Tuesday, 21 January 2020 00:00

ኢራን በሚሳኤል ከተመታው አውሮፕላን ጋር በተያያዘ በርካታ ሰዎችን አስራለች

Written by 
Rate this item
(2 votes)

  የኢራን መንግስት ባለፈው ረቡዕ ከመዲናዋ ቴህራን በረራውን እንደጀመረ በስህተት በተፈጸመበት የሚሳኤል ጥቃት በአሰቃቂ ሁኔታ ከወደመውና 176 ሰዎች ለሞት ከተዳረጉበት የዩክሬን አውሮፕላን ጋር በተያያዘ በርካታ ሰዎችን ማሰሩን አስታውቋል፡፡
የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ሃሰን ሩሃኒ ባለፈው ረቡዕ በሰጡት መግለጫ፤ በአውሮፕላኑ ላይ የተፈጸመውን ጥቃት በቪዲዮ ቀርጾ አሰራጭቷል የተባለውን ግለሰብ ጨምሮ ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ የተጠረጠሩ በርካታ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውንና ጉዳዩ በልዩ ፍርድ ቤት ምርመራ እንደሚደረግበት ማስታወቃቸውን አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል፡፡
ኢራን አውሮፕላኑ በሚሳኤል ጥቃት አልተፈጸመበትም በማለት ስታስተባብል ከቆየች ከ3 ቀናት በኋላ በአየር ሃይሏ በስህተት ጥቃት እንደተፈጸመበት ባመነችውና ይቅርታ በጠየቀችበት አውሮፕላን ጉዳይ አንድ ግለሰብ ብቻ ተጠያቂ እንደማይሆን የገለጹት ሩሃኒ፤ ከጥቃቱ ጋር በተያያዘ እጃቸው ያለበት ባለስልጣናትና ወታደራዊ ሃላፊዎች ጭምር ለፍርድ እንደሚቀርቡም ተናግረዋል፡፡
የአገሪቱ መንግስት በጥቃቱ እጃቸው አለበት ብሎ ከጠረጠራቸው ሰዎች በተጨማሪ በመንግስት ላይ ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ተቃውሞ እንዲቀሰቀስ አስተባብረዋል ያላቸውን 30 ያህል ሰዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉንም ዘገባው አመልክቷል፡፡
የአገሪቱ የጦር ሃይል በአውሮፕላኑ ላይ እንዴት ጥቃቱን እንደፈጸመ ዝርዝር ማብራሪያ ሊሰጥ ይገባል ማለታቸውን የጠቆመው ዘገባው፣ የኢራን መንግስት ድርጊቱን አልፈጸምኩም ብሎ ከካደ በኋላ ማመኑ ያበሳጫቸው ኢራናውያን በተለያዩ የአገሪቱ ከተሞች ተቃውሞ ማስነሳታቸውንና በአገሪቱ ውጥረት መንገሱንም አመልክቷል፡፡
በአውሮፕላኑ ላይ በተፈጸመው የሚሳኤል ጥቃት ከኢራናውያን በተጨማሪ የካናዳ፣ ዩክሬን፣ አፍጋኒስታንና ስዊድን ዜግነት ያላቸው መንገደኞች ለሞት መዳረጋቸውን ያስታወሰው ዘገባው፤ የአገራቱ መንግስታት ከሰሞኑ ስብሰባ በማድረግ በኢራን ላይ ህጋዊ እርምጃ መውሰድ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ይወያያሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም አመልክቷል፡፡

Read 8434 times