኩል ብቻህን ትወጣለህ:: ሆኖም መልስ    
ያገኘህ ካልመሰለህ አሁን በምወጣበት በር በኩል ትመጣና በአዲስ መልክ ማውራት እንችላለን፡፡ ምርጫው ሙሉ በሙሉ ያንተ እና ያንተ ብቻ ነው፡፡››
ከኔ መልስ ሳይጠብቅ ቲቪውን ከፍቶ ወጣ:: ዞሬ የጓሮውን በር ተመለከትኩት፡፡ ለማምለጥ ሙሉ ምርጫ እንዳለኝ ገብቶኛል… ሆኖም ይህን እያሰብኩ ባለበት ጊዜ ላይ በቲቪው ውስጥ የራሴን ምስል ተመልክቼ ትኩረቴን ወደ ተዓምረ መስኮቱ አዞርኩት፡፡ በቲቪው ውስጥ አይኖቼን ጨፍኜ አየሁኝ፡፡ በሆነ በማይታይ ገመድ ተንጠልጥዬ ያለሁ ነው የምመስለው:: ድንገት የዛ ፂም አልባ ተዓምረኛ ሰው ድምፅ መሰማት ጀመረ፡፡ መልኩ ግን በቲቪው ውስጥ አይታይም፡፡
‹‹ስምህ ማነው?››
‹‹ዮሴፍ ነኝ ነገር ግን ልረሳ የምፈልገውን ነገር እንዳስታውስ አታርገኝ፡፡››
‹‹ምንህን አሞህ ነው የመጣኸው?››
‹‹የሚያመኝ ሰው ነው፡፡ ከሰው መጠጋቱ፣ ማውራቱ፣ ማስመሰሉ፣ ማማቱ፣ መሳቁ… ምን ልበልህ ከስነፍጥረት ሚስጥራት በላይ ከፍ ብዬ ስመለከት የሰው ልጅ የተባለ በስህተት የተሰራ ፍጥረትን ነው የምመለከተው፡፡››
‹‹ራስህን ሰው አድርገህ መመልከቱስ… ምን አይነት ስሜት ይሰጥሀል?››
‹‹የእስር ስሜት ነው ውስጡ ያለው፡፡ በመወለድና በመሞት መሀል ቅዥቴን ራሴው አብስዬው ራሴ ቀቅዬ ስበላው ይታወቀኛል፡፡ አንደኛውን ማንነት በገደልኩት ቁጥር ሌላኛው እንግዳ ማንነት ይተካል፡፡ ከማንነት ውጭ ያለ… ከባዶው አየር በላይ የማይታይ… ጣቶች ሊጠጉት የማይሹት ሰው ነው መሆን የምፈልግ የነበረው፡፡ ሆኖም እንዳልከው ሰው ነኝ፡፡ ከዛ ውጭ አለመሆኔ ሁሌ ያመኛል… ይቀፈኛል፡፡››
‹‹አፍቅረህ ታውቃለህ ዮሴፍ?››
‹‹እርግማኔን እንዴት እሸሸዋለሁ ብለህ ነው፡፡ ምናልባትም በየቀኑ አፈቅር የነበረበት ወቅት ነበር፤ አሁን እረስቼዋለሁ… ስሜቱንም ማስታወስ አልፈልግም፡፡ ፍቅር የፍላጎትህ ባሪያ ከማድረግና ተፈጥሮ በጅራፏ ጀርባህን ቀዳድዳ የምትጥልበት የስቃይ ገነት ከመሆን ውጭ ላንተ ብሎ መንገዶች የሚያበጅልህ ነገር የለውም፣ ሲጀመር አንተንም አያውቅህም፡፡››
‹‹እስቲ የሰው ልጅን ከመጥላትህ በፊት ስለነበረህ ማንነት ንገረኝ? ያኔ ምናቸውን ወደህላቸው ነው አብረሀቸው እንድትኖር የወሰንከው?››
‹‹በትውስታ ውስጥ ያለ የተሰበረ ተክል ደግመህ ደጋግመህ በህሊናህ ውስጥ መልሰህ ለመግጠም ብትሞክር ራስህን እየዋሸኸው ካልሆነ በስተቀር ለዘላለም ተክሉ እንደተሰበረ ይቆያል፡፡ አሁን ካለው እምነቴ አንፃር ውጭ ሆኜ በፍጹም የጠየከውን ጥያቄ መመለስ አልችልም:: ሆኖም ሕጻናት ይመቹኝ ነበር፡፡ እንሰሶችም ቢሆኑ ስለማይናገሩ ነው መሰል ዝምታቸውና እምነታቸው ድረስ ሕሊናዬን ልኬ በፍቅር ስሜት መብከንከኑን አዘወትር ነበር፡፡ ግን አሁን ሁሉም ነገር ትዝታ ነው። ትዝታ ደግሞ ድክመቴ ነው፡፡››
