Print this page
Saturday, 18 January 2020 13:50

“ሼክስፒር ያገባው በግዳጅ ነው”

Written by 
Rate this item
(4 votes)

    ሼክስፒር በህይወት በነበረበት ዘመን ማንም ሰው ይህን ያህል ትኩረት አልሰጠውም፡፡ ከዚህ ዓለም በሞት ከተለየ ከመቶ ዓመት በኋላም እንኳ ቢሆን ይህን ያህል የሚታወቅ አልነበረም:: ሆኖም ግን ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ስለ እርሱ ብዙ ሚሊዮን ቃላት ተጽፈዋል፡፡
በዝይ ላባ ብዕር የጥበብን ጥርስ ከሞረዱ ታላላቅ ደራሲያን በላይ ስለ እርሱ ብዙ አስተያየት ተሰጥቷል፡፡ ከዚህም ሌላ በብዙ ሺህ የሚቆጠር ህዝብ ወደ ተቀደሰ ስፍራ እንደሚደረግ ጉዞ፣ ወደ ተወለደባት ስፍራ ለአፍታ ጋብ ሳይል ይተማል፡፡ እኔ እራሴ በ1921 እዚያ ነበርኩ፡፡
እንደ ሞገደኛ የገጠር ልጅ፣ የከንፈር ወዳጁ የነበረችውን አን ዋትሊይን በድብቅ ወደሚያገኝበት ስፍራ፣ ከስትራትፎርድ እስከ ሺትሪ ያሉትን ሰፋፊ ሜዳዎች በእግሩ አቆራርጦ በጥድፊያ የገሰገሰባትን ስፍራ በማየቴ ተደንቄአለሁ፡፡
ዊሊያም ሼክስፒር ስሙ ለዘመናት በክብር በማስተጋባት እየተወደሰ እንደሚኖር ቅንጣት ጥርጣሬ አልነበረውም፡፡ እንደ እድል ሆኖም፣ የልጅነት ጣፋጭ ፍቅሩ፣ ወደ አሳዛኝ እጣ ፈንታና ወደ ዓመታት ፀፀት ይለወጣል ብሎ አንዳችም ጥርጣሬ አልገባውም፡፡ ሆኖም ግን የሼክስፒር አሳዛኝ ህይወት በጋብቻው ላይ ተከሰተ፡፡
በእውነት አን ዋትሊይን ከልቡ ያፈቅራት ነበር - የሆነው ሆኖ በጨረቃ ምሽት አን ሃታዌይ ከምትባል ከሌላ ልጃገረድ ጋር በመቅበጥ ስህተት ፈፀመ፡፡ አን ሃታዌይም፣ ሼክስፒር አን ዋትሊይ የምትባል ፍቅረኛውን ለማግባት የጋብቻ ፈቃድ ማውጣቱን ስትሰማ፣ በድንጋጤ ትንፋሿ ቀጥ አለ - ከዚያም በፍርሃት ቀወሰች:: የምታደርገው ብታጣ ከጐረቤቶቿ ቤት ዘላ ገብታ፣ በውርደት እንባዋን እየዘራች፣ ሼክስፒር ለምን ሊያገባት እንደሚገባ በግልጽ ዘርዝራ ነገረቻቸው፡፡ ጐረቤቶቿም በቀላሉ የሚረዱ፤ ቅን ልቦና ያላቸው ገበሬዎች ነበሩና፣ በሞራል አስገዳጅነት ከጐኗ ቆሙ፡፡ በነጋታው በማለዳ በፍጥነት ተነስተው ወደ መዘጋጃ ቤት ይሄዱና ሼክሰፒር፣ አን ሃታዌይን ማግባቱን የሚገልጽ ህጋዊ የውል ስምምነት ለጠፉ፡፡ የሼክስፒር ሙሽሪት በእድሜ ከእርሱ በስምንት ዓመት ትበልጥ ነበር - ገና ከመጀመሪያው ጋብቻቸው አሳዛኝ ቧልት (ፋርስ) ነበር፡፡ በመሆኑም፤ በሚጽፋቸው ተውኔቶቹ ውስጥ ወንዶች በእድሜ የምትበልጣቸውን ሴት እንዳያገቡ መልሶ መላልሶ ያስጠነቅቃል፡፡ በእርግጥም ሼክስፒር ከአን ሃታዌይ ጋር አብሮ የኖረው በጣም ትንሽ ጊዜ ነበር፡፡ አብዛኛው የጋብቻ ጊዜውን ያሳለፈው ለንደን ሲሆን፣ ወደ ቤተሰቡ ተመልሶ የሚመጣው ምናልባት በዓመት ከአንድ ጊዜ አይበልጥም፡፡