‹‹እንግዲያውስ ልንገርህ ዮሴፍ፡፡ ሁላችንም የሆነ ቀንና ቦታ ሕጻናቶች ነበርን፡፡ አንድ ነገር ስንፈልግ አልቀሰናል፡፡ ያሻንን ስናገኝ በምድር ስፋት ልክ ተደስተናል፡፡ እነዚህን ስሜቶች በራሳችን ላይ ስናፈራርቃቸው የነበረው ነፃነት ስላለን ነው፡፡ መደሰትንና መከፋትን ግን ተርጉመን አልነበረም እንደዛ ስንሆን፤ ነገር ግን የጊዜን ሚስጥር ባልተረዳነው መንገድ ስለገባን ነው፡፡››
‹‹ጊዜ ራሱ እርግማን ነው፡፡ ውሸት፡፡››
‹‹ጊዜ እኛ ነን ዮሴፍ፡፡ ሕይወትህ ውስጥ ጊዜ የሰጠኸው ነገር ነው ማንነትህን መተርጎም የሚጀምረው፡፡ ዮሴፍ አንተ እስከዛሬ የሰው ልጆችን ሚስጥር የተረዳኸው የመሰለህ ባካባቢህና በሚዲያ ውስጥ በምታየው አስከፊ መረጃዎች ስር ነፍስህን አንበርክከህ ስላሰርካት ነው፡፡››
‹‹የምትለው ወደ ስድብ ሊቀየር እንደሆነ እየተሰማኝ ነው፡፡ እራስ ወዳድና አስተዋይ አይደለህም እያልከኝ ነው?››
‹‹ተሳሳትክ፡፡ እንዲያውም እያልኩህ ያለሁት ተቃራኒውን ነው፡፡ ሁላችንም የተፈጥሮ ግኝቶች እርስ በርሳችን ልክ ሰውነታችን ውስጥ እንዳለው የደም ስር ውስብስብ ገመዶች አይነት ከተፈጥሮም ጋር እንዲሁ ግንኙነት አለን:: የአንድ ሰው ሞት የሌላን ሰው ሕይወት ያወድማል፡፡ የአንድ ሰው አዕምሮ ማጣት ምናልባት የብዙ ቤተሰቦች  ቀውስ ሊሆን ይችላል፡፡ የአንዲት ቅጠል መበጠስ የአንድ አገር ውድመትን ሊነግርህ ይችላል፡፡ ምድር ወደድክም ጠላህም በፍቅርና በቀውስ ውስጥ ትቀጥላለች፡፡ አንዱ ለመኖር ሌላውን ይገድላል፡፡ ይህም ሕግ ነው፤ ምናልባትም ውበትም ነው፡፡ የሌላውን ሰው ውበት መመልከት መጀመር ከፈለክ በቅድሚያ የራስህን ውበት ተመልከት፡፡ የተፈጥሮን አብሮነት ለማድመጥ ከፈለክ… በላይህ ላይ ያለውን ጥላቻ ወዲያ አድርገህ ከራስህ ጋር ያለህን መግባባት ከነሹክሹክታው ለነፍስህ አስጠጋው፡፡ ከራሱ የተሰወረ  ሰው ከፊቱ ያለውን አየሁ ቢል ገና ማየት አለመጀመሩን አሁን አንተ ያለህበት የማንነት ቀውስ ውስጥ ሲገባ ያውቀዋል፡፡
‹‹እና ከማንነት ቀውስ ለመዳን ራስህን ውደድ እያልከኝ ነው?››