ዛሬ ስትራትፎርድ ኦን አቮን በእንግሊዝ ውስጥ ካሉ እጅግ በጣም ተወዳጅ ከተሞች አንዷ ነች፡፡ ከተማዋም እጅግ አነስተኛ የሳር ክዳን ጐጆዎች፣ የሚያማምሩ አበቦች ያሉት ቁጥቋጦዎች የያዙ የአትክልት ስፍራዎችና በጥንታዊነታቸው የሚማርኩ ነፋሻ መንገዶች አሏት፡፡ ይሁን እንጂ፣ ሼክስፒር እዚያ በሚኖርበት ጊዜ ምን ትመስል ነበር? ቆሻሻ ነበረች፤ ህዝቡም በድህነትና በበሽታ የተጠቃ ነበር፡፡ ምንም አይነት የቆሻሻ ቱቦ አልነበራትም:: በዋና ዋና መንገዶች ላይ ቆሻሻ እየለቃቀሙ የሚበሉ አሳማዎች የሚርመሰመሱባት ነበረች፤ የሼክስፒር አባትም ከከተማዋ ባለስልጣናት አንዱ ቢሆንም ከፈረስ ጋጣ የሚወጣ ቆሻሻ ደጃፉ ላይ በመከመሩ ይቆጣ ነበር፡፡
በአሁን ጊዜ አስቸጋሪ ጊዜያት ውስጥ እንዳለን አድርገን አንዳንዴ እናስብ ይሆናል፤ ነገር ግን እነ ሼክስፒር በነበሩበት ጊዜ የስትራትፎርድ ከተማ ግማሽ ህዝብ የሚኖረው በበጐ አድራጐት እርዳታ ነበር፡፡ በዚህም ላይ አብዛኛው ህዝብ ፊደል ያልቆጠረ ማሀይም፡፡ የሼክስፒር አባት፣ እናት፣ እህት፣ ትንሽ ልጁና ትልቋ ልጁ ማንበብም ሆነ መፃፍ የማይችሉ ጨዋ ነበሩ፡፡
ለእንግሊዝ ስነ-ፅሁፍ ጉልበት፣ ከፍተኛ ክብርና ዝና አስቀድማ እድል የመረጠችው ሰው፤ በአስራ ሶስት ዓመቱ ትምህርቱን አቋርጦ ወደ ስራ ተሰማራ፡፡ አባቱ ከከተማዋ ባለስልጣንነቱ ሌላ ጓንት ሰራተኛና ገበሬ ነው፡፡ ሼክስፒርም ላሞች በማለብ፣ የበጐች ፀጉር በመሸለት፣ ወተት በመናጥ፣ ቆዳ በማልፋትና በማለስለስ ቤተሰቡን ይረዳ ነበር፡፡
ሼክስፒር ከዚህ ዓለም በሞት ሲለይ በዘመኑ የደረጃ መለኪያ ሃብታም ሰው ነበር፡፡ በለንደን የአምስት ዓመት ቆይታው በተዋናይነት ጥሩ ገንዘብ አግኝቷል፡፡ የሁለት ቤተ-ተውኔት አክሲዮን (ሼር) ገዝቶ ነበር፡፡ እንዲሁም በሪል ስቴት ለስሙ ያህል ተሳትፏል፡፡ በተለይ ደግሞ በከፍተኛ ወለድ ገንዘብ ይበደር ነበር፡፡
በዚያን ጊዜ፣ ገቢው በዓመት ሶስት መቶ ፓውንድ ሲሆን የገንዘብ የመግዛት አቅሙ ከአሁኑ በአስራ ሁለት በመቶ ከፍ ያለ ነበር:: በመሆኑም ሼክስፒር የአርባ አምስት ዓመት ጐልማሳ በነበረበት ጊዜ፣ የዓመት ገቢው አራት ሺህ ፓውንድ ደርሷል፡፡ ከዚህ ሁሉ ገንዘብ ታዲያ ለሚስቱ ምን ያህል ገንዘብ ትቶላት እንዳለፈ ይገምታሉ? አንዲት ሳንቲም፤ ከአልጋው በቀር ምንም ነገር አልተወላትም፡፡ አልጋውም ቢሆን በኋላ ላይ የመጣለት ሃሳብ ሲሆን በኑዛዜ ጽሑፉ ላይ በመስመሮች መሃል ጣልቃ አስገብቶ ነበር የፃፈው፡፡
ሼክስፒር ከአረፈ ከሰባት ዓመት በኋላ ሁሉም ተውኔቶቹ በመጽሐፍ ታተሙ:: ዛሬ የመጀመሪያውን ህተመት ለመግዛት ብትፈልግ፣ በኒውዮርክ ሁለት መቶ ሃምሳ ሺህ ፓውንድ ከፍለህ እጅግ የተዋበ መጽሐፍ መውሰድ ትችላለህ፡፡ ይሁን እንጂ ሼክስፒር እራሱ ለ “ሐምሌት”፣ “ማክቤዝ” ወይም ለ “ኤ ሚድሰመር ናይትስ ድሪም” ለእያንዳንዱ የአንድ መቶ ፓውንድ ተመጣጣኝ ክፍያ እንኳ በፍፁም አላገኘም፡፡
ኤስ.ኤ ታኒንባውም ስለ ሼክስፒር ብዙ መፃሕፍት የፃፈ ብርቱ ብዕረኛ ነው፡፡ በአንድ ወቅት የሼክስፒር ቴያትሮችን የፃፈው “የስትራትፎርድ ኦን አቮንኑ” ዊሊያም ሼክስፒር እንደነበረ የተሟላ ማረጋገጫ እንዳለው ጠይቄው ነበር፡፡ እርሱም አብርሃም ሊንከን፣ በጊቲስበርግ ንግግር እንደ ማድረጉ እርግጠኞች ነን በማለት መልስ ሰጥቶኛል፡፡ ሆኖም ግን፤ ብዙ ሰዎች፣ ሼክስፒር በህይወት ያልነበረ ሰው ነው ይላሉ፡፡ ብዙ መፃሕፍትም ይህንኑ ለማረጋገጥ ተጽፈዋል፡፡
ተውኔቶቹ በእርግጠኝነት የሰር ፍራንሲስ ባኮን ወይም የኦክስፎርዱ ኧርል ድርሰቶች ናቸው ብለውም ነበር፡፡ ከመቃብሩ ፊት ለፊት ቆሜ በመቃብር ድንጋዮች ላይ ከሚፃፉ ጽሑፎች ሁሉ ባልተለመደ መልኩ በመቃብር ድንጋዩ ላይ የሰፈረውን ግጥም ቁልቁል ወደ ታች ብዙ ጊዜ አትኩሬ ተመልክቼአለሁ፡፡
“ወዳጄ ስለ እየሱስ ብለህ፣ ተወው አትንካው ይቅር
አትቆፍር፣ ይህን መቃብር!
ድንጋዬን ያልነካም ስሙ ይወደስ፣ ዘሩም ይቀደስ
ውጉዝ ወአርዮስ አጽሜን የሚያንቀሳቅስ፡፡” ይላል፡፡
በአንድ ትንሽ መንደር ውስጥ ከሚገኝ ቤተ-ክርስቲያን ከአውደ ምህረቱ ፊት ለፊት ነበር የተቀበረው፡፡ ይህን የመሰለ የክብር ቦታ የተሰጠው ለምን ነበር? በታላቅ ተሰጥኦው ወይም ከሶስት መቶ ዓመት በኋላም ቢሆን ሰዎች እስካሁን ስለሚያፈቅሩትና ስለሚያከብሩት? አልነበረም፡፡ በእንግሊዝ ስነ ጽሑፍ ደማቅ አብሪ ኮከብ ለመሆን አስቀድማ እድል የወሰነችለት ባለቅኔ፣ በቤተ ክርስቲያኑ በእንዲህ ያለ ስፍራ አስክሬኑ በክብር እንዲያርፍ የተደረገበት ምክንያት ለተወለደባት ከተማ ህዝብ ገንዘብ በአራጣ ያበድር ስለነበረ ነው፡፡ የሻይሎክን ገፀ - ባህርይ የፈጠረው ይህ ሰው ለተወለደባት ከተማ ገንዘብ በአራጣ ባያበድር ኖሮ፤ ዛሬ አጽሙ ምልክት ባልተደረገበት መቃብር ውስጥ አርፎ፤ የት እንደተቀበረ እንኳ ሳይታወቅ ተረስቶ ይቀር ነበር፡፡
ምንጭ፡- (በዴል ካርኒጊ ተጽፎ፣ በደጀኔ ጥላሁን ከተተረጎመው “የ5 ደቂቃ የህይወት ታሪኮች” መጽሐፍ፤ 2010 ዓ.ም)


Read 2256 times
Administrator

Latest from Administrator