ምንም የሚያስከፍልህ ዋጋ አይኖርም:: ማፍቀርና ማክበር በነፃ የተሰጠን ፀጋ ነው፡፡ በዛውም ልክ ስትጠጋው እንደሚርቅ ሚራዥም ሚስጥራዊነቱ ከስሜት ህዋስ በላይ ሊወስድህ ይችላል፡፡ ይህን ፀጋ ካሁን ጀምረህ ሞክረው። ከዛም የጎደለህ ነገር ካገኘህ ደግመህ ወደኔ ተመለስ፡። ሆኖም አንድ ጊዜ ወደኔ ተመልሰህ መጥተህ ለሁሉም ነገር መልስ የምትፈልግ ከሆነ የኔን ካልሆነ የማንንም ኑሮ መኖር ያቅትሀል:: ስለዚህ ከነፍስህ ጥጋት ስር ያለችውን የይቅር ባይነትና መለኮታዊው የማፍቀር ጥበብህን ከሞተበት ቀስቅሰህ በስጋዊው አይንህ ማየት ስትጀምር ያመለጠህን ጊዜ አስታውሰህ ሰኮንዶችን ስትንከባከብ ራስህን ታገኘዋለህ፡፡ ስለዚህ ውሳኔህን ወስን…››
ቲቪው ተቋረጠ፡፡ የማየውን ነገር ለመተርጎም ትንሽ ጊዜ ፈጀብኝ፡፡ የፂም አልባውን ሰውዬ ንግግሮች ቁርጥምጥም አድርጌ በህሊናዬ ጥርሶች አድቅቄ ዋጥኳቸው:: ሞክሬ የማላውቀውን የሕይወት ተሞክሮ ነው የሰማሁት… ምናልባት ብሞክረው ብየ አሰብኩት፡፡ ከተቀመጥኩበት ተነስቼ ግራና ቀኜ ያሉትን በሮች ተመለከትኳቸው፡፡ የጓሮውን በር ከፍቼ ወጣሁ፡፡
ወጥቼም አካባቢየን መቃኘት ውስጥ ገባሁኝ፡፡ ከፊት ለፊቴ አንድ እናትና ልጅ ሲመጡ ተመለከትኩኝ፡፡ ልጁን ትኩር ብዬ ተመለከትኩት፡፡ አይኖቹ ላይ ያለው ንፅህና ከዚህ በፊት አስተውዬው በማላውቀው መልኩ ውስጤ ገብቶ ተቀረቀረ፡፡ የማላውቀው የእንባ ዘለላ አይኖቼን አዳልጦ ጉንጩ ላይ የደስታ ሀዲድ እየሰራ መጓዝ ጀመረ፡፡ እናትና ልጁ አጠገቤ ሲደርሱ ልጁን ተንደርድሬ ሄጄ አቀፍኩት፡፡ እንዴት ያለ የፍቅር ዜማ ልቤ ላይ መደመጥ ጀመረ፡፡ ፍርሀቴ ጥሎኝ ሲኮበልል ተሰማኝ ሕጻኑን ልጅ እናትየው ከእኔ ነጥቃ እየገላመጠችኝ ቶሎ ቶሎ መሄድ ጀመረች፡፡ እናትየው የቅድሙን እኔን አስታወሰችኝ፡፡ ሆኖም አልተከፋሁም፡፡ ሁለቱም መፈጠራቸውን እያከበሩት ነው፡፡  እናትየው እናት ሆና ልጇ ትጠብቃለች፡፡ ልጁ የናቱን ጥበቃና ፍቅር እየተመገበ ያድጋል፡፡ ሕይወት እዚህ ድረስ ቀልላ የምትታየኝ አይመስለኝም ነበር፡፡
የዛን ቀን ወደተከራየሁበት ቤት ሄጄ ምሽቱን እንዳለ ከአከራዬ ጋር እያወጋሁ አመሸሁ፡፡ እውነታችን ያለው ከስሜት ህዋሳቶቻችን በላይ እንደሆነ ተረዳሁ፡፡
እንደ አዲስ በራሴና በተፈጥሮ እውቀት ውስጥ ሆኜ አድጋለሁ፡፡ ሚስት አገባለሁ፡፡ ራሱንና መላው ተፈጥሮን ወክሎ የሚከራከርና የእውቀቱንና የስሜቱን ልኬት ለሌሎች የሚመግብ ልጅ እወልዳለሁ፡፡ እሱም ቀውስ፣ ጥላቻ፣ ግላዊነት፣ ሀሜት እና ሞትን ከውስጥዋ አስግራ ያለችው ሀገሬ ላይ ሕይወት መዝራት ይጀምራል፡፡
ተበታትነን ያገኘነው የመሰለንን ግላዊ የሀያልነትን መንፈስ ወደ ማህበራዊ አንድነት አምጥቶ ያቆሙን ራሳቸውን የሆኑ ሰዎችን ለመስራት ይታትራል፡፡ እኔንም ያድነኛል፣ እኔም ሰው እሆናለሁ… ሰው…
የሕይወትን ሚስጥር መመስጠሩ ግን ይቀጥላል፡፡ ሞቴ ትንሽ ቆየኝ አንድ ጊዜ ልኑር፡፡        



Read 2159 